Wednesday, December 11, 2013

በቃ! በለን አምላክ (say us enough! O’ God)



(ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

prayer1


ያ የምትወደው ፤ ያ የምታሞካሸው
ልጆቸና ሕዝቤ ፤ እያልክ ያከበርከው
መከራ አፈናቅሎት ፤ ከሀገሩ ከቀየው
ከአሕዛብ ደጅ ወድቆ ፤ ግፍ ሰቆቃ ቆላው፡፡
የጭንቅን ልክ ዓየ ፤ ሞት በዓይነት ቆጠረ
የሰቆቃን ጣራ ፤ ከፍ ብሎ በረረ
ሞትን ተላመደ ፤ ንቆም ተዳፈረ
በእሱ እየተበላ ፤ በእሱ ላይ ፎከረ
የአውሮችን አውሬነት ፤ ተበልቶ አጋለጠ
ድብቁን አወጣ ፤ ነፍሱን ለሀቅ ሰጠ፡፡

   ምን ዓይነት ፍጥረቶች ፤ ምን ዓይነት ጉዲራ
   እውን ሰዎች ናቸው ? የሆኑ የእጅህ ሥራ ?
   ወይስ ሰይጤ እንዳለው ፤ እኔ ነኝ ፈጣሪ
   ይሆኑ ይሆን የሱ ፤ የዚያ እርኩስ መሠሪ
   በሁለ ነገሩ ፤ እሱን አስመስሎ
   እንደራሱ አድርጎ ፤ ፈጥሯቸው አንቦልቡሎ ?
   ወይስ ከነገዱ ፤ ከሆኑት እንደሱ
   ሥጋ ለብሰው መጡ ? ሰው መስለው ሊያረክሱ
   ሕዝብህን በመቅጣት ፤ አንተን ለመበቀል
   ልጆች እንዳይኖሩህ ፤ ከርስትህ በመንቀል
   ካልሆነ እንዴት ታዲያ ፤ ሰው ሆነው የአዳም ዘር
   ሰብአዊ ሕሊና ፤ እንዴት አጡ ፍቅር ?
   ጥቂት ሐዘኔታ ፤ ሩኅሩኅ መሆን ገር
   እውን ከዚህ እርጉም ዘር ፤ ከእኩያን ልቡና
   ጽድቅ ይወጣል ብሎ ፤ ሰው ያምናል ሊቀና ?
   ካልሆነ የዋህ ጅል ፤ ዕውቀት የገደፈ
   በሥጋዊ ጥቅም ፤ ልቡ የተነደፈ
   የዝሙት ጥማቱን ፤ ሊያረካ የወደደ
   ያማሩትን ሁሉ ፤ መርጦ እያጠመደ
   በሴት ለመጫወት ፤ በአንድ ቤት አጉሮ
   አንጋግቶ ለመንዳት ፤ በእንስሳ ተፈጥሮ
   ሴት ሰው እንዳልሆነች ፤ እንደ እቃው ቆጥሮ
   የእሱ መጠቀሚያ ፤ ሆና የሱ ቋጠሮ
   የራሷን ፍላጎት ፤ አሳጥቶ ቀብሮ
   እሷም ልክ እንደሱ ፤ ሰው መሆኗ ቀርቶ
   እንደ ሰውነቷም ፤ እኩል መብቷን ነስቶ
   ጨቁኖ ለመግዛት ፤ ለመርገጥ አፍኖ
   የሚሻ ማስበርገግ ፤ እንደ ባሪያ አባክኖ
   ጾም ሳይልም ፍስክ ፤ ለመክተት ጮማ እርጎ
   በቅቤ እንቁላሉ ፤ ለመውዛት መግምጎ
   ገደብ ሳይኖርበት ፤ ለመድለብ ጠራርጎ
   ይሄን ይሄን ምቾት ፤ ኃጢአት ነው ሳይባል
   ማግኘት የፈለገ ፤ ራሱን የሚያታል
   ይሄ ዓይነት ተላላ ፤ አዎ እሱ ይሆናል ፡፡
   ታዲያ እሱ ምን ያርገው ፤ ከአውሬ ቢሆን አቻ
   ሆድ እንዲህ ሲሞላ ፤ ሲፈረጥም ጡንቻ
   ባዶ መሆኑ አይቀር ፤ ጭንቅላት ተራቁቶ
   ለማሰብ ተስኖት ፤ ሰብአዊነት አጥቶ
   ከእጁ የወደቁትን ፤ ከወልደ ሳጥናኤል
   በእስር ቤት አጉሮ ፤ በምድር ላይ ሲዖል
   ሕፃናት አልቀሩ ፤ አሮጊት ሕሙማን
   ሴቷ አልቀረች ወንዱ ፤ ደፍረው አረከሱን
   ብረት እያጋሉ ፤ በአፈ ማኅጸኗ
   በወንዱም ፊንጢጣ ፤ ወዮ ወዮ ቀኗ
   በዘይት መላጡ ፤ በፎቅ መወርወሩ
   የሰው ልጅ እንደ በግ ፤ በሰይፍ መመተሩ
   በረሀብና ጥም ፤ ሲሰቃይ በጠኔ
   ተሰዶ መግባቱ ፤ ሆኖበት ኩነኔ
   ብልቱን ሲቆርጡት ፤ ሲያስጓራው ሰቆቃ
   የስቃዩን ጩኸት ፤ የጣሩን ድምፅ ሲቃ
   መስማት የሚናፍቁ ፤ ሁሌ እንደ ሙዚቃ
   እያዩ የሚያሽካኩ ፤ እንደ አዝናኝ ድለቃ
   ስንቱ ጉድ ተነግሮ ፤ ቢወራ አያበቃ፡፡
ታዲያ እነዚህን ፤ ጭካኔ የተሞሉ
ግእዛነ አእምሮ ፤ ሕሊና አልባ ሁሉ
ትንሽ ከርኅራኄ ፤ ቅንጣት ያልታደሉ
ግብረ-ገብነትን ፤ ጽድቅን የሚጠሉ
እንዴት ብየ ልመን ፤ ሰዎች ናቸው ሲሉ
ሰብአዊ መለያ ፤ ሳይዙ ቢምሉ
ከቶ እንዴት ይሆናል ፤ ነው ሌባ ለአመሉ
ውስጥ የሌላቸውን ፤ እንዲያው ሲያስመስሉ
ግን ሰውን ነው ጌታን ? ማንን ያታልላሉ?
   ራሔል ስታለቅስ ፤ ጩኸት ስታሰማ
   የሰቆቃ እንባዋን ፤ ያየኸው ከራማ
   ምን ነው ጨከንክብን ፤ ፍጹም ድምፅህ ጠፋ
   የረድኤት ክንድህ ፤ ርቆን ቀን ከፋ
   ሽ ራሔሎች ጮኸው ፤ ደም እያመነጩ
   ከዓይን ወደሰማይ ፤ ቀድተው እየረጩ
   አምላከ አበዊነ ፤ እግዚአብሔር አዶናይ
   በእውነት የለህማ ! አንተ በዚህ ሰማይ
   እያሉ አልጮሁም ? በሰቆቃ እንባ ?
   የገባኸውስ ቃል ? ሆነ እንዴ ቁብ አልባ ?
   የሰጠኸን ኪዳን ፤ ምን በላው የት ገባ ?
   አንተም ደሞ እንደሰው ፤ ቃልህን ታጥፋለህ ?
   ወይንስ ወዴት ሔድክ ፤ ምን በላህ ምን ዋጠህ ?
   እንደምን ያለ እንቅልፍ ፤ ያዘና ወሰደህ ?
   ማን ቀርቦ ይቀስቅስህ ፤ ማን ጎትጉቶ ያንቃህ ?
   አቅም አልባ ሆነናል ፤ ጽድቅ ርቋል ከኛ
   አንተኑ ለማንቃት ፤ እንድትሆነን ዳኛ
አንቂልና እመ አምላክ ፤ ቀስቅሽው ልጅሽን
የእናትነት ቁጣሽ ፤ ቶሎ ያሥነሣልን
ንቃሕ እግዚኦን ደግመሽ ፤ ለምንት ትነውም
በእግዚኦ ኩነኔከ ፤ እንዲሰጠን ሰላም
ስለ ዐሥራትነት ፤ ስላለሽ ቃል ኪዳን
ብለሽ አሳስቢልን ፤ ከልጅሽ አማልጅን
ፍረድ በይው ታደግ ፤ ሕዝቤን ከመከራ
በቀልህን ተበቀል ፤ ደማቸውን አጥራ
በይልን ጩሂልን ፤ አታስተኝ አደራ
ይሄው እንላለን ፤ እግዚኦ ቀን አብራ
ማረን ይቅር በለን ፤ ፍቅርህን አድሰው
ምንድን ነው ያስጨከነህ ? አንልም ለምን ነው ?
በደል ኃጢአታችንን ፤ በደንብ ስለምናውቀው
እንዳስተማርክ ሁሉ ፤ በቃልህ እንዳልከው
የምወደውን ነው ፤ እኔ የምቀጣው
አባቱ የማይቀጣው ፤ ልጅ የሆነ ማነው ?
ያለ ቅጣት ብትኖር ፤ ዲቃላ ነህ እንጅ
ከአብራክ የተከፈልክ ፤ አይደለህም ልጅ
ቅጣቱ ለጊዜው ፤ ደስ አያሰኝህም
ዳሩ ግን በኋላ ፤ ፍሬውን የሰላም
ያፈራላቹሀል ፤ ጽድቅን የዘለዓለም
ብለኸናልና ፤ ይሁን  እንዳንተ ፈቃድ
ግን ደሞ በቃ በል ፤ ምሕረትህን አውርድ
አፈፍ አርገህ አንሣን ፤ እግዚኦ ማረን ወልድ
መከራ የምታውቀው ፤ አንተ የኛ ዘመድ
ከዚህስ በኋላ ፤ ሌላ ዓይነት መከራ
ደሞ ሌላ ፍዳ ፤ ሌላ ሕይዎት መራራ
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
የሚሸከም ጉልበት ፤ የሚችል ትክሻ
የሚያስተናግድ ቅስም ፤ ስቃይ መታገሻ
ጨርሶ የለንም ፤ ደቂቃም ማማሻ
በዚሁ ይብቃ በለን ፤ ይሁን መጨረሻ
ትንሣኤያችንን አውጅ ፤ ይምጣ የኛ ድርሻ፡፡
ኅዳር 2006 ዓ.ም.

No comments:

Post a Comment