Thursday, April 24, 2014

ባርያ ነጻ የሚወጣው መቼ ነው? እሱ ሲፈቅድ ነው? ወይስ ጌታው ሲፈቀድለት?


ክፍል አንድና ሁለት ፕ/ር መስፍን ወልደ ማርያም

freedom

አንድ

በአለፈው ሳምንት (ፋክት ቁጥር 36) ወይዘሮ መስከረም የተለያዩ መጻሕፍትን በመጥቀስ በሴቶች ላይ ያለውን መጥፎ ጫና በደንብ ያስመሰከረች ይመስለኛል፤ ግን እኮ በሴቶች ላይ ያለው ጫና የቆየ፣ ክፉና ጎጂ መሆኑን ማንም ያውቀዋል፤ ቁም-ነገሩ ያለው ከዚያ የባህል ጭነት በራስ ጥረት ወጥቶ፣ ነቀፌታንም ሆነ እርማትን ለመቀበል ሳይፈሩና ሳያፍሩ እንደመስከረም በአደባባይ ሀሳብን በመግለጽ በአገርና በወገን ጉዳይ መሳተፍና ሌሎችም እንዲሳተፉ የተቻለን ሁሉ ማድረጉ ላይ ነው፤ ለዚህ ነው ይህንን መልስ የምጽፈው፤ ወይዘሮ መስከረም በአጋጠሟትና በምታያቸው እንቅፋቶች ላይ ማተኮርዋ እንደርስዋ መንፈሳዊ ወኔው የሌላቸውን ያስፈራራቸዋል እንጂ አያበረታታቸውም፤ የማንንም አፍአዊ ጫና ተቋቁመው በራሳቸው የውስጥ ኃይል እንዲመሩ እናድርግ።
አንድ መጽሐፍን በመጥቀስ ወይዘሮ መስከረም የሚከተለውን ጽፋለች፡–
ፈጣሪ የሠራውን  ውጫዊ  ገጽታን ማሽሞንሞን በቂ እንደሆነ ሲነገራት የኖረች ሴት፣ በምን ተነሳሺነት አእምሮዋን የሚመግብ  እውቀት ልትሻ ትችላለች? … በልጅነት እውቀትን  ወደመሻት ያልተገፋ ማንነት በጉብዝና ወራት አላዋቂ በመሆን ቢወቀስ ትርጉም አይኖረውም፤ … ››
ወይዘሮ መስከረም ሔዋን ሲነገራት የማትሰማ የመጀመሪያዋ ሰው (ልብ በሉ ሴት አላልሁም፤) መሆንዋን እንዴት እስከዛሬ ሳታውቅ ቀረች? ባለመጽሐፉም ይሁን መስከረም የሔዋንን ታሪክ ሳያነሡ መቅረታቸው መሠረታዊ ስሕተት ነው፤ በተጠቀሱት ሁለት ዓረፍተ ነገሮች ውስጥ አንድም እውነትን የሚመስል ነገር የለም፤ መስከረም ‹‹የሔዋን ዘር›› ከማለት በፊት የሔዋንን ሥራ ቆም ብላ ብታስታውስ የጠቀሰችውን መጽሐፍ እኔ እንደምነቅፈው ትነቅፈው ነበር፤ የሔዋን ታሪክ የሚነግረን የሚከተለውን ነው፡ ‹‹ዛፉ ለመብላት ያማረ እንደሆነ ለዓይንም እንደሚያስጎመጅ፣ ለጥበብም  መልካም እንደሆነ አየች፤ ከፍሬውም ወሰደችና በላች፤ ለባልዋም ደግሞ ሰጠችው፤ እርሱም ከእርስዋ ጋር በላ፤ የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ፤›› ዘፍ. 3

የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ ማለት ‹‹እንደእግዚአብሔር መልካምንና ክፉን የሚያውቁ›› ሆኑ ማለት ነው፤ አሁንም ሔዋን መስከረምና ባለመጽሐፉ እንዳቀለሏት አለመሆንዋን መረዳት ይቻል ነበር፤ እንዲያውም ከዚህ በፊት እንደጻፍሁት ሔዋን የመጀመሪያዋ አብዮተኛና የነጻነት እናት ነች ለማለት ይቻላል! በአንጻሩ አዳም የፍርሃት አባት ነው፤ ‹‹ራቁቴን ስለሆንሁ ፈራሁ፤›› ያለው እሱ ነው! ስለዚህ ወይዘሮ መስከረም ‹‹የሔዋን ዘር›› የምትለውን በድላለችና ይቅርታ መጠየቅ ሳያስፈልጋት አይቀርም!
ሔዋን የተጠቀመችው ውጫዊ ገጽታን የሚያሽሞነሙን ሳይሆን የውስጥን የመንፈስ ኃይል ቆፍሮ በማውጣት ነበር፤ በዚህ የውስጥ ኃይል ለሚጠቀም ከውጭ ግፊት አይጠብቅም።
‹‹እውቀትን ወደመሻት ያልተገፋ ማንነት›› አይወቀስም፤ ትላለች ወይዘሮ መስከረም፤ እየተገፉ የሚገኘው ባርነት ነው፤ እውቀት የሚገኘው በነጻነት ነው፤ መገፋት ከእውቀት ያርቃል እንጂ ወደእውቀት አያስቀርብም፤ የመስከረም ዋናው መልእክት ሰላቢውን እንጂ ሰለባውን አትውቀስ የሚል ነው፣ ወይም የኔ ሀሳብ አህያውን ፈርቶ ዳውላውን ዓይነት ሆኖባታል፤ ለመሆኑ ሰለባ የሚሆን ከሌለ ሰላቢ ይኖራል ወይ? ሰለባ ከመሆን በፊት ሰለባ ላለመሆን መጣር አንዱ የኑሮ ዓላማ አይሆንም ወይ? ከዚህ በፊት ስለጨቋኝና ተጨቋኝ ደጋግሜ ጽፌ ነበር፤ ጭቆና የጨቋኙ ባሕርይ የሚሆነውን ያህል የተጨቋኙም ባሕርይ ይሆናል፤ ለጨቋኙ ጭቆና የሚጠቅመውን ያህል ለተጨቋኙም ጭቆና ይጠቅመዋል፤ ለጨቋኙ ጭቆና የኑሮው መሠረት የሆነውን ያህል ለሚርመሰመሱት የጨቋኝ ሎሌዎች ጭቆና የኑሮ መሠረታቸው ነው፤ እንዲህ እያለ ወርዶ ወርዶ የጭቆና ጠቃሚነት ለሎሌው ሎሌ፣ ለሎሌው ሎሌ ሎሌ … በኢትዮጵያ ምናልባትም የመጨረሻዋ የጭቆና ሰለባ ሚስት ትሆናለች፤ ወይም ልጆች ይሆናሉ! ጨቋኝና ተጨቋኝ የባሕርይ ቁርኝት አላቸው፤ አንዱ ያላንዱ አይኖርም፤ ወይዘሮ መስከረም ይህ እውነት ያልሆነበት ሁኔታ ወይም አጋጣሚ የምታውቀው ካለ ብታጋራን ደስ ይለኛል፤ ኢየሱስ ክርስቶስ ‹‹ሙታናቸውንም እንዲቀብሩ ሙታንን ተዋቸው፤›› የሚለው ኢየሱስ ክርስቶስ የሞቱትንና በቁማቸው የሞቱትን ሲያመሳስላቸው ነው! ለእኔ የሚታየኝ እንዲህ ነው።
መስከረም ብዙ ታላላቅ ሴቶችን ጠቅሳለች፤ በእስዋ ግምት ሁሉም በአባታቸው ወይም በባላቸው እየተገፉ ወደትልቅነት መድረኩ የወጡ ናቸው፤ አዙራ ብታየው የጠቀሰቻቸውን ሴቶች ገፉ የምትላቸው ወንዶች መጀመሪያውኑ በሴቶቹ ተገፍተው እንደነበረስ ሊታሰብ አይገባም? ምናልባት ከጠቀሰቻቸው ሴቶች ይልቅ መስከረም የሄለን ኬለርን ታሪክ ብታስታውስ ኖሮ መገፋትን አታነሣም ነበር፤ ሄለን ኬለር በሕጻንነትዋ ዓይኖችዋም ጆሮዎችዋም ሥራቸውን አቆሙ፤ የሄለን ኬለር የመንፈስ ጥንካሬ ከውስጥዋ አዲስና የተሻሉ ዓይኖችንና ጆሮዎችን እንድታበቅልና እንድትማር፣ ከታወቀ ዩኒቨርሲቲም የመጀመሪያዋ ሴት ምሩቅ ለመሆን እንድትበቃ አድርጓታል፤ ይህች አስደናቂ ሴት ከመቶ ሠላሳ ዓመታት ግድም በፊት ማኅበረሰቡ በሴቶች ላይ የነበረውን አጥር ሰብራ፣ ዓይኖችዋ ባለማየታቸውና ጆሮዎችዋ ባለመስማታቸው የገጠማትን እክል አሸንፋ ራስዋን ከወንዶች በላይ ለማድረግ በቅታለች።
መገፋትን የሚፈልግ ሁሉ፣ ካልገፉት የማይነቃነቅ ሁሉ፣ ሬትን ሲግቱት ይጣፍጣል እያለ የተቀበለ ሁሉ፣ ዶሮ ማታ፣ ዶሮ ማታ፣ እያሉ አታልለው እንኳን ዶሮ የለም ሹሮ ሲሉት የማይናደድ ሁሉ፣ ምኞቱ ልደግ ልመንደግ እያለ ሲነዘንዘው በአፈና ጭጭ የሚል ሁሉ ለወቀሳ ብቻ አይደለም ለውርደትም ክፍት ነው፤ ስለዚህም ተወቅሶ ከውርደት ከዳነ ወቀሳው ትልቅ አስተዋጽኦ ያደርጋል ማለት ነው፤ ዞሮ ዞሮ የሰው ልጆች ሁሉ — ሴት፣ ወንድ፣ ወጣት ሽማግሌ-አሮጊት፣ ባለሥልጣን ተራ፣ ገበሬ ነጋዴ፣ ወታደር ፖሊስ፣ አስተማሪ አስተዳዳሪ፣ ዳኛ ጠበቃ፣ ሀኪም መሀንዲስ፣ … — የፈለገውን ቢሆን ላለበት ሁኔታ ኃላፊነቱ የራሱና የግሉ ነው፤ ራሱን የሚገነባው ወይም ራሱን የሚንደው ራሱ ነው፤ ሰበብ እየፈለጉ ከዚህ ኃላፊነት መውጣት ቀላል ቢመስልም ተመልሶ እምቦጭ ነው፤ ዳገቱን ለመውጣት የሚመረውን እውነት መቀበል ያሻል።
በመጨረሻም በማናቸውም መንገድ፣ በማናቸውም ጊዜ፣ በየትኛውም ቦታ ወደቁልቁለት የሚገፉትን ወይም የሚነዱትን ‹‹እምቢ!›› ብሎ ድምጹን ያላሰማ ገደል ገብቶ ሲንፈራፈር ከራሱ በቀር የሚወቅሰው የለም፤ አቅመ-ቢስነት ከውጭ አይመጣም።

ሁለት

አንድ በሀርቫርድ የኒቨርሲቲ ያጋጠመኝን ነገር መግቢያ ላድርገውና ልቀጥል፤ በአንድ ሴሚናር (የጥናት ውይይት) ላይ አንድ ጥቁር አሜሪካን ፕሮፌሰር ወደአሜሪካ በባርነት በመጡት አፍሪካውያን ላይ የተፈጸመውን ግፍ በመዘርዘር አስረድቶ አሁን ለእነሱ ልጆችና የልጅ ልጆች ካሣ መከፈል አለበት የሚል ክርክር አነሣ፤ ካሣውን የመክፈል ግዴታ የሚጣለው ማን ላይ ነው? ካሣውንስ የመቀበል መብት የሚሰጠው ለማን ነው? የሚሉ ጥያቄዎችን ሳናነሣ ብዙ ሌሎች ጥያቄዎች ይኖራሉ፤ — እነዚያ ከአፍሪካ በባርነት ተይዘውና ተሸጠው የመጡት ሰዎች ዛሬ የሉም፤ እነሱ በባርነት ሞተዋል፤ ዛሬ በሕይወት የሚገኙት ጥቁር አሜሪካውያን ነጻነታቸውን አግኝተው ባለሙሉ መብት ዜጎች ሆነዋል፤ በአንጻሩ ደግሞ ለባሪያዎች ነጻነት የተጋደሉ ነጮች አሉ የእነዚህ ልጆች ከባሪያዎቹ ወይንስ ከጌቶቹ ወገን ይመደባሉ? ዛሬ ለልጆቻቸው ካሣ ይከፈል ማለት ልጆቹ የራሳቸውን ነጻነት ችላ ብለው ከአባቶቻቸው ባርነት ጋር እንዲቆራኙ ማድረግ አይሆንም ወይ? የባርነት ምልክቶችን ሁሉ ደምስሰው ነጻ ሰዎች ለመሆን የመጀመሪያው ግዴታ ራስን ችሎ በሁለት እግሮች መቆም ነው፤ ካሣ ክፈሉን ማለት አንደኛ ዋጋ ለማይሰጠው ነጻነት ዋጋን በማውጣት ማርከስ ነው፤ ከሰውነት ወደቤት እንስሳነት መውረድ ነው፤ ሁለተኛ በጌታና በባርያ መሀከል ያለው ግንኙነት መልኩን ለውጦ እንዲቀጥል መድረግ ነው፤ የውይይቱ ባለቤት እኔ ያቀረብሁትን ሀተታ እንዳላሰበበት ቢናገርም የእኔ ጥያቄ የተወደደ አልመሰለኝም፤ ካሣ ተቀባዮች ባርነታቸውን ካሣ ከፋዮች የባሪያዎች ባለቤትነታቸውን ጠብቀው እንደተቆራኙ መቀጠላቸው ባርነትን አያጠፋም፤ ለእኔ ጤናማ አልመሰለኝም።
ባሪያና ኃላፊነት አይተዋወቁም፤ ባሪያ ለገዛ ራሱ ኑሮም ቢሆን ኃላፊነት የለውም፤ ለምግቡም ሆነ ለልብሱ፣ ለመጠለያውም ሆነ ለቀብሩ ኃላፊነት የለበትም፤ ለሁሉም ነገር ኃላፊነቱ የጌታው ነው፤ ከባርነት መውጣት ማለት፣ ከባርነት መላቀቅ ማለት ነው፤ ለገዛ ራስ ሕይወት፣ ለገዛ ራስ ኑሮ ሙሉ ኃላፊነትን መሸከም ነው፤ ስለዚህም ከባርነት ወደነጻነት መሻገር ከግድዴለሽነት ወደኃላፊነት መሻገር ነው፤ ስለዚህም ከግዴለሽነት ወደኃላፊነት ሳይሻገሩ ከባርነት ወደነጻነት መሻገር አይቻልም! ኤልሪድጅ ክሊቨር የሚባል ጥቁር አሜሪካዊ በእስር ቤት ሆኖ የጻፈው (Soul on Ice) የሚል መጽሐፍ በዚህ ጉዳይ ላይ አፍአዊ ምልክቶችን ዘልቆ የሚገባ የነጻነትንና የባርነትን ባሕርያት ያሳያል፤ በአንድ በኩል በሴት ባርያና በወንድ ጌታ መሀከል ያለውን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በወንድ ባርያና በሴት እመቤት በኩል ያለውን ግንኙነት በግላጭ ያወጣዋል፤ ባርነትን የባሕርዩ ያደረገ መገለጫው ለምንም ነገር ኃላፊነት የማይሰማው መሆኑ ነው፤ ለምንም ነገር ሳያስብ፣ በትእዛዝ ብቻ መመራት የተመቸው ባርያ ነው።
ደግ ጌታ በራሱ ተነሣሺነትና በራሱ ፈቃድ ባሪያውን ነጻ ቢያወጣው ባሪያው ሙሉ በሙሉ ነጻ የሚሆን አይመስለኝም፤ በሕግ ነጻ ይሆናል፤ በውስጡ ግን ገና ከባርነት አልተላቀቀም፤ ከጌታው ጥገኛነት ለመውጣት ባለመዘጋጀቱ በኑሮውም ቢሆን ከጌታው አልተላቀቀም፤ ሳይለቀለቅ ከነእድፉ እንደተሰጣ ልብስ ነው፤ ተፈቅዶለት ከባርነት የወጣ ገና ነጻነትን አላገኘም፤ ከባርነት ለመላቀቅ በፍላጎቱና በፈቃዱ ወስኖ ነጻነቱን ከጌታው በግድ ፈልቅቆ ማውጣት አለበት፤ ለምን? የነጻነቱንና የሰውነቱን ቁርኝት ተገንዝቦ፣ የዜግነት እኩልነቱን ተረድቶ፣ በሰውነትም በዜግነትም ጌታህ-ነኝ ከሚለው የማያንስ መሆኑን አምኖ በቆራጥነት ሲነሣ ነው፤ የሰውነቱንና የዜግነቱን ልክ፣ የነጻነትን ትርጉምና ጣዕም አውቆ በትግል ነጻነቱን ሲያገኝ ያለጥርጥር ከባርነት ወጣ ማለት ይቻላል፤ አለዚያ ነጻነቱን በስጦታ፣ በጌታው መልካም ፈቃድ የሚያገኘው የነጻነት ሙሉ ባሕርይ አይኖረውም።
የአፍሪካን አገሮች ብንመለከት የመረረ የነጻነት ትግል የተካሄደባቸው ደቡብ አፍሪካ፣ ኬንያ፣ አልጂርያ፣ ዚምባብዌ ናቸው፤ እንደሚታወቀው እነዚህ አራቱም አገሮች ለአውሮፓውያን ሰፈራ የታጩ ነበሩ፤ ምናልባት በእነዚህ ዘገሮች ለነጻነት የተደረገውን ትግል መራራ ያድረገው ዋናው ምክንያት አፍሪካውያኑ አገር-አልባ ሆነው እንዳይቀሩ የነበረው ስጋት ሊሆን ይችላል፤ በአንጻሩ ሱዳን የነጻነት ትግል አልነበረም፤ የኢትዮጵያ ጎረቤት ስለሆነ ቶሎ ነጻነትን በመስጠትና ወዳጅ በመፍጠር፤ በሶማልያም በኩል እንዲሁ ቶሎ ነጻነትን በማሸከም ምዕራባውያን ወደፊት ከኢትዮጵያ ጋር የሚኖራቸውን ግንኙነት እየቀረጹ ነበር ለማለት ይቻላል፤ ግብጾች ከስንት ሺህ ዓመታት በኋላ ነው አሁን በዘመናችን ወንዶችና ሴቶች በአደባባይ ወጥተው እምቢ! በማለት ሙባረክን ያስወረዱት! ለነጻነት የመታገሉ ልምድ ስለሌላቸው፣ በዚያም ላይ ባህልና ሃይማኖት ተጨምሮበት ሙባረክን አስወርደው ነጻነትን አላገኙም፤ እንደዚሁም የኢትዮጵያ ሕዝብም አጼ ኃይለ ሥላሴን አስወርዶ ነጻነቱን አላገኘም::
እያንዳንዱ ሰው የተፈጠረው ከነፍላጎቱና ፍላጎቱን ለማሟላት ካለው አዛዥነት ጋር ነው፤ ባርያ ፍላጎቶቹን ለማሟላት አዛዥነቱ የለውም፤ አዛዡ የራሱ ፈቃድ ነው፤ የራሱ ፈቃድ የሌለው ሰው ወና ሰው ነው፤ ዋናውን የሰውነት ባሕርዩን ያጣ ባዶ ዕቃ ነው፤ ከባዶ ዕቃ ውስጥ የሚወጣ ነገር የለም፤ ለዚህ ነው ለነጻነቱ መታገልና በራሱ ጥረት ድልን ለመጎናጸፍ የማይችለው።

No comments:

Post a Comment