December 15, 2012 12:27 am By
Editor
ሰንደቅ ጋዜጣ ረቡዕ ታህሳስ 3 /2005 ዓ.ም
አንድነት ፓርቲ ሹም ሽር ያደርጋል
አቶ ስዬ አብርሃ ማስጠንቀቂያ ሊሰጣቸው ይችላል
በዘሪሁን ሙሉጌታ
የአንድነት ለፍትህና ለዴሞክራሲ ፓርቲ (አንድነት) ብሔራዊ ምክር ቤት በመጪው እሁድ በሚያካሂደው መደበኛ ስብሰባ በአራት ቁልፍ አጀንዳዎች ላይ ውይይት በማድረግ በፓርቲው አጠቃላይ እንቅስቃሴ ላይ ድክመት ባሳዩ አመራሮች ምትክ ሌሎች እንደሚመርጥ ለም/ቤቱ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ገለፁ።
በተመሳሳይ ለአንድ ዓመት ትምህርት ለመማር ወደ አሜሪካ የሄዱት የፓርቲው የብሔራዊ ም/ቤት አባል የሆኑት አቶ ስዬ አብርሃ ም/ቤቱን ለአንድ ዓመት አስፈቅደው ቢሄዱም በተደጋጋሚ ጊዜያት በም/ቤቱ ስብሰባ ላይ አለመገኘታቸው የም/ቤቱን አባላት አሳስቧል። በፓርቲው ሕገ-ደንብ መሠረት በፓርቲው የብሔራዊ ም/ቤት ስብሰባ ላይ ለሦስት ተከታታይ ስብሰባዎች አለመገኘት ከም/ቤቱ አባልነት የሚያሰርዝ መሆኑ እየታወቀ አቶ ስዬ አብርሃ ያለበቂ ምክንያት በፓርቲው እንቅስቃሴ ውስጥ አለመገኘታቸው በአንዳንድ የም/ቤቱ አባላት ዘንድ ቅሬታ ፈጥሯል።
ፓርቲው ባስቀመጠው የአምስት ዓመት የስትራቴጂ እቅድን ከመተግበር ባለፈ በፓርቲው ሊቀመንበር የተዋቀረው የካቢኔ አባላት ሁሉም በሙሉ ኃይላቸው የፓርቲውን የዕለት ተዕለት ተግባር ማከናወን ባለመቻላቸው ከፍተኛ የስራና የአፈፃፀም ድክመት መታየቱ የም/ቤቱን አባላት በሰፊው ያወያያል ተብሎ ይጠበቃል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል ከፓርቲው በክብር ተሰናብተው የነበሩት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራሁ እና የቀድሞው የአዲስ አበባ ወጣቶች ፌዴሬሽን ስራ አስፈፃሚ አባል የነበረው እና “ባለራዕይ የወጣቶች ማኅበር” ሊቀመንበር ወጣት ሐብታሙ አያሌው የፓርቲውን የአባልነት መስፈርቶች ሳያልፍ የፓርቲው ከፍተኛ የስልጣን አካል ወደሆነው የብሔራዊ ም/ቤት አባል ቢሆኑም ወደ አመራርነት ሊመጡ የሚችሉበት ሁኔታ እንደሚፈጠር ከም/ቤቱ አካባቢ የሚወጡ መረጃዎች እየጠቆሙ ነው።
የአንድነት ፓርቲ የብሔራዊ ምክር ቤት ሰብሳቢ የሆኑት አቶ ዘካሪያስ የማነብርሃን በመጪው እሁድ የሚካሄደውን የብሔራዊ ምክር ቤቱን መደበኛ ስብሰባ በተመለከተ ለሰንደቅ ጋዜጣ እንደገለፁት፤ በመጪው እሁድ ታህሳስ 7 ቀን 2005 ዓ.ም መደበኛ ስብሰባው እንደሚካሄድ አረጋግጠዋል። በመደበኛ ስብሰባው አራት የሚሆኑ አጀንዳዎች እንደሚነሱ ገልፀዋል። አራቱ አጀንዳዎች ያለፉ ቃለ ጉባኤዎችን መርምሮ ማፅደቅና ከቃለ-ጉባኤው በሚነሱ ጉዳዮች ላይ መወያየት፣ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴውን የሦስት ወራት የስራ አፈፃፀም ሪፖርት ማዳመጥ እንዲሁም የፓርቲውን የፋይናንስ መመሪያ መርምሮ ማፅደቅና የልዩ ግብረኃይል ሪፖርት ማዳመጥና ውሳኔ ማስተላለፍ መሆኑን አመልክተዋል።
“ልዩ ግብረኃይል” የሚባለው አካል ሥራና ተግባር በተመለከተ አቶ ዘካሪያስ ተጠይቀው ልዩ ግብረኃይሉ ህዳር 1 ቀን 2005 የፓርቲው ብሔራዊ ምክር ቤት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የተቋቋመ ኮሚቴ መሆኑንና ይህ ኮሚቴ ከፓርቲው የፖለቲካ ቋሚ ኮሚቴና ከፓርቲው የኤዲቶሪያል ቦርድ ኮሚቴ ጋር በጥምር የተቋቋመ መሆኑን፣ ተልዕኮውም የፓርቲው ልሳን “ፍኖተ ነፃነት” ከሕትመት እንዲወጣ የተደረገበትን አፈና እንዲቀለበስ የሚያደርግ እንዲሁም መንግስት በሃይማኖት ጣልቃ የመግባቱን ሁኔታ የሚያጣራ ነው። በተጨማሪም በአዲስ አበባ በዘመቻ መልክ እየፈረሰ ያለውን የዜጎች መኖሪያ ቤቶች ሁኔታ የሚከታተል፣ ከኑሮ ውድነቱ ጋር የተያያዙ ችግሮችን የሚመረምርና መረጃውን ለሕዝቡ በማድረስ ሕዝቡም በችግሮቹ ላይ ድምፁን እንዲያሰማ የሚያደርግ ኮሚቴ መሆኑንም አብራርተዋል።
በተጨማሪም ህዳር 1 ቀን 2005 ዓ.ም በተደረገው የም/ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባ የፓርቲውን የስምንት ወራት የስራ እንቅስቃሴ መገምገሙንና ማፅደቁን ያስታወሱት አቶ ዘካሪያስ የፀደቁት እቅዶች ምን ያህሉ ተተግብረዋል? ምን ያህሉስ አልተተገበሩም የሚለው መገምገሙን ገልፀዋል። በዚያ ግምገማ የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ብቻ ሳይሆን ብሔራዊ ም/ቤቱም እራሱን መገምገሙን ገልፀዋል። በቀጣይ ታህሳስ 7 ቀን 2005 በሚካሄደው ስብሰባ ቀደም ሲል በተካሄዱ ግምገማዎች መሠረት የተሰሩ ስራዎች ከእቅዳችን አኳያ በቂ እንዳልሆኑና ከአቅም በታች እንደሆኑ ግንዛቤ በመውሰዱ በታህሳስ 7ቱ ስብሰባ ላይ የፓርቲው ሊቀመንበር ዶ/ር ነጋሶ ካቢኔአቸውን እንደገና በውዘው አቅም ያላቸውን ሰዎች በካቢኔአቸው አካተው ይመጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ፣ ከስብሰባውም በኋላ ሹም ሽር እንደሚኖር ፍንጭ ሰጥተዋል።
ህዳር 1 ቀን ም/ቤቱ ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ የተቀበላቸው አዳዲስ የም/ቤት አባላት እነማን እንደሆኑና በምንስ መስፈርት ወደ ም/ቤቱ እንደተቀላቀሉ ከሰንደቅ ጋዜጣ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ዘካሪያስ ሲመልሱ፤ “ሰዎቹ ወደ ፓርቲው ምክር ቤት የገቡት በፓርቲው መተዳደሪያ ደንብ አንቀፅ 11 ንዑስ ቁጥር 11(1)ሐ እና 4 መሠረት ነው። የብሔራዊ ም/ቤቱ ከ10 ያላነሱ አባላት ለፓርቲው ከፍተኛ አስተዋፅኦ ሊያበረክቱ ይችላሉ ብሎ ያመነባቸውን ሰዎች ም/ቤቱ አባል ማድረግ ይችላል በሚለው መሠረት ባላቸው ተነሳሽነትና ቁርጠኝነት ተገምግመው ወደ አራት የሚሆኑ አዳዲስ አባላት ወደቋሚ የምክር ቤት አባልነት ተሸጋግረዋል” ሲሉ መልሰዋል።
እንደ አቶ ዘካሪያስ ገለፃ ከላይ በጠቀሱት ሁኔታ የም/ቤቱ አባል የሆኑት ቀደም ሲል ከፓርቲው በገዛ ፈቃዳቸው ለቀው የነበሩትና የፓርቲው ተቀዳሚ ሊቀመንበር ሆነው ሲሰሩ የነበሩት ኢንጂነር ግዛቸው ሽፈራው፣ አቶ አበበ አካሉ፣ አቶ ተስፋዬ ረታ እና ወጣት ሀብታሙ አያሌው መሆናቸውን ዘርዝረዋል።
ወጣት ሐብታሙ አያሌው በዋናነት ወጣቶችን ማዕከል ባደረገው የሲቪል ሶሳይቲ ድርጅት መሪ ሆኖ ሳለ እንዴት ወደ ም/ቤቱ ሊገባ እንደቻለ የተጠየቁት አቶ ዘካሪያስ፤ “ወጣት ሐብታሙ ግልፅ በሆነ መንገድ አባል ሆኗል። የሲቪክ ማኅበራትን የመሩ ግለሰቦች የፓርቲ አባል አይሆኑም የሚል ሕግ ባለመኖሩ ወጣቱ የፖለቲካ ንቃቱ ታይቶ የበሰለ የፖለቲካ አመለካከት ያለው መሆኑ ታይቶ ከፓርቲው ደንብ ጋር የማይጋጭ መሆኑ በሚገባ ተጣርቶ ነው አባል የሆነው” በማለት መልሰዋል።
ሆኖም ወጣት ሐብታሙ የፓርቲው ሕገ-ደንብ በሚጠይቀው መሠረት ከተራ አባል ተነስቶ ወደ ብሔራዊ ም/ቤት አባል የሚሆንበትን አሰራር ተከትሎ አባል ሆኗል ወይ? ለተባሉት አቶ ዘካሪያስ ሲመልሱ የፓርቲው የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ያልሆነን ግለሰብ በአባልነት መልምሎ ካፀደቀ በኋላ ለብሔራዊ ም/ቤት ማቅረብ ስለሚችል ወጣት ሐብታሙ የብሔራዊ ም/ቤት አባል ሊሆን እንደቻለ ነው የገለፁት። ቀደም ሲል እነ ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እና አቶ ስዬ አብርሃ በዚህ መልክ ወደ ፓርቲው መግባታቸውንም አስታውሰዋል።
አቶ ስዬ አብርሃ በተመለከተ ለአንድ ዓመት ለትምህርት ወደ አሜሪካን ሀገር ቢሄዱም ትምህርታቸውን ካጠናቀቁ በኋላ ወደ ፓርቲው አለመመለሳቸውን በተመለከተም አቶ ዘካሪያስ ተጠይቀው፣ ቀደም ሲል አቶ ስዬ ብሔራዊ ም/ቤቱን አስፈቅደው ለትምህርት ውጪ ሀገር መሄዳቸውን፣ ፓርቲውም የክብር አሸኛኘት ማድረጉን ነገር ግን የተባለው የትምህርት ጊዜ መጠናቀቁን አስታውሰዋል። ሆኖም አቶ ስዬ በትምህርት ላይ እያሉ የፓርቲውን ልዩ ልዩ ስራዎች ሲሰሩ መቆየታቸውን፣ ትምህርታቸውንም ካጠናቀቁ በኋላም በቅርቡ የመድረክ ልዑካን ቡድን ወደ አሜሪካ በሄደበት ወቅት ከልዑካን ቡድኑ ጋር በመቀላቀል ሲንቀሳቀሱ መቆየታቸውንም አስታውሰዋል። ይህም አቶ ስዬ ፓርቲው የሰጣቸውን ተልዕኮ እያከናወኑ ቢቆዩም ከዚህ በኋላ ስላለው ሁኔታ ግን ም/ቤቱ የሚወያይበት ጉዳይ ይኖራል ብለዋል። ባለፈው ህዳር 1 ቀን 2005 ዓ.ም በተደረገው የም/ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባ ላይ ይህ ጉዳይ ተነስቶ ውይይት እንደተደረገበት አመልክተዋል። የብሔራዊ የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ አቶ ስዬንም በቀጥታ አነጋግሮ ሪፖርት ይዞ እንዲመጣ መመሪያ እንደተሰጠም ጨምረው ገልፀዋል። በመሆኑም አቶ ስዬን በተመለከተ የፓርቲው ሊቀመንበር ለብሔራዊ ም/ቤቱ በሚያቀርቡት ሪፖርት ላይ ተንተርሰው ም/ቤቱ መመሪያ ይሰጥበታል ብለዋል።
የፓርቲው ሊቀመንበር የሚያቀርቡት ሪፖርት ታይቶ አቶ ስዬ ያለበቂ ምክንያት ወደፓርቲው እንደማይመለሱ ከተረጋገጠ ማስጠንቀቂያ ሊሰጣቸው እንደሚችልም አንዳንድ የም/ቤቱ አባላት በተለይ ለሰንደቅ ገልፀዋል።
በተያያዘ ም/ቤቱ በአዲስ አበባ አስተዳደር ምርጫ በተመለከተ ፓርቲው በቅርቡ 33ቱ ፓርቲዎች ባቋቋሙት ስብስብ ውስጥ ያለውን አካሄድ ከመረመረ በኋላ አቋም እንደሚወስድም ገልፀዋል።
የአንድነት ፓርቲ ብሔራዊ ም/ቤት 40 ቋሚ ኮሚቴ አባላት ያሉት ሲሆን 15 ተለዋጭና አምስት የኦዲትና ኢንስፔክሽን አባላት የሚገኙበት ከጠቅላላ ጉባኤው ቀጥሎ ከፍተኛው የፓርቲው የውሳኔ ሰጪ አካል ነው።
No comments:
Post a Comment