Wednesday, April 30, 2014

የኢህሃዴግዬ የቀለም አብዮት …!


ቀለምየኢህሃዴግዬ የቀለም አብዮት …!
እንግዲህ መጀመሪያ ለቃላቶቻችን ፍቺ እንስጥ፤
ኢህአዴግ ያው ምንም ፍቺ አያስፍልጋትም ያው ኢህአዴግ ናት! (በቅንፍም፤ ቢቻል ከያዛት አባዜ ራሷ በራሷ ወይም በንስሃ አባቷ በኩል ትፋታ እንጂ እኛ እርሷን ስንፈታ አንገኝም፤ ብለን እንጨምራለን… እርሷ ለንጹሃን እስረኞች ፍቺ መስጠት እምቢኝ እያላት እኛ ንጽህና ለተሳናት ገዢ ምን ፍቺ አሰጠን ብለን ለመቀለድም እንሞክራልን!)
ቀለም ማለት፤ እውቀት ትምህርት ንባብ እና የአዕምሮ ከፍታ ማለት ነው። (ከፈለግዎ መዘገበ ቃላት ያገላብጡ ወላ ከሳቴ ብርሃን ወላ ያሰኝዎን መዝገብ ይፈትሹ… በኔ ይሁንብዎ ወዳጄ ቀለም ማለት የሄው ነው ትርጉሙ!)
አብዮትንስ ምን ብለን እንፍታው… ያልን እንደሆን፤ አዲስ አበባ ዩንቨርስቲ ያሳተመው የአማርኛ መዝገበ ቃላት፤ “አብዮት ፤በአንድ ነገር ክስተተ ወይም ሂደት ውስጥ ያሉ ቅራኔዎች ተካረው ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሲደርሱ የሚፈጠር መሰረታዊ ለውጥ፤ አዲስ ከፍተኛ እና የተሻለ ነገር ክስተት እና ሂደት ወይም አስተሳስብ እና እውቀት የሚከሰትበት” ሲል ይተረጉመዋል።
እና እነዚህን ሁለት ነገሮች ብናቀናጃቸው የቀለም አብዮት ክፋቱ ምን ላይ ነው… ብለን መጠየቃችን አይቀርም።
የቀለም አብዮት ክፋቱ የአምባገነኖችን ዱላ ማበርታቱ….! ካልሆነ በስተቀረ ምንም ከፋት የለውም። ቀለምም እውቀት ነው፤ አብዮትም የተሻለ ለውጥ ነው። (ታድያ ነውጥ እንጂ ለውጥ ምን ጉዳት አለው…. መልሱ ምንም! የሚል ነው።)
ኢህሃዴግ ግን ቀለም ትፈራለች፤ አብዮትማ ጠላቷ ነው። (ሳስበው በአብዮት ጠባቂዎች የያዘችው ቂም ሰላልለቀቃት ነው፤ እዝችጋ የፈጀውን ይፍጅ ሳቅ አል…ሃሃ) ቀለም እና አብዮት ተቀላቀለው፤ የቀለም አብዮት ሲሆንባት ደግሞ ዶክመንተሪ ፊልም ሁላ ለመስራት እስኪያነሳሳት ድረስ የምትጠላው ነገር ነው።

ኢህሃዴግ ቀለም ለምን ተፈራለች…ብለው እንዳይጥይቁኝ፤ ግን እውነት ትፈራለች ወይ… ካሉኝ ግን፤ እና የዩንቨርስቲ ተማሪዎችን በቆመጥ የምታስቀጠቅጠው ለምንድን ነው…. እልዎታለሁ… እና እነዛን ሁሉ ቀለሜ ቀለሜ ወጣቶች ሰብስባ ያሳሰረችው ለምንድነው ብዬም ጠይቅዎታለሁ…
የምር ግን ወዳጄ እስቲ ልብ ብለው ያስቡት አሁን አሁን እኮ የተማረ ሰው መገኛው ወይ ኮብል ስቶን ላይ፤ ወይ ደግሞ እስር ቤት እየሆነ ነው። (ኮብል ስቶን ንጣፍ አልቋልኮ ብለው እንዳያሳቅቁኝ ብቻ ንጣፉ ቢያልቅም የሚቆምበት ያው ቀለሜው ነው) ለምን ቢሉ ኢህሃዴግዬ ቀለም ስለምትፈራ ወይ ቀለሙን እና ሞራሉን አፍስሳ ኮብል ስቶን አንጣፊ እና ኮብል ስቶን ላይ ተነጣፊ ታደርገዋለች፤ ወይ ደግሞ… ቀለሜም ሞራሌም አይፈስም ብሎ ድርቅ ካለ እስር ቤት ታስገባዋለች። ለምን… ምክንያቱም ኢህሃዴግዬ ቀለም አትወድም።
እውነት እውነት እልዎታለሁ ወዳጄ መንግስታችን ”የቀለም አብዮት ሴራ ያሰጋኛል” ብላ ስትል የተማሩ ሰዎች ገና ለገና መንግስት አልተማረም ብለው አብዮት ወይም ለውጥ ሊያደርጉብኝ ይችላሉ ብላ መስጋቷ ነው። (እኛም በቅንፋችን መንግስታችንን እንላታለን፤ ኢህአዴግዬ ሆይ…እና ታድያ መማር ነበራ… ከማማረር መማር እነደሚበልጥ ማወቅ ነበረብሽኮ!)
እኔ የምለው ግን መንግስትን ያህል ነገር ከቀለም ሸሽቶ የት ሊደርስ ነው…. ዛሬ ከ….ፍ ብለው የምናያቸው ሀገሮችን እኮ ከፍ ያደረጋቸው ቀለም ነው። እውቀት፤ የአስተሳስብ ከፍታ! ሰው እንዴት ከቀለም ይጠላል… ይበልጡንም ደግሞ መንግስት እንዴት ከቀለም ይጣላል….!
ጎበዝ ይሄ ህመም ነው፤ እና… መንግስት የሚታከምበት ሃኪም ቤት ካለ ግዴየላችሁም ተጋግዘን እንውሰደው!
#Freezone9Members #AllEthiopiauniversitystudents #FreeAllEthiopiajournalists #freeallEthiopiapoliticalprisoners #FreeAllMuslimEthiopians #FreeEthiopia ኧረ #FreeEPRDFዬም !
በመጨረሻም የድረ ገጻችን ጎብኚዎች ተጠፋፋን አይደል… የሰው ልጅ ካለችግር ይኖር ዘንድ አይቻለውምና ችግር ገጥሞኝ ነበር የተጠፋፋነው! እንግዲህ ብርታቱ ከተገኘ ቶሎ ቶሎ ለመከሰት እሞክራልሁ!
ይመቻችሁ!

No comments:

Post a Comment