(ሉሉ ከበደ)
ሀገራችን በየጊዜው የስርዓቱ መገለጫና በስልጣን ላይ ያሉት ግለሰቦች ውለኛ ባህሪ ነጸብራቅ የሆኑ ርካሽና አደገኛ እርምጃዎች፤ ሲወሰዱ ማየት እንግዳ ነገር አይደለም። ሀያ አንድ አመት። አሁን የባሰው ነገር የኢትዮጵያን ህዝብ ቁርጠኝነትና ቁጣ ለመፈታተን ወያኔ ህዝባዊ ሰሜትን የሚአነቁር ስራ ባለመታከት እየሰራና ወንጀልም እየፈጸመ መቀጠሉ ነው።
"ራእዩን.. ራእዩን" እያሉ፤ ኢትዮጵያን የማጥፋት ተልኮውን ሳያስጨርሳቸው እግዜር ስላነሳው ሰው እያንቃረሩ፤ የኢትዮጵያን ምድር በሞተ ሰው ፎቶ ማበስበሳቸው እንዳለና እንደቀጠለ ሆኖ፤ የአጼ ሚኒሊክን እና የአቡነቤጥሮስን ሀውልት አናፈረሳለን ያሉት ነገር የጀግናው ኢትዮጵያዊ አሉላ አባነጋን መታሰቢያ ትምህርት ቤት ስም ለውጠው ለአንድ የባንዳ ልጅ ለቀንደኛው የኢትዮጵያ ጠላት ስያሜውን መስጠታቸው፤ የኢትዮጵያን ህዝብ የመናቅ የማዋረድ የብልግና ስራ እና ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን የማጥፋት ተልኮ ቀጣይ እንቅስቃሴ በመሆኑ የሚገርም ነገር አይደለም።
የሚገርመው ነገር ሰማንያ ሚሊዮን ህዝብ ምን አስኪያደርጉት፡ ምን እስኪያሳዩት እንደሚጠብቅ ነው። ተነስቶ የሚያስቆማቸው ህዝብ እስከሌለ ድረስ፤ ጠራርጎ የሚያጠፋቸው ጀግና እስከሚነሳ ድረስ ድሉ የነሱ ነው ይቀጥሉበት።
አንድ የኢሳት ቴሌቭዢን አድማጭ " .. ሰው ሁሉ ወደ ሴትነት ተቀየረ እንዴ?...በኢትዮጵያ ወንድ የለም እንዴ?.." ብሎ በአንክሮ የጠየቀው አንጀቱ አሮ ኖሯል።
የዜጎችን ሰብዓዊ መብትም በተመለከተ በኦሮሚያ ክልል ላፍቶ ውስጥ ችግሩን በህዝብ ላይ እንዲያባብሱ ከሚያሰማሯቸው የወያኔ ቅጥረኞች አንዱ "የጸጥታና የፍትህ ሀላፊ" የሚል ትልቅ ማእረግ የተሰጠው ሰው፤ በዛሬዋ አለም ውስጥ ወደር የማይገኝለት ወንጀል እንዲፈጽም ታዞ ነበር። ሁለት ድሆች አርሶ አደር ባልና ሚስት፤ እርቃናቸውን ባደባባይ አቁሞ (ስርዓቱ ለሂሁ አይነት ተልኮ ያጎናጸፈውን ስልጣን በመጠቀም) እኒያን ንጹሀን ኢትዮጵያውያን ለሰው ልጅ አእምሮ የሚከብድ ጸያፍ ድርጊት እንዲፈፅሙ አድርጓል።በዓለም ላይ ያለፉም ሆነ ያሉ የፋሺሽት የጭካኔ አገዛዞች፤ ባይሆን ይገላሉ እንጂ ወንድን ልጅ ከነሚስቱ ባደባባይ እርቃናቸውን እንዲቆሙ አድርገው፤ የባልየውን ብልት በገመድ አስረው፤ ሚስትን "ጎትቺ… ሳሚ" ብለው፤ አስገደዱ የሚል ታሪክ የተጻፈ የለም።ይህ በኢትዮጵያ የተፈጸመ፤ ወያኔ ያቀነባበረው በአለም ላይ "መንግስት አለ" በተባለበት አገር የተፈጸመ የመጀመሪያ አስደንጋጭ ጸያፍ ድርጊት ነው። ይህ ድርጊት "ህዝቡ ያምጽብናል ወይስ እስከመጨረሻው እንደፈራን ይገዛልናል? " የሚለው የህውሀት ድብቅና ተለምዷዊ ጥያቄ ነው። የድንቁርና ድፍረት ድርጊት ነው።የኢትዬጵያን ህዝብ ወኔ ለመለካት ከሚያደርጉአቸው የማያቋርጡ እኩይ ተግባራት አንዱ ነው። ይቀጥላልም።
እርግጥ ይህ አጋጣሚ ድንገት ለኢትዮጵያ ሳተላይት ቴሌቪዥን ደረሰ እንጂ፡ ድርጊቱ ሞልቶ የተረፈ በገጠሪቱ ኢትዮጵያ በወያኔ አፈና ስር የሚገኘው አርሶ አደር የሚደርስበት የለትተለት ጥቃት አንዱ አይነት ነው።ይህን ህዝብ በአሁኑ ሰዓት ጠላት(ህውሀት) ከሚያደርስበት ማናቸውም ጥቃት የሚታደገው ወገን የለም።ለኢትዮጵያ ህዝብ የአካልም የህግም ጥበቃ የሚያደርግለት መንግስት የለም። ከሁሉም በላይ ደግሞ እግር ተወርች ታስሮ፤ በልጓም የፍጢኝ ተይዞ፤ ታፍኖ፤ ከሌላው ህዝብ በተለየ መልኩ ሰቆቃና የሰብዓዊ መብት ረገጣ እየተካሄደበት ያለው የትግራይ ህዝብ ነው። ወያኔን በተመለከተ፤ የኢትዮጵያ ህዝብ ችግር ተወደደም ተጠላም ሰላማዊ ሳይሆን በህዝባዊ ወታደራዊ አመጽ የሚፈታ ነው የሚመስለው። ሕዝቡ እራሱ በቁጣ ተነስቶ በቃ እስካላለ ድረስ ወንጀሉ ይቀጥላል።ኢትዮጵያዊነትን የማዋረድ ተልእኮ ይቀጥላል።
ሰላማዊ ትግል …ድርድር .ሰላማዊ …ሰላማዊ ..ሰላማዊ ይባላል ሓያ አንድ አመት። እንዲህ ሲባል ወያኔ ራሱን እስከወዲያኛው አጠናከረ። በመጀመሪያ ደረጃ ሰላማዊ ትግል የሚባለው የበሰለ የሰከነ ሁለንተናዊ አመለካከት እንዲኖራቸው ተደርገው ከተማሩ ካደጉ ሰዎች አይደለም አንዴ የሚጠበቀው? ከትግራይ ባላገሮች ምንድነው የሚጠበቀው? ከዱር አራዊት ያልተናነሰ ጭካኔ ካላቸው ሰዎች ምንድነው የሚጠበቀው? በኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተኮትኮተው ተረድተው ለዚህ ከበቁ ከብቶች ምንድነው የሚጠበቀው?...ሰላማዊ ትግልማ ምርጫ 97 ላይ ስራውን ሰርቷል። እርግጥ የኢትዮጵያ ህዝብ ሰላምን ይወዳል። በሰላም የሚፈልገውን ነገር ተናገረ። የሚፈልገውን የመንግስት አይነት መረጠ። ከዚያ
በሗላ ወያኔ እንዴት ወደ ስልጣን አንደተመለሰ አይተናል። ወታደራዊ ሀይል ተጠቅሟል። ወታደራዊ መንግስት ሆኗል ማለት ነው። ኢትዮጵያ በወታደራዊ አስተዳደር ስር ነች…ነች!
ምላሹን ግን አላገኘም። አሁን የኢትዮጵያ ህዝብ ማድረግ ያለበት ሁለት ቀላል ነገሮችን ነው። "ሰላማዊ ..ሰላማዊ" የሚሉትን ማደናገሪያ ከጭንቅላቱ አውጥቶ ግማሹ በሀይል፤ ግማሹ በሰላም ከነሱ ጋር መነጋገር አለበት። ሰላማዊ ትግሉን የያዙ ወገኖች አዎ አስፈላጊ ነው እስከመጠረሻው ይቀጥሉ ። ሰላምን እንደ አማራጭ ለመያዝ የሚያስገድደው የሚቦቅሰው፤ የሚነፋው፤ የሚደፋው ወገን ለሕውሀት ግድ..ግድ..ግድ ያስፈልጋል። እነዚያም ጀግኖች ብቅ ማለት አለባቸው። ከየአቅጣጫው።በግድ ካልተወገዱ በውድ አይለቁም ስልጣን።
ኢትዮጵያውያን ከንግዲህ ወዲያ ወያኔ ከከለለላቸው የዘር አጥር ውጭ ከተገኙ ስቃያቸው ይቀጥላል። ሰሞኑን ከባህርዳር ወደ ጅጅጋ ለመምህርነት ቅዱስ ስራ የሄዱ ኢትዮጵያውያን ወጣት ምሁራን ወያኔ በክልልሉ ባስቀመጣቸው የመለስ ራእይ ፈጻሚዎች ተደብድበው ተዘርፈው ታስረው ወደ መጡበት እንዲመለሱ ተደርገዋል። ዘጠኝ ወጣቶች ኢትዮጵያውያን ናቸው። ይህ ድርጊት የተፈጸመባቸውም ከሀያ አንድ አመት በፊት ኢትዮጵያ በምንላት ሀገር ውስጥ ነው፡ …ጅጅጋ። ማንም ወደፈለገበት ሄዶ በሰላም የሚፈልገውን እየሰራ የሚኖርባት አገር ነበረች ኢትዮጵያ። ዛሬ ከጎንደር ወቶ ሀረር ከመሄድ፤ ከወለጋ ወቶ ትግራይ ከመሄድ፤ ባጠቃላይ ካንዱ ክፍለሀገር ወቶ ወደሌላ ክፍለሀገር ከመሄድ ለኢትዮጵያውያን ሱዳን ኬንያ ሶማሊያ ሳይቀር መሄድ የተሻለ ሖኗል። ባንድ ስም በስደተኝነት ታውቀው በሰላም ይኖራሉ። በኢትዮጵያ ውስጥ ከክልል ክልል ተላልፈው ሲሔዱ ከሚከተላቸው አደጋ ከሚከተላቸው ችግር የበለጠ ምንም አይደርስባቸውም። አፋር ውስጥ አማርኛ ተናገራችሁ ተብለው ለግል ስራ ጉዳይ እዚያ የሄዱ ሰዎች ተደብድበው ተዘርፈው ወደመጡበት እንዲመለሱ ተደርገዋል።
የገዛ ሀገራቸው ሶማሊያን አፍርሰው የመጡ የሱማሌ እብዶች በወያኔ ቸርነትና ጀግነት የሶማሌ ክልል ተብሎላቸው የኦጋዴን ግዛታችንን ተሹመው ተሸልመው ኢትዮጵያውያንን እንደፈለጋቸው እያደረጉ ነው። በሶማሌ ክልል በስልጣን ላይ ያሉት አብዛኛዎቹ ሰዎች ኢትዮጵያን ይወጉ የነበሩ የዚያች አገር ተወላጆች ናቸው። ኢትዮጵያውያን ይህንን ጥቃት ችለን ተሸክመን አሜን ብለን ተቀብለን መኖሩን ከቀጠልን ይናፍቀን የነበረው ባርነት ነበረና እንደፈለጋቸው ሲያደርጉን እየተደሰትን እያመሰገናቸው ኑሮ ይቀጥል።
የሚደንቀው ነገር ይህን ሁሉ በሽታ፤ ይህን ሁሉ የመጠላላት ከልት፤ ይህን የመከፋፈል ነቀርሳ፤ ወረርሽኝ፤ መርዝ፤ በሀገር ላይ አምጥቶ ረጭቶ በግዚአብሄር እርዳታ የተገላገልነውን ሰው "ራእዩን" እናስፈጽማለን ብለው የቀሩት የወያኔ ልክፍተኞች እና እብዶች ለሊትና ቀን በጩኸት በሴጣናዊ ዋይታ የኢትዮጵያን ህዝብ ማደንቆር መቀጠላቸው ነው። የሚያስፈልገን ራእይ አብሮ የመኖር የመቻቻል ራእይ ነው።በዘር የመጠላላት የመበላላት ራእይ አይደለም። የዘር ጥላቻ ፈጣሪውን ተከትሎ መቃብር ሊገባ ይገባዋል።
ወደ ጀመርኩት ነገር ልመለስና በዚያች አቅመቢስ፤ ደራሽ የሌላት አርሶ አደር የቤት እመቤት ላይ ወያኔ የፈጸመው ወንጀል እናትነትን፤ እሕትነትን፤ ሴት ልጅነትን የሚያረክስ አባትነትን ወንድምነትን የወኔ ፈተና ላይ የሚጥል፤ የሚያዋርድ ኢሰብአዊ ወያኔያዊ ስራ ነው።የወያኔ መሪዎች እነሱም ከእናት ተፈጥረዋል። እነሱም ከሴት እህት ጋር ተፈጥረዋል። እነሱም ሴት ልጅ ወልደዋል።እንደምን ካውሬ ያልተለየ ባህሪ ሊኖራቸው ቻለ? የስነልቡና ሊቃውንት ምርምር ቢያደርጉ መልሱ ይገኝ ይሆናል። ይህ ወንጀል የስርዓቱ ፈጣሪዎች የነስብሀት ነጋ፤ የነመለስ ዜናዊ ግለሰባዊ ውለኛ ባህሪ መገለጫ ድርጊት ነው።የህውሀት አገዛዝ መገለጫ ድርጊት ነው።
ለምሳሌ፤ መለስ ዜናዊ በቁሙ በህይወት እያለ ብልቱ በገመድ ታስሮ አዜብ መስፍን ህዝብ ፊት እየጎተትሽ ሳሚ ብትባል ወይንም ሴት ልጃቸው እንዲህ ብትደረግ ደስ ይላቸዋል? ደስ የሚለው ኢትዮጵያዊስ አለ? አሁን በህይወት ያለው ስብሀት ነጋ ይህንን ተአምር በሱ ላይ የሚፈጽም ቢመጣ ምን ይሰማው ይሆን?.. ሌሎቹም ሁሉ !
እዚህ ደረጃ የዘቀጠ ስነምግባር ያላቸውን ግለሰቦች፤ በቂ መደበኛ ትምህርት የሌላቸው፤ የህይወትም ሆነ የስራ ልምድ የሌላቸው ያይምሮ ደህንነታቸው የታወከ፤ መልካም የቤተሰብ አስተዳደግ የሌላቸውን መረንና ጨካኝ መሀይማንን እየመለመሉ፤ በጸጥታ ፡ በስለላ ፡ በአፈና ስራ ማሰማራት የወያኔ አመራሮች ውለኛ ባህሪ ነው።ሰው ግደል ሲባል ስንት አንጂ ለምን ማለት የማይችል ሰው በመመልመል እጅግ የተካኑ ናቸው።
ሕገመንግስት አንቀጽ 18፤ ኢሰብአዊ አያያዝ ስለ መከልከሉ፤ ንኡስ አንቀጽ 1 እንደሚለው፤
ማንኛውም ሰው ጭካኔ ከተሞላበት ኢሰብዓዊ ከሆነ ወይም ክብሩን ከሚያዋርድ አያያዝ ወይም ቅጣት የመጠበቅ መብት አለው።
ወጣቱ ፖለቲከኛ አንዱአለም አራጌ ወህኒ ቤት ውስጥ በነፍሰገዳይ እንዲደበደብ ሲደረግ ወያኔ ድርጊቱ እንዲደረግ የፈቀደው በወጣቱ ፖለቲከኛ ላይ የሞራል ውድቀት የአካል ድቀት ለማድረስ የታለመ እርምጃ መውሰድ እንዳለበት በማመኑ ነበር። ያድርጊትና የተመረጠው ሰው የስርዓቱ መገለጫዎች ናቸው።ስርዓቱ ማናቸውንም በዜጎች ላይ የሚፈጽመውን ወንጀል አደገኛ ወንጀለኞችንም በማሰማራት ያስፈጽማል።ይህን ነፍሰገዳይ ነገ ወደህብረተሰቡ ውስጥ በሚስጢር በማሰማራት ጠንካራ ፖለቲከኞችን ሊያስገድልበት ይችላል።ሰውየው ባጋጣሚ እጅከፍንጅ እንኳ ቢያዝ ቀድሞ ወህኒ የተዶለበት ወንጀለኝነቱ እንደማስረጃ ተቆጥሮ ከመንግስት ጋር ምንም ግንኙነት እንደሌለው በሰፊ የፕሮፓጋንዳ ስራ ህብረተሰቡን ማደናገር ይቻላል።ያንዷለም ጉዳይ በሰፊው ስለተነገረ አነሳሁት እንጂ በከተማና በገጠር በየእስርቤቱ በእስረኞች ላይ የሚፈጸመው ድብደባ በተለያዩ አጋጣሚዎች በሰብዓዊ መብት ጥበቃ ድርጀቶች መነገሩ እንግዳ ነገር አይደለም።
ሕገመንግስት አንቀጽ 20፤ የተከሰሱ ሰዎች መብት፤ ንኡስ አንቀጽ 3 የተከሰሱ ዎች በፍርድ ሂደት ባሉበት ጊዜ በተከሰሱበት ወንጀል እንደጥፋተኛ ያለመቆጠር በምስክርነት እንዲቀርቡም ያለ መገደድ መብት አላቸው።
ባለፉት ሀያ አንድ አመታት ካለን ተሞክሮ አንጻር ወያኔ የሚቃወሙትን ዜጎች ሲያስር ገና የፍርድ ሂደታቸው በመካሄድ ላይ እያለ ወይም ደግሞ በፖሊስ ጣቢያ እያሉ የቀድሞው የወያኔ መሪ በምክር ቤት፤ ባደባባይ፤ በመገናኛ ብዙሀን፤ ‘’እነእገሌ ወንጀለኞች ናቸው’’ እያለ አፉን ሞልቶ በእብሪት ይናገር ነበር። በንጹሀን ዜጎች ላይ እንዲፈረድ መመሪያ ይሰጥ ነበር። በየፍርድቤቱ ያስቀመጣቸው የህብረተሰብ መግደያ ዳኞችም ያንን ተቀብለው ያንኑ በተግባር ተርጉመው በኢትዮጵያውያን ላይ የሞት፤ የእድሜ ልክ፤ የአመታት ፍርድ ይሰጣሉ።የፖለቲካ እስረኞች አንዳቸው በአንዳቸው ላይ እንዲመሰክሩ ማሰቃየት የአካል የስነልቡና ጉዳት ማድረስ ያለና የሚቀጥል ተግባር ነው። ለዚህ ጥሩ ማስረጃ ከወራት በፊት አኬልዳማ በሚል ርዕስ በኢትዮጲያ ቴሌቪዢን የተላለፈውን ድራማ መሰል ፕሮፓጋንዳ መመልከት ይጠቅማል።
ሕገመንግስት 26፤ የግል ህይወት የመከበርና የመጠበቅ መብት፤ ማንኛውም ሰው በግል የሚጽፋቸውና የሚጻጻፋቸው በፖስታ የሚልካቸው ደብዳቤዎች እንዲሁም በቴሌፎን በቱሌኮሚኒኬሽንና በኤሌትሮኒክ መሳሪያዎች የሚያደርጋቸው ግንኙነቶች አይደፈሩም።
ህጋዊና ሰላማዊ ሆነው በዚሁ የተንኮለኞች ገዢ ቡድን እውቅና ተሰቷቸው የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ መሪዎች ጋዜጠኞች ታዋቂ ግለሰቦች ስልካቸው ኢሜላቸው ፖስታቸው በወያኔ ደህንነቶች እየተጠለፈ ባልፈጸሙት ወንጀል ባልሰሩት ስራ የውሸት ክስ እየተመሰረተባቸው ያየተጠለፈው ስልካቸው ወይም ደብዳቤአቸው እንደማስረጃ እየቀረበ ንጹሀን ኢትዮጵያውያን ወህኒ የሚጋዙበት ስርዓት ውስጥ ነው ያለነው።እስክንድር ነጋ ርዕዮት አለሙ የተጻጻፏቸው የግል ጉዳዮች በወያኔ ደህንነቶች እየተሰረቁ ለማስረጃ ቀርበዋል። የኢሳቱ ፋሲል የኔ አለም ከቤተሰቦቹ ጋር የሚደዋወለው ስልክ ተጠልፎ እንደማስረጃ ቀርባል።እነዚህ ንጹሀን ኢትዮጵያውያን የሀገር መድህን እንጂ እንደወያኔ የጠላት ቅጥረኞችና የሀገር ጠንቆች አለመሆናቸውን የኢትዮጵያ ህዝብ ጠንቅቆ የሚያውቀው ጉዳይ ነው።
ሕገመንግስት አንቀጽ 25፤ የእኩልነት መብት፤ ሁሉም ሰዎች በሕግ ፊት እኩል ናቸው። በመካከላቸው ማናቸውም አይነት ልዩነት ሳይደረግ በሕግ እኩል ጥበቃ ይደረግላቸዋል። በዚህ ረገድ በዘር፤በብሄር፤ብሄረሰብ፤በቀለም፤በጾታ፤በቋንቋ፤በሀይማኖት፤በፖለቲካ፤በማህበራዊ አመጣጥ፤በሀብት በትውልድ፤ወይም በሌላ አቋም ምክንያት ልዩነት ሳይደረግ ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የሕግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው።
ባለፈው አመት ከደቡብ ኢትዮጵያ ከሀያ ሺህ በላይ አማሮች በባእድ ሀገር እንደሚኖር ህገወጥ ስደተኛ (በባእድ ሀገር እንኳ በማይደረግ መልኩ) ያፈሩትን ሀብትና ንብረት አስረክበው ያጠለቋትን ልብስ ብቻ እንደለበሱ የኖሩበትን አካባቢ ለቀው እንዲወጡ ሲደረግ በምክንያትነት የተጠቀሰው አማሮች መሆናቸው ብቻ ነበር። ይህች ሀገር ኢትዮጵያ ነች። እንዚህም ዜጎች ኢትዮጵያን ናቸው።ወያኔ ይህንን ግፍ ሲያስፈጽም "በብሄር በቋንቋ ልዩነት አይደረግም። ሰዎች ሁሉ እኩልና ተጨባጭ የህግ ዋስትና የማግኘት መብት አላቸው" የሚለው ሀረግ ከወያኔ ሕገመንግስት ውስጥ ተሰርዞ አይደለም። ወይም ደግሞ
ኢትዮጵያዊ በሀገሪቱ ወደመረጠው ወደፈለገው አካባቢ ሄዶ መኖር፤ ሀብት ማፍራት ይችላል የሚለው አንቀጽ ተሰርዞ አይደለም። ወያኔ ሀገሪቱን እየገዛ ያለው በጫካ ህጉ በመሆኑና እንቢ አንገዛም ብሎ አምርሮ የሚነሳ ህዝብ በመጥፋቱ ነው እንጂ!
በፖለቲካ ተቃዋሚነት የተፈረጀ ዜጋ በአሁኑ ሰአት ኢትዮጵያ ለሱ የሲኦል ምድር መሆኗ የሚያከራክረን ጉዳይ አይደለም።ረሀብ ልጆቹን ያጠወለገበት ድሀ አርሶ አደር ተቃዋሚዎችን ደግፈሀል ተብሎ የባእድ መንግስት የሚያቀርበውን ነፍስ አድን ጥሬ ወያኔ ካባቱ ጎተራ ዘግኖ የሚሰጥ ይመስል የራበው አርሶ አደር ከነልጆቹ እንዲሞት እርዳታ ይነፍጋል። ባእዳን በጎ አድራጊዎች የቸሩትን ምጽዋት ወያኔ የፖለቲካ ድጋፍ ይገዛበታል።ኢህአደግን ያልደገፈ ኢትዮጵያዊ ተምሮ ስራ አያገኝም። የተቀጠረም እድገት፤የትምህርት እድል፤የደሞዝ ጭማሪ አያገኝም። ይህንን ደጋግሞ ማንሳቱ የሞኝ ለቅሶ መልሶ መልሶ እንደሚባለው ከመሆን አያልፍም።ለኢትዮጵያ ህዝብ የሚያስፈልገው አንድ ነገር ብቻ ነው ዛሬ ነገ ሳይባል ለሰላማዊም ሆነ ወያኔ እንደሚፈልገው በሀይል ለመጋፈጥ በቁርጥኝነት መነሳት ብቻ ነው። ሕውሀት የሚባል ድርጅት ከርሰመቃብር ካልወረደ ኢትዮጵያውያን ህልውናአችን የሚያከትምበት ጊዜ እሩቅ አይሆንም።
ኢትዮጵያ ለዘላለም ትኑር
lkebede10@gmail.com
ኢትዮሚድያ
- Ethiomedia.com
December 10, 2012
No comments:
Post a Comment