አፈናው ከበረታ ገና በ“ፓፒረስ”ላይ እንጽፋለን!
አፈናው ከበረታ ገና በ“ፓፒረስ”ላይ እንጽፋለን!
ብሩክ ከበደ
ኢህአዴግ ኢትዮጵያን ከተቆጣጠረ በኋላ የምዕራባውያኖቹን ቀልብ ለመሳብ የሶሻሊዝም ካባውን በብርሃን ፍጥነት አውልቆ የመናገርና የመፃፍ መብትን “ሲፈቅድ” አስቦበትና ቆርጦ እንዳልነበር በዛወቅትም ሆነ አሁን ፕሬሱ ላይ የሚያደርሰውና እያደረሰ ያለው ችግር በቂ ምስክር ነው፡፡ ለስልጣናቸው መደላደልና ለርዳታ ፍጆታ ሲሉ “ፈቅደናል” ማለታቸው ያፀደቁትንም ሆነ የሕሊናን (equity) ሕግ እንዲደፈጥጡ አስችሏቸዋል፡፡
ሕዝብ የማወቅና የማሳወቅ መብቱ ሙሉ ለሙሉ እንዲገፈፍ በየወቅቱ የተለያዩ “ውሃ አይቋጥሬ” ምክንያቶች እየተፈጠሩ አፋኝ እርምጃዎች ተወስደዋል፡፡ በዚህ ተቃርኖአዊ አያያዝም በርካታ ጋዜጠኞች ታስረዋል፣ ተደብድበዋል፣ ተሰደዋል፣ ራሳቸውን አጥፍተዋል፡፡ ምንም ነገር ባልተሟላለትና በማይሟላለት ነፃ ፕሬስ ዙሪያም ለተሰባሰቡ ጋዜጠኞች ዓለም አቀፉ የጋዜጠኞች ማህበር ከአፍሪካ ለመጀመሪያ ጊዜ ቀዳሚ የሆነውን ሽልማት ለኢነጋማ (አቶ ክፍሌ ሙላት ይመሩት ለነበረው ማህበር) መስጠቱ በዚያ አስቸጋሪ ሁኔታ ሳይበገሩ ይሰሩ ለነበሩት የነፃው ፕሬስ አባላት እውቅና የሰጠ ነበር፡፡
ሕዝብ እንዲመሩት ይሁንታ ያልሰጣቸው አምባገነን ገዢዎች ከሕዝባቸው የሚነሳውን ጥያቄና ቅሬታ በፍፁም ማድመጥም ሆነ ማንበብ ስለማይፈልጉ፣ እነሱ ብቻ የሚናገሩትና የሚያስቡት በጭብጨባ ፀድቆ በመሳሪያ ኃይል ተግባራዊ እንዲሆን ለማድረግ ካላቸው ፍላጐት ስላላቸው፣ ለዚህ እኩይ አላማቸው የማይተባበረውን ነፃ ፕሬስ የጦር ያህል ይፈሩታል፡፡ በተለይ በአምባገነኖች ዙሪያ የተኮለኮሉ ሆድ እንጂ ሚዛናዊ ህሊና ያልፈጠረባቸው ግለሰቦችና ቡድኖች በግል ያካበቱት በዘረፋ የተገኘ ሀብት እንዳይነካባቸው ስለሚፈልጉ ዋንኛ የፕሬስ ጠላት ሆነው በፊት መስመር ይሰለፋሉ፡፡ ሟቹ ጠቅላይ ሚ/ር “የመንግስት ሌቦች” ያሏቸው አይነቶች ለዚህ በቂ ማስረጃ ናቸው፡፡ እኚህ ሟች ጠቅላይ ሚ/ር አፋኝ ህጐችንና ደንቦችን የማውጣት ሥራ አይመለከታቸውም እንዳንል ሀገሪቷን ለ21 አመታት ብቻቸውን እንደመሯት ሰዎቻቸው በሚገባ ነግረውናል አሁንም እየነገሩን ነው፡፡ አቶ መለስ ዜናዊ ለድምፅ ወያኔ ሬዲዮ የተለያዩ ጽሁፎቹን የሚያቀርቡ፣ አዲስ ራዕይ መጽሄትን (ከአሁን በኋላ የምትታተም አይመስለኝም) የሚያዘጋጁ፣ በደርግ ጊዜም አዲስ አበባ ድረስ የፃፉትን መጽሐፍ በድብቅ ልከው ያሳተሙ፣ የኢህአዴግን ፖሊሲና ርዕይ (ራዕይ አይደለም ርዕይ ነው፡ የሁለቱ ትርጉም የማይገናኝ ነው)፣ የሪፖርተሩን አማረ አረጋዊን ጨምሮ ለሌሎቹም በረሀ ላይ የጋዜጠኛነት ኮርስ ሰተዋል የተባለላቸው መለስ ዜናዊ የጽሁፍ ነፃነትን የሚገድብ አዋጅና መመሪያ ለምን ያወጡ እንደነበር በርግጠኝነት መናገር አይቻልም፡፡
ሙያው ስለሚያስፈልገው ጥበቃ በቂ ግንዛቤም እየነበራቸው ሆነብለው ፀረ ፕሬስ አቋም ማራመዳቸው የስርአታቸው ገበና በነፃው ፕሬስ አባላት ለህዝብ እንዳይጋለጥ በመስጋታቸው ሊሆን ይችላል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ሰውየው ከሳቸው ውጪ ማንም ልቆ እንዲወጣ ፍላጐት እንዳይወጣ ከነበራቸው ተፅእኖ አድራሽነት የመነጨ ሊሆንም እንደሚችል ለመገመት ይቻላል፡፡ ነፃው ፕሬስ የሀገራችንን ህዝብ የማወቅና የማሳወቅ መብቱና ኃላፊነቱ በየጊዜው ከሚወጡ አዳዲስ የማጥበቢያ ብሎም የማጥፊያ አዋጅና ደንቦች ውጪ ከምርጫ97 በኋላ ለሁለት ዓመታት ያህል ተከርችሞ ቆይቶ እንደገና ብልጭ ቢልም አፈናው ግን አሁንም የሚያሰራ አልሆነም፡፡ የኢህአዴግ መንግስት ስውር የአፈና አሰራር ምናልባት አቶ በረከት “ከጫካ ጀምረን ምስጢር ጠባቂ ነን” ያሉት ውጤት ሊሆን ይችላልና አንድ ቀን ይፋ እስከሚሆን መጠበቅ ነው፡፡ አሁን ደግሞ ቀ.ኃ.ሥ በ1930 ዓ.ም አጋማሽ ለሀገራቸው እውቀት መዳበር ሲሉ የተከሉትና አሁን በመንግስት ቁጥጥር ስር የሚገኘው ብርሀንና ሰላም ማተሚያ ቤት ለፕሬስ አፈና ተጨማሪ ኃይል ሆኖ ብቅ ማለቱ ሁሉንም ወገን ያስገረመ ብቻ ሣይሆን ያስደነገጠ ሆኗል፡፡
ለመሆኑ ፕሬስን በተዘዋዋሪ የማፈን “ድንቅ” ብልጠት የማንትሆን? መቼስ ቻይናዎች ይህቺን አያውቋትም!! በሟቹ የኦሎምፒክ ኮሚቴ ፕሬዝዳንትና ታጋይ በነበሩት አቶ አሰፋ ማሞ ባለቤት ሥራ መሪነት የሚመራው ተቋም እንደስሙ“ብርሃንንና ሠላምን” ማምጣት ተስኖት ወደ ፊት በትውልድ ዘንድ አጠያያቂ በሆነ የእንቢተኝነት አቋሙ ፀንቷል፡፡ ተቋሙ ለሕዝቦች የማወቅ መብት በፅናት የቆመ ቢሆን ምንኛ የታደለ ነበር፡፡ ይሄኔ በጮሌዎች የታሸውን ምላሽ እንዲሰጥ የታዘዘው የነጮች ተቋም ቢሆን ኖሮ የሥራ ኃላፊዎቹ ሥራቸውን በገዛ ፈቃዳቸው በለቀቁ ነበር፡፡ ለዚህ ይሆን በገና ድርዳሪው “እጆቹን ለነጮቹ መስቀሉን ለጥቁሮቹ!” ያለው? መንግስታዊው የህትመት ተቋም አንዴ “የቆዩ ደንበኞች ሥራ ስላለብኝ አዲሶችን አልቀበልም(ፍኖተ ነፃነት ከድርጅቱ ጋር መሥራት ከጀመረ አመት ሞልቶታል)” ሌላ ጊዜ ደግሞ “ወቅቱ ት/ቤት የሚከፈትበት ጊዜ በመሆኑ በመጽሐፍት ህትመቶች ተወጥሬያለሁ” የሚሉና መሰል ሰንካላ ምክንያቶችን እየሰጠ የሚያፈገፍግበትን ሁኔታ የኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ም/ሀላፊ አቶ ሽመልስ ከማል ተቀብለው አንፀባርቀውለታል፡፡ “ጐሽ እንዲህ ነው እንጂ” ብለውለታል፡፡
ገዢው ፓርቲ (ኢሕአዴግ) ይኽን ቢያስብም ሳምንታዊው የህትመት ኮታቸው ከሃያ ሺህ በላይ የደረሰው ፍኖተ ነፃነትና (ይኽ ጋዜጣ የፓርቲ ልሳን ነው ቢባልም ነፃ ጋዜጦች በጠፋበት ሀገር እንደ አማራጭ ሆኖ የወጣ ጋዜጣ ነው፡፡ ለዚህም ተፎካካሪ ፓርቲው ሕዝባዊነቱን አረጋግጦበታል፡፡) ፍትሕ ጋዜጣ ራሳቸውን ችለው ማተሚያ መሣሪያ እስከሚተክሉ ድረስ የዲሞክራሲና ፍትህ ነፃነት የተጠማ ህዝባቸውን ጩኽት ሊጋሩ በመጽሄት መልክ ተመልሰው መጥተዋል፡፡ የመጽሄቱ ህትመትም በሌላ ማተሚያ ቤት የሚከናወን መሆኑን አንባቢ ልብ ልትል ይገባል፡፡ በጋዜጣ ከሆነ ከተወሰነ የጋዜጣ ገጽ በላይ ማተም የሚችለው ብርሃንና ሠላም ብቻ መሆኑንም በዚህ አጋጣሚ ልገለጽልህ እወዳለሁ፡፡ የሚገርመው ግን የህዝብ ጉዳይ በጋዜጣ ሆነ በመጽሄት መልክ ቢቀርብ ህዝባዊነቱ ይገፈፋል እንዴ? የምታውቁ ካላችሁ ወዲህ በሉኝ፡፡
ጽሁፌን ከማጠቃለሌ በፊትም ግን አንድ ጉዳይ ማንሳት ፈለኩ፡፡ በሀገራችን ታሪክ የዘመናዊነት መሠረትን የጣሉ፤ ሞታቸው አስደንጋጭ ሆኖ ለህዝባቸው ሳይነገር አደባባይ ሳይታዩ ሦስት ዓመት ሙሉ “አሉ” እየተባሉ የመሩት እምዬ ምኒልክ በዘመናቸው በህትመት ማሽን ሣይሆን በእጅ እየተፃፈ በቤተ መንግስታቸው በጧት ይደረስ እንደነበረው ጋዜጣ ወይንም ከክርስቶስ ልደት በፊት ጥንታውያኖቹ ምስሮች (ግብፆች) በዓባይ ወንዝ ከሚያለሙት ዛፍ መሰል ተክል ግንድ ላይ በሚልጡት ልጥ በሚያዘጋጁት ፓፒረስ የተሰኘ የጽሑፍ ወረቀት መረጃን ለህዝብ ለማቀበል እንገደድም ይሆናል፡፡ ምክንያቱም አንዴ ቁልቁል እንድንወርድ ከተፈረደብን፡፡ ዕድሜ ለሰው ልጅ እውቀትና ዲሞክራሲ ተሟጋች ህዝቦች ሀገራቸው ለዜጐቻቸው ምቹ እንድትሆን ለማድረግ በሚያደርጉት ያላሳለሰ ጥረት ዩቲዬብ፣ ቲዩተር፣ ፌስቡክና ሌሎች ሕዝባቸው የተለያየ ጉዳዮችን እያነሳ የሚወያይባቸው ድረገፆችን ስላበረከቱልን በእጅጉ እያመሰገናቸው ቀደምቱን የጽሑፍ ወረቀት ለፓፒረስን የምንዘነጋው አንሆንም፡፡ ሕዝባችን ሞባይል እንደማይጠቀሙት ሰሜን ኮርያዎች፣ የተለያዩ ማህበራዊ ድረገፆች እንደተነፈጉት ቻይናዎችና፣ በቅርቡ ሞባይል ሲፈቀድላቸው እንደፈነጩት ኩባዎች ወዘተ ከመሆኑ በፊት ራሱን ነፃ ማውጣት ያለበት አሁን ነው።
No comments:
Post a Comment