Saturday, December 15, 2012

ኢህአዴግ እያስታመመ ነው

የአቡነ መርቆሪዮስ ጉዳይ አልተቋጨም

peace and unity

 የአቡነ መርቆርዮስ ወደ አገር ቤት መመለስ ከስምምነት ላይ ተደረሰ፡፡ ልዩነት የተፈጠረው መንበራቸውን በመረከባቸው አብይ የቤ/ክርስቲያን ቀኖና ላይ ነው፡፡

ይህ የተገለጸው ከህዳር 26 እስከ ህዳር 30፤ 2005ዓም (December 5 – 9, 2012) በዳላስ ከተማ በቴክሳስ ጠቅላይ ግዛት በአገርቤቱ ሲኖዶስና በአሜሪካ ከሚገኘው ስደተኛ ሲኖዶስ ተወካዮች ድርድራቸው ካጠናቀቁ በኋላ ባወጡት የጋራ መግለጫ ነው፡፡

የጋራ መግለጫው ከመውጣቱ በፊት ፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ አቡነ መርቆሪዮስ ከነሙሉ መንበራቸው አገር ቤት እንዲመለሱ የሚጠይቅና ማረጋገጫ የሚሰጥ ደብዳቤ ልከው ነበር፡፡

“የኔው የራሴ ደብዳቤ ነው” በማለት ለቪኦኤ የአማርኛ ክፍል በቃላቸው ጭምር ያረጋገጡት ፕሬዚዳንቱ ከአፍታ በኋላ “ያለሥልጣኔ ገብቼ የፈጸምኩት ነው” በማለት ደብዳቤውን መሰረዛቸውን አስታውቀው ነበር፡፡ ከጀርባው “እንዲህ ያለ ጣጣ አልመሰለኝም” በሚል ድፍን ምላሽ በመስጠት “የቀድሞ አቋሜን ትቸዋለው” ሲሉ ለቪኦኤ መልስ የሰጡት የመጀመሪያ ሃሳባቸውን በመቃወም ከአቡነ ህዝቅኤል ወቀሳ እንደተሰነዘረባቸው አልሸሸጉም፡፡

በቀጣይ አሜሪካ ሬዲዩ ለድጋሚ ጥያቄ ለፕሬዚዳንቱ ያደረገው የስልክ ጥሪ “እኔ የፖለቲካ ጉዳያቸው ልዩ አማካሪያቸው ነኝ” በማለት አቶ አሰፋ ከሲቶ ጉዳዩን አስመልክቶ የሰጡት መልስ ዳላስ በተደረገው ድርድር የአገርቤት ተወካዮች የሚይዙትን አቋም አስቀድሞ ያንጸባረቀ ነው፡፡

የመንግሥት አቋም ምን እንደሆነ የተናገሩት አቶ አሰፋ፤ አቡነ መርቆሪዮስ ወደአገራቸው መግባት እንደሚችሉ፤ ፍላጎት ካላቸው ለርዕሳነ ፓትሪያርክነት መወዳደር መብታቸው እንደሆነ፤ ቀደም ሲል የተወሰነላቸውን ውሳኔ ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ መንግሥት ተቃውሞ እንደሌለው ጨምረው አብራርተዋል፡፡

በዚሁ ሬዲዮ አስተያየታቸውን እንዲሰጡ የተጠየቁት አቡነ ህዝቅያስ ፕሬዚዳንቱ ስለተናገሩት ሲጠየቁ ያስቀደሙት “ኢህአዴግ ስለሾማቸው ፕሬዚዳንቱ መዘላበድ አይችሉም” በማለት የፕሬዚዳንቱን ንግግርና አካሄድ በማውገዝ ነበር፡፡

ፕሬዚዳንቱ በጻፉት ደብዳቤ መንግሥትም መቆጣቱን ያስታወቁት አቡነ ህዝቅኤል፤ አቡነ መርቆሪዮስ ሟቹ አቡነ ጳውሎስ ፓትሪያርክ ከመሆናቸው በፊት የተወሰነላቸውን ተግባራዊ ከማድረግ ውጪ አዲስ ነገር እንደሌለ ተናግረዋል፡፡ አቡነ ህዝቅኤል እንዳሉት አቡነ መርቆሪዮስ በመረጡት ቦታ አስፈላጊውን ሁሉ ተሟልቶላቸው ለአገራቸው አፈር እንዲበቁ ከተወሰነው ውጪ የሚደረግ ነገር እንደሌለ ጨምረው አስታውቀዋል፡፡

ከመንግሥትና ከአገርቤት ሲኖዶስ በኩል ያለው ተመሳሳይ አቋም እየተገለጸ ባለበት ወቅት በውጪ ባለው ስደተኛው ሲኖድና በአገርቤቱ ሲኖድ መካከል አራት አራት ተወካዮች ያካተቱበት ድርድር እየተካሄደ ነበር፡፡ በድርድሩ መጨረሻ ሁለቱ አካላት በጋራ ባወጡት መግለጫ አንኳር ጉዳይ ከላይ የተቀመጠው የውሳኔ ሃሳብ ላይ የሚያጠነጥን ነው፡፡ በውጪ አገር የሚኖረው ሲኖዶስ አቡነ መርቆሪዮስ አገር ቤት ከነሙሉመንበራቸው ይመለሱ ሲል የአገርቤቱ ደግሞ ደግሞ ከላይ የተጠቀሰውን የመንግሥትንና የወከላቸውን ሲኖዶስ መሰረታዊ አቋም ከማስጠበቅ የዘለለ ነገር አላቀረበም፡፡ አብዛኛዎች የኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቀኖና ሊከበር ነው፤ መንግሥትና አገር ቤት ያለው ሲኖዶስ የህዝብን ፍላጎት ሊያስተናግዱ የተዘጋጁ ይመስላሉ በሚል አስቀድመው ሙገሳና ምስጋና ያቀረቡለት ድርድር ዋናውን ጉዳይ አስቀምጦ ቀጣዩንና አራተኛውን ድርድር ከጥር 16 እስከ ጥር 18፤ 2005ዓም (January 24 – 26, 2013) በሎስ አንጀለስ ከተማ፤ ካሊፎርኒያ ጠቅላይ ግዛት ለማድረግ ቀጠሮ ይዞ ተለያይቷል፡፡

አስተያየት ሰጪዎች ከሙስሊሙ ማኅበረሰብ ጋር አጣብቂኝ ውስጥ የገባው ኢህአዴግ ከወትሮው በተለየ የአቡነ መርቆሪዮስን ጉዳይ የሚያስታምመው እንደሌሎች የፖለቲካ ድርድሮች ሰጥቶ መቀበል ወይም ውጤትን በእኩል መጋራት (win-win) የሚባል አማራጭ ስለሌለው ነው ይላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት አገር ቤት ቤተክህነት አካባቢ ያሉትን የመንግሥት ወዳጆች እና ህዝበክርስቲያኑን ላለማስከፋት መለሳለስ የመረጠው ለዚህ ነው የሚል አስተያየት ሰጥተዋል፡፡

የመግለጫው ሙሉ ቃል ይህ እዚህ ላይ ይገኛል፡፡

 

No comments:

Post a Comment