(ናትናኤል ካብትይመር)
እኛ የምናውቃት ኢትዮጵያ ከግማሽ በላይ ህዝቧ በመብራትና በውሃ እጦት የሚሰቃይባት ፣ በስልክና በኔትወርክ ችግር የሚማረርባት ፣ በመልካም አስተዳደር እጦት አሳሩን የሚበላባት ፣ አብዛኛው ህዝቧ የዛሬን እንጂ የነገን ማቀድ የማይችልባት፣ የተለያዩ ተንታኞችና አለማቀፍ ድርጅቶች “ችግር አለ” ብለው የሚያስጠነቅቋት ፣ ለዲሞክራሲ ፈር ቀዳጅ መሆን የሚገባው የፖለቲካ ስርዓት የሚያስፈራና ደም ደም የሚሸትባት ፣ ብዙ ዜናና ትንታኔ ስለ አንዲት የመንግስት ፕሮጀክት ለአመታት የሚነገርባት ፣ ከአንዲት ፕሮጀክት ብዙ ሚሊዮን ብር በሙስና ተዘርፎ ጥቂቶች የሚከብሩባት ፣ መንግስት ተብየው ሃገርና ህዝብ ከማስተዳደር ይልቅ ስልጣኑን ለማደላደል ተግቶ የሚሰራባት ፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎቿን በየአመቱ በስደት የምታጣ ፣ ለቁጥር በሚታክቱ አሰቃቂ የመኪና አደጋዎች በየቀኑ ዜጎቿ የሚረግፉባት ፣ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ዜጎቿ በህክምና እጥረት በሞት የምትነጠቅ ፣ ችግሮቿ ለቁጥር የሚታክቱ ነገር ግን ኩሩ ታሪክ ያላት ጥቂት ሆዳሞች በፈጠሩት ችግር አንገቷን የደፋች ሃገር ናት።
እነሱ ግን ልክ እንደማናውቃት ሌላ ሃገር ኢኮኖሚዋ አለምን ባስገረመ መልኩ ለተከታታይ ብዙ አመታት የተመነደገባት ፣ የአለማችን መዓት ሃገራት የሚቀኑባትና ልምድ የሚቀስሙባት ናት ይሉናል። ለመሆኑ ይህች እነሱ የሚሏት ሃገር የት ነው ያለችው? ለምን ይሆን ስለገዛ ሃገራችን ከአመት አመት ልክ እንደማናውቃት በሞኝ ውሸት የሚሰብኩን?
ሃገራችን ችግር ላይ መሆንዋን ችግርዋም ከግዜ ወደ ግዜ እየተወሳሰበ ለመፍታት ወደሚያስቸግር ሂደት ውስጥ እየገባ መሄዱን የተለያዩ ምሁራን ፣ ፖለቲከኞች ፣ ተንታኞች እንዲሁም አለማቀፍ ድርጅቶች ሲወተውቱ በአንፃሩ ደግሞ መንግስት ነኝ ብሎ የተቀመጠው አካል የዝሆን ጆሮ ይስጠኝ እያለ ነው። ሁላችንም የምናውቀው አንድ እውነት ከጥቂት ሆዳሞች በስተቀር ኢትዮጲያዊ ሆኖ ሃገር እንድታድግለት የህዝቡም ኑሮ እንዲሻሻልለት የማይፈልግ የለም። ነገር ግን መንግስት ተብየው የሃገራችንን ችግር ለመፍታት ከመሞከር ይልቅ የባሰ እያወሳሰበውና ጭርሱንም እየሸፋፈነ ወደ መፍትሄ አልባነት እየገፋው ይገኛል። የችግሩንም መኖር የሚጠቁሙ ዜጎችና አለማቀፍ አካላት እንደመንግስት ተቀራርቦ መፍትሄ ከመፈለግ ይልቅ እንደሃገር ጠላት እየፈረጀ ይገኛል።
ሃገራችን ለዘመናት ለተጫናት ችግር የህወሃት መንግስት በጉልበት መመካት መፍትሄ ሳይሆን ሌላ ችግር ፈጣሪ መሆን ነው። ይህንንም መንግስት ተብየው በሚገባ ያውቀዋል። ነገር ግን ሃገር ወዳድነት ወደጎን ተብሎ በራስ ወዳድነትና አድር ባይነት ውድ ሃገራችን ኢትዮጵያ ወደ አጓጉል ሁኔታ ውስጥ እየተገፋች ነው። ጥቂት ራስ ወዳዶችና በግለኝነት የተዋጡ ተራ ብልጣ ብልጦች ለሃገር እድገት ከመጣር ይልቅ አንዲት ነገር እየተቀባበሉና ቅርፅ እየቀያየሩ ትንታኔ በመስራት የማናቃት ኢትዮጲያ በመፍጠር ህዝባችንን የህልም ዳቦ እየበላህ ኑር እያሉት ነው።
የሃገራችን ህዝብ ከመቼውም ግዜ በበለጠ የለት ተለት ኑሮው እጅግ አስቸጋሪ እስኪሆን ድረስ በዘርፈ ብዙ ችግሮች ተይዟል። በመንግስት ቴሌቪዥን የሚያይዋት ኢትዮጵያ የት እንዳለች አያውቁም። ደስተኝነት ከአብዛኛው ህዝባችን ርቋል። የሃገራችን ህዝብ በመንግስት ሚዲያ የሚነገረው የህልም የኢኮኖሚ ትሩፋት የት እንዳለ አያውቅም። በዋና ከተማ እየኖረ የሚጠጣው ያጣን ህዝብ ፣ በዋና ከተማ እየኖረ ለወራት በመብራት እጦት ሳቢያ በሻማ ለሚኖር ህዝብ ፣ በትራንስፖርት እጦት እየተሰቃየ ለሚኖር ህዝብ ፣ በመኪና አደጋ ፍራቻ በሰቀቀን ውሎ ለሚገባ ህዝብ በጥቂት ሆድ አደር ብልጣ ብልጦች ስለ ሃገር ኢኮኖሚ መመንደግ ፣ ስለ ከተማ ውበትና ስለትራንስፖርት መትረፍረፍ ይነገራዋል።
ሃገራችን ችግር ላይ ነች። ይህን ማለት ችግር መፍጠር አይደለም። መንግስት ነኝ ብሎ የተቀመጠው አካል የተሞላው በራስ ወዳዶች ፣ ብልጣ ብልጦችና የህዝብ ብሶት በማይሰማቸው ሆዳም ግለሰቦች ነው። ይህንን የሃገራችንን ችግር ከነችግር ፈጣሪዎቹ ማስወገድ የማንኛውም ሃገር ወዳድ ዜጋ ሃላፊነትና ግዴታ ነው። ሃገራችን ጭርሱን የማይፈታና ወደውሃላ የማይመለስ አደጋ ውስጥ ከገባች በውሃላ ጣት መጠቋቆሙ ከክፉ ፀፀት ውጪ የሚፈይደው ነገር አይኖርም። እኛም ሆነ እነሱ የምናወራው ስለ አንድ ሃገር ነው። ስለ ኢትዮጵያ። ኢትዮጵያን ከችግር የማውጣት ግዴታ ያለብን ደግሞ እኛው ኢትዮጲያውያን ነን። አዎ ኢትዮጵያችን ከመቼውም ግዜ በላይ ችግር ላይ ነች።
No comments:
Post a Comment