ከአዘጋጆቹ፤ ኢህአዴግ የፈጠራትና “በሕዝቦች መፈቃቀድ ላይ የተመሠረተችው” ኢትዮጵያ ይህንን ትመስላለች፡፡ ሰላማዊ ሰዎችን “አሸባሪ” እያሉ ለማሰር ሕግ ከማውጣትና ዜጎችን በፍርሃት ከመሸበብ ይልቅ እንዲህ ያለው አስጸያፊ ተግባር በህጻናት ላይ ከመፈጸሙ በፊት እጅግ ከረር ያሉና ቅጣታቸው የከበደ ሕጎችን ማውጣት፤ የማኅበረሰቡ ድርና ማግ የሆኑትን እና ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን የሚያደፋሩ አማራጮችን መፍጠር፤ ወዘተ ጥቂቶቹ የመከላከያ አማራጮች ናቸው፡፡ ይህ በአንድ ት/ቤት የተፈጸመና ይፋ የሆነ ነው እንጂ በየጊዜው በተመሳሳይ ሁኔታ እየተደፈሩ ተበላሽተው የቀሩ ልጆች ስንት እንደሆኑ ለማወቅ አንዱ ህጻን እዚሁ ዜና ላይ እንደተናገረው ከሌሎች አራት ት/ቤቶች ተደፍሮ መጥቶ ወደዚህኛው (ካራክተር ሆልማርክ አካዳሚ) ከገባ በኋላም ተመሳሳይ ጥቃት እንደተሰነዘረበት ማንበቡ ከበቂ በላይ ማስረጃ ነው፡፡
ግብረሰዶም ፈጽመዋል በተባሉ ተጠርጣሪዎች ላይ ምስክሮች ተሰሙ
በሁለት ሕፃናት ተማሪዎቻቸው ላይ የግብረሰዶም ጥቃት ፈጽመዋል በተባሉ ስድስት መምህራን ላይ የፌዴራል ዓቃቤ ሕግ ስድስት ምስክሮች፣ ሰኔ 28 ቀን 2005 ዓ.ም. በፌዴራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሰባተኛ ወንጀል ችሎት ቀርበው የምስክርነት ቃላቸውን ሰጡ፡፡
በቦሌ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታው ሩዋንዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የሚገኘው ካራክተር ሆልማርክ አካዳሚ በሚባል ትምህርት ቤት ውስጥ፣ የአሥርና የ11 ዓመት ዕድሜ ያላቸው የአራተኛና የአምስተኛ ክፍል ተማሪዎች ላይ የግብረሰዶም ወንጀል ፈጽመዋል በሚል ተጠርጥረው ክስ የተመሠረተባቸው የትምህርት ቤቱ ዳይሬክተር አቶ ደሳለኝ ኃይለየሱስ፣ ሱፐርቫይዘሩ አቶ የኔዓለም ጌታቸው፣ መምህር አለማየሁ ገብሬ፣ መምህር ደበበጥሩነህ፣ አቶ መልካሙ ቀለብና አቶ ሳምሶን መኩሪያ ሲሆኑ፣ አካዳሚው ካራክተር ሆልማርክ አካዳሚም በክሱ መካተቱ ይታወሳል፡፡
ዓቃቤ ሕግ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ለመሠረተው ክስ ያስረዱልኛል ያላቸውን ሁለቱ ተጠቂ ሕፃናትና እናቶቻቸውን፣ እንዲሁም አንድ የሥነ ልቦና አማካሪና አንድ የሕግ ባለሙያ አቅርቦ አስመስክሯል፡፡
የግል ተበዳይ መሆኑ የተገለጸው የአሥር ዓመቱና የአራተኛ ክፍል ተማሪ ሕፃን ለፍርድ ቤቱ የሚያስረዳለትን ዓቃቤ ሕግ በጭብጡ ያስያዘው፣ ተጠቂው ወደ አካዳሚው የተቀላቀለው በጥቅምት ወር 2005 ዓ.ም.፣ የግብረሰዶም ድርጊቱ የተፈጸመበት በገባበት ቀን ነው፡፡ በየካቲት ወር 2005 ዓ.ም. ለሁለተኛ ጊዜ ድርጊቱ እንደተፈጸመበትና ሁሉም መምህራን በመፈራረቅ ድርጊቱን እንደፈጸሙበት እንደሚያስረዳለት አስይዟል፡፡
ሕፃኑ በሲሲቲቪ ለችሎቱ እንደገለጸው፣ አካዳሚውን መቼ እንደተቀላቀለ አያስታውስም፡፡ አራተኛ ክፍል ሆኖ መቀላቀሉን ግን ያውቃል፡፡ ወደ አካዳሚው ሊገባ የቻለው ቤተሰቦቹ ከኮተቤ ወደ ቦሌ ቤት በመቀየራቸው ነው፡፡ በመጀመርያ ትምህርት ቤት ሲሄድ ዳይሬክተሩ ጠርተውት ለምን ወደ አካዳሚው እንደመጣ ሲጠይቁት ‹‹ቀድሞ በነበርኩበት ትምህርት ቤት ተደፍሬ ነው አልኩት፤›› በማለት ተናግሯል፡፡
ዳይሬክተሩ በሌላ ቀን ጠርተውት የግብረሰዶም ጥቃት እንዳደረሱበትና ሌሎቹም መምህራን (ሙሉ ስማቸውን ጠርቶ) ድርጊቱን እንደፈጸሙበት ያስረዳው ሕፃኑ፣ ድርጊቱን የፈጸሙበት በባዶ ክፍል ውስጥ በዕረፍትና በምሳ ሰዓት መሆኑን ተናግሯል፡፡
አንደኛው መምህር ድርጊቱን ሲፈጽም ሌላኛው መምህር እንደሚይዘው የተናገረው ተጠቂው፣ ድርጊቱን አንዳንድ ጊዜ በቢሮ ውስጥ እንደሚፈጽሙበት አስረድቷል፡፡
የተጠርጣሪዎቹ ጠበቆች ለሕፃኑ ‹‹ስንት ጊዜ ተደፈርክ?›› የሚል ጥያቄ ሲያቀርቡለት፣ ‹‹ብዙ ጊዜ ቀን ቀን እያሳለፉ፣ አንዳንድ ጊዜ ደግሞ በተከታታይ ደፍረውኛል፤›› ብሏል፡፡ የመምህራኑን ስም እየጠራ በተደጋጋሚ ድርጊቱን እንደፈጸሙበት ገልጿል፡፡
ለቤተሰቡ መጀመሪያ ጊዜ የተናገረው ለማን እንደሆነ ተጠይቆ ለእናቱ መሆኑን ተናግሯል፡፡ ከነገራቸው በኋላም ትምህርት ቤት መሄዱን አለማቋረጡን አክሏል፡፡ ለምን ለአባቱ እንዳልተናገረ ሲጠየቅ፣ ‹‹እኔ እንጃ የሰማ አልመሰለኝም›› ብሏል፡፡ በተደጋጋሚ ድርጊቱ ሲፈጸምበት ለእናቱ ቢናገርም ከትምህርት ቤት አለመቅረቱን ገልጿል፡፡ ወደ ሆስፒታል እናቱ እንደወሰዱት ነገር ግን አባቱ ይወቁ አይወቁ የሚያውቀው ነገር እንደሌላ ገልጿል፡፡ ሲደፈር መጮህ አለመጮኹን እንዲያስረዳ ተጠይቆ እንዳልጮኸ ተናግሯል፡፡ አካላዊ ጉዳት እንዳልደረሰበት ግን ትንሽ አሞት እንደነበር ገልጿል፡፡ ሲፀዳዳ አንዳንድ ጊዜ እንደሚያመውም አክሏል፡፡ ድርጊቱ ከተፈጸመ በኋላ እዚያው ከተደረገበት ቦታ ትተውት ሲሄዱ ወደ ጨዋታው መሄዱንና ብቻውን መጫወቱን ተናግሯል፡፡ ሌላ ጊዜም በተደጋጋሚ ሲደፈር ጊዜ ካለው ወደ ጨዋታ እንደሚሄድ ጊዜ ከሌለው ወደ ትምህርቱ እንደሚገባ ገልጿል፡፡ የትምህርት ቤቱን ሠራተኞች ስለሚፈራም ለማንም አለመናገሩን አስረድቷል፡፡ ሊደፍሩት የሚወስዱት ብቻውን ሲያገኙት መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
ሁለተኛው የግል ተበዳይ የ11 ዓመት ዕድሜ ያለው የአምስተኛ ክፍል ተማሪ ሕፃን ሲሆን፣ ዓቃቤ ሕግ ለአንደኛው የግል ተበዳይ ባስያዘው ጭብጥ መሠረት የተፈጸመበትን ድርጊት ለችሎቱ እንዲያስረዳ ጠይቆት ሕፃኑ አስረድቷል፡፡
የሁሉንም ተጠርጣሪዎች ስም ሲጣራ ‹‹ምን አደረጉህ?›› በማለት ዓቃቤ ሕግ ጠይቆት እንዳስረዳው፣ የሚኖረው በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ለቡ ነው፡፡ ወደ ትምህርት ቤቱ የገባው በየካቲት ወር ነው፡፡ አምስት መምህራን ገና የገባ ዕለት ድርጊቱን እንደፈጸሙበት ተናግሯል፡፡ ድርጊቱን ለመፈጸም ጣታቸውንም መጠቀማቸውን ሕፃኑ አክሏል፡፡
የተጠርጣሪዎች ጠበቆች ‹‹ድርጊቱን የፈጸሙብህ መጀመሪያ የገባህ ቀን ነው?›› በማለት ለሕፃኑ ላቀረቡለት መስቀለኛ ጥያቄ፣ ‹‹አዎ›› ብሏል፡፡ ለእናቱ እንደነገራቸውና ከሦስት ሳምንታት በኋላ ወደ ትምህርት ቤቱ መመለሱን አስረድቷል፡፡ እናቱ ወደ ትምህርት ቤት ሲልኩት ሞባይል ስልክ አስይዘውት ‹‹ሲጠሩህ ደውልልኝ›› እንዳሉት የተናገረው ሕፃኑ፣ መምህራኑ ሲጠሩት ሊደውል ሲል ሱፐርቫይዘሩ እንደከለከሉት ገልጿል፡፡
በሌላኛው ሕፃን ላይ ጥቃት መፈጸሙንና እንዴት እንዳወቀ ጠበቆች ሲጠይቁት እናቶቻቸው ተገናኝተው ሲነጋገሩ መስማቱን፣ በሌላ በኩል ደግሞ በስልክ ሲያወሩ መስማቱን፣ በመቀጠል ደግሞ ተጠቂ ነኝ ያለው ልጅ እንደነገረው አስረድቷል፡፡
ለቤተሰቦቹ ለምን እንዳልተናገረ ሲጠየቅ ደግሞ፣ ተጠርጣሪዎቹ እንደሚገድሉት ስላስፈራሩት መሆኑን ሲናገር፣ ‹‹ታዲያ እንዴት ለእናትህ ተናገርክ?›› ሲባል ከንፈሩ በልዞ ተመልክተው ‹‹ካልነገርከኝ ራሴን መኪና ውስጥ ከትቼ አጠፋለሁ›› ስላሉት ፈርቶ መናገሩን አስረድቷል፡፡
ከተደፈረ በኋላ ወዴት እንደሚሄድ ተጠይቆ ወደ ጨዋታ እንደሚሄድ ተናግሯል፡፡ እናቱ ወደ ትምህርት ቤት ሲልኩት ቲሸርቱንና የሱሪውን ወገብ ሰፍተው መሆኑን፣ ነግር ግን ድርጊቱን የሚፈጽሙበት ስፌቱን ቀደው መሆኑን አስረድቷል፡፡ መፀዳጃ ቤት እንዴት እንደሚጠቀም ሲጠየቅ፣ ‹‹ጠዋት ቤት ከተፀዳዳሁ ስመለስ ነው የምጠቀመው፤›› ብሏል፡፡
ሆስፒታል ስለመወሰዱ ተጠይቆ፣ የመጀመርያው ቀንና የመጨረሻው ቀን ጋንዲና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል እንደተወሰደና ድርጊቱ የተፈጸመበት ለሦስት ቀናት መሆኑን ገልጿል፡፡
የመጀመርያው ተጠቂ እናት በሰጡት ምስክርነት እንደገለጹት፣ መምህራኑ በልጃቸው ላይ ተፈራርቀው ጥቃት አድርሰውበታል፡፡ በሌላ ትምህርት ቤትም ተደፍሮ ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ከነበረበት ትምህርት ቤት አስወጥተው ወደ ካራክተር ሆልማርክ አስገቡት፡፡ በጥቅምት ወር 2005 ዓ.ም. መጀመርያ ቀን ዳይሬክተሩ ከየትና እንዴት እንደመጣ ከጠየቀው በኋላ፣ እንደደፈረውና ሌሎቹም ደጋግመው እንዳደረጉት እንደነገራቸው አስረድተዋል፡፡
ለአካዳሚው የቦርድ አባል ለሆኑ ግለሰብ ሲደውሉላቸው፣ ተደፈረ የሚባለው ነገር ሊደረግ እንደማይችልና ስህተት መሆኑን ሲገልጹላቸው፣ ለሌሎች የአካዳሚው ሰዎች ቢናገሩም ምንም ዓይነት ዕርምጃ እንዳልተወሰደ ገልጸዋል፡፡
ጠበቆች እንዴት ከሌላ ትምህርት ቤት ሊያስወጡት እንደቻሉ ሲጠይቋቸው፣ በነበረበት ትምህርት ቤት ሌሎች ሲደፈሩ በማየቱ በቀጣይ እሱም ጋ ይደርሳል የሚል ሥጋት ስላደረባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡ ይህንን አካዳሚም የመረጡት በግብረሰዶማውያን ዙሪያ የሚያስተምሩትንና የአካዳሚው የቦርድ አባልን አግኝተዋቸው ሲያስረዷቸው፣ ‹‹አምጭው እኛ ጋ ይማር›› ስላሏቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡ በሌላ ትምህርት ቤት ጥቃቱ ደርሶበት ወንጀለኞቹ እንደተፈረደባቸውም ተናግረዋል፡፡
ባለቤታቸው ትልቅ ቦታ ያሉ በመሆናቸውና ታማሚ በመሆናቸው እንዲሁም ልጁ አንድ ልጃቸው በመሆኑ ፈርተው እንዳልነገሯቸው ገልጸዋል፡፡ ከጥቅምት እስከ መጋቢት ድርጊቱ እንደተፈጸመበት እየነገራቸው ትምህርት ቤት እንደወሰዱት አስረድተዋል፡፡ ለምን ወደ ሕግ እንዳልወሰዱት ተጠይቀው፣ ከአባቱ ጋር ካልተስማሙ የማስቀረት አቅም እንደሌላቸው ገልጸዋል፡፡ ባለቤታቸው ቢነግሯቸውም ‹‹ሊሆን አይችልም›› እንደሚሏቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ በመጀመርያው ቀን ስድስቱም አስተማሪዎች እንደደፈሩት እንደነገራቸው ገልጸዋል፡፡ ገና እንደገባ እንዴት ሊያውቃቸው (ስማቸውን) እንደቻለ ሲጠየቁ፣ ሁሉንም ከነስማቸው እንደሚያውቃቸው ጠቁመዋል፡፡
የሁለተኛው ተጠቂ እናትም በልጃቸው ላይ ጥቃቱ እንደደረሰ ያወቁት ከሦስት ሳምንታት በኋላ መሆኑን ተናግረው፣ ድርጊቱን የፈጸሙበት ግን ትምህርት ቤቱ በገባ ከሁለተኛው ቀን ጀምሮ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
አምስት መምህራን እንደደፈሩት ለትምህርት ቤቱ ቦርድና ኃላፊዎች ማሳወቃቸውን፣ ካሜራ ለመግጠም ቢሞከርም መነቀሉን፣ ጋንዲና ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ወስደው ማስመርመራቸውንም መስክረዋል፡፡ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ወስደው ለሥነ ልቡና ባለሙያዎች ማማከራቸውንም አክለዋል፡፡
ልጃቸው ካራክተር ሆልማርክ አካዳሚ አምስተኛው ትምህርት ቤቱ መሆኑን የገለጹት የተጠቂው እናት፣ በአራቱም ትምህርት ቤቶች መደፈሩን አስረድተዋል፡፡ የትምህርት ቤቶቹን ስምም ጠቅሰዋል፡፡ ለፖሊስ እንዲደውል ስልክ አስይዘው ቢልኩትም ዳይሬክተሩ እንደነጠቁት፣ እናቱ ስልኩን ሲያዩት መደወሉን አይተው ‹‹ተደፈርክ?›› ሲሉት ‹‹አልተደፈርኩም›› ቢላቸውም፣ ‹‹እውነቱን ካልነገርከኝ መኪና ውስጥ እገባለሁ›› በማለታቸው በድጋሚ መደፈሩን እንደነገራቸው አስረድተዋል፡፡
ጠበቆች እውነቱን እየነገራቸው ለምን እንዳስጨነቁት ሲጠይቋቸው፣ ‹‹ስለፈራ እንጂ እንደተደፈረማ አውቃለሁ፤›› ብለዋል፡፡ ሌላዋ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የጠቅላይ ፍርድ ቤት ሠራተኛ የሆኑ ግለሰብ ሲሆኑ፣ ልጆቹ እሳቸው ዘንድ የመጡ ቢሆንም ያነጋገሯቸው ከ20 ደቂቃ የማይበልጥ በመሆኑ ሙያዊ ማብራሪያ ሊሰጡ እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡
የመጨረሻዋ የዓቃቤ ሕግ ምስክር የሕግ ባለሙያና የሕፃናት የሕግ ከለላ ማዕከል ኃላፊ ሲሆኑ ወደ ማዕከሉ መምጣታቸውን፣ ነገር ግን ጉዳዩ ስለሚቀፍ መስማት እንዳልፈለጉ፣ ነገር ግን ተጠቂዎቹ ፖሊስ ጣቢያ ቀርበው ቃላቸውን ሲሰጡ አዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ተገኝተው መስማታቸውን መስክረዋል፡፡
ፍርድ ቤቱ የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች ቃልንና ክሱን ከሕጉ ጋር በማገናዘብ ብይን ለመስጠት ለሐምሌ 15 ቀን 2005 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡ (ምንጭ፤ ሪፖርተር)
No comments:
Post a Comment