"ባለሃብቶች በእድሳት ስም ቤተ መቅደስ ዘልቀው ጽላት ይቀይራሉ"
በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦች ክልል በከፊቾ ዞን በጥንታዊ አድባራት ጽላት መዘረፉን እናውቃለን ያሉ ለጎልጉል፡ የድረገጽ ጋዜጣ ገለጹ። የዜናው ምንጮች የዞኑ አገረ ስብከት በዞኑ በሚገኙ አድባራት ላይ ምርመራ እንዲያካሂድ ጠይቀዋል። ዝርፊያውን የሚያካሂዱት “ባለሃብቶች” መቀመጫቸውን አዲስ አበባና ጅማ ከተማ ያደረጉ የክልሉ ተወላጆች መሆናቸውን አስታውቀዋል።
ነዋሪነታቸው ቦንጋና ጊምቦ እንደሆነ የሚገልጹት የዜናው ምንጮች “ቀበኞች” በማለት የሚጠሯቸውን የጽላት ዘራፊዎች የዝርፊያ ስልት ተናግረዋል። በመጀመሪያ እድሜ ጠገብ የሆኑትን አድባራት ይለያሉ። በቃፊሮቻቸው አማካይነት መረባቸውን ዘርግተው ሰዎችን ያጠምዳሉ። ህዝበ ክርስቲያን በሚሰበሰብበት ወቅትና ዓመታዊ የበዓላትን ቀን መርጠው በርዳታና በእድሳት ስም ውዳሴ ይቀበላሉ።
በዞኑ የሚገኙት አቢያተ ክርስቲያናት እድሜ ጠገብ በመሆናቸው በርካታ ጥንታዊ ቅርስም እንዳላቸው የሚጠቁሙት ክፍሎች “ያረጁትን አድባራት እናድሳለን በማለት ጥቁር ለምዳቸውን ለብሰው መቅደስ ውስጥ ይዘልቃሉ” በማለት የዝርፊያው ድራማ እንዴት እንደሚከናወን ያስረዳሉ።
ለሃይማኖታቸው የቀኑና የታመኑ የቤተ መቅደስ ጠባቂዎችና አገልጋዮች ሲያጋጥሟቸው መቅደስ ውስጥ ተመላልሰው በሚሰበስቡት መረጃ መሰረት አብረቅራቂ ሃሰተኛ ጽላት በመተካት ዝርፊያ እንደሚካሂዱ፣ ለዝርፊያ የሚመችና ስብናው የወደቀ አገልጋይ ሲያገኙም በግልጽ ያሻቸውን አድርገው ስርቆቱን እንደሚፈጽሙ የዜናው ሰዎች ያስረዳሉ።
ድርጊቱ የቆየና ሰዎቹም የሚታወቁ እንደሆኑ የሚጠቁሙት እነዚሁ ክፍሎች፣ “ቀበኞቹ” ካላቸው የገንዘብ አቅም አንጻር እጃቸው ከወቅቱ ጉልበተኞችና የቤተ ክህነት ከፍተኛ አመራሮች ጋርም የጠበቀ ግንኙነት ሊኖራቸው እንደሚችል ከግምት በላይ አመላክተዋል። በዚህ ተነሳ “እንፈራለን፤ ፊት ለፊት ለመግጠምም እንቸገራለን” በማለት ለጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ ምስጢራቸው እንዲጠበቅ አስጠንቅቀው መረጃውን ለመስጠት ችለዋል።
“ይህንን ዜና ጥቅማቸው የሚነካና ችግር ያለባቸው አካላት ዙሪያ ያሉ ጥቅመኞች ሊያስተባብሉት ይችሉ ይሆናል” ሲሉ ዜናው የሚያስደነግጣቸው ክፍሎች የሚወስዱትን የመጀመሪያ ርምጃ ያመላከቱት ተቆርቋሪዎች፣ “የእኛ ጥያቄ ግን ማጣራትና ምርመራ ተደርጎ ውጤቱ ከታወቀ በኋላ እውነታው እንዲረጋገጥ ነው” ብለዋል።
የዞኑ አገረ ስብከት ዛሬ ነገ ሳይል በተቀደሱ የማምለኪያ አድባራት ላይ የተፈጸመውንና እየተፈጸመ ያለውን ዝርፊያ የማጣራት ሃላፊነት እንዳለበት ያሳሰቡት ክፍሎች፣ ቀበኞቹ በርዳታ ስም እድሳት ባካሄዱባቸው አድባራት ላይ የሙከራ ምርመራ ቢደረግ ጥቆማው ምላሽ እንደሚያገኝም በርግጠኛነት ተናግረዋል።
በእድሳትና በርዳታ ስም መቅደስ በመዝለቅ ከሚከናወነው ዝርፊያ በተለየ በድርድር የሚካሄዱም ዝርፊያዎች ስለመኖራቸው ያመለከቱት ክፍሎች “ጉዳዩ እጅግ ጥንቃቄ የሚፈልግ በመሆኑ ስምና ቦታን ለይተን ለመጠቆም እንቸገራለን” ብለዋል። “መልዕክቱ ለቀበኞቹ፣ ለተባባሪዎቻቸውና የሚሰማ ተቆጣጣሪ አካል ካለ ለነሱ ነው” ሲሉም አክለዋል። በዞኑ ያሉ የህዝብ ወኪል እንደራሴዎችም በዚህ ጉዳይ ላይ ጥንቃቄ ወስደው እንዲሰሩ ጠይቀዋል።
“የቃል ኪዳን ጽላት ዘርፎ ከማነከስና ሰልሎ ከመሞት ውጪ ሌላ ዕድል የለም” ሲሉ ማስጠንቀቂያ ያስተላለፉት ተቆርቋሪ አዛውንቶች በ2005 መገባደጃ ላይ ዋሻ ውስጥ ተገኘ የተባለ ጽላት የት እንደገባ እንደማይታወቅ አመልክተዋል። ዜናው የመገናኛ ሰዎች ዘንድ ሁሉ ደርሶ እንደነበር፣ ነገር ግን በማይታወቅ ሁኔታ ተዳፍኖ መቅረቱ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ አካላትን እስካሁን እንደሚከነክናቸው አመልክተዋል።
ከዝግጅት ክፍሉ
ይህ ዜና ከመታተሙ በፊት ከጥቆማው በተጨማሪ ሰዎችን ለማነጋገር ተሞክሯል። የዞኑን አገረ ስብከት ለማግኘትም ተሞክሯል። ከዜናው ባህሪ በመነሳት ጉዳዩ ሳይጣራ ግለሰቦችን የሚያመላክቱ መገለጫዎችን ከመጠቀም ተቆጥበናል። በተጠቀሰው ቦታ ብቻ ሳይሆን በመላው አገሪቱ በርካታ ቦታዎች ነዋያትና ጥንታዊ ቅርሶች እንደሚዘረፉና ለዝርፊያው ተባባሪ ሆነው የሚያገለግሉት የድንበር ጠባቂዎች መሆናቸውን በተለያዩ ጊዜያት የሚሰማ እውነት በመሆኑ ተጨማሪ ጥቆማ ለምታቀርቡልን መድረኩ ክፍት ነው። ከቦንጋና አካባቢው፣ እንዲሁም ከጅማ ነዋሪዎች ለደረሰን ጥቆማ እናመሰግናለን። በዜናው ላይ ቅሬታም ሆነ ተቃውሞ ካለ እናስተናግዳለን።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
No comments:
Post a Comment