Monday, December 3, 2012

ህወሓት ደብረጽዮንን ቀጣይ ጠ/ሚ/ር ያደርጋል!

 

የአሁኑ ምደባ ለመለስ ቀርቦ ነበር
debretsion gebremichael
 
ከአቶ መለስ መለየት በኋላ ወደ አደባባይ የወጡት ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ቀጣዩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሊሆኑ እንደሚችሉ ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ግምታቸውን ሰጡ። አገር ቤት ተቀምጠው በኢህአዴግ ላይ የሰላ ትችት በማሰማት ቀዳሚውን ስፍራ የያዙት በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የፍልስፍና መምህርና እንደ ፕ/ር መስፍን ወ/ማርያም የአደባባይ ምሁር በመባል የሚታወቁት ዶ/ር ዳኛቸው ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ይፋ እንዳደረጉት ለግምታቸው ምክንያት ሰጥተዋል።
አቶ መለስ በህይወት እያሉ የስልጣን ክፍፍሉን በሶስት ለመመደብ መታሰቡን ሰምተው እንደነበር ያስታወሱት ዶ/ር ዳኛቸው፣ ሃሳቡ ከስምምነት ላይ ሊደረስ ባለመቻሉ ተግባራዊ ሊሆን እንዳልቻለ አመልክተዋል። አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር ማንም ይሁን ማን ከዚህ ቀደም እንደነበረው ስልጣኑ በአንድ ሰው ላይ ተጭኖ ሊቀጥል እንደማይችል ከስምምነት ላይ በመደረሱ አሁን የተደረገው ምደባ ተግባራዊ ሊሆን እንደቻለ በማመልከት ስለቀጣዩ ጠ/ሚኒስትር ግምታቸውን አኑረዋል።
“በእኔ ግምት” አሉ ዶ/ር ዳኛቸው የወደፊቱን ሲተነብዩ “… ህወሃት የጠቅላይ ሚኒስትርነቱን ቦታ ለመያዝ በሁለት መንገድ እየሄደ ነው፡፡” ሕወሓት አሁንም ቢሆን ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ መቀመጡን ያመለከቱት ዶ/ር ዳኛቸው ህወሃት ቁልፍ ቦታዎችን መያዙን ለቀጣዩ ዋና ስልጣን መንደርደሪያ አድርጎ እንደሚጠቀምበት ጠቁመዋል።
የመጀመሪያው ህወሓት ከያዘው ቁልፍ የሚኒስቴር መ/ቤቶች ስልጣን አኳያ ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላ ሊሆን የሚችለውን ሲገመት አመራሩ እንደ ዱላ ቅብብል የሚተካካ እንደሆነ ተደርጎ የሚነገረው ሁሉ ጥያቄ ውስጥ እንደሚያስነሳ የተናገሩት ዶ/ር ዳኛቸው፣ የውጪ ጉዳይ ሚኒስትርነትና ወሳኝ የሚባለው የፋይናንስና የኢኮኖሚ ዘርፎች መከላከያውን ጨምሮ ህወሃት እጅ መውደቃቸው የወደፊቱን የስልጣን ተረካቢ አመላካች መሆኑን ገልጸዋል።
ሌላው ከሁለት ዓመት በፊት የጠ/ሚኒስትርነት ስልጣኑ የተጠናከረ በመሆኑ “ለሶስት መክፈል አለብን” የሚል ሃሳብ ተነስቶ በጊዜው ተቀባይነት ያላገኘው የጠ/ሚ ቦታ ከህወሓት እጅ ከወጣ የህወሓት የበላይነት ያከትማል የሚል ስጋት ስለነበራቸው እንደሆነ ዶ/ር ዳኛቸው ጠቁመዋል። በማያያዝም “ህወሓት ሁለት አመራሮቹን አጭቷል፤ ዶ/ር ደብረጽዮንና ዶ/ር ቴድሮስን፡፡ ከሶስት ዓመት በኋላ ስለጠ/ሚኒስትሩ ማንነት ስገምት ግምቴ ወደ ዶ/ር ደብረጽዮን ያደላል” ሲሉ የሶስቱ ጠ/ሚኒስትሮች ምደባም ሆነ የአቶ ሃይለማርያም ወንበር ይሁንታ “እስክንዘጋጅ ጠብቁን” ዓይነት መሆኑን አመላክተዋል።
መለስ በድንገት የተለዩት ህወሃትን ማን ይመራዋል? ቀጣዩ የኢትዮጵያ ጠ/ሚኒስትርስ ማን ሊሆን ይችላል? የሚለው የወቅቱ አንገብጋቢ አጀንዳ በነበረበት ወቅት ዶ/ር ደብረጽዮን ለጠቅላይ ሚኒስትርነት መታሰባቸውንና በኦህዴድ በኩል ተቀባይነት አለማግኘታቸውን ለመዘገብ ጎልጉል ቅድሚያ ነበረው። ጎልጉል በዘገባው “ህወሓት በምርጫው ያልተገመቱና አዲስ አመራር ወደ ሃላፊነት አምጥቷል። እርሳቸውም ዶ/ር ደብረጽዮን ወልደ ሚካኤል ናቸው። በሚኒስትር ማዕረግ የኢንፎርሜሽንና ደህንነት ኤጀንሲ ዳይሬክተርና የኢትዮ ቴሌኮም ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ዶ/ር ደብረጽዮን በነባር ታጋዮች ዘንድ እይወደዱም” ብሎ ነበር።
ደብረጽዮን ወልደ ሚካኤል በደኅንነቱ የሚከናወኑ ከፍተኛ ጉዳዮችን የሚመሩ፣ ከፍተኛ ውሳኔዎችን የሚወስኑ፣ የአገሪቱን የደኅንነት መዋቅር ከቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር ጋር ጎን ለጎን የሚመሩ መሆናቸውን በቅርብ የሚያውቁ ይገልጻሉ። ህወሓት የገነባውን የደህንነት መዋቅር በታማኝነት የሚቆጣጠሩት አዲሱ የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር ህወሓት ለሁለት በተከፈለበት ወቅት አቶ መለስ በአሸናፊነት እንዲወጡ ታላቅ ሚና መጫወታቸውን በብዙዎች ይፋ ያልወጣ ግለ ታሪካቸው ነው።
ለአቶ መለስ እጅግ ቅርብ የሆኑት ደብረጽዮን ህወሓትን ወክለው የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራር እንዲሆኑ በህወሓት በኩል ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለ የጎልጉል የመረጃ ምንጮች አስታውቀዋል። በዘመነ ህንፍሽፍሽ ህወሓት ለሁለት መሰንጠቁ ይፋ ከመሆኑ በፊት ልዩነቱ ውስጥ ውስጡን በተጋጋመበት ወቅት አቶ ደብረጽዮን ከአቶ መለስ የተቀበሉትን ልዩ ተልዕኮ ለመተግበር ያስችላቸው ዘንድ የሽሬ ምክትል አስተዳዳሪ ተደርገው ተሹመው ነበር። አፈንጋጭ የተባለውን ቡድን ከሚመሩት መካከል ዋና ኃይል አላቸው ተብለው የሚፈሩት አቶ ስዬ አብርሃ በትውልድ መንደራቸው ተምቤን ውስጥ ያላቸውን ሰንሰለት ለመበጣጠስና ለማምከን ልዩ ተልዕኮ ይዘው ወደ ሽሬ ያመሩት ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል ሃላፊነታቸውን በመወጣት ለመለስ አሸናፊነት ጉልህ ሚና መጫወታቸውን ምንጮቹን ጠቅሶ ጎልጉል ዘግቦ እንደ ነበር የሚታወስ ነው። የጎልጉል ምንጮች አሁንም ቢሆን ቀጣዩ ጠ/ሚኒስትር ደብረጽዮን እንደሚሆኑ ከግምት በላይ ይናገራሉ።
ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ጋር ያደረጉት ቃለ ምልልስ እነሆ
ጥያቄ፡- ጠ/ሚ ሃይለማርያም ደሳለኝ ለምክር ቤቱ አቅርበው ያፀደቁትን አዲስ የካቢኔ አደረጃጀት እንዴት ያዩታል?
ዶ/ር ዳኛቸው፡- ከዚህ በፊት ሰምቼ ነበር፤ ሶስት ቦታ እንክፈለው የሚለውን፡፡ በዚያን ጊዜ ግን ስምምነት ላይ አልተደረሰም፡፡ በአንድ ነገር ላይ ግን ስምምነት ላይ ተደርሶ ነበር፡፡ አዲስ የሚመጣው ጠ/ሚኒስትር ማንም ይሁን ማን ከዚህ በፊት የነበረው ጠ/ሚ የነበረውን ሃይል ክምችት ይዞ መቀጠል እንደማይችል ተነጋግረው ጨርሰዋል፡፡ ማን ጠ/ሚ ይሆናል የሚለው አይደለም ወሳኙ፤ ህወሓት አካባቢ ማን እየተሾመ ነው የሚል ነው ወሳኙ፡፡ አሁንም ቢሆን ምንም ወዲያና ወዲህ የለኝም፡፡
በእኔ ግምት ሕወሓት አሁንም ቢሆን ስትራቴጂካዊ ቦታ ላይ ተቀምጧል – ጠ/ሚ ለመሆን፡፡ በሁለት መንገድ ነው እየሄዱ ያሉት፡፡ በውጭ ጉዳይም ትክክለኛ የስልጣን ቅብብል ነው የሚባለው ጉዳይ አሁን ጥያቄ ውስጥ የገባ መሰለኝ፡፡
ህወሓት ከያዘው ቁልፍ የሚኒስቴር መ/ቤቶች ስልጣን አኳያ ከሁለት ዓመት ተኩል በኋላ ሊሆን የሚችለውን ለመገመት ስንሞክር አመራሩ እንደ ዱላ ቅብብል ነው የሚባለው ጥያቄ ውስጥ የገባ ይመስለኛል፡፡ ወሳኝ ወሳኝ ቦታዎችን ወስደዋል፣ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሄዷል፤ እዛው ተመልሶ ቦታው ገብቷል፡፡ ወሳኝ የሚባለው የፋይናንስና ኢኮኖሚው ሄዷል፤ ተመልሶ ቦታው ገብቷል፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት የጠ/ሚኒስትርነት ስልጣኑ (ቢሮ) የተጠናከረ ነውና ለሶስት መክፈል አለብን የሚል ሃሳብ ተነስቶ ነበር፡፡
በጊዜው ያ ተቀባይነት አላገኘም፡፡ የጠ/ሚ ቦታ ከህወሓት እጅ ከወጣ የህወሓት የበላይነት ያከትማል የሚል ስጋት ነበራቸው፡፡ አሁን እንግዲህ አንድ ጠ/ሚኒስትርና ሦስት ምክትል ጠ/ሚኒስትሮች አሉን ማለት ነው፡፡ እያንዳንዳቸው ደግሞ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች በክላስተር ተከፋፍለው አስተባባሪነት ተሾሞባቸዋል፡፡
ከዚህ ጋር ተያይዞ መተያየት ያለበት ማንኛውም ለየትኛው ክላስተር (ዘርፍ) በአስተባባሪነት እንደተመደበ ነው? ሽግሽግ ሲመጣ ሹመት ሲመጣ ህወሓት ተጠናክሮ እንደመጣ እንመለከታለን፡፡ ፋይናንስና ኢኮኖሚውን ዶ/ር ደብረጽዮን ያዘ፤ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩን ዶ/ር ቴዎድሮስ ያዘ፤ በሶስተኛ ደረጃ መከላከያው የት ቦታ እንዳለ እናውቃለን፡፡ ይህንን ሁሉ የያዘ ፓርቲ የስልጣን ፍፁም የበላይነቱን ያዘ፣ ተቆጣጠረ ማለት ነው፡፡ ሕወሓት አካባቢ ማን ነው የበላይነት የያዘ የሚለው ወሳኝ ጥያቄ ነው፡፡
ህወሓት ሁለት አመራሮቹን አጭቷል፤ ዶ/ር ደብረጽዮንና ዶ/ር ቴዎድሮስን፡፡ ከሶስት ዓመት በኋላ ስለጠ/ሚኒስትሩ ማንነት ስገምት ግምቴ ወደ ዶ/ር ደብረጽዮን ያደላል፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ህወሓት ተደከመ፣ ሞተ የሚባለው ወሬ የተጋነነ ይመስለኛል፡፡
ታላቁ መሪያችን የፃፈውን እንተገብራለን ብለው የአሁኑን ጠ/ሚኒስትር በመሾም የመጀመሪያውን ፎርሙላ ካሳዩን በኋላ፣ በይደር ያስቀመጡት ሁለተኛው ፎርሙላ መሆኑ ነው የአሁኑ ለሶስት መካፈል – እኛ እስከምንዘጋጅ ነው ነገሩ፡፡ በዚህ ክፍፍል ለማን ምን እንደደረሰው አሁን ግልጽ የሆነ ይመስለኛል፡፡ ምክትል ጠ/ሚኒስትር ከተቀመጠ በኋላ ሌሎች ሁለት ምክትሎች ከጐኑ ማሰለፍ የሚገርም ነው፡፡ አንዳንዶቹ ሰውዬው ልምድ ስለሚያንሳቸው ነው ይላሉ፡፡ መቼ እድል ተሰጠው፡፡ እስከ አሁንስ በመለስ ምስል አይደል እንዴ ያለነው፡፡
አቶ ሃይለማርያም መከላከያው፣ ደህንነቱ፣ ዲፕሎማሲው በጠ/ሚኒስትሩ ስር እንደሆነ ተናግረዋል? ይህማ እንዳልሆነ ሊሾሙ አራት ቀን ሲቀራቸው 37 ከፍተኛ መኮንኖች መሾማቸውን ሰምተናል፡፡ እነዚህን ከፍተኛ መኮንኖች ማሾም የነበረበት ማን ነው? ከዚህ አንፃር የህወሓት የበላይነት ተመልሷል ለሚሉት ቀድሞስ መች ጥያቄ ውስጥ ገባና እንላቸዋለን፡፡ አቶ ሃይለማርያም የካቢኔውን አደረጃጀት ሲያስረዱ፤ ከሌሎች በፓርላሜንታዊ ዲሞክራሲያዊ ሲስተም ከሚተዳደሩ ኢኮኖሚያቸው በፍጥነት እያደገ ከሚገኙት አገሮች የካቢኔ አወቃቀር የተወሰደ ልምድ እና የተካሄደ ጥናት እንዳለ ገልፀዋል … ይህ የተለመደ የኢህአዴግ ፊሊጥ (Modus Operandi) ነው፡፡ ከግሪክ አመጣነው ከግብጽ ወሰድነው ይላሉ፡፡ ሌጂቲሜሲ ለመመስረት የሚደረግ ነው፡፡

 

 

No comments:

Post a Comment