Friday, November 16, 2012

"ሰንበት ምሳ"



አቤ ቶኪቻው



 

እኛ ሰፈር ሽሮሜዳ የሰንበት ምሳ የሚባል ነገር አአለ። እሁድ እሁድ ቤተሰቦች ለልጆቻቸው የሚሰጡት ሳንቲም፤ አንዳንዴም ወዳጅ ለወዳጁ በእሁድ ቀን የሚያበረክተው ስጦታ (ብዙ ጊዜ ይህ ስጦታ ወይ ስሙኒ ወይ ደግሞ ሃምሳ ሳንቲም ነው) ብቻ ግን "ሰንበት ምሳ" ነው የሚባለው። ሰሞኑን በሌላ መስኮት ልመጣ አስቤ ተጠፋፍተን ሰነበትን አይደል!? እስቲ ዛሬ በዝች ሰንበት "ሃይ" እንባባል

ይቺ ፅሁፍ አዲስ ታይምስ (ፍትህ) ትላንት ይዛት ትወጣ ዘንድ ልኪያት ነበር። ከርዕሷ በቀር እንዳለች ናት! (ሃ አንዳንድ ቦታ ትንሽ ነካ ነካ ተደርጋለች) እስቲ ለማንኛውም እንቋደሳት፤ ተጀመረች


ከብዙ ጊዜ በኋላ ወደ ሀገሩ መመለሱ ነው። ከቦሌ ኢንተርናሽናል አውሮፕላን ማረፊያ ታክሲ ለመኮናተር አይኑን ቃኘት ቃኘት ሲያደርግ አንዱ ቀልጣፋ ቀልጠፍ ብሎ፤ "ታክሲ ፈልገህ ነው!?" አለው።

"
አዎ"

"
የት ነህ?"

"
ስታድየም አካባቢ ካደረስከኝ ይበቃኛል።"

"
ሶስት መቶ ብር"

"
አልተወደደም…?" ብሎ እየጠየቀ ለመሳፈር ሳይሆን ለመከራከር የሚገባ ይመስል ወደ ታክሲዋ ገባ። ሹፌሩም ለወጉ ያህል እንጂ ሊከራከረው እንዳልሆነ ገባውና "ባይሆን ፀባዬን አይተህ ትጨምርልኛለህ!" ብሎ ቀልዶ ታክሲዋን ሊዘውራት ተሰነዳዳ።

ታክሲዋ ውስጥ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን አባላትን እና የሟች መለስ ዜናዊ ፎቶዎች ተለጣጥፈውባታል። እንግዳው ዙሪያ ገባዋን እየቃኘ ሳለ ድንገት "የት ነበርክ!?" ሲል ባለ ታክሲው ጠየቀው። ጨዋታ መጀመሩን እንግዳው አልጠላውም፤

"
አውሮፓ ነበርኩ"

"
ታድያ ምነው በደህና ተመለስክ?"

"
ትምህርት ላይ ነበርኩ ስጨርስ መጣሁ!"

ባለታክሲው በሀሳቡ ባለስልጣኑ እና የመንግስት ጋዜጠኛው ሁሉ እየወጣ በሚቀርበት በዚህ ዘመን ትምህርት ስለጨረስኩ መጣሁ ብሎ የሚናገር ሰው በመስማቱ ተገረመ። ምናልባትም የመንግስት ታማኝ ሰው ይሆናል! ሲልም አሰብ።

አሁን ደግሞ ተጠያቂ ባለተራው ሹፌሩ ሆነ!

"
ስራ እንዴት ነው!?" አለው።

"
ጥሩ ነው ይኸው ራዕያቸውን ለማሳካት ቀን ተሌት እየለፋን ነው።" አለ ወደ ተለጠፈው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ፎቶ እየጠቆመ። እንግዳው ግር አለው።

"
የእኔ ጥያቄ የታክሲ ስራ እንዴት ነው!? ለማለት ነበር…" ሲል ምናልባት ጥያቄዬን አልተረዳው ይሆን ብሎ አሻሻለለት።

"
እኔም የመለስኩልህ ስለ ታክሲው ስራ ነው። ለእርሳቸው ራዕይ ስንል በትጋት እየነዳን ነው!" አለ። ምን ታመጣለህ! የሚለው መሰለው። እንግዳው፤ ፈገግ ብሎ "አይ ጥሩ ነዋ!" ብሎት ሲያበቃ፤ ማንሰላሰል ጀመረ።

አሁን በቅርቡ በህይወት እያሉ ታላቁ ሩጫ ላይ "ሳንፈልጋቸው ሃያ አመታቸው!" ሲባሉ የነበሩ ሰውዬ ዛሬ ሲሞቱ እንዲህ ወዳጃቸው መብዛቱ አስገረመው። ወደ ውጪ ሲመለከት በየመንገዱ በአጭር አጭር ርቀት ፎቶግራፋቸው ተሰቅሏል። ከተቀበሩ ቆይተዋል። ታድያ ይሄ ነገር እስከመቼ ነው የሚቀጥለው!? ሲል ራሱን ጠየቀ። ልክ ይሄን ጊዜ "ዘላለማዊ ክብር ለመለስ" የሚል አንድ "ፖስተር" ተመለከተ።

ዝምታ መስፈኑን ያልወደደው ባለታክሲ ራዲዮ ከፈተ። ጋዜጠኛው በስልክ አንድ ሰው እያናገረ ነው። እንግዳው ተሳፋሪ ፕሮግራሙ ከግማሽ ስለጀመረ ጫፉን ለመያዝ ትኩረት ሰጠ። ስለ ውበት የሚያወራ የራድዮ ዝግጅት መሆኑ ወድያው ገባው።

አዎ በዛኛው መስመር አንዲት የፀጉር ማስተካከል
"ዲዛይነር" ስራዎቿን እያስተዋወቀች ነው።

"
እስኪ ለአድማጮቻችን ስለ አሰራሩ አስረጂልን!"

"
እንግዲህ እንዳልኩህ አዲስ የወንዶች ፀጉር ስራ ነው ነውከፊት ያለው ፀጉር እስከ ግማሽ ድረስ ይላጫል። የተቀረው በአጭሩ ይከረከማል። በጥቅሉ ሰው ሰራሽ በራ በለው!"

"
….ያያአሪፍ ፋሽን ነው።ይህ የፀጉር ፋሽን የጠቅላይ ሚኒስትሩን ራዕይ ከማስቀጠል አንፃር የሚኖረውን አስተዋፅኦ እንዴት ትገልጭዋለሽ!? የህዝቡስ አቀባበል እንዴት ነው!?"

እንግዳው ፈገግ አለ።

"
ይሄ የፀጉር ፋሽን የተሰራው የእርሳቸውን ራዕይ ለማስቀጠል ታስቦ ነው። ስያሜውንም ጀግና አይሞትም ብለነዋል…"

አሁን ሳቁ አመለጠው። ከት ብሎ ሳቀ። ይሄኔ የታክሲ ሹፊሩ እንግዳው እንዳሰበው የመንግስት ቤተዘመድ እንዳልሆነ ገመተ። ቢሆን ኖሮ እንዲህ አይስቅም ነበር። ሲልም አሰበ። እናም የራድዮኑን ድምፅ እየቀነሰ "ምን እናድርግ ብለህ ነው አለበለዛ መኖር አልቻልንም እኮ!" አለው።

ይሄን ጊዜ መስቀል አደባባይ ደርሰው ነበር። ባለታክሲው ስልክ ተደወለለት። "ጩኸት" ላይ አድርጎ ማውራት ጀመረ።፡

"
አቦ የት ነህ ባክህ!" አለው ደዋዩ የቅርብ ጓደኛው መሆኑ ያስታውቃል።

"
ከመለስ ኤርፖርት ተነስቼ ወደ ስታድየም እየሄድኩ ነው። አሁን መለስ አደባባይ ደርሻለሁ። የት ነህ አንተ!"

"
እኔ ይሳካል ራዕዩ ድራፍት ቤት ነኝ አዝዤ ጠብቅሃለሁ ቶሎ ና!"

"
እሺ ባይ!"

ስልኩ ተዘጋ። እንግዳው ነገሩ ሁሉ እንግዳ ሆነበት። "የጉድ አገር ገንፎ እያደር ይፋጃል" የሚለው ተረት ድንገት ትዝ አለው። ወድያውም ጠየቀው።

"
ኤርፖርቱ መለስ ኤርፖርት! ተባለ እንዴ!?"

"
አልሰማህም እንዴ!?"

እሺ ይሁን መስቀል አደባባይ መቼ ነው መለስ አደባባይ የተባለው!?

"
ቆየ እኮ!"

ግራ ገባው።

ወደ ስታድየም ሲቃረቡ ግረግር ነገር አየ።
"ምንድነው?" ብሎ ጠየቀ።

"
ዛሬ እግር ኳስ ጨዋታ አለ።" አለው። እንግዳው ሌላ አይነት ወሬ በመምጣቱ ደስ እያለው። "ይገርምሀል ድሮ ቀንደኛ የስታድየም ታዳሚ ነበርኩ" ሲል ትዝታው በአይኑ እየመጣ ነገረው።

"
የማን ደጋፊ ነበርክ?" ብሎ ጠይቆት መለሱንም ሳይጠብቅ "እኔ የመለስ ቡና ደጋፊ ነኝ ዛሬ መለስ ቡና ከመለስ ጊዮርጊስ ነበር ጨዋታው። ስራ ባይኖረኝ አልቀርም ነበር። ይገርምሃል የመለስ ፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ገና መጀመሩ ነው!"

እንግዳው እንግዳ ስሜት ተሰማው። እይኑ እንባ አቀረረ። ሊያጥወለውለው የፈለገም መሰለው… "ምንድነው ጉዱ!?" ሲል ጠየቀ። የታክሲ ሹፌሩ ገብቶታል። "ያው ራዕያቸውን ለማስፈፀም ግድ ነው! ተብሏል" አለው።

እንግዳው ዛሬን ሆቴል አድሮ ነገ ወደ እናቱ ሀገር ሀዋሳ ያመራል። ሁሉ ነገር በመለስ ተሰይሞ አንዱን ከአንዱ ለመለየት የምንቸገርበት ቀን ሳይመጣ አንቀርም! ሲል በሆዱ እያሰበ። አዲሳባ ስታድየምን ገርመም ሲያደርገው፤ "አዲሳባ መለስ ስታድየም!" የሚል በጉልህ ተፅፎ ተመለከተ። ሰዎቹ ምን ሆነዋል…!?

"
ለማንኛውም እስቲ ራስ ሆቴል አድርሰኝ!" አለው። ለማረፍ ያሰበበት ሆቴል ነው።

ዘወር እንዳሉ ደረሱ "እንኳን ወደ ራስ መለስ ሆቴል በሰላም መጡ!" ተብሎ የተፃፈ ተመለከተ። ግራ እየገባው ለባለታክሲው የተነጋገሩትን ሂሳብ ከፈሎ ወረደ።

እንግዳ ክፍሏ ከጀርባዋ "የመለስን ራዕይ እናስፈፅማለን" የሚል ፅሁፍ ተለጥፏል።

"
ምን ልታዘዝ"

"
አልጋ ፈልጌ ነው!"

ከዱላ የማይተናነስ ማንጠልጠያ ያለው ቁልፍ ሰጥታ ቁጥሩን ነገረችው። አቅጣጫውንም ጠቆመችው። እና ሄደ። የቁልፍ ማንጠልጠያው ላይ "የመለስን ራዕይ ለማሳካት ቁልፍዎን በአግባቡ ይያያዙ!" የሚል ተፅፎበት ተመለከተ።

መኝታ ክፍሉን ሲከፍተው "ጀግና አይሞትም ያንቀላፋል እንጂ! መልካም እንቅልፍ!" የሚል ከመለስ ፎቶ ስር ተፅፎ ከራስጌው ተሰቅሏል። የሚያየው ነገር ሁሉ ሊያሰክረው ነው።

ትንሽ ማረፍ ፈልጎ ነበር። ይቅርብኝ ብሎ፤ ወጣ እግሩ እንደመራው ሄደሄደሄደአንድ ምሽት ቤት አገኘ። ዘው ብሎ ገባ። ቤቱ በቆነጃጅት ተሞልቷል። እንደገባ አልኮል አዘዘ እና ዥው አድርጎ ጠጣ። "አሁን ልክ ሆንኩኝ" ሲል አሰበ። እጁን ጨብጨብ ሲያደርግ አንዲት ቆንጆ መጣች ከመብራቱ ይበልጥ የሚያብረቀርቅ ፈገግታ ለገሰችው። እና፤ "ይጨመር!?" ስትለው፤ ቅድም ይቺ ቆንጆ እንደታዘዘችው አላስተዋለም ነበር። "አዎ…! ላንቺም አንጪ ለኔም ቅጂ…" አለ ጨዋታ ለማሳመር! እውነትም ለራሷም ለእርሱም ይዛ መጣች። ይሁን አለ በሀሳቡ

"
እሺስራ እንዴት ነው!?" አላት።

"
ጥሩ ነውየእርሳቸውን ራዕይ ለማስቀጠል እየለፋን ነው!" አለችው ወደ ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር ፎቶ እያመለከተችው። አሁን ሁለተኛውን ትዕዛዝ ሳይጠጣ ሰከረጢንቢራው ዞረ!

ጢንቢራው እንደዞረ ዞር ሲል በቡና ቤቱ ግድግራ ላይ አንድ ማስታወቂያ ተመለከተ። "ለቆነጃጅት በሙሉ ከነገ ጀምሮ ሁላችሁም በግልፅ በሚታይ የሰውነታችሁ አካል ላይ "የመለስን ራዕይ እናሳካለን" የሚል ንቅሳት ተነቅሳችሁ እንድትመጡ ድርጅቱ በትህትና ስንጠይቅ፤ ይህንን የማያደርግ ከበራፉ ድርሽ እንዳይል አሁንም በትህትና እንገፃለን" ይላል።

እያለ እያለ ይቀጥላል

የመለስ ረዕይ ግን ምን ነበር!?

No comments:

Post a Comment