Wednesday, December 12, 2012

አልአሙዲ ያጠሩትን መሬት ተነጠቁ

 

huda mexico bldg

 የሼክ መሐመድ ሁሴን አልአሙዲ ኢንቨስትመንት ላይ ጥያቄ ያላቸው ጥቂት አይደሉም። የራሳቸውን ህንጻ ከመጨረስ ይልቅ በኪራይ አንድ ህንጻ የሚያሰራ ገንዘብ ለዓመታት ሲከፍሉ ማየትና መስማት የተለመደ ነው። የንግድ ሰዎች ይህንን ዝንባሌያቸውን ከነጋዴ የሚጠበቅ እንዳልሆነ ይናገራሉ። በዙሪያቸው ተሰባስበው ያሉትም ቢሆኑ አመቺ ቦታ ሲያገኙ በዚሁና በሌሎች ጉዳዮች ያሟቸዋል።

ናኒ ህንጻ

ጊዮን ሆቴል አጠገብ የተሰራው የናኒ ህንጻ ሲጀመር የተወለደ ህጻን አስራ ሁለት ዓመት ሲሞላው ነው ያለቀው። ከጊዮን ሆቴል ፊትለፊት ለአስራ ሁለት ዓመት ለህንጻው መጋዘን ሆኖ ሲያገለግል የነበረው የአዲስ አበባ ስታዲየም የመኪና ማቆሚያ ተገቢው ክፍያ ሳያገኝ ቢኖርም የሳቸውን ፎቶ በስታዲየም ውስጥ ለመለጠፍ ቀዳሚ ነው። አሁን መለስ መጡና አሳነሷቸው እንጂ ስታዲየሙ የእርሳቸው የሚመስልበት አጋጣሚም ነበር።

“መበደር፣ መጀመርና ማጠር እንጂ መክፈል፣ መጨረስና አጥር ማፍረስ አይወዱም” የሚባሉት ሼኽ መሐመድ፣ ግርግር ባለበት ቦታ መታየትና፣ አጋጣሚዎችን በመጠበቅ በሚያበረክቱት ስጦታ ስማቸው ከመነሳቱ ውጪ ከብድርና ከእዳ የጸዳ ፕሮጀክትም ሆነ ንብረት ባገር ውስጥ እንደሌላቸው የሚናገሩት ቀርበው የሚያውቋቸው ናቸው። በሌላ በኩል ብድር የሌለበት ንግድ ሊኖር አይችልም፣ ዋናው የተበደሩትን መክፍሉ ላይ ነው በሚል የሚደግፏቸውም አሉ።

በአዲስ አበባ በቦሌ፣ በልደታና በአራዳ ክፍለከተማ የያዟቸው መሬቶች በርካታ ቢሆኑም እንደ ሌሎች ባለሃብቶች ግንባታ አላከናወኑም በሚል ሲቀጡ አይሰማም። መሬታቸውም ሲወሰድ አይታይም። ባለስልጣናትም የእርሳቸው ድርጅቶች ላይ ውሳኔ ለመውሰድ አይደፍሩም። በተለይም መሃል ፒያሳ የታጠረው አጥር ላለፉት አስራ ሁለት አመታት እግረኞችን ጤና መንሳቱ እየታወቀ የተናገረ የለም። የአዲስ አበባ አስተዳደር አፍንጫው ስር ህዝብ መረማመጃ በማጣት ሲሰቃይ ተመልክተው ውሳኔ አለማሳለፋቸው አነጋጋሪ ነበር።

ከፕሮጀክቱ መጀመር በላይ ኩማ ደመቅሳ አዲስ አበባን ሲረከቡ አንድ ሚስጥር ይፋ ሆነ። የባለሃብቱ ድርጅት ከሆኑት መካከል አንዱ ሆነው ሁዳ ሪል ስቴት አዲስ አበባ መሃል ፒያሳ አራዳ የተሰጠው ሰፊ መሬት ከሊዝ ክፍያ ነጻ በስጦታ መሆኑ ታወቀ፤ አዲስ አበባ እምብርቷ ላይ ዘመናዊ የገበያ አዳራሽ (mall) ይሰራል ተብሎ ዲዛይኑ ቀረበ። ባለስልጣኖች ዲዛይኑን ሲመለከቱ የምርቃት ሪባን መቁረጥ ታያቸው። ከሊዝ ነጻ የተሰጠው ይህ ሰፊ መሬት ሳይገነባ አፈር ቁፋሮ እያካሄደ ዓመታትን አስቆጠረ።

ቀደም ሲል ጀምሮ የሚነገር ቢሆንም የአዲስ አበባ አስተዳደር ካለፈው ወር ጀምሮ ጠንካራ ርምጃ ለመውሰድ ማቀዱ፣ ባለፈው ሳምንት ደግሞ የዚሁ ርምጃ አካል የሆነው ውሳኔ ሃሳብ ጫፉ መነካቱን ሪፖርትር ለንባብ አብቅቶ ነበር። ሪፖርተር በነካ እጁ ሰሞኑን የባለሃብቱ አንድ ድርጅት የሆነው ሁዳ ሪል ስቴት ሜክሲኮ ዋቢሸበሌ ሆቴል አጠገብ ወስዶት ነበረውን መሬት እንደተነጠቀ አስነብቧል።

የሁዳ ሪል ስቴት መንትያ ሕንፃ ዲዛይን

በዚሁ ዜና መሰረት ሁዳ ህዳር 25 ቀን 2005 ዓ ም የተነጠቀው መሬት 6‚400 ካሬ ሜትር ሲሆን ቀደም ሲል ግንባታው ሳይጀመር ላለፉት ስምንት ዓመታት ታጥሮ የተቀመጠ ቦታ ነው። ይኸው ቀደም ሲል የመኪና መለማመጃ የነበረው ቦታ ሁለት ዘመናዊ ባለ ሃያ ፎቅ (እስከ 25 ሊደርስም ይችላል) መንትያ ህንጻዎች ይገነቡበታል ተብሎ እቅድና ዲዛይን የቀረበበት ነበር።

የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮው በጻፈው ደብዳቤ ሁዳ ሪል ስቴት በገባው ውል መሥሪያ ግንባታ ባለመጀመሩ ለቦታ ባለቤትነት የተሰጠው ካርታ መምከኑን ሪፖርተር ጽፏል። አያይዞም ቁፋሮው በሚገባ ተከናውኖ ሕንፃውን መገንባት ባለማስቻሉና አስተዳደሩ በኩባንያው ተግባር ትዕግሥቱ በመሟጠጡ ዕርምጃ መውሰድ እንደቻለ ሪፖርተር የቢሮው የሥራ ኃላፊዎችን ጠቅሶ አስታውቋል።

የሁዳ ሪል ስቴት መንትያ ሕንፃ ዲዛይንን የሠራው ናሽናል ኮንሰልት ኩባንያ ነው፡፡ ግዙፉና ውበት የተላበሰው የሕንፃ ዲዛይን መሬት ላይ ባለማረፉ ፕሮጀክቱ እንዲመክን ተደርጓል፡፡ ሼክ መሐመድ ሁሴን አሊ አልአሙዲ በሚድሮክ ኢትዮጵያ፣ በሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕና በደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ሥር በርካታ ኩባንያዎች አሏቸው፡፡ በእነዚህ ግሩፖች ሥር ሁዳ ሪል ስቴት፣ ሚድሮክ ኮንስትራክሽን፣ ሚድሮክ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤትና ሚድሮክ ፋውንዴሽን በኮንስትራክሽን ሥራዎች ላይ የተሰማሩ ኩባንያዎች ናቸው፡፡

ሁዳ ሪል ስቴት በሚረከባቸው ቦታዎች ላይ ሚድሮክ ኮንስትራክሽንና ሚድሮክ ፋውንዴሽን የግንባታ ሥራዎችን የሚሠሩ ቢሆንም፣ ሚድሮክ ኮንስትራክሽን በሥራው ውጤታማ ባለመሆኑ ካለፉት ወራት ወዲህ ግንባታውን የማካሄዱን ሥራ ተነጥቆ በደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ሥር ለሚገኘው ሚድሮክ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት እየተሰጠ ነው፡፡

ለሁዳ ሪል ስቴት የተሰጠው መሬት መነጠቁንና በቀጣይነት ሁዳ ሪል ስቴት ስለሚወስደው ዕርምጃ የደርባ ሚድሮክ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሌ አሰግዴ ቢጠየቁም፣ ከከተማ ውጭ በመሆናቸው ጉዳዩን እንዳልሰሙ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

የሁዳ ሪል ስቴት የሜክሲኮ አደባባይን ፕሮጀክት መሬት የነጠቀው የአዲስ አበባ አስተዳደር፣ ሁዳ ሪል ስቴት በመሀል ፒያሳ ከከተማው አስተዳደር ሕንፃ ፊት ለፊት የተሰጠውን መሬትም እንደሚነጥቅ በቅርቡ አስጠንቅቋል፡፡

ፒያሳ የታጠረው ቦታ ከአትክልት ተራ በኩል

ኩባንያው ከ15 ዓመታት በፊት በመሀል ፒያሳ 36 ሺሕ ካሬ ሜትር ቦታ ቢሰጠውም በገባው ውል መሠረት ልማቱን ማካሄድ አልቻለም፡፡ በከንቲባ ኩማ ደመቅሳ የሚመራው የከተማው አስተዳደር ሥልጣኑን እንደተረከበ ቦታውን ለመንጠቅ ሙከራ ቢያደርግም፣ ከንቲባ ኩማና የወቅቱ የከተማው አስተዳደር ሥራ አስኪያጅ አቶ መኩሪያ ኃይሌ ከሼክ አልአሙዲ ጋር ባካሄዱት አንድ ሰዓት የፈጀ ውይይት፣ ኩባንያው በአሥራ አምስት ቀናት ውስጥ ግንባታውን እንዲጀምር ስምምነት ላይ ተደርሶ ተጨማሪ ጊዜ ተሰጥቶ ነበር፡፡ በዚህ መሠረት ግንባታውን አጓትቷል ከተባለው ሚድሮክ ኮንስትራክሽን ፕሮጀክቱ ተነጥቆ ለሚድሮክ ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤት ተሰጥቶ ነበር፡፡

ነገር ግን ከዓመታት በኋላም ፕሮጀክት ጽሕፈት ቤቱ በተደረገው ስምምነት መሠረት ግንባታውን ሊያከናውን ባለመቻሉ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመሬት ልማትና ማኔጅመንት ቢሮ ኃላፊ አቶ ጌታቸው አምባዬ ኩባንያው ዕርምጃ ሊወስድበት እንደሚችል ፍንጭ መስጠታቸውን ባለፉት ሳምንታት የወጡ የዜና ጥንቅሮች ጠቁመዋል።

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

 

 

No comments:

Post a Comment