Wednesday, January 8, 2014

ዋናውን “ሌባ” ማን ይከሰዋል?


አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ የ“ሰው” ንግድ!

ethio human trafficking
ኢህአዴግ ልዩ ምክንያት ከሌለው በስተቀር የውጪ ጠላት አያፈራም የሚሉ በርካታ አስተያየት ሰጪዎች አሉ። ምክንያት ካለው ግን ቅንድቧን አንደተላጨችው ነገረኛ ሴት ለመጋጨት ይፈጥናል። ከፊትለፊቱ ገንዘብ ካየ ደግሞ ኢህአዴግ ገደል ሜዳው ነው የሚሉም አሉ። ገንዘብ በሌለበት ቦታ ኢህአዴግ አይታይም በማለት ከበረሃው ኑሮ ጀምሮ የሚከሱት ጥቂቶች አይደሉም። በቅርቡ በሳዑዲ አረቢያ ምድር በሁለት ምድብ ተከፍለው የሚሰቃዩትን ወገኖች አስመልክቶ የያዘው አቋምም ከዚሁ መርሁ የተቀዳ እንደሆነ የሚከራከሩ በርካታ ናቸው። “ምን ያድርግ የኖረው የአገሪቱ ችግሮች ሁሉ ተቆልለው እሱ ላይ ወደቁ” በማለት ኢህአዴግን ለኢትዮጵያ የተቀመጠ “የተቀባ” መፍትሔ አድርገው የሚያወድሱ አሉ።
ኳስ ሜዳ ያደገችው ኑሪያ መሐመድ አሁን የምትኖረው ኳታር ነው። ኑሮ እንዳሰበችው የተመቻቸ ባይሆንላትም ወደ አገርዋ ለመመለስ አትፈልግም። አታስበውም። “ኢትዮጵያ ምን አለ?” ከማለቷ በቀር ለምክንያቷ ብዙ ማብራሪያ መስጠት አትፈልግም። አገሯ እሷንና መሰል ወገኖቿን ለማኖር አልቻለችም። በኳታር ባይመቻትም የታናናሽ እህቶቿንና የምትወዳቸውን እናቷን ጉሮሮ መሸፈን የሚያስችላትን አቅም አግኝታለች። ይህ ለእርሷ ታላቅ በረከት ነውና ችግሯን በበረከቷ እያዋዛች ትኖራለች። በኳታር በረሃ!!
ኑሪያ ኳታር የሄደችው አሜሪካን ግቢ በሚገኝ አንድ የጉዞ ወኪል ቢሮ ውስጥ ሰዎችን ወደ አረብ አገራት የመላክ ህጋዊ ፈቃድ አለው በተባለ ሰው አማካይነት ነው። የላካትን ሰው በአካል አታውቀውም። ቢሮውንም የረገጠችው የመጓጓዣ ቲኬትና ሰነዶቿን ለመቀበል ብቻ ነው። በወቅቱ እዛው ቢሮ ወደ ሳዑዲ ለመሔድ በዝግጅት ላይ የነበረች እህት ተዋውቃለች። ልጅቷ ከደቡብ ክልል ሆሳዕና ከተማ የመጣች ነበረችና ቤቷ ወስዳ ጋብዛታለች። በዚያው በመሰረቱት ጓደኝነት ከያሉበት ሆነው ይጠያየቁ ነበር። እድሜ ለጊዜና ለስልጣኔ!!

ኑሪያ እንደምትለው ጓደኛዋ ወደ ጅዳ ለመሄድ እንደትችል ቤተሰቦቿ የሚያርሱባቸውን ሁለት በሬዎች ሸጠዋል። ገንዘብ በአራጣ ተበድረዋል። አሁን የተፈጠረው ትርምስ ከመከሰቱ ስድስት ወር በፊት በህጋዊ መንገድ ሳዑዲ አረቢያ ሄዳ የነበረችው ጓደኛዋ “ህገወጥ” ተብላ ተመልሳለች። ቅድሚያ እቅዷ ለቤተሰቦቿ ሁለት በሬዎች መግዛትና የተበደሩትን ገንዘብ መክፈል ሲሆን፣ በየደረጃው ሌሎች እቅዶችም ነበሯት።
ሁሉም እንደታሰበው ሳይሆን ቀረና የኑሪያ ጓደኛ እዳ ተሸክማ ቤተሰቦቿ ዘንድ ገባች። በሬዎች የሉም፣ እዳ አልተከፈለም። አርሶ ለመብላትም አልተቻለም። ኑሪያ ስለ ጓደኛዋ ብዙ ተናግራለች። በኳታር ከምትኖር ሌላ ጓደኛዋ ጋር በመሆን የአቅሟን ለመርዳት ሞክራለች። ወደ ፊትም ከእህቶቿ ለይታ እንደማታያት ገልጻለች። መንገዱ ካለም “ከኢትዮጵያ የማይሻል ነገር የለምና እወስዳታለሁ” ብላለች።
የሚገርመው የኑሪያ ጓደኛ በህጋዊ መንገድ የላካት ድርጅት ዘንድ ስትሄድ የተሰጣት መልስ ነው። በስም የጠራችውና እሷን የላካት ሰው የለም። ድርጅቱ የጉዞ ወኪል ሆኖ ይሰራል። ሰውየው ግን የለም። ሌሎችም ተመሳሳይ ጥያቄ ለተመሳሳይ ድርጅቶች ያቀርባሉ። ላኪዎቹ የውሃ ሽታ ሆነዋል። መልስ የለም … እንቆቅልሽ!!
ባለኮብራዎቹ ሰው ነጋዴዎች
ባለ ኮብራዎቹ የጉዞ ወኪል ድርጅት ባለንብረቶች ናቸው። ለጸሎት ወደ ጅዳ የሚሄዱትን መንገደኞች በኮታ እየተከፋፈሉ የጉዞ ቲኬትና ማረፊያ በማዘጋጀት ብር ሲያመርቱ ኖረዋል። ከአንድ ሰው እስከ አምስት ሺህ ብር ድረስ ንጹህ ትርፍ ያተርፋሉ። ስለ ስራው የሚያውቁ “ዝርፊያ” የሚሉትን ስራ ህጋዊ ለማድረግ በማህበር ተደራጅተው ሊቀ መንበር፣ ምክትል ሊቀመንበር፣ ጸሐፊና ገንዘብ ያዥ፣ እንዲሁም የኦዲት ኮሚቴ አቋቁመው ኢህአዴግ ህጋዊ እውቅና አጎናጽፏቸዋል።
infinitiወደ ሳዑዲ ለጸሎት የሚደረገው ጉዞ እጅግ ከፍተኛ ገንዘብ የሚገላበጥበት በመሆኑ በማህበር የተደራጁት ነጋዴዎች ሳዑዲ ድረስ በመሄድ ለጸሎት የሚሄዱ ምዕመናን የሚያድሩበትን፣ ስለ አጠቃላይ የጉዞ ኮታና ስለ ጉዞ መስፈርቶች ከመንግሥት አካላት ጋር ይነጋገራሉ፤ ያቅዳሉ። አንዳንዴም የመጅሊሱን ስራ ይሰሩለታል። የኢህአዴግንም የውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ስራ ያከናውኑለታል። በዚህ ያልተገደበ የስልጣንና የስራ ደረጃቸው ባከማቹት ሃብት ተብለጭልጨዋል። የሚያሽከረክሩት ኮብራ ነው። አንዳንዶቹ ፊታቸው የሚፈርጥ ይመስላል። ኑሯቸው የተቀናጣ ሲሆን ከትምህርት ጋር ብዙም የሚዋደዱ አይመስሉም። የሃብታቸውን መጠን በልጆች ብዛት፣ በዘመናዊ መኪናና በሌሊት የዝግ ቤቶች በመመንዘር ከማሳየት የዘለለ የሚስብ ነገር የላቸውም። ሰውነታቸው ግዙፍና አብዝተው ጫት የሚጠቀሙ የሺሻ ወዳጆች ናቸው። ቢሯቸው ውስጥ ለእለት ጉርስ ሳይሆን “ሱስ” የሚሆኑ ቁሳቁሶች አሉ። በዚህ መካከል በድንገት በተደረገ የመጅሊስ ሹም ሽር መሰረታቸው ቆዳ ንግድ የሆነው ሃጂ ኤሊያስ ሬድዋን ወደ መጅሊስ ተመርጠው ገቡ።
ሃጂው ንግዱን ከውጪ ሆነው ጠንቅቀው ስለሚያውቁት የመጅሊሱን ወንበር እንደተቀመጡበት አፍታም ሳይቆዩ ዘመቻ “የጉዞ ወኪል” ጀመሩ። ጉዞ ወደ ጅዳ አድርገው ከሳዑዲ ባለስልጣናት ጋር መከሩ። አዲስ መስመር ዘርግተው መጡና ከማህበራዊ ጉዳይ ጋር ስትራቴጂ ነደፉ። ጎን ለጎን በዘመዶቻቸው ስም የጉዞ ወኪል ድርጅቶችን ከፈቱ።
ዳግም ወደ ሳዑዲ በመሔድ ራሳቸው በዘመድ አዝማድ ስም ከፍተዋቸዋል ለተባሉት ስምንት የሚደርሱ የጉዞ አመቻች ድርጅቶችና ቁጥራቸው በጣም ውስን ከሆኑ ሌሎች የቀድሞ ድርጅቶች በስተቀር የተቀሩት ተቀባይነት እንዳይኖራቸው በመጅሊሱ ሰም ከስምምነት ላይ ደረሱ። ሳዑዲ ድረስ በመሄድ ከመንግስት ባለስልጣናት ጋር ባካሄዱት የፊርማ ስምምነት የቀድሞዎቹን የንግዱ ፈጣሪዎች አራገፉዋቸው። ድርጊቱና ውሳኔው ድንጋጤ ፈጠረ።
በድንገት የገንዘብ ምንጫቸው የደረቀባቸው ባለኮብራዎቹ በግልና በድርጅት ተሯራጡ። ሃጂ ኤሊያስ ሙሉ የኢህአዴግ ድጋፍ ስለነበራቸው የሚነቀንቃቸው ጠፋ። አሸነፉ። ንግዱንም አስተዳደሩንም ተቆጣጠሩት። ያለ ከልካይ ብር ያመርቱ ጀመር። አምርተው የሚያቋድሱት የማይገፋ ሃይል ስላደራጁ እሳቸውን ለማሳጣት የሚደረጉ ሙከራዎች መዝናኛዎቻቸው ሆኑላቸው። በጉዳዩ ዙሪያ ሚዲያዎች ሲጠይቁዋቸው ያረገፉዋቸውን የቀድሞ ቱጃሮች አፈር ከመሬት እያስገቡ ከመናገር ውጪ አንዳችም ስጋት አልነበረባቸውም።
ባለኮብራዎቹ ገንዘብ በማፍሰስ ከዳር እስከዳር ቢሮጡም የሃጂ ኤሊያስን ሃይል መግፋት ተሳናቸው። ስልት በመቀያየር ሞከሩ አልሳክም ሲል ሁሉም ባይሆኑም አንዳንዶቹ ከባለ ጊዜዎቹ ጋር ሽርክና መስርተው ተገን በማግኘት ንግዳቸውን ለማስፋት ወሰኑ ። በዘመኑ ቋንቋ ድርጅታቸው ቀይጠው “ዲጂታል” ሆኑ። ሃጂ ኤሊያስ በተራቸው ተገዘገዙ። በመጨረሻም ኢህአዴግ በቃውና ከሃጂ ኤሊያስ ጋር የነበረውን ፍቅር ጨረሰ። ቀን ጠብቀው ሃጂ ኤሊያስን አሰናበቱዋቸው። በየአቅጣጫው ጠላት ያበዙት ሃጂ ኤሊያስ ከፍተኛ ሃብት ስላላቸው ከዛሬ ነገ ይከሰሳሉ ሲባል ሳይሆን ቀረ። እንደውም አክሲዮን ማህበር ከፍተው እየሰሩ ነው።
ዲጂታሎቹ የሰው ነጋዴዎች
በጉዞ አመቻችነት ስም ተደራጅተው ቀስ በቀስ ሰው መነገድ የጀመሩት “ዜጎች” ካዝናቸው ማፈስ የለመደውን ጥቅም ሲያጣ ሁሉም ባይሆኑም በከፊል መልካቸውን ቀይረው “ከባለ ጊዜዎች” ጋር በየፊናቸው ተጎዳኙ። ድርጅታቸውን ለጋራ ባለቤትነት መስዋዕትነት አቅርበው “ካድሬ ተኮር” አካሄድ ጀመሩ። ለከርሳቸው ሲሉ የካድሬ ሚና መጫወት ጀመሩ። አብረዋቸው በተቀናጇቸው የጊዜው “ፊት አውራሪዎች” አማካይነት “አብዮታዊ ዲሞክራሲያዊ” ስብዕና የተላበሱ “የሰው ነጋዴ ሆኑ” በሌላ ቋንቋ “ዲጂታል” ሆኑ።
ድህነት ካቃጠላቸው ወገኖች ላይ ገንዘብ ለመሰብሰብ እየተገለባበጡ ድፍን አረብ አገራት ሰራተኛ የማስቀጠር ህጋዊ ውክልና በአጋሮቻቸው አማካይነት ተረከቡ። ሃጂ ኤሊያስ የቆረጡትንና ወደ ራሳቸው ካዝና ያዞሩትን ንግድ መልሰው ገቡበት። ያልቻሉና በቀደመው “ያረጀ/አናሎግ” አካሄድ የዘለቁ የያዙትን ይዘው ተንጠባጠቡ። ቀደም ሲል ባከማቹት ሃብት ስራ ቀየሩ።AlAmoudi_Saudi
ስራው ከፍተኛ ገንዝብ የሚያስገኝና አንዳችም ኪሳራ ስላልነበረው የከፍተኛ ባለሃብቶችንም ቀልብ ስቦ ነበርና በዚህ ሁሉ ሂደት ውስጥ “የሰው ንግድን” ስራ በጅምላ ለመቆጣጠር የአብዮታዊ ዲሞክራሲን ስብዕና የተላበሱት በረጅሙ አቅደው ተንቀሳቀሱ። ከስራቸው ባሉት ጭፍራዎቻቸውና የአብዮታዊ ዲሞክራሲ አመራሮች ታግዘው ባደባባይ ከመንግሥት ጋር በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን ወደ ሳዑዲ ለመላክ ተፈራረሙ። አዲሱ ጠ/ሚኒስትርም ሳዑዲ 50ሺህ ሰራተኛ ሃይል ትፈልጋለች ሲሉ ተናገሩ። አቶ መለስ የጀመሩትን ለማስቀጠል ክርስቶስን ወደ ኋላ አድርገው የሚምሉት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝ ስራው በህጋዊ መንገድ እንደሚሰራም ወተወቱ።
ቅምጦቹን ሚዲያዎች ጨምሮ ሁሉም በየደረጃው ዜናውን አራገቡት። “የኢትዮጵያን ድህነት ታሪክ አደርጋለሁ” በማለት የሚወተውቱን ሼኽ መሐመድ አላሙዲ በስተመጨረሻ የሰው ንግድ ውስጥ መግባታቸው ታወጀ። “ዘመነ ዲጂታል”!! እርሳቸው በህግ ከገቡት ውል ጋር ተያይዞ ወደ ሳዑዲ የሄዱት ዜጎች ብዛት መረጃው ባይገለጽም ታይቶ በማታወቅ መልኩ ዜጎቻችን “ከአገር ውጡ” ተብለው ሲገደሉ፣ አስከሬናቸው አደባባይ ሲጎተት፣ ሴቶቻችን ሲደፈሩ፣ ወገኖቻችን ማጎሪያ ገብተው ሲሰቃዩ፣ ከሰብአዊነት ውጪ ሲሰቃዩ፣ የሰይፍና የካራ ስለት ሲሳልባቸው፣ የጦር መሳሪያ ሲሳብባቸው ለመጀመሪያ ጊዜ ተሰማ፣ ታየ፣ ተመሰከረ። ይህንን አስደንጋጭ ድርጊት ለመቃወም ወይም በህግ ለመጠየቅ አንድም በገሃድ ወጥቶ ሃላፊነት የወሰደ የንግዱ ተዋናይ አለመኖሩ ሃዘኑን ድርብ አደረገው። ቢያንስ እርሳቸው ይህንን ድርጊት በመቃወም ወይም ሃዘናቸውን በመግለጽ ግንባር ቀደም አለመሆናቸው በርካታ ጥርጣሬዎችን አነገሰ። ከሳዑዲ ጋር በተያያዘ ቀደም ሲል የሚነሱ ሃሜቶችን አስታወሰ። ዛሬስ ሳዑዲ ምን አዲስ ነገር አጋጠማትና ነው ወደ እንደዚህ ያለው አስከፊና አስነዋሪ ተግባር ለመሸጋገር የወደደችው?
ኢህአዴግ ስልጣን በያዘ ማግስት ጀምሮ
ኢህአዴግ ስልጣን በያዘ ማግስት ዜጎችን ለስራ ወደ ተለያዩ አረብ አገራት የሚልኩትን በማደን አከሰማቸው። በየመንደሩ በደላላ የሚሰሩትንና ቢሮ ከፍተው የሚንቀሳቀሱትን ህጋዊ ፈቃድ እንዲያወጡ በማወጅ ኢህአዴግ ንግዱን ወደ ራሱ ሰዎች በተለይም ለህወሃት ምርጦች አስተላለፈው። አዲሱን አሰራር ተከትሎ በቦሌ ቪላ ቤት ውስጥ በተከፈቱ ቢሮዎች ሰዎች አገራቸውን ጥለው ለመውጣት ለአይን የሚታክት ሰልፍ ያደርጉ ጀመር። ድሆች ተሰልፈው ተዘረፉ። ባደባባይ ህጋዊ ፈቃድ አላቸው የተባሉ ባለጊዜዎች ከድሃው ላይ በቀሙት ገንዘብ ኑሯቸውን አመቻቹ። ቀደም ሲል ቤህሩት፣ ኳታር፣ ዱባይ፣ ኩዌት፣ … ዘመድና ጓደኞች የነበራቸው በተባራሪ ጀምረውት የሰፋው የሰው ንግድ ኢህአዴግ ካስቆመውና በራሱ ሰዎች ከተካው በኋላ የተከለከሉት የቀድሞዎቹ ሰው ነጋዴዎች ለአዳዲሶቹ “ኩባንያዎች/ኤጀንሲዎች” ሰው አቅራቢ ደላላ ሆነው ማገልገል ጀመሩ። ደላላ መሆን ያልፈቀዱትም ለኢሚግሬሽን ባለስልጣኖች የደንቡን እየከፈሉ ስራቸውን ይሰሩ ቀጠሉ።
አገሪቱ ውስጥ በተፈጠረው የስራ እድል መመናመንና ወገን እየለየ የሚከናወነው የስራ እድል ተስፋ ያስቆረጣቸው እየበረከቱ በመሄዳቸው ኤጀንሲ ከፍቶ መስራት ታላቅ ቢዝነስ ሆነ። በዚህም የተነሳ ታዋቂ ሰዎችና የፖለቲካ ሹመኞች ከሰው ንግድ ጀርባ ሆነው መጫወት ጀመሩ። በእንዲህ መልኩ የመንግስት ከፍተኛ ሰዎች ያሉበት ዝርፊያ ተከናወነ። ሌቦቹም፣ ህግ አስከባሪዎቹም ራሳቸው ስለሆኑ ለህዝብ በደል ጆሮ የሚሰጥ ጠፍቶ የድሆች እምባ ተደፋና ቀረ።
በመርከብ ስራ እናስቀጥራለን በማለት የድሮው አውሮፕላን ማረፊያ የተሰራውን ድራማ ለአብነት እናንሳ። ቢሮው በአደባባይ ማስታወቂያ አስነግሮ ስራ ሲጀምር የድሃ ልጆች መርከብ ላይ ስራ እናገኛለን በማለት የሚያርሱበትን በሬ በመሸጥ፣ የእርሻ መሬታቸውን በማስያዝ ተበድረው፣ የቤተሰቦቻቸውን ንብረት ሸጠው፣ የሚፈለግባቸውን ከፈለው ተመዘገቡ። አስቀድሞ የህክምና ምርመራ ማድረግ ግዴታ ነው ተብሎ አንድ የግል ክሊኒክ ብቻ በመሄድ 500 ብር እየከፈሉ ከጉበትና ከሳንባ በሽታ ነጻ የሆኑበትን ማስረጃ እንዲያመጡ ተደረገ። አራት ጉርድ ፎቶግራፍ ያስፈልጋል በሚል አሁንም አንድ ቦታ ብቻ እየሄዱ 50 ብር እየከፈሉ ፎቶ እንዲነሱ ተደረገ። በጥቅሉ አንድ ሰው ገና ሳይመዘገብ 550 ብር ይከፍላል።
ማስታወቂያው የጨበጣ መሆኑ ሲታወቅ የድርጅቱ ባለንብረት ካገር ወጡ ተባለ። ጉዳዩ ሲጣራ 11 ሺህ የሚጠጋ ሰው በሰልፍ ከመመዝገቢያ ውጪ ለፎቶና ለሜዲካል ብቻ ከ6.5 ሚሊዮን ብር ገደማ ተሰብስቧል። የህክምና ክሊኒኩ ባለቤትና የፎቶ ቤቱ ባለቤት ስራ እናስቀጥራለን በሚለው የቁጭበሉ ድርጅት ውስጥ መስራች ናቸው።
ገንዘቡ ከተበላ በኋላ ድሆች የደም እንባ ሲያነቡ “ድርጅቱ ተዘግቷል። ሰውየው አገር ለቀው ወጥተዋል” ከመባሉ ውጪ የተወሰደ አንድም ርምጃ የለም። ገንዘቡን ከዘረፉት መካከል አሁንም ሹመት የሚፈራረቅላቸው አሉ። የሚገርመው ይህ ሁሉ ሲሆን ኢህአዴግ ደጅ፣ ኢህአዴግ አፍንጫ ስር፣ በራሱ አባላት፣ በራሱ ዳኞችና በራሱ የጸጥታና የፍትህ አስከባሪ ሃይሎች ፊት መሆኑ ነው። ከዚህ አንጻር ይመስላል በርካታ አስተያየት ሰጪዎችና የአረብ አገራት ሰለባ ከሆኑት መካከል ከኢህአዴግ “ተቆርቋሪነት አይጠበቅም” ሲሉ የሚደመጠው።
አስካሉካ ትሬዲንግ ደቡብ አፍሪካ ዓለም ዋንጫ ማየት ለሚፈልጉ እንደሚያመቻች ጠቅሶ በመንግሥትና በግል ሚዲያዎች ማስታወቂያ አስነገረ። አቶ ሳምሶን ማሞና ኢቲቪ ቅስቀሳውን ተያያዙትና የሰው ጎርፍ ከደቡብ ኢትዮጵያ ጎረፈ። በተለይም የሃድያ ዞን አስተዳደር ልዩ መድረክ አዘጋጅቶ ቅስቀሳው ተካሄደ። ዜጎች የመንግስት ሰዎችንና ሚዲያዎችን አምነው በሰው 32ሺህ 582 ከ65 ሳንቲም ከፍለው ተመዘገቡ። 1200 ሰዎች ይህንን ገንዘብ ገቢ አደረጉ። በዚህም 40 ሚሊዮን የሚጠጋ ገንዘብ ተሰበሰበ።wegagan
አሳዛኙ ጉዳይ ገንዘቡ ገቢ የሚደረገው የህወሃት ንብረት በሆነው የወጋጋን ባንክ ሲሆን፣ ከስራው በስተጀርባ “አንቱ” የሚባሉት የህወሃት ሰዎች አንዳሉበት የአደባባይ ምስጢር መሆኑ ነው። ቀበና በተከፈተው የአስካሉካ ቢሮ ሰዎች ጉዳያቸውን ለመከታተል ሲመላለሱ ጊዜ ነጎደ። ዓለም ዋንጫ ሲቃረብ የደቡብ አፍሪካ ኤምባሲ ተጠይቆ የሚያውቀው ነገር እንደሌለ አስታወቀ። አስካሉካም ግቢውን በፖሊስ እያስጠበቀ ገንዘባቸውን የዘረፋቸውን ለመመልከት ተጸየፋቸው። ሁከት ፈጣሪ ናቸው አስብሎ በፖሊስ አደባባይ ላይ አስደበደባቸው። ቀበናና የቀበና ጎዳና ይፍረዱት እንጂ ብዙ ግፍ ተሰራ። በተፈጠረው ሁኔታ የተደናገጡና ወፍጮ ቤት ውስጥ ተጠግተው ያድሩ ከነበሩት ዜጎች መካከል የአስካሉካ ባለቤት አገር ጥለው መጥፋታቸው ማስታወቂያውን በሰራው የመንግስት መገናኛ ይፋ ሲሆን ራሳቸውን ያጠፉ አሉ። ኢህአዴግና የፍትህ አካላቱ ከተቀሙት ንጹሃን ይልቅ ያለ አንዳች ብጣሽ የፈቃድ ወረቀት ድሆችን ሲዘርፍ የነበረ ማጅራት መቺ በልጦባቸው ድሆችን ቀጠቀጡ። ጎዳና ለጎዳና አሳደዱ። ሁሉም ነገር ታሪክ ከሆነ በኋላ ፖሊስና መንግሥት የአዞ እንባ አነቡ። የከረከሱ መኪናዎችና 5ሚሊዮን የሚሆን ገንዘብ ማገዳቸውን አበሰሩ። አቶ ግርማይ ገ/ሚካኤልንም ከተሰወሩበት ጀርመን አገር ለፍርድ አዲስ አበባ እንዳስመጣ አስታወቀ። ድሆች ግን ተዘርፈው ቀሩ። ለሞቱትም ነፍስ ይማር። ቂሙ ግን ቀን የሚቆጥር ነው።
ከድህነት በላይ ክህደት ያደቀቃቸው ዜጎች
በዱባይ፣ በኳታር፣ በኩዌት በሳዑዲ እና በተለያዩ የስደት ምድር ድህነትን ለማሸነፍና የመንግስት ሸክም ላለመሆን በሚንከራተቱ ወገኖች ላይ በተደጋጋሚ ለጆሮ የሚዘገንኑ በደሎች ተፈጽመዋል። ከፎቅ የተወረወሩ አሉ። በፈላ ውሃ የተቀቀሉ አሉ። በስለት የተወጉና የታረዱ አሉ። ማን እንዳደረገው ባይታወቅም የተሰቀሉ ጥቂት አይደሉም። በመርዝ ህይወታቸው ያለፈ … ተዘርዝሮ አያልቅም። ከሁሉም በላይeth saudi dubai ኤምባሲዋ በር ላይ ከለላ አገኛለሁ ያለች ወገናችን እንደ ውሻ እየተጎተተች ህይወቷ ሲያልፍ የሚያሳየውን ትዕይንት ለሚያስታውሱ ኢህአዴግ ድህነት በሚያሰቃያቸው ወገኖች ላይ በግልጽ ክህደት የፈጸመ ስለ መሆኑ ነው።
በሌላ በኩል ኢህአዴግ በተለይም ህወሃቶች በተመደቡበት የቆንስላ ጽ/ቤቶች፣ እንዲሁም ድንበር በማሻገር ህገወጥ ከሚሏቸው ስደተኞች ገንዘብ የሚያግበሰብሱ መሆኑ፣ በሌላ በኩል በርካታ ስራውን የሚሰሩ ኤጀንሲዎች የህወሃት ሰዎች መሆናቸው፣ በመንግስት ደረጃም ሰዎችን ወደ አረብ አገር ለመላክ በኦፊሻል የተዋዋለው ኢህአዴግ መሆኑ በየትኛውም ደረጃ በዜጎች ላይ ለሚደርሰው በድል ተጠያቂ ከመሆን እንደማያመልጥ የሚስማሙ ይበረክታሉ።
በሳዑዲ አረቢያ መከራ እየተጋፈጡ ያሉ ዜጎች ህገወጥ ይሁኑም ህጋዊ የስራ ተቀጣሪዎች አገር አላቸው። በጠመንጃና ደም በማፍሰስ በጉልበት የሚገዛቸውም ቢሆን አገራቸውን የሚመራ ድርጀትና “ጉልቻ” ፓርላማ አላቸው። በዘር እየለየ ድጋፍ የሚሰጥና ለወደፊቱ ቂም የሚያከማች ድርጅት ቢያረክሰውም የሚኮሩበት ባህልና ወግ አላቸው። ገንዘብ ካገኘ ገደል የማይታየው ኢህአዴግ ከድህነታቸው በላይ ክህደት ቢፈጽምባቸውም እጁን ዘርግቶ የሚቀበል ቤተሰብ ከድህነቱ በላይ ተካፍሎ መብላት የሚያስጨንቀው ማህበረሰብ አካል ናቸው።
ከድሆች ገንዘብ እየሰበሰቡ የሚንደላቀቁ ሁሉ በቅድሚያ ከራሳቸው ህሊና፣ ቀጥሎም ከተጎጂዎችና በዙሪያቸው ካሉ ወገኖች እንዲሁም አገር ወዳዶች የበቀል ቋት ውስጥ ከቶውንም አይወጡም። ኢህአዴግ በተለይም ህወሃት የተሸከመውን የነፍጥ ብዛትና የሰበሰበው የሃብት ክምችት ትምክህት ሆኖባቸው ወገኖቻቸው ላይ ለሚሳለቁ “ወዮልኝ” አብዛኞች እየራባቸውና ችግር እያዳፋቸው በጥጋብ ድሃው ህዝብ ላይ ለምታገሱ አሁንም “ወዮልኝ”። የበቀል ሽታው እየናኘ ነውና “ከወዮልኝ” እንድንሰወር ይሁን። አገር ውስጥ ያላችሁ የተቃዋሚ ፓርቲዎች አላችሁ? ኢህአዴግና ጭፍራዎቹ የደርግ ያበቃበት ዘመን ዛሬም ይመጣልና አስቡ። የመጣል ቀን ቀጠሮ የለውም። አሁን ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ካለው የሃዘንና የድህነት መጠን አንጻር የሚያጨካክነውን አስተሳሰብ ወደ መደጋገፍ ለመቀየር ትጉ!!the bees
አንድ አገር ያላት ዜጋ አደባባይ ተገድላ አስከሬኗ ሲጎተት፣ አንድ ወገንና አገር ያለው ጀግና ድህነት ክብሩን አሳጥቶት አስከሬኑ በስለት ሲወጋ ከማየትና አህቶቻችን ሲደፈሩ እየሰማ ቁጣውን በትዊተርና በፌስቡክ የሚገልጽ መንግስት ለዜጎቹ ማፈሪያ ነው። ይህንን ያህል ተለሳላሳሽነትስ መነሻው ምንድ ነው? ኢህአዴግ ልዩ በጥቅሙ ካልተነካ በስተቀር፣ ኢህአዴግ በተለይም ህወሃት የሚጎዳበት ነገር ከሌለ በስተቀር ሁሉም ሰላም፣ አገር አማን ነው ማለት ነውን? አገርን፣ ዜጎችንና ብሄራዊ ክብርን በጎጥ ሂሳብና በከርስ መጠን በመለካት መኖር መጨረሻ ላይ ዋጋ ያስከፍላል። ታሪክም የሚነግረን ይህንኑ ነው። ዳሩ ምን ያደርጋል ሌባ ሌባን አይከስ?

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

No comments:

Post a Comment