በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ ተመዝብሯል
- ተጠርጣሪዎቹ ሽፈራው ጃርሶ የሚመሩት ቦርድ ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች ናቸው
ከሙስና ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ አሥር የኦሮሚያ ክልል ውኃ ሥራዎችና ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ባለፈው ሰኞ በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡
ኮሚሽኑ በቁጥጥር ሥር ካዋላቸው ከእነዚህ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች በተጨማሪ፣ ሌሎች 15 የሥራ ኃላፊዎችን በቁጥጥር ሥር ለማዋል የፍርድ ቤት ማዘዣ አውጥቶ ፍለጋ መጀመሩን ምንጮች ገልጸዋል፡፡
ተጠርጣሪዎቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት የኮንስትራክሽን ዕቃዎች ግዥና የመንግሥትን የፋይናንስ ሕግ ባልተከተለ መንገድ ኪራይ ፈጽመዋል በሚል ጥርጣሬ መሆኑን፣ የክልሉ ሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን አስታውቋል፡፡ ኮሚሽኑ ለአንድ ዓመት ባካሄደው ጥናታዊ ምርመራ በዚህ የሙስና ወንጀል መንግሥትን በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እንዳሳጣው ለጉዳዩ ቅርበት የኮሚሽኑ ምንጮች ገልጸዋል፡፡
በቁጥጥር ሥር የዋሉት የክልሉ ውኃ ሥራዎችና ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ቢፋ በዳዳ፣ ምክትላቸው አቶ ጎዳና ዳባ፣ የፋይናንስ ቡድን መሪ አቶ ተሾመ አዱኛ፣ አቶ ተክሉ ተፈራ፣ የማኔጅመንት ኮሚቴ አባላት ወ/ሮ መስከረም ኤጀርሳ እና አቶ ግርማ ቂጣታ፣ የመጋዘን ኃላፊዋ ወ/ሮ ራሔል አሰፋና የክፍያ ሰነድ አዘጋጅዋ ወ/ሪት ሳምራዊት ግርማ፣ የጨረታ ኮሚቴ አባላት አቶ ዘለቀ ጎንፋና አቶ ዱላ ማሞ ናቸው፡፡
የኦሮሚያ ክልል ውኃ ሥራዎችና ኮንስትራክሽን ኢንተርፕራይዝ ከተመሠረተ ሁለት አሥርት ዓመታትን ያስቆጠረ የክልሉ ግዙፍ የልማት ድርጅት ነው፡፡
ኢንተርፕራይዙ በኦሮሚያ ክልልና በሌሎች ክልሎች የሚካሄዱ የመስኖ ግድቦችና የመጠጥ ውኃ ፕሮጀክቶችን ግንባታ ሲካሄድ ቆይቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ መንገዶችንና ስታዲየሞችን ከመገንባቱም በላይ፣ በፌዴራል መንግሥት የሚመራውን ለደዴሳ ስኳር ፋብሪካ አገልግሎት የሚውል ግድብ በደዴሳ ወንዝ ላይ በመገንባት ላይ ይገኛል፡፡
በጉዳዩ ላይ የክልሉን የሥነ ምግባርና ፀረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ታከለ እንኮሳ አስተያየት እንዲሰጡ የተደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡ (ሪፖርተር)
No comments:
Post a Comment