Wednesday, November 14, 2012

ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ በጀርመን አገር ዋና ከተማ በርሊን ላይ ተደረገ

በጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን በአይነቱ ልዩ የሆነ በተለያዩ መፈክሮች እና በኢትዮጵያ ባንዲራ ያሸበረቀ ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ በጀርመን ዋና ከተማ በርሊን አደረጉ። ሰላማዊ ሰልፉን ያዘጋጀው በጀርመን የፖለቲካና የሲቪክ ማህበራት አንድነት ድርጅት (EPCOU) ሲሆን በእለቱም ከተለያዩ የጀርመን አካባቢ የሚኖሩ ቁጥራቸው ከ290 በላይ የሚገመት ኢትዮጵያውያን ተሳትፈዋል::መነሻውን በርሊን ከተማ SPD (ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ) ዋና ቢሮ ፊት ለፊት ያደረገው ሰላማዊ ሰልፍ የኢትዮጵያውን አምባገነን ስርአት ቁንጮ የሆነውን ስብሃት ነጋ በጀርመን ተጋብዞ ንግግር እነዲያደርግ መጋበዙ ኢትዮጵያውያንን እጅግ በጣም ያሳዘነ እና ያስቆጣ ድርጊት መሆኑን በመፈክር አሰምቷል። የሰላማዊ ሰልፍኛው ተወካዮች ከሶሻል ዲሚክራቲክ ፓርቲ ተወካይ ጋር አጠር ያለ ንግግር አድርገው የተዘጋጀውን ፅሁፍ ለተወካዩ ሰተዋል። ሰላማዊ ሰልፈኞቹ SPD (ሶሻል ዲሞክራቲክ ፓርቲ) ዋና ቢሮ ፊት ለፊት ሲያሰሙት ከነበረው መፈክር መካከል ስብሃት ነጋ ስለ ሰብአዊ መብትና ዲሞክራሲ የመናገር የሞራል ብቃት የለውም ! Shame on SPD for inviting Ethiopian dictator Sebehat Nega ! እና ሌሎችም ይገኙበታል።


የኸው ደማቅ ሰላማዊ ሰልፍ በመቀጠል ያመራው ወደ ጀርመን የኢኮኖሚ ልማትና እርዳታ ሚኒስቴር ቢሮ ነበር በቦታው እንደደረሰ በሚንሰትር ቢሮው ፊት ለፊት ቆሞ ካሰማው መፈክሮች መካከል Germany Stop Supporting Ethiopian Dictatorial regime ! እንዲሁም ሌሎች መፈክሮችን ከፍ አድርጎ ጩኸቱን አሰምቷል። በቦታውም የዚህ ሰላማዊ ሰልፍ አዘጋጅ በጀርመን የሲቪክ እና የፖለቲካ ድርጅት አንድነት አባላት ዋና ፀሃፊ የሆኑት አቶ ፍቅረሰብ አበበ አማካኝነት የተዘጋጀውን ፅሁፍ በማስገባት የህዝቡን ጥያቄ እንዲያውቁት ያደረገ ሲሆን ይህ ስርአት ከጀርመን መንግስት በእርዳታና ልማት ሚኒስቴር አማካይነት የሚሰጠውን እርዳታ የኢትዮጵያ መንግስት ህዝቡን ለማፈን እየተጠቀመበት ስለሆነ ጀርመን ለኢትዮጵያ መንግስት ምትሰጠውን እርዳታ ባጋባቡ መዋሉን እንድትቆጣጠር ጠይቋል።ሰላማዊ ሰልፉ በበርሊን ጎዳና መፈክሮችን እያሰማ የመጨረሻ ጉዞውን ያደረገው ወደ ጀርመን ካውንስለር አንጄላ ማርኬል ቢሮ ሲሆን ሰላማዊ ሰልፈኞቹ የተለያየ መፈክሮችን እያሰሙ የበርሊንን ጎዳና አድምቀውታል። ሰልፈኛው በጀርመን ካውንሰለር አንጄላ ማርኬል ቢሮ ሲደርስ ባንዲራውን እያውለበለበ መፈክሮቹን ከፍ አርጎ ይዞ ድምፁን ሲያሰማ በሁኔታው የተገረሙት የቢሮው ሰራተኞች ከህንፃው በረንዳ ላይ ሆነው ትእይንቱን ተከታትለውታል ። ለጀርመኗ መሪ አንጄላ ከውንስለር የተዘጋጀውን ፅሁፍ ያቀረቡት የሰላማዊ ሰልፉ አዘጋጅ በጀርመን የሲቪክ እና የፖለቲካ ድርጅት አንድነት አባላት የባየር ሊቀመንበር የሆኑት አቶ የወንድወሰን አናጋው እና የባየር የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት አቶ አንቀሳዊ ምስጋኑ ናቸው።በመጨረሻም ሰልፉ ከመጠናቀቁ በፊት የዚህ ሰላማዊ ሰልፍ አዘጋጅ ኮሚቴ አስተባባሪ የሆኑት አቶ በላይነህ ወንዳፍራሽ ለሰላማዊ ሰልፈኛው ባሰሙት ንግግር እኛ በስደት የምንገኝ ኢትዮጵያውያን ከምንጊዜውም በበለጠ ህብረትና ወገናዊ ፍቅርን በመካከላችን በመመስረት በህዝባችን ላይ እየደረሰ ያለውን የሰብዓዊ መብት እረገጣ ሰለቸኝ ደከመን ሳንል ለምንኖርበት ህዝብና መንግስት ማሰማት ከኛ የሚጠበቅ የዜግነት ግዴታችን መሆኑን ጠቁመው በማያያዝም የኢትዮጵያውያን በጋራ መቆም የሚያስፈራቸው ከመከፋፈላችን ተጠቃሚ ለመሆን የሚሯሯጡ ወገኖች በተለያየ መንገድ የሚያራግቡትን ተራ ወሬና አሉባልታ ግምት ሳትሰጡ ወደፊት በስደት አለም ውስጥ እራሳችንን እረድተን በጋራ በመቆም ሳይማር ያስተማረንን ህዝብ ለመርዳት ያለን ብቸኛ ምርጫ በኢትዮጵያዊነት እጅ ለጅ ተያይዘን መጓዝ በመሆኑ ይህንን አላማ የምትደግፉ ወገኖች በሙሉ አብራችሁን እንድትቆሙ በማለት ጥሪ አስተላልፈዋል፥ በመቀጠልም በጀርመን የኢትዮጰያ የሰብአዊ መብት ኮሚቴ ሊቀመንበር አቶ ስዩም በበኩላቸው ድርጅታቸው ከማንኛውም የፖለቲካ ድርጅት ጋር ሳይወግንና ነጻ በመሆን በሰብዓዊ መብት መከበር ዙሪያ በመንቀሳቀስ ላይ ያለና ወደፊትም ለሰብዓዊ መብት መከበር ከቆሙ ወገኖች ጋር አጋር በመሆን ድጋፍ እንደሚያደርጉ የተናገሩ ሲሆን አያይዘውም የስደተኞችን መብት በማስጠበቅ ዙሪያም ድርጅታቸው ከሚመለከታቸው ክፍሎች ጋር ግኑኝነት በመፍጠር የተለያዩ የመረጃ ልውውጦች እንደሚያደርጉ ለሰልፈኛው አስረድተዋል።በመጨረሻም ከሆላንድ ድረስ ተጉዘው የመጡት የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ(ሸንጎ) የፕሮፖጋንዳ እና ቅስቀሳ ሃላፊ ንግግር ያደረጉ ሲሆን በንግግራቸውም ላይ በቀጣይ ይህ አይነቱ የተቃውሞ እንቅስቃሴ በዛሬው ዕለት ብቻ ተወስኖ እንዳይቀር በቀጣይነትም አለም አቀፍ መልክ ይዞ እንዲካሄድ የኢትዮጵያ ሕዝብ የጋራ ትግል ሸንጎ በውጭ አገር የሚገኘው ለዲሞክራሲ ስርአት መስፈን ፤ለአገር አንድነት ፤ለሰብአዊ መብት መከበር ፤ለዜጎች እኩልነትና ለአምባ ገነኖች ስርአት መወገድ የሚታገለው የተቃዋሚ ድርጅትና ዜጋ እጅ ለእጅ ተያይዞ በየመድረኩ ትግሉን እንዲቀጥልበት ጥሪ አድርገዋል። ለኢትዮጵያ ህዝብ ዲሞክራሲያው ስርአት መስፈን ድርጅቶች በጋራ መስራት እንዳለባቸው አሳስበው ድርጅታቸውም የተለያዩ የሲቪክ እና የፖለቲካ ድርጅቶች በጋራ የተቋቋመ መሆኑን ገልፀው ወደፊትም ድርጅታቸው በጀርመን የሲቪክ እና የፖለቲካ ድርጅት አንድነት አባላት ማህበር ጋር በጋራ መስራት ፍላጎት እንዳለው ገልፀው የድርጅታቸውን አላማ አጠር ባለ ፅሁፍ አዘጋጅተው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ለተገኘው በመበተን ህዝቡ እንዲያነበው አድርገው ሰልፉ ተበትኗል።


No comments:

Post a Comment