Friday, December 14, 2012

ሰብኣዊ መብቶች፣ ሕገ-መንግሥቱ እና መንግሥት

ሰብኣዊ መብቶች፣ ሕገ-መንግሥቱ እና መንግሥት

 
Ethiopian-constitution-sm

አዘጋጅ Zone 9

በሶልያና ሽመልስ

ሰሞኑን የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን የማዳመጥ ፍቃደኝነት ካሳያችሁ የብሔር ብሔረሰቦች ቀን ከሕገ -መንግሥቱ መጽደቅ ጋር ተያይዞ ለአንድ ሳምንት እየተከበረ ይገኛል፡፡ በትምህርት ቤቶች እና በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ደግሞ በዓሉ ለቀናት (ለአንድ ሳምንት) እንዲከበር ተወስኗል፡፡ ይህ ሕገ መንግሥቱ የጸደቀበትን ቀን ተከትሎ ለ7ተኛ ጊዜ የሚከበረው በዓል ሕገ መንግሥቱ ያጎናጸፋቸው መብቶች ብሎ ብዙዎቹ ብሔር ብሔረሰብ ላይ ያተኮሩ መብቶችን ሲያነሳ ሌሎቹን ደሞ ከተግባራዊነታቸው አለያይቶ ለብቻቸው ያስተዋውቃቸዋል፡፡

የኢፌድሪ ሕገ መንግሥት በሶስተኛው ምእራፍ መሰረታዊ መብቶች እና ነጻነቶች ብሎ በተለምዶ ሰብአዊ እና ሲቪል መብቶች የምንላቸውን ያስቀምጣል፡፡ በክፍል አንድ በ15 አንቀጾች ሰብኣዊ መብቶች የተቀመጡ ሲሆን በዚሁ ምዕራፍ ክፍል ሁለት ዴሞክራሲያዊ መብቶች ስር16 አንቀጾች ተካተዋል፡፡ በሕገ መንግሥቱ ውስጥ የተካተቱት መብቶች ከጥቂቶቹ (አንቀጽ 39 ለዚህ ምሳሌ ነው) በስተቀር በዓለም አቀፍ ደረጃ ሕገ መንግሥቱን ሰብኣዊ መብቶች ጉዳይ ላይ ትኩረት የሰጠ እና የተለየ ያደርጉታል፡፡

ወደ ተግባሩ ሲመጣ ባለፉት 18 ዓመታት ከጽሑፉ ጋር በፍጹም የማይገናኙ ብዙ የተግባር ጥሰቶችን አንደግለሰብም እንደ አገርም አስተናግደናል፡፡ ከነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ግልጽ ጥሰቶች አስተዳደራዊ ይምሰሉ እንጂ በባሕሪያቸው በሕገ መንግሥቱ የተቀመጡትን የሰብኣዊ መብት ድንጋጌዎች በግልጽ የሚቃረኑ ከመሆናቸውም ባሻገር በተለያዩ የመንግስት አካላት በመጣሳቸው እንደቁምነገር እንደማይቆጠሩ ያሳያል፡፡

የተናቁ አንቀጾች

በምዕራፍ ሦስት ክፍል አንድ በሰብኣዊ መብት ክፍል ከተደነገጉት ዐሥራ አምስት (15) አንቀጾች መካከል ቢያንስ ዐሥራ ሁለቱ በግልጽ በተደጋጋሚ በመንግስት ተጥሰዋል፡፡ ከነዚህ መካከል አንዳንዶቹ ድንጋጌዎች ሊያከብሩዋቸው በሚገቡ የመንግስት አካላት ዘንድ እንደ ቅንጦት ሲቆጠሩ ሌሎቹ ደግሞ በአፈጻጸም ወለምታ ይታሻሉ፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 15 ማንኛውም ሰው በሕይወት የመኖር መብቱን አረጋግጦ በሕግ ካልተደነገገ በስተቀር ሕይወቱን እንደማያጣ ይናገራል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ ሕጻናት እና ወጣቶች ሳይቀር በየመንገዱ ሲገደሉ ምስክር የሆንበት ጊዜ ቅርብ ትዝታ ነው፡፡ ይህንን ዓይነት ዜጎች ሕይወታቸውን በሕግ ባልተደነገገ ሁኔታ ማጣት እንደ አንድ ሰብኣዊ መብት ጥሰት ሳይሆን እንደ የአንድ ሰሞን የፓለቲካ አለመረጋጋት ውጤት ብቻ መቆጠሩ፣ የኦጋዴን ጭፍጨፋን ዓይነት የብዙ ሰዎች ሕይወት ያለምንም ሕጋዊ ድንጋጌ የተቀጠፈበትን የመብት ጥሰት በዝምታ መታለፉ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ 15 መናቅ ውጤት ነው፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 16 ማንም ሰው በአካሉ ላይ ጉዳት እንዳይደርስበት የመጠበቅ ሕጋዊ ከለላ ቢሰጠውም ይህንን የመብት ጥሰት በዋናነት የሚፈጽሙት ሕግ አስከባሪዎቹ የመንግስት አካላት ናቸው፡፡ ከመንገድ ላይ አንስቶ እስከ ሕጋዊ የፓሊስ ጣቢያዎች ድረስ ያለምንም ማቅማማት እንደሥራም ጭምር ቆጥረው ከፍተኛ የአካል ጉዳት የሚያደርሱት እነዚሁ የመንግስት አካላት ናቸው፡፡ (ይህ አንግዲህ በደህንነት ነኝ ባይ አባላት እና በስርዓቱ ተጠቃሚዎች የሚፈፀመውን የአካል ጉዳት ሳንጨምር ነው፤) ይህ ከማንኛውም አካላዊ የአካል ጉዳት የመጠበቅ መብት በራሱ በመንግሥት ማረሚያ ቤቶች እንኳን መከበር አቅቷቸው የተለያዩ እስረኞች በተለያየ ወቅት የሚደርስባቸውን የአካል ጉዳት ለአደባባይ ሲያቀርቡ መስማት ለሕግ አስፈጻሚ አካላት የተለመደ እና እርምጃ ያልተወሰደበት የመብት ጥሰት ነው፡፡ የቅርብ ጊዜዎቹን የአንዱአለም አራጌን እና ዘሪሁን ገ/እግዜያብሔር በእስረኞች የደረሰባቸውን ከፍተኛ የአካል ጉዳት እና ማረሚያ ቤት ውስጥ ተቀምጠው እንኳን ያጡትን የአንቀጽ 16 ሕጋዊ ከለላ ማስታወስ ይቻላል፡፡ ዜጎች ክስ ሳይቀርብባቸው እና ሳይፈረድባቸው እንደማይታሰሩ አንቀጽ 17 ቢደነግግም በተቃራኒው ግን ለረዥም አመት ሳይፈረድባቸው ሕይወታቸውን በእስር ቤት የሆኑ ዜጎች ቁጥር መንግሥት የሚታማበት ሰብኣዊ መብት አያያዝ ነው፡፡

በሕግ ጥበቃ ስር ያሉ ሰዎችን መብትን አስመልክቶ ሕገ መንግሥቱ በቤተሰቦቻቸው በሃይማኖት አባቶች እና በወዳጅ ጓደኞቻቸው መጎብኘት መብት እንዳላቸው ቢደነግግም በተቃራኒው ግን የተለያዬ “የፓለቲካ እስረኞችን” ማግኘት መጠየቅ እና ማናገር የማረሚያ ቤቶች ቸርነት ሲሆን ‹‹ኧረ ተው ሕገ መንግሥቱን አክብሩ›› የሚል የሕግም ሆነ የመንግሥት አካል አልተገኘም፡፡ ወ/ት ብርቱካ ሚደቅሳን ማየት (ከእናቷ አና ከልጇ) በስተቀር ፍጹም የማይፈቀድ የነበረ ሲሆን ዛሬ ደግሞ እነእስክንድርንና አንዱአለምን መጠየቅ አለመፈቀዱ እንደትክክለኛ አስተዳደራዊ አሠራር ተቆጥሯል፡፡ ከፓሲስ ጣቢያ እስከ ቃሊቲ የሕገ መንግሥቱን አንቀጽ መናቅ የመንግሥት ተቋማት ቋሚ አሠራር አካል ሆኗል፡፡ (ጠያቂዎችን ሳይቀር ኢ-ሰብኣዊ በሆነ መንገድ እንደሚያስተናግዱ ለማየት ለአንድ ቀን ወደ እነዚህ አካላት ጎራ ማለት ይበቃል፡፡)

በተደጋጋሚ ሲጣስ የቆየው የሃይማኖት የእምነት እና የአመለካከት ነጻነት መብት በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 27 በግልጽ ተቀምጧል፡፡ ይህ አንቀጽ ነጻ የሃይማኖት፣ ትምህርት እና አስተዳደር ተቋማትን በነጻነት ስለማቋቋም እና ትምህርቶችን ስለማስተማር ቢፈቅድም በተቃራኒው ላለፉት 8 ወራት አካባቢ የሚታየው የሙስሊም ኢትዮጵያውያን ጥያቄ ለአንቀጹ መናቅ ትልቅ ምሳሌ ሆኖ መጠቀስ ይችላል፡፡ (ይህ እንግዲህ የሌሎች ሃይማኖት ተቋማት ነጻነት ዙሪያ ያሉትን ብዙ ጥያቄዎች ሳናነሳ ካለፍን ነው፡፡)

በዴሞክራሲያዊ መብቶች ተርታ ከተመደቡት ውስጥ አንቀጽ 29 የአመለካከት ሐሳብን በነጻ የመያዝና የመግለጽ መብት የመጀመሪያው ነው፡፡ ይህ አንቀጽ መኖሩ ራሱ አጠራጣሪ እስኪመስል ድረስ ሙሉ በሙሉ በሚባል ሁኔታ በመንግሥት ተጥሷል፡፡ የዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 2 የሐሳብ መግለጽ መብትን “በማንኛውም የሕትመት እና የስነ ጥበብ መልክ በመረጠው ማሰራጫ ማስተላለፍ” እንደሚችል ይናገራል፡፡ በተቃራኒው የተለያዩ የሕትመት ውጤቶች ቁጥር ቀን ከቀን እየቀነሰ ለመጥፋት አዝማሚያ ላይ ሲደደርስ አገራችን ከዋናዎቹ የኢንተርኔት አጋጅ አገሮች አንዷ ነች፡፡ የዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 5 ደግሞ በመንግሥት ቁጥጥር ስር ያለ የመገናኛ ብዙኃን የተለያዩ አስተያየቶችን የሚያስተናግድ እንዲሆን ያስገድዳል፡፡ (አንባቢያን ኢቲቪን ካሰባችሁ አንቀጽ 29 ምን ያህል እንደተናቀ ትረዳላችሁ፡፡)

አንቀጽ 30 የመሰብሰብ፣ ሰላማዊ ሰልፍ የማድረግ እና የአቤቱታ መብትን ቢያረጋግጥም በተግባር ግን ሰላማዊ ሰልፍን አገራችን ውስጥ ማሰብ መንግሥት ላይ እንደማሴር ታላቅ ወንጀል ከተቆጠረ ዓመታት አልፈዋል፡፡ (የመጨረሻዎቹ የሚያዚያ 1997 ሰልፎች እንኳ በፎቶ ከቀሩ ስንት ዓመት ሆናቸው?) ሰላማዊ ሰልፍ በሕገ መንግሥቱ የተሰጠ መብት መሆኑን የማያስታውሱ የመንግሥት ባለስልጣናት ያሉባት ኢትዮጵያ የተለያዩ ሕገ መንግስታዊ የመሰብሰብ መብትን በተግባር ለመተግበር የባለሥልጣን ይሁንታን እና ችሮታን (ማስፈራራት፣ ፍቃድ መቀማት…) የምትፈልገው አዲስ አበባ የሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 30 ከናቀች ቆይታለች፡፡

አንቀጾች እንዴት ይናቃሉ?

በተለምዶ የአፈጻጸም እንጂ የፖሊሲ ችግር የለብኝም የሚለው የኢሕአዴግ መንግሥት ሕገ መንግሥቱ ላይ ያሉ የመብት ጥሰቶችን ግን በአፈጻጸም ደረጃም ሲቀበል አይታይም፡፡ የመሻሻል ዕድሉን ጠባብ የሚያደርገው አንዱ የመንግሥት ችግር ሕገ መንግሥታዊ መብቶች በተደጋጋሚ መጣሳቸውን አለማመኑ ነው፡፡ ይህንን ተከትሎ ለተለያዩ ኃላፊነት ላለባቸው አስተዳደራዊ ሰዎች የሚሰጠው ቅጥ ያጣ ታማኝነትን መሠረት ያደረገ ስልጣን አንቀጾችን በቀላሉ እንዲጣሱ ይረዳል፡፡ ከሕገ መንግሥቱ በላይ የፓርቲ የበላይትን የሚያስቀድመው የኢሕአዴግ መንግሥት የፓርቲ ስልጣኑን እና ታማኝነቱን ካረጋገጠ ሕገ መንግሥቱን ማክበር እና አለማክበሩ የመንግሥት ስልጣን መስፈርት አለመሆኑ የቀድሞ ጠ/ሚኒስተርም ቢሆን ያረጋገጡት ሐቅ ነው፡፡

ሌላው ሕገ መንግሥቱ ላይ የተጠቀሱትን መብቶች በግልጽ የሚጣሱባቸው መንገዶች አንዱ ያለምንም ማቅማማት ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረኑ ሕጎችን ማውጣት እና ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ ከነዚህ መካከል ዋና ዋናዎቹ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማኅበራት አዋጅ፣ የተሻሻለው የፕሬስ አዋጅ እና የፀረ-ሽብርተኛነት ሕጉ ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ አዋጆች በሕገ መንግሥቱ የተሰጡ መብቶችን ከመሸራረፋቸውም በላይ ገለልተኛ ተቋማት መብቶችን እንዳያስተዋውቁ ያደረጉና እና ዜጎች ስለሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው እንዲያውቁ የሚደረጉ ጥረቶችን የገደሉ ናቸው፡፡

ዜጎች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን የሚያስከብሩባቸው ሁኔታዎች የሚመቻቹት መብቶቻውን በደምብ እንዲያውቁና እንዲጠይቁ በማበረታታት ቢሆንም መንግሥት ከስርዓተ ትምህርት ጀምሮ እስከተቋማት ድረስ የመብት ማስተዋወቂያና መጠየቂያ መንገዶቹን ከመገደቡም ባለፈ ሌሎች ተቋማት ተመሳሳይ ኃላፊነት እንዳይወጡ ኢ-ሕገ መንግስታዊ አዋጆችን መጠቀሙ የመብቶችን ጉዳይ አትኩሮት እንዳያገኝ እና በጠያቂዎቻቸውም ዘንድ እንደቅንጦት እንዲታዩ ምክንያት ሆኗል፡፡

የሕገ መንግሥቱ አንቀጾች እንዲከበሩ – መፍትሄው

መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት መብቶችን ማስተዋወቅ አንዲችሉ ሕገ መንግሥታዊ መብቶቻቸው፡፡ የመንግሥት ባለሥልጣናት የዜጎችን ሕገ መንግሥታዊ መብት እንደችሮታ ሳይሆን እንደ ግዴታቸው ይቁጠሩ፡፡ ይከበሩ፡፡ መንግሥት ራሱ ሕገ መንግሥቱን ያክብር፡፡

ሕገ መንግሥቱ ይከበር!!!

 

 

No comments:

Post a Comment