Wednesday, July 17, 2013

ትንሽ ቁምነገር፤ ለብሄር ብሄረሰቦች በሙሉ


አበበትንሽ ቁምነገር፤ ለብሄር ብሄረሰቦች በሙሉ
ኢህአዴግ በአራት ድርጅቶች ግንባር የተገናበረ ነው፡፡ (የተደናበረ፤ አላልኩም፡፡ የተገናበረ ማለት፤ በእኔኛ ቋንቋ ግንባር የፈጠረ ማለት ነው) ስማቸውም ኦህዴድ፣ ብአዴን፣ ደህዴን እና ህውሃት ይባላሉ፡፡
ደሞ አሉልህ አጋር ተብለው አገር የሚበጠብጡ እንደ እነ ሶህዴፓ፣ ጋህዴን ቤህዴፓ ምናምን የመሳሰሉት፡፡
ብታምንም ባታምንም… ልልህ ነበር በአደባባ የምታውቀውን ሀቅ ማመን አለማመንን ምን አመጣው… ብቻ እነዚህ ሰዎች ኦሮሞዎች ናቸው፣ አማሮችም ናቸው፣ ደቡቦችም ናቸው፣ ትግሬዎች ናቸው  ቤኒሻጉልም ናቸው ሶማሌዎችም ናቸው ጋንቤላዎችም ናቸው፡፡
ሁሉም በየክልላቸው ላይ ቢያንስ ቢያንስ ዜጎቻቸውን አበሳ የማሳየት ፈቃድ አላቸው፡፡
የትግራዩ ባለስልጣን ትግራይ ላይ ትግሬዎችን ያስራል ከመኖሪያቸው ያፈናቅላል… ወዘተ ይወዝታል፡፡ የኦሮሞው ባለስልጣን ኦሮሞ ዘመዶቹን ኦነግ ነህ እያለ ይገርፋል ያስራል ያሳድዳል ሻ ሲለው ደግሞ ተኮሶ ይገድላል፡፡ አማራ ክልል ብትሄድ ራሱ አማራው ባላስልጣን መርጠውኛል የሚላቸውን አማራ ወገኖቹን ሲያማርር ታየዋለህ፡፡ ደቡብም ብትሄድ ተመሳሳይ ነው፡፡
እውነቱን እንነጋገር ከተባለ ሁሉም መከራውን እያየ ያለው ኢህአዴግን እንደ ግል አዳኛቸው እና አዳኛቸው (ጠብቆ እና ላል) በተቀበሉ ዘመዶቹ ማናለብኝነት የተነሳ ነው፡፡ የምሬን ነው የምልህ ኦሮሞው በአሁኑ ሰዓት በደል እየደረሰበት ያለው በኦሮሞ ዘመዶቹ ነው አማራውም ትግሬውም ደቡቤውም እንደዛው፡፡
ስለዚህ በዝምድና መደራጀት የትም አያደርስም በሀሳብ መዛመድ ነው የሚበጀው፡፡
ብሄሮችን መዋጋት ሳይሆን አጉራ ዘለል ዘመዶቻችንን ነው ተዉ ማለት ያለብን፡፡
ለራስህ ብዬ ነው!

No comments:

Post a Comment