(በላይ ማናዬ)
‹‹እኔ ጆርጅ ቡሽን (ፕሬዚዳንት) አላደንቅም፤ ጠፈር ላይ የወጡትንም አላደንቅም፡፡ የማደንቀው እነዚህን ሰዎች ለትልቅ ደረጃ ያደረሷቸው መምህራንን ነው፡፡››
መምህራን የሀገር ምሰሶዎች… መምህርነት የሙያዎች አባት… መምህር የእውቀት ብርሃን…ይህ እውነት ነው፡፡ እውነቱ ግን ዛሬ ላይ ተጋርዷል፡፡ መምህርነትም ሆነ መምህራን የነበራቸው ክብር ዛሬ ላይ በኢትዮጵያ መሬት በአስደንጋጭ ፍጥነት እየወረደ ይገኛል፡፡ መምህራን በሙያቸው እያፈሩ ነው፡፡ እውቀታቸውን እየሰሰቱ ነው፡፡ አዎ፣ መምህራን ጫንቃቸው ጎብጦ ነገን በደበዘዘ ተስፋ የሚጠባበቁ ‹ምስኪኖች› እየሆኑ ነው፡፡ ግን እንዴት?
ካድሬነት Vs መምህርነት
ወጣት ነው፤ ገና ለስራው ዓለም ብዙ አበርክቶት የሚጠበቅበት፡፡ ወጣቱ በአዲስ አበባ አብዮት ቅርስ መሰናዶ ት/ቤ የኬሚስትሪ መምህር ነው፡፡ በስራው ዓለም ለአራት ዓመታት ያህል ቆይቷል፡፡ በእነዚህ ዓመታት ግን የሚሽተው ሙያዊ ተግባሩን ለመወጣት ከብዶታል፡ ፡ መምህርነቱን የሚፈታተኑ በርካታ ጉዳዮች እየተፈራረቁበት ተቸግሯል፡ ፡ ወጣቱ ትዳር መሥርቶ፣ ወልዶና ከብዶ መኖር ቀርቶ ጥሩ ጫማና ልብስ ገዝቶና ጥሩ ምግብ ተመግቦ ለመኖር እንኳ እንዳቃተው ይናገራል፡ ፡ ከተማሪዎቹ በታች እየሆነ የሚታይበትን የኑሮ ጫና መቋቋም እንደተሳነውም ይገልጻል፡፡ በዚህ ሁኔታም ሆኖ ማስተማር ይፈልግ ነበር፡፡ ዳሩ ግን መምህርነቱ ከዚህም በላይ ፈተና አሳይቶታል፡፡ ነጻነቱን ነፍጎታል፡፡
የፖለቲካ ሰዎች (ካድሬዎች) የሚያስተምርበት ድረስ እየሄዱ ተጽዕኖ ያደርጉበታል፡፡ ት/ቤቶች የእውቀት ማበልፀጊያና መጋሪያ ደጆች ቢሆኑም አሁን አሁን ስልጣን ፈላጊዎች መናሃሪያ አድርገዋቸዋል፤ የፖለቲካ ማዕከላት ሆነዋል፡፡
ወጣቱ መምህር ይናገራል፤ ‹‹… የኢህአዴግ ካድሬ ካልሆንክ ችግር ነው፡፡ ካድሬነት ወደህ የምትገባበት ሳይሆን ካድሬ ባለመሆንህ ከሚደርስብህ አድሎአዊ አሰራር ለማምለጥ ብለህ የምትገባበት ሲኦል ሆኗል፡፡ መምህርነት መሰረቱ እውቀት ነው፡፡ አሁን ግን ያ አይደለም መሰረቱ፤ ካድሬነት ነው፡፡ በእውቀት ላይ ብቻ ተመስርቼ አስተምራለሁ ካልክ በድህነት እያከክ ትኖራታለህ፡፡ አንድ ተራ ካድሬ ከአንተ በላይ ገንዘብ ይከፈለዋል፡፡ እናም ብታምንበትም ባታምንበትም ካድሬ ሆነህ ወደ ቀበሌ ከተሾምክ ደመወዝህ 4000 ብር ይደርሳል፡፡ መምህርነት ላይ ከቆየህ ግን ይህን ደመወዝ በ20 ዓመት እንኳ አትደርስበትም፡፡››
እንደ ወጣቱ ገለጻ መምህራን ሙያቸውን አሻሽለው ነገን በተስፋ ለማለም አልታደሉም፡፡ በሙያቸው ክብርን አያገኙም፡፡ ወርን ጠብቃ ከምትመጣ መናኛ ደመወዝ በቀር ሌላ ማበረታቻ ጥቅማጥቅሞች የላቸውም፡ ፡ በእርንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ደግሞ መምህራን ከተማሪዎቻቸው ሳይቀር የሚደርስባቸው ንቀትና ማንጓጠጥ እየጨመረ ይገኛል፡ ፡ ‹‹የሚገርምህ አንዳንድ ተማሪዎች ከመምህራን በላይ ስልጣን አላቸው፡፡ ያዝዙሃል ማለት ይቻላል፡፡ ምክንያቱም ካድሬ ተማሪዎች በዝተዋል፤ የተማሪ ደህንነቶችም አሉ፡፡ ስለምታስተምረው ነገር ነጻነት የለህም፡፡ ይህ መምህራንና ተማሪዎች እርስ በእርስ እንዳይግባቡ እየተገነባ ያለ የበርሊን ግንብ ነው፡፡
‹‹ተማሪ መምህሩን እየደበደበ እንዴት ማስተማር ትችላለህ…ለምሳሌ በቅርብ ጊዜ በተማሪ ድብደባ የደረሰበት አንድ መምህር ኮማ ውስጥ ይገኛል፡ ፡ የተማሪ ወላጆችም እኛ መምህራንን እንደ ተላላኪ ነው የሚያዩን፡፡ ምን ታደርጋለህ…አንዱ ልጅ አንዱ የእንጀራ ልጅ የሆነበት ስርዓት ለዚህ አበቃን፡፡ እንደ ባለሙያ ሳይሆን እንደ ሎሌ ነው እየታየን ያለነው፡፡››
ሌላው ያነጋገርኩት መምህር በእንጦጦ አንባ ት/ቤት ታሪክ ያስተምራል፡፡ መምህሩ ቀደም ብሎ የተጠቀሰውን የባልደረባውን አባባል ይጋራል፡፡ ት/ቤቶች የፖለቲካ ማዕከላት እየሆኑ መምጣታቸውንም ይጠቅሳል፡፡ ‹‹…የኢህአዴግ መሰረታዊ ድርጅት የሚባሉ የአደረጃጀት አባላት ት/ቤት ውስጥ ይገኛሉ፡፡ ስብሰባ የሚያደርጉት ት/ቤት ውስጥ ነው፡፡ ለድርጅት ስብሰባ ተብሎ የትምህርት ጊዜ ይባክናል፤ የት/ቤት ንብረት ለፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ይውላል፡ ፡ የተማሪ አደረጃጀት የሚባል ነገርም አለ፡፡ በትምህርት ሽፋን የፖለቲካ ስራ የሚሰሩባቸው ናቸው፡፡››
እንደ መምህሩ አባባል፣ መምህራን ሁለት ሚዛን ላይ ሆነው ነው የሚመዘኑት፡፡ የኢህአዴግ አባል የሆኑት በአንድ ወገን፣ አባል ያልሆኑት በሌላ ወገን፡፡ በዚህም አባል ያልሆኑ መምህራን ከሌላው የበለጠ አስተዳደራዊ በደል ይደርስባቸዋል፡ ፡ በፖለቲካ አመለካከታቸው ብቻ እየተለኩ ጫና ይደረግባቸዋል፡፡ ‹‹አንድ ለአምስት የሚባል አደረጃጀት አለ፡፡ መምህራንን በአመለካከታቸው ልዩነት ‹ታርጌት› ይደረጉበታል፡፡ ይህ አንድ ለአምስት የሚባለው አደረጃጀት የፖለቲካ ስራውን ለመከወን የተዘየደ መረብ ነው፡፡ አንዱ አንዱን እየሰለለ እርስ በእርሱ መተማመንን እንዳያጎለብት ነው እንዲህ የተደረገው፡ ፡ በእውነት ት/ቤቶች ዋና የፖለቲካ ማዕከላት እንደሆኑ ደግሜ ደጋግሜ ልነግርህ እችላለሁ፡፡››
የደመወዝ ማነስ፣ መገለልና ንቀት
ደመወዝና መምህራን አልተገናኙም፡፡ ጭማሪ ተደረገላቸው ሲባልም የይስሙላህ ይሆናል፡፡ ለአብነትም 2004 ዓ.ም ላይ መንግስት ለመምህራን የደመወዝ ጭማሪ አደረኩ ብሎ የጨመረውን መጠን ማስታወስ ይቻላል፡፡ የዛኔው የደመወዝ ጭማሪ የመምህራንን ሕይወት የሚለውጥና የሚያሻሽል ሳይሆን ክብረ ነክ እንደነበር ይታወሳል፡፡ እናም የተደረገው ጭማሪ ለመምህራን የማይመጥን እንደነበር በመግለጽ ተቃውሟቸውን ያሰሙ መምህራን (በተለይ በአዲስ አበባ) እንደነበሩ የሚዘነጋ አይደለም፡፡ ከመንግስት የተሰጣቸው ምላሽ ግን ህገ-ወጥ ተብለው ከስራ መሰናበት ነበር፡፡
የመምህራኑ ጥያቄ ግን ተገቢነት ነበረው፡፡ የኑሮ ውድነቱ እየጦዘ ባለበት ወቅት የሰባ ሦስት ብር ጭማሪን ከቁምነገር ቆጥሮ ‹ጭማሪ ተደረገላቸው፤ ጭማሪውም ህይወታቸውን ይለውጣል› እያሉ መልፈፍ በመምህራን ሞራል ላይ ክፉኛ መዘባበት ነበር፡፡ መምህራንም ይህን ሐቅ ይዘው የስራ ማቆም አድማ ሳይቀር አድርገው ነበር፤ ሰሚ አላገኙም፡፡
መምህራን አሁንም ዝቅተኛ ተከፋዮች እንደሆኑ ነው የሚናገሩት፡ ፡ አንድ መምህር በሶስት ዓመት አገልግሎት 1700 ብር ገደማ ይከፈለዋል፡፡ ከዚህ ወርሃዊ ገቢ ላይ በትንሹ 800 ብር የቤት ኪራይ ይከፍላል፤ ግብር አለ፤ የተለያዩ መዋጮዎችም ይቀነሱበታል፡፡ ‹‹በቸርነቱ እንጂ ገቢያችንማ ሊያኖር የሚችል አይደለም፡፡ መምህር በነጻ እየሰራ እንደሆነ ነው የማምነው፡፡›› ይላል የአብዮት ቅርስ መምህሩ፡፡
የገቢ ልክ ማነስ መምህራን በማህበረሰቡ ዘንድ ያላቸውን ቦታ ዝቅ እንዲል እንዳደረገ መምህራን ይናገራሉ፡፡ ‹‹እንደድሮው ሳይሆን አሁን ላይ መምህራን በማህበረሰቡ ዘንድ እጅግ ዝቅተኛ ተቀባይነት ነው ያለን፡፡ መምህር በምንም ሁኔታ ከተማሪው ተሽሎ መታየት አልቻለም፡፡ እስኪ አሁን ከተማሪና ከአስተማሪ የትኛው ነው ላፕቶፕ በእጁ የሚገኘው…ተማሪው ነው፡፡ መምህራን ላፕቶፕ እንኳ መግዛት ይከብዳቸዋል፤ ሳያስፈልጋቸው ቀርቶ ግን አልነበረም የማይገዙት፡፡››
እንደመምህራኑ ከሆነ ማህበረሰቡ ለመምህራን ቦታ አጥቷል፡፡ ‹‹መምህር የተናቀበት ማህበረሰብ ፈጥረናል፡፡ ወዴት እያመራን እንደሆነ አይገባኝም፡፡ ያለመምህር አንዲት ሀገር ወዴትም ልትደርስ አትችልም፡፡›› በእርግጥም መምህራን ቀደም ባለው ጊዜ የነበራቸው ክብር ከፍተኛ ነበር፡፡ እንዲያውም፡-
የእኛ ሙሽራ ኩሪ ኩሪ
አገባሽ አስተማሪ፤ ወሰደሽ አስተማሪ፤
ይባል ነበር፡፡ ‹‹…ዛሬ ላይማ ገና መምህር መሆንህ ሲታወቅ ሰው ይሸሽሃል፡፡ ተስፋ አስቆራጭ ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው፡፡ ለምሳሌ ተማሪዎች ሁሌም መምህሩን እያዩ ተስፋ ይቆርጣሉ፡፡ መማርን ሲያስቡ የተማረውስ የት ደረሰ ብለው ይጠይቃሉ፤ የመምህሩን ህይወት በአጠገባቸው ያያሉ፡፡ ብዙ ተማሪዎች ወደ አረብ ሀገራት ለመሄድና መንጃ ፍቃድ ለማውጣት የሚያስችላቸውን ደረጃ ነው የሚያልሙት፡፡ ተስፋ አይታይባቸውም፡፡ ለምን አትምሩም የሚል መምህር ካለም አንተ የት ደረስክ ብለው ነው የሚጠይቁት፡፡›› ይላል የእንጦጦ አምባ መምህሩ፡፡
የአብዮት ቅርስ ወጣት መምህሩ በበኩሉ፣ ‹‹መምህራን የምንኖረው በኩሽና ቤትና በሽንት ቤት ውስጥ ነው ማለት እችላለሁ፡፡ ጥራት ሳይሆን ዋጋ የሚቀንስ ቤት ነው የምንፈልገው፡ ፡ ገንዘብ የለማ! ይህን ህይወታችንን ደግሞ ተማሪዎች ያያሉ፡፡ ምክንያቱም መምህሩ የሚኖረው በተማሪ ወላጆች ቤት ተካራይቶ ነው፡፡ የወረደ የሚባል ኑሮ ሲኖር እያዩ እንዴት መምህሩን ማክበር ይቻላቸዋል?›› ሲል ይጠይቃል፡፡
ይህ ሁሉ በመምህራን ላይ ለምን?
ያነጋገርኳቸው መምህራን መንግስት ሆን ብሎ መምህራንን የማዳከም ስራ እየሰራ እንደሆነ ያምናሉ፡፡ አንድ ፀሐይ ጮራ ት/ ቤት የሚያስተምር የእንግሊዝኛ ቋንቋ መምህር እንዲህ ሲል ይገልጻል፤ ‹‹የመንግስት ዓላማ መምህራንን ከማንኛውም ለውጥ ለማግለል ነው፡፡ በቀደመው ጊዜ መምህራን ግንባር ቀደም የለውጥ ጠንሳሾችና አንቀሳቃሾች ነበሩ፡፡ በራሳቸው መብታቸውን ያስከበሩና ለሐገርም አለኝታ ነበሩ፡፡ ይህም የሆነው መምህራን በራሳቸው የቆሙ ስለነበሩ ነው፤ በገቢም በእውቀትም ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኙ ስለነበር ነው፡ ፡ ስለሆነም ማንኛውንም አይነት ጥያቄ ማንሳት ይችሉ ነበር፡፡ አሁን ግን ስለዕለታዊ ዳቦህ ብቻ እንድታስብ ነው የተፈለገው፡፡ የመብት ጥያቄ ለማንሳት እንዳይቻለን አድርገው ነው የያዙን፡፡››
በእርግጥም አብዛኛውን ጊዜ በማንኛቸውም የለውጥ እንቅስቃሴዎች ውስጥ መምህራን ይኖራሉ፡ ፡ ራሳቸው ነቅተው ማህበረሰቡን በማንቃት የመብትና የዴሞክራሲ ጥያቄዎችን በማንሳት መምህራን ግንባር ቀደሞች ናቸው፡፡ ለአብነትም በኢትዮጵያ አብዮት ወቅት መምህራን ተማሪዎችን በማስተባበርም ሆነ በራሳቸው ተደራጅተው በመንቀሳቀስ ጉልህ ድርሻ ነበራቸው፡፡
ስለዚህም መምህራን አሁንም ለስርዓቱ የማይመቹ ሊሆኑ እንደሚችሉ ኢህአዴግ የተገነዘበ ይመስላል፡፡ ‹‹…ስለዚህ መምህራንን አጥብቆ መያዝ አለበት፡፡ በገቢም በፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎችም መምህራን ከእጁ እንዳይወጡ መንግስት ሆን ብሎ የሚሰራ ይመስለኛል፡፡ እንዲያውም አንድ ለአምስት ይህን ለመቆጣጠር የተዘረጋ ነው፡፡ ስለሀገርህ ለውጥ እንዳትወያይ ተራ አጀንዳ በየጊዜው እያወረደ በስራ ይጠምድሃል፡፡ በገቢ እንዳትደረጅ ከልክሎሃል፡፡ ድሮ መኪና ያለው መምህር ነበር፡፡ የራሱ ቤት ነበረው፡ ፡ ሱፍ ለባሽ ነበር፡፡ አሁንስ? አሁን ይህ ሁሉ እንዲኖርህ አይፈለግም፡፡›› ይላል የፀሐይ ጮራ ት/ቤት መምህሩ፡ ፡
የእንጦጦ አምባ መምህሩም ይህን ሐሳብ ይጋራል፡፡ ‹‹…በእርግጥም መንግስት ይህ (መምህራንን ማዳከም) ዓላማዬ ብሎ የያዘው ነገር ባይሆን ኖሮ ህይወታቸውን መቀየር ቀላል ነበር፡፡ ግን አይፈልግም፤ ጥገኛ ሆነው እንዲኖሩ ብቻ ነው የሚፈልገው፡፡ አሁን መምህራን ላይ ቀልድ የማይቀልድ ማን አለ…እንደ መምህራን ደመወዝ ቡን ያድርገኝ የሚሉ ወጣቶች ስንት ናቸው? ይህ ምን ማለት ነው? በራስ እንዳትተማመን ማድረግ አይደለም? ይህ ሆን ተብሎ የተሰራ ስራ ነው፡፡››
ተቆርቋሪ ማጣት!
የኢትዮጵያ መምህራን በ1960ዎቹ መጨረሻና 70ዎቹ ጠንካራ የሙያ ማህበር ነበራቸው፡፡ ያን የመሰለ ጠንካራ መምህራን ማህበር አሁን ላይ ማግኘት እንዳልተቻለ ነው ያነጋገርኳቸው መምህራን የሚገልጹት፡፡ ‹‹ያን ጠንካራ ማህበር አሁን አታገኘውም፤ አፈራርሰውታል፡ ፡ ለምን ያልክ እንደሆን ማሽመድመድ ስለፈለጉ ነው፡፡ ማህበር ለይስሙላ አለ፤ ዳሩ ግን የመምህሩን ጥቅምና ሙያዊ ክብር ማስጠበቅ አልቻለም፡፡ ሲመስለኝ የማህበሩ ዓላማ መንግስትን ማገልገል ነው፡፡
‹‹የሙያ ማህበሩ ተለጣፊ ነው፡ ፡ ለሙያውና ለመምህራን ጥቅም ሳይሆን እንደማፈኛ መሳሪያ የዋለ አድርጌ ነው የማየው፡፡ የሆነ ጊዜ ማህበሩ አይወክለንም ብለን ፊርማ ብናሰባስብ ‹‹የህዝብ ክንፍ ለማፍረስ ተንቀሳቅሳችኋል›› ተብለን ፍዳችን ነው ያየነው፡፡ ይህ የሚያሳይህ ማህበሩ እንደ አንድ የፖለቲካ ክንፍ ሆኖ የሚያገለግል እንጂ ለመምህራን ጥቅም አለመቆሙን ነው፡፡›› ሲል ያብራራል የእንጦጦ አምባ የታሪክ መምህሩ፡፡
እንደ መምህራኑ ገለጻ የሙያ ማህበሩ በየጊዜው መዋጮ ይሰበስባል፡ ፡ ሁሉንም መምህራን በአባልነት እንዳቀፈ አድርጎ ራሱን ይስላል፡ ፡ እውነታው ግን ሌላ ነው፡፡ ‹‹… መምህር ከሆንክ የማህበሩ አባልነት ግዴታ ነው፡፡ ወደድህም ጠላህም ከደመወዝህ ላይ የአባልነት መዋጮ ተብሎ ይቆረጣል፡፡ ከአንድ መምህር በአማካይ 4 ብር ወርሃዊ መዋጮ አለ፡፡ አሁን ባለው መረጃ መሰረት በኢትዮጵያ ያለው የመምህራን ቁጥር ከ350000-400000 ይደርሳል፡ ፡ በአዲስ አበባ ብቻ ወደ 16000 መምህራን አሉ፡፡ ብዙ ገንዘብ እየገባ ግን መምህራን ምንም ሲደረግላቸው አታይም፡፡›› ሲል ይናገራል የአብዮት ቅርስ የኬሚስትሪ መምህሩ፡፡
‹‹ከመምህርነት ማምለጥ››!
እንደ መምህራኑ ገለጻ አሁን ላይ መምህርነት የሚሸሽ ሙያ እየሆነ ነው፡፡ የኬሚስትሪ መምህሩ ይናገራል፤ ‹‹በፊት በፊት መምህር ስትሆን የሞራል እርካታ ይኖርሃል፡ ፡ በማህበረሰቡ ዘንድም ተቀባይነትህ ከፍተኛ ነበር፡፡ ይህም መምህራን ሙያውን እንዲወዱት ያደረገ ነበር፡፡ አሁን ክብር ማጣት አለ፤ ትናቃለህ፡ ፡ መምህር ነኝ ካልክ እንደ አንዳች የሚዘገንን ነገር ፊቱን የሚያዞርብህ ነው የሚበዛው፡፡ እኔ መምህር ነኝ ብዬ አልናገርም፡፡ መምህር ነኝ ስል እንደ መጥፎ ሽታ ሰው የሚያርቀኝ ከሆነ ለምን መምህር ነኝ እላለሁ…? በሙያህ ማፈርን የመሰለ አሳዛኝ ነገር ምን አለ…? ግን እየሆነ ያለው ይህ ነው፡፡››
መምህሩ ከመምህርነት ሙያ መውጣት ይፈልጋለሁ፡፡ ለዚህም ሌላ ዲግሪ እየተማረ ነው፡፡ ‹‹ማምለጥ እፈልጋለሁ፡፡ መምህር ሆኜ መሞት አልፈልግም›› ሲል ተስፋ በቆረጠ ስሜት ይናገራል፡፡ እንደ መምህሩ እምነት መምህራን ሌላ አማራጭ ስራ ቢያገኙ ሁሉም በአንድ ሴኮንድ ት/ቤቶችን ትተው ሊሄዱ ይችላሉ፡ ፡ ‹‹አንዳንዶች ጡረታ ለማስከበር ነው ቀናቸውን የሚጠብቁት፡፡ በዚህ ከቀጠልን ት/ቤቶች ኦና ከመሆን አያመልጡም፡፡››
አሁን ባለው የደመወዝ ስኬል መሰረት አንድ መምህር ከ21 ዓመት በኋላ (በሚገባ እርከኖችን ካለፈ) 3060 ብር ላይ ነው መድረስ የሚችለው፡፡ ለዚያውም ታታሪ የሚባለው መምህር ነው፡፡ ‹‹ታዲያ ተስፋህ ምንድነው? …በግሌ መምህርነት ትልቅ ሙያ መሆኑን አምናለሁ፤ ነውም ደግሞ፡ ፡ ግን አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ምክንያት እጠላዋለሁ፡፡ ከማስተማር ሙያ መውጣት አለብኝ፡፡››
የእንጦጦ አምባ ት/ቤት የታሪክ መምህሩም ይህን ሀሳብ ይጋራል፡ ፡ ‹‹እኔ በመምህርነት ዲግሪ አለኝ፡፡ ነገር ግን አሁን ከሙያው መውጣት እፈልጋለሁ፡፡ ለዚህም ወደታች ወርጄ ሌላ ትምህርት በዲፕሎማ እየተማርኩ ነው፡፡ ሙያውን ጠልቸው አይደለም፤ የሚያሰራኝ ሁኔታ ግን የለም፡ ፡ መኖር እኮ አልቻልኩም፡፡ ትዳር መመስረት አልችልም፤ ምን አለኝና ትዳር እመሰርታለሁ፡፡››
•በመጨረሻም የዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ ሁለት ነገሮችን ብቻ ማስቀመጥ ይፈልጋል፡፡ አንድ፣ የመምህራንን ጩኸት መንግስት እንዲሰማ ያሳስባል፡ ፡ ሁለት፣ መምህራን ህብረታችሁን አጠናክራችሁ በመታገል ጥቅማችሁን ማስከበር ይቻላችኋልና አድርጉት፡ ፡ ከሙያችሁ መሸሽ ዘላቂ መፍትሄ አይሆንም፤ ስርዓቱ ባይፈልጋችሁም ኢትዮጵያ ትፈልጋችኋለች! ሐገር ያለእናንተ ባዶ ነች፡፡
በመግቢያየ ላይ የጠቀስኩት አባባል የአንድ የባዮሎጅ መምህር የዘወትር ንግግር ነው፤ ታመነ ይባላሉ (ጋሽ ታመነ)፡፡ ይህን ግሩም የጋሽ ታመነ አባባል በድጋሜ ልዋስ፣ ‹‹እኔ ጆርጅ ቡሽን (ፕሬዚዳንት) አላደንቅም፤ ጠፈር ላይ የወጡትንም አላደንቅም፡፡ የማደንቀው እነዚህን ሰዎች ለትልቅ ደረጃ ያደረሷቸው መምህራንን ነው፡፡››
(በቀጣይ፣ ተያያዥ ጉዳዮች ላይ ሌሎች ጽሑፎችን ለማስነበብ እሞክራለሁ፡፡)
ብሩህ ጊዜ ለመምህራን ይሁን! (ምንጭ: ነገረ ኢትዮጵያ)
No comments:
Post a Comment