Monday, July 22, 2013

ሀገራችን ኢህአዴግ አክራሪነትን እንደሚያሰሰጋት ተሰጋ!


1004887_10201012302803720_363214582_n
ሀገራችን ኢህአዴግ አክራሪነትን እንደሚያሰሰጋት ተሰጋ!

ይቺ ጨዋታ ፍትህ ጋዜጣ አዲስ ታምስ መጽሄት ከዛም ልዕልና ጋዜጣ ባደረጉት መተካካት አሁን ተራውን ለተቀበለችው አዲሲቱ ፋክት መፅሄት የተላከ ነው፡፡ እስቲ የድረ ገፃችን አንባቢዎች ደግሞ ከተመቻቸው ያንበቧት ተብላ የተለጠፈች ናት!
ርዕሴ እንዳይረዝምብኝ ሰግቼ ነው እንጂ፤ “ሀገራችን ኢህአዴግ አክራሪነት እንደሚሰጋት  ተሰጋ (ድርብ ሰረዝ) ሁላችንም ይሄንን ጉዳይ እንዋጋ (አሁንም ድርብ ሰረዝ) ኋላ ይቆጨናል ሲያስከፍለን ዋጋ…(ቃል አጋኖ)  ብለው ደስ ይለኝ ነበር፡፡
እንግዲህ ጥናት አትኚዎች እና ምርምር አድራጊዎች ከፈለጉ ተመራምረው የምለውን “ፉርሽ” ያድርጉት እንጂ የእኔ አነስተኛ ጥናት ግን በአሁኑ ሰዓት ሀገሪቷን በጣም እያሰጋት ያለ አንድ አደገኛ ነገር እንዳለ አመላክቶኛል፡፡ እርሱም ኢህአዴግ አካራሪነት ነው፡፡
በተደጋጋሚ ኢህአዴግዬ እንደነገረችን ሀገራችን የኃይማኖት አክራሪነት ያሰጋታል ተብለናል፡፡ አረ ምን መባል ብቻ በዚህ የተነሳ የተለያዩ እርምጃዎች እና እርግጫዎች እየተወሰዱብን አይደል እንዴ…
እኔ ሳስበው (አረ ምን እኔ ሳስበው ብቻ ሁላችንም እንደምናውቀው … የሀይማኖት አክራሪነት ለአንድ ማህበረሰብ ከባድ ችግር ነው፡፡ ሀይማኖተኞች እምነታቸውን ለራሳቸው በቅጡ ማመናቸው ብቻ አልበቃ ብሏቸው “ሌላ እምነት የሚያምን የተረገመ ነው” ብለው ማሰብ ሲጀምሩ ጦሱ ያኔ ይጀምራል፡፡ ይህ ችግር እጅግ ሲበረታ ውጤቱ በአለማችን ላይ ያየናቸውን በርካታ አሰቃቂ ጉዳቶች መንስኤ ወደ መሆን ያመራል፡፡ ይሄ ደግሞ ያማርራል፡፡ ይደብራልም፡፡ እዝች ላይ ምልክት ያድርጉልኝ….
አረ ቆይ ወዳጄ እስቲ በቅጡ ሰላምታ እንሰጣጥ … እንዴት አሉልኝ… ጤናዎ እንዴት ነው… ከዶክተር ቴውድሮስ ወዲያ የመጡት ጤና ጥበቃ ሚኒስትር እንዴት ናቸው… ምንውሳ ድምጻቸው ብዙ አይሰማም…! አንገታቸውን ደፍተው እና ድምፃቸውን አጥፍተው ለእኛ ጤና እየደከሙ ስለሆነ ነው… ይበሉ እና እስቲ ያስደስቱኝ በሞቴ!
ዶክተር ቴውድሮስ አድሃኖምን ካነሳን አይቀር እኒህ ሰውዬ “ፖዘቲቭ” ሆነው ተገኙ የሚባለው ነገር እንዴት አዩት…
ይሄን ጊዜ እርስዎ በልብዎ …ታድያ ለአንድ የኢህአዴግ አባል ፖዘቲቭ መባል ብርቅ ነው እንዴ… ብለው፤ አምባ ገነንነት ፖዘቲቭ፣ ሙስና ፖዘቲቭ፣ ኢመልካም አስተዳደር ፖዘቲቭ፣ ጉራ መቸርቸር ፖዘቲቭ፣ መሬት መቸርቸር ፖዘቲቭ፣ ትዕቢት ፖዘቲቭ፣ ማን አለብኝነት ፖዘቲቭ፣ ኪራይ ሰብሳቢነት ፖዘቲቭ… አባል ሰብሳቢነት ፖዘቲቭ ኡ ኡ… ደከመኝ… ፖዘቲቭ… እያሉ ሲደረድሩት ታየኝ፡፡

እኔ እንኳ በግሌ የኢህአዴግ አባላት እና አባታት ከዚህ ሁሉ ችግር አብረው የሚኖሩ ናቸው ብዬ አላምንም፡፡ ያላመኑ ብጹሃን ናቸው እንዲል አብዮታዊ ዴሞክራሲ ስለ ድርጅታችን የሚወራውን ክፉ ባለማመን ለእናት ድርጅቴ ያለኝን ታማኝነት ማረጋገጥ እወዳለሁ፡፡
እና ዶክተር ቴውድሮስ ከሌሎች የኢህአዴግ አባላት ተለይተው “መልካም ስብዕና ፖዘቲቭ” ናቸው ሲባል ሰምቻለሁ፡፡ ይህንን ነገር ያወጋሁት አንድ ወዳጄ መጀመሪያ በጥርጣሬ አያየኝ “…አንተ ሰውዬ እኒህን ሰውዬ ማመስገን አበዛህ ሀገርህ ናፈቀችህ መሰለኝ…” ብሎኛል፡፡ እንደርሱ አባባል ከውጪ ጉዳዩ ሰውዬ ጋር ጠጋ ጠጋ ያበዛሁት ከውጪ ወደ ውጫሌ ወይም ወደ ሰላሌ ወይም ወደ ጉለሌ ለመመለስ ባለኝ ፅኑ ፍላጎት ነው… (ለዚህ ወዳጄ አስተያየት ትንሽ ፈገግ እንበልለት እና እንቀጥል…)
እውነቱን ለመናገር ሰውየውን “መልካም ስብዕና ፖዘቲቭ” ያልኳቸው ትዊተር ስለሚጠቀሙ የመሰለው ካለ “ኤክስ” ነው የሚያገኘው፡፡ በእርግጥ እርሱም አንድ ቁምነገር ነው… በማህበራዊ ደረ ገጽ በኩል ለማህበረሰቡ ቀረብ ብሎ ትችቱንም ሙገሳውንም መስማት ጥሩ ነገር ነው፡፡ በነገራችን ላይ በዚህ በዚህ ጎላ ካሉት ተቀናቃኝ ፓርቲ ሰዎች አቶ ግርማ ሰይፉ እንደ ዶክተር ቴውድሮስ ሁሉ ተጠቃሽ ናቸው፡፡ አሁንም በነገራችን ላይ ባለፈው ጊዜ ብሄራዊ ቡድናችንን ለማበረታታት እነዚሁ ሁለት ሰዎች ጎን ለጎን ቆመው በማየቴ በአራዶቹ ቋንቋ “አቦ ሙድ አለው” ብዬ አድንቄያለሁ፡፡
የሆነ ሆኖ ባለፈው ጊዜ የእኔን ሀሳባዊ የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ዝርዝር ለማስቀመጥ ስሞክር ዶክተር ቴውድሮስን በሶስተኛ ደረጃ አካባቢ ነበር ያስቀመትኳቸው፡፡ በእግር ኳስ “ድሪም ቲም” የሚባለው አይነት ነው ነገርየው፡፡
ቆይ እስቲ ይሄንን ነገር ድጋሚ ጊዜ ወስጄ እሰራውና፤ የራሴን ካቢኔ ለማደራጀት እሞክራለሁ፡፡ ከአሸባሪውም ከተሸባሪውም ቀላቅዬ ለዛች ሀገር ሁነኛ እና “የሰው ማኛ” የምላቸውን በየሙያ መስካቸው አደራጅና ለኢትዮጵያ ህዝብ አቀርባለሁ፡፡ ከዛ… ከዛማ… በቃ እነበብን እንስቃለን…! ማን ያውቃል አንድ ቀን ሁሉም በፖለቲካ አሰላለፉ ሳሆን በችሎታው የሚሾምባት በየእውቀቱ የሚቀመጥባት ሀገር ትኖረን ይሆናል፡፡
እኔ የምለው አቶ ሃይለማሪም ደሳለኝ አዳዲስ የሚኒስቴሮች ሹመት አንበሻበሹ አይደለም እንዴ….! በዛ ሰሞን “አዲስ ካቢኔ የሚቋቋምበት ምክንያት የለም… የእርሳቸውን ራዕይ ለማስቀጠል እርሳቸው የያዙትን ይዘን እንጂ አዲስ ጥንስስ አንጠነስስም አዲስ መጠጥም አናመርትም” ብለውን አልነበር እንዴ…!
ታድያ አሁን ይሄ ሁሉ አዳዲስ የካቢኔ ሹመት እና ሽረት አዲስ ጠጅ የመጥመቅ ያክል አይደለም አንዴ…  ይሄ በአዲስ መልክ የሚያሰክሩ አዳዲስ ጥንስሶችን ማበጀት አይደለም እንዴ…! አንዳንዶቹን ሹመቶችማ ልብ ብለን ስናያቸው ማስከር ብቻ ሳሆን “ጢንቢራ” የሚያዞሩ እንደሆኑ ከወዲሁ ያስታውቃሉ፡፡ (ጢንቢራ ምን ነበር…!) እውነቴን እኮ ነው እስቲ አሁን የፖሊስ ሹመኛን መንገድ ትራስፖርት ሚኒስትር ማድረግ ምን ይሉት ሹመት ነው…
አረ ሳልጠይቅዎ ወዳጄ ክረምቱ እና የባቡር መንገድ ግንባታው አንድ ላይ ሆነው እንዴት አደረጉዎት… የአዲሳባ መንገድ እንኳንስ ለባቡር፣ ለቴሌ ሲቆፈር፤ እንዴት እንደሚመር… አወቀዋለሁ፡፡ እና ገና የመንገድ ትራንስፖርት ሚኒስትር ብዬ ስል በአዕምሮዬ የመጣው እሱ ነው… እና እንዴት አደረግዎት… ብሎ መጠየቅ ወገኛ ደንቡ ነው… እሱን ተወው ብሎ መመለስም የአንባቢ ደንብ ነው፡፡ እንግዲህ ጽናቱን ስጠን ብሎ መመረቅስ ሌላው የወገና ደንብ አይደል እንዴ…
የእኔ ነገር አንዱን ስጥል ሌላውን ስቀጥል ዋና ጨዋታችን ተቆርጣ ልትቀርኮ ነው… እስቲ አዲስ መስመር ላይ እንውረድና እንቀጥላት…
ሀገራችን ኢህአዴግ አክራሪነት እንደሚሰጋት ተሰጋ… አልኩዎ አይደል…!ማን ሰጋ… ብለው የጠየቁኝ እንደሁ እኔ እልዎታለሁ፡፡
ከላይ እዝችጋ ምልክት ያድርጉልኝ ያልኩዎትን ቦታ አስታወሷት…
…የሀይማኖት አክራሪነት ለአንድ ማህበረሰብ ከባድ ችግር ነው፡፡ ሀይማኖተኞች እምነታቸውን ለራሳቸው በቅጡ ማመናቸው ብቻ አልበቃ ብሏቸው “ሌላ እምነት የሚያምን የተረገመ ነው” ብለው ማሰብ ሲጀምሩ ጦሱ ያኔ ይጀምራል፡፡ ይህ ችግር እጅግ ሲበረታ ውጤቱ በአለማችን ላይ ያየናቸውን በርካታ አሰቃቂ ጉዳቶች መንስኤ ወደ መሆን ያመራል፡፡ ይሄ ደግሞ ያማርራል፡፡ ይደብራልም፡፡ እዝች ላይ ምልክት ያድርጉልኝ…
ብዬዎት ነበርኮ… የሀይማኖት አክራሪነት ኢትዮጵያን ያሰጋታል ብሎ መንግስታችን በንጹሀን ዜጎቻችን ላይ ሳቀር እርምጃ፣ እርግጫ፣ ግልምጫ፣ ቡጥጫ፣ ጡጫ… ሲወስድ አይተነዋል፡፡
እኔ ግን እላለሁ ሀገራችን ከሀይማኖት አክራሪነት ይልቅ ኢህአዴግ አክራሪነት ያሰጋታል፡፡ በኢህአዴግ አክራሪነትም ከእኛ የባሱቱ ካድሬዎች ለራሳቸው የከደሩት አንሷቸው ከኢህአዴግ ሌላ ፓርቲ (የጭፈራ እንኳ ቢሆን)፣ ከኢህአዴግ ሌላ ግንባር (የቴስታ እንኳ ቢሆን)፣ ከኢህአዴግ ሌላ ድርጅት (የንግድ እንኳ ቢሆን)፣ ከኢህአዴግ ሌላ እናት (ወላጅ እንኳ ብትሆን) አለኝ ብሎ የሚመካ ካለ እርሱ የተረገመ ነው ብለው ያወግዛሉ፡፡ ማውገዝ ብቻ ደግሞ አይደለም ያግዛሉም እንጂ….
በዚህ የተነሳ ስማቸውን ጠቅሰን የማንጨርሳቸው ወዳጆቻችን እስር ቤት የገቡት፡፡ በዚህ የተነሳ ነው ቁጥራቸውን ቆጠረን የማንጨርሳቸው ሰዎች ከሀገር የተሰደዱት፡፡ በዚህ የተነሳ ነው ስንትና ስንት የሀገረሰብ ድረ ገፆች ለሀገራቸው ባዳ የተደረጉት፡፡ በዚህ የተነሳ ነው ስንት እና ስንት ሰዎች ከሀገር ተሰደዱት በዚህ ተነሳ ነው…
እስቲ የሚሰማ ካለ ድምጻቸ ጮክ አድርገን እንናገር፤
ከኢህአዴግ ውጪም ፓርቲ ከኢህአዴግ ውጪም ድርጅት ከኢህአዴግ ውጪም ግንባር አለ፡፡ እኔ ብቻ ነኝ ትክክል ከእኔ ውጪ ሌላው የተረገመ ነው ማለት አክራሪነት ነው፡፡ አክራሪነት ደግሞ ለማንም አይበጅም፡፡ እንኳንስ ለሌላ ለራሱ ለአክራሪውም አይበጀው፡፡ ስለዚህ ውድ የኢህአዴግ ወዳጆቼ  ኢህአዴግ አክራሪነትን በጋራ እንከላከል!
ወዳጄ ግድየሎትም የዛሬ ወጋችንን እዝች ላይ እንቋጨው…

No comments:

Post a Comment