ኢህአዴግና ኢህአዴግ ተፈራርተዋል
“[ሙስና] የስርዓቱ አደጋ ነው” ርምጃ ግን የለም!!
December 26, 2012 12:25 pm By Editor
“ትልቅ ጫካ ሰርታችሁ የኛንም የናንተንም ሌቦች መደበቅ በመቻላችሁ ሁሉንም መመንጠር ስላልቻልን እየተተራመስን ነው” በማለት ጣታቸውን ወደ ነጋዴው ህብረተሰብ በመቀሰር ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር በአገሪቱ ያለውን ሙስና አስከፊነት በገለጹበት መድረክ “ስልጣን የመክበሪያ ብቸኛው መንገድ በሆነበት አገር ዘላቂ ሰላም ይኖራል ማለት ዘበት ነው። በኪራይ ሰብሳቢነት እንደ መንግስትም፣ እንደ ባለሃብትም መቀጠል አንችልም። እንደ ሶማሌ ነው የምንሆነው። እንተራመሳለን። በድጎማ እየኖርን ሙስናው ከከፋ አገር የሌለው ባይተዋር እንሆናለን” ሲሉ የጉዳዩን አሳሳቢነትና በኢህአዴግ ስሌት ሙስናው የሚያስከትለውን የመጨረሻ ጣጣ አመላክተው ነበር።
“በሁሉም አቅጣጫ እየታረድን ነው” ሲሉ የፖለቲካውና የሙስናውን መዘዝ ያመለከቱት አቶ መለስ፣ ተፈጥሯል ያሉት ጫካ አይጥና እባብ ብቻ ሳይሆን ዝሆንም እንደሚደበቅበት ሲገልጹ በማግስቱ “ዝሆኖቹን” ይለዩና እሳቸው በሁሉም ችግር ውስጥ የማለፍ ብቃት እንዳለው የሚገልጹት ኢህአዴግ ማንነቱን ያሳያል ተብሎ ሲጠበቅ ሁሉም ነገር ተረት መሆኑ የስርዓቱን ተያይዞ በሙስና መበስበስ አመላካች እንደሆነ አስተያየት ሰጪዎች ይስማማሉ።
ይህ ሁሉ ካለፈ በኋላ የመንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ለህዝብ እንዲተላለፍ በመወሰን ያካሄዱት ስብሰባ እንደተባለው በይፋ ሙሉ በሙሉ መረጃ የማግኘት መብት አለው ከሚባለው ህዝብ ጆሮ እንዳይደርስ ቢደረግም በተባራሪ የተገኙት መረጃዎች አስገራሚ ነበሩ። ከሁሉም በላይ የኢንፎርሜሽን መረብ ደኅንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ሚኒስትሩ ደብረጽዮንና የስኳር ልማት ድርጅት ፊት አውራሪ የሆኑት አባይ ጸሃዬ “ግንዱን ካልቆረጥነው፣ ግድግዳውን ካላፈረስነው ጣጣው ብዙ ነው” በማለት የተናገሩት ስለ ሙስና ነበር።
በኢትዮጵያ በሙስና የአገሪቱን ሃብት የሚጋልቡበት፣ የፍርድ ቤቶችን ውሳኔ የሚያዛቡ፣የራሳቸው አገር፣ ህግና፣ አስተዳደር የመሰረቱ ስለመኖራቸው በስፋት መነገር ከጀመረ ሰንብቷል። እነዚህ ከህግና ከስርዓት ውጪ የሆኑ አካሎች ከባለስልጣናት ጋር በሽርክና፣የባለስልጣን ሚስቶችን በድርጅታቸው ውስጥ በማስገባት፣ የባለስልጣን ዘመዶችን በየጥጋጥጉ በመወተፍ በቅምጥ ጋዜጦች፣ አርቲስቶችና በራሱ በኢህአዴግ መገናኛዎች ሳይቀር እየተወደሱ አገሪቱን ሲዘሉባት መመልከት እንደተባለው አገሪቱ እንደ አገር መቀጠሏ አሳሳቢ መሆኑንን የሚያረጋግጥ እንደሆነ በስፋት እየተተቸበት ነው። አቶ መለስም አስቀድመው የተናገሩት ይህንኑ ራሳቸው ገንብተው ራሳቸው ማፍረስ ያቃታቸውን የሙስናና ልቅነት አሠራር ነበር።
ህዝብ ሁሉንም ጠንቅቆ እንደሚያውቅ በተለያዩ አጋጣሚዎች ቢገልጽም ሰሚ ማጣቱ አሁን አገሪቱ ላይ ከሰፈነው የኑሮ ቀውስ፣ የህዝብ ቁጥር መጨመር፣ የፖለቲካ አለመተማመን፣ የሃብት ክፍፍል፣ የሃይማኖት የመብት ጥያቄዎችና “ማን እየበላ ማን ጦሙን ያድራል” ከሚለው የመኖርና አለመኖር ጥያቄ ጋር ተዳምሮ አቶ መለስ እንዳሉት እንደ መንግስትም፣ እንደ ባለሃብትም መቀጠል የማይቻልበት ደረጃ ሊደረስ ይችላል የሚለው ፍርሃቻ ሚዛን የሚደፋ እየሆነ ነው።
በተደጋጋሚ በሙስና ጉዳይ ላይ የሚጽፈው ሪፖርተር በእሁድ እትሙ ጠንካራ ርዕስ በመስጠት በርዕሰ አንቀጹ “ትልቁ ጥያቄ ተግባሩ የት አለ? የሚል ነው፡፡ የመንግሥት ሌቦች ተራ ሌቦች አይደሉም፡፡ አደገኞች ናቸው፡፡ ምክንያቱም በገንዘብ የታጀቡ ናቸው፡፡ በሥልጣንም የተደገፉ ናቸው፡፡ ምግባረ ብልሹነት የተጠናወታቸው ስለሆኑ ሕገወጥ ገንዘብና ሥልጣናቸውን ላለማጣት ሕግን ከመጣስና ወንጀል ከመፈጸም ወደኋላ አይሉም፡፡ ሌላውን አስወግደው እነሱ ብቻ የሚቆጣጠሩትና የእነሱን ፍላጎት ብቻ የሚያረካ መንግሥት ከማቋቋም ወደኋላ አይሉም፡፡ የመንግሥት ሌቦች ካልተወገዱ የሌቦች መንግሥት ያቋቁማሉ ያልነውም ለዚህ ነው” ሲል የተግባራዊነት ጥያቄ አንስቷል።
ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለምልልስ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን ያወገዙት የኢህአዴግ ፅ/ቤት ሃላፊ ከአቶ ሬድዋን ሁሴን ሙስናን አስመልክቶ ለተጠየቁት “… በዚህ አገር ላይ፡፡ ሲሾም ያልበላ የሚባል በጥረት ያልተደገፈ፣ በብልጥነት አስተምህሮ ላይ የተመሠረተ አካሄድ ነበር፣ ይሄን መስበር ያስፈልግ ነበር፡፡ ይሄንንም ለመስበር አመለካከቱን ደጋግሞ መውቀጥ መቀጥቀጥ ያስፈልጋል፡፡ በርግጥም የስርዓቱ አደጋ ነው፣ እንታገለዋለን፡፡ ዕድገታችንን የሚፈታተነን አንዱ አደጋም ይሄ ነው” የሚል መልስ ነበር የሰጡት።
የፌደራሉ የስነምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽነር አሊ ሱሌማን “መንግስት በከፍተኛ ደረጃ ሙስና ላይ እንድንዘምት መመሪያ ሰጥቶናል” በማለት በሪፖርተር ጋዜጣ ላይ ተናግረዋል። ይህንኑ በተናገሩበት አንደበታቸው ከስዊዝ ባንክ እንዲመለስ የተደረገው ገንዘብ ለማን ተሰጠ ለተባሉት የሼኽ መሐመድ አላሙዲንን ስም መጥራት ፈርተው “ይለፈኝ” ማለታቸውን ተረድተናል።
ጎልጉል ያነጋገራቸው እንደሚሉት የፖለቲካውን የበላይነት በመጠቀም በብርሀን ፍጥነት ብር የሰበሰቡትን፣ ህንጻ የገነቡትን፣ አስመጪና ላኪ የሆኑትን፣ ኢንዱስትሪ የከፈቱትን፣ ኮንትሮባንድ የሚነግዱትን፣ ቀረጥ የማይመለከታቸውን “አይጥና ዝሆኖች” ከፍተኛ የአገሪቱን ፕሮጀክቶች በብቸኛነት የተቆጣጠሩትን፣ ጨረታውንና ግዢውን በብቸኛነት የተረከቡትን፣ ተለጣፊ የሚባሉትን፣ ጉቦ አቀባባዮቹን፣ አማላጅ ሆነው ጉዳይ በማስፈጸም የሚነግዱትን የመንግስት ሌቦች፣ በብድር ገንዘብ ባለስልጣን እያሳከሙ የሚዘመርላቸው፣የፓርቲዎች ንብረት ናቸው ስለሚባሉት “እርም ተቋሞች” ህዝብ ጠንቅቆ ያውቃል። ባለፈ ባገደመ ቁጥር ስም እየሰየመ የሚቆጥራቸው ሃብቶች መነሻቸው፣ መድረሻቸውና የማን እንደሆኑ ኮከብ ከደረደሩት ወታደሮች ጀምሮ በዝርዝር ያውቃቸዋል።
ጥያቄው ተራ ዜጎች የሚያውቁትን “እርም የተሞሉ” ሃብቶች በደህንነት የተደራጀው የጸረ ሙስና ኮሚሽንና የባልና ሚስት የመኝታ ቤት ወሬ ሳይቀር የሚለቅመው ኢንሳ ዝምታን የመረጡበት አግባብ ነው። “መለስ የቆፈሩት ጉድጓድ” በሚል ርዕስ ለጎልጉል ቃለ ምልለስ የሰጡት የኢህአዴግ ሰው “የስርዓቱ አይነተኛ መገለጫ ሆን ብሎ በሙስና ማበስበስ ነው” ይሉና ስለዝምታው ሲናገሩ “አቶ መለስ ሁሉንም ያውቃሉ። ልንካው ቢሉ ለራሳቸውም አደጋ ነው። ሙስናው ውስጥ የደህንነት ኃይሉ፣ መከላከያው፣ ባለስልጣናቱ፣ … ተነክረውበታል። ስለዚህ ማን ማንን ይነካል?” ማንስ በማን ላይ ይመሰክራል?” በሚል በወቅቱ አስገራሚ የተባለ ማብራሪያ ሰጥተው ነበር።
በድርጀት ደረጃ ሙስና የስርዓቱ አደጋ ነው የሚል አቋም ቢያዝም ርምጃ ለመውሰድ ማን ማንን ይደፍረዋል የሚለው መከራከሪያ ኢህአዴግና ኢህአዴግ ተፈራርተዋል ወደ ሚለው ድምዳሜ አድርሷል። የአዲስ አበባ አስተዳደር ጊዚያዊ ከንቲባ የነበሩት አቶ ብርሃነ ደሬሳ “ዜጎቿ ምግብ ማግኘት ባልቻሉባት አገር ውስጥ የሚከናወነው ሙስና ስጋ ከሌለው አጥንት ላይ ስጋ ፍለጋ የመጋጥ ያህል ነው” በማለት ሙስና የደረሰበትን አስከፊ ደረጃ መግለጻቸው የሚታወስ ነው።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡