ቅርስም ሆነ ሌላ ነገር ከባቡር ተርሚናሉ ጋር የሚገናኝ ከሆነ (ይፈርሳል)-የአራዳ ክፍለ ከተማ አስተዳደር
“በቅርስነት ሊጠበቅ ሲገባው በድንገት ሊፈርስ ነው መባላችን አሳዝኖናል” የአካባቢው ነዋሪዎች
ከአዲስ አበባ ከተማ ምሥረታ ጋር ተያይዞ በቀደምትነት ከተመሠረቱ አካባቢዎች ቀዳሚነቱ የሚነገርለትና በተለምዶ “ውቤ በረሃ” በሚል መጠሪያ የሚታወቀው ደጃች ውቤ ሠፈር፣ በከፊል የሚፈርስ መሆኑ ለነዋሪዎች ተነገራቸው፡፡
በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ አምስት ንዑስ ቀበሌ 05 ከጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት ወደ አፍንጮ በር በሚወስደው መንገድ በቀኝ በኩል በ11.6 ሔክታር ቦታ ላይ ያሉ ነዋሪዎች እንደሚነሱና ከ100 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ሠፈር እንደሚፈርስ ለነዋሪዎቹ የተነገራቸው፣ መስከረም 11 ቀን 2006 ዓ.ም. በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት ለግማሽ ቀን በተደረገ ውይይት ነው፡፡
ከራስ መኮንን ድልድይ ወደ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን በስተቀኝ በኩል በሚያስወጣው አስፓልት እስከ አደባባዩ ድረስ የተገነቡ የመኖሪያ ቤቶች፣ የንግድ ቤቶችና የተለያዩ ቢሮዎች፣ ሆቴሎችና ምግብ ቤቶችን ጨምሮ እስከ አፍንጮ በር ድልድይ መዳረሻ ድረስ እንዲፈርሱ ምክንያት የሆነው፣ የባቡር ተርሚናልና ኃይል መስጫ ጣቢያ ሊገነባበት በመሆኑ እንደሆነ በሀገር ፍቅር ቴአትር ቤት በተደረገው የግማሽ ቀን ስብሰባ እንደተነገራቸው ነዋሪዎቹ ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡
ነዋሪዎቹ እንደገለጹት፣ በጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አደባባይ ፊት ለፊት ከሚገኙት ንግድ ቤቶች ጀምሮ ከሦስት ሔክታር በማይበልጥ ቦታ ላይ ያሉ ነዋሪዎች እንደሚነሱ ቀድመው ተነግሯቸዋል፡፡ መስከረም 11 ቀን አስቸኳይና ድንገተኛ ስብሰባ እንዳለና ማንም ቢቀር ኃላፊነቱ የራሱ እንደሆነ በማስጠንቀቅ ነዋሪዎች እንዲገኙ ከተደረገ በኋላ፣ በሰሙት ጉዳይ እጅግ በጣም መደንገጣቸውንና ማዘናቸውን አስረድተዋል፡፡
የባቡር ተርሚናልና ኃይል መስጫ ጣቢያ ግንባታ በሚል በዳር ያሉት እንደሚነሱ በቅድሚያ ከተነገራቸው በኋላ በድንገት “የሚያስፈልገው ስምንት ሔክታር ነው፡፡ የሚቀረው 3.6 ሔክታር ተቆርጦ መቀጠል ስለሌለበት ለመልሶ ማልማት መፍረስ አለበት፡፡ ይኼ ደግሞ ተወስኖ አብቅቷል” መባላቸው ተገቢ አለመሆኑንና ኅብረተሰቡን መናቅ እንደሆነ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
በቅርስነት ተጠብቆ መኖር ሲገባው እንደ መርዶ ነጋሪ በድንገት እንደሚፈርስ መወሰኑን ለነዋሪዎች ማርዳት ማን አለብኝነት ነው የሚሉት ነዋሪዎቹ፣ ከወረዳ እስከ ማዕከል ድረስ መረጃ በመጠየቅ በሁለትና በአራት ሚሊዮን ብር በቅርቡ ከሚፈርሱት ቤቶች ውስጥ የመኖሪያ ቤትና የንግድ ቤቶችን የገዙትን ለመጉዳት ሆን ተብሎ የተደረገ እንደሚያስመስለውም ጠቁመዋል፡፡
ነዋሪዎቹ እንደተነገራቸው ከሆነ፣ አስተዳደሩ ሁለት አማራጮችን አስቀምጦላቸዋል፡፡ የመጀመሪያው 20 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ በመፈጸም የጋራ መኖሪያ ቤት ማግኘት ሲሆን፣ ሁለተኛው አማራጭ የቀበሌ ወይም የኪራይ ቤቶች ተዘጋጅተውላቸው ወደዚያ መግባት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ አስተዳደሩ አስቀምጦላችኋል የተባሉትን አማራጭ ነዋሪዎቹ ተቃውመዋል፡፡ ምክንያታቸውም መንግሥት አቅማቸውን በማወቅ 20 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ ፈጽመው የኮንዶሚኒየም ቤት ባለቤት ለመሆን አምስት ዓመታትን መጠበቅ ግድ እንደሚላቸው ነግሯቸው፣ ተመዝግበው እየቆጠቡና እየጠበቁ መሆናቸውን ነው፡፡ ይኼ ሆኖ ሳለ በድንገት 20 በመቶ ክፍያ እንዲፈጽሙ መጠየቅ ተገቢ አለመሆኑን አውስተዋል፡፡
ደርግ እንኳን “ሠፈራ” በማለት ነዋሪዎችን ከቀያቸው ሲያስነሳ ባለአንድ ፎቅ ሕንፃ ገንብቶ በማስረከብ እንደነበር የሚናገሩት ነዋሪዎቹ፣ “ምን ያመጣሉ” በማለት ከአራት ወር በኋላ በጥር ወር ውስጥ ለዘመናት የኖሩበት ቤት እንደሚፈርስ ማሳወቅ ተገቢ ባለመሆኑ፣ መንግሥትም ሆነ የሚመለከተው አካል ለነዋሪዎች ክብር በመስጠት ነገሩን እንዲያጤነው ጠይቀዋል፡፡
የነዋሪዎቹን ቅሬታ በመግለጽ ማብራሪያ እንዲሰጡን ያነጋገርናቸው በአራዳ ክፍለ ከተማ የመሬት ልማት ማኔጅመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ሙሉጌታ፣ “አስተዳደሩ ወይም መንግሥት ማንንም መጉዳትና መበደል አይፈልጉም፡፡ የደጃች ውቤ ሠፈር ነዋሪዎች ወደ ሌላ አካባቢ እንደሚዛወሩ የነገርናቸው ተማሪዎችን ታሳቢ ባደረገ መንገድ ዕቅዳችንን ነው” ብለዋል፡፡
ነዋሪዎቹ በዋናነት እንዲነሱ የተነገራቸው መንግሥት እያስገነባው ላለው የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ከሚያስፈልጉት አራት ተርሚናሎች መካከል አንዱ ፒያሳ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ፊት ለፊት በቀኝ በኩል እስከ ደጃች ውቤ ሠፈር ስምንት ሔክታር ቦታ ላይ መሆኑን አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡ ጫፍ ላይ ላሉ ነዋሪዎች ቀደም ብሎ የተነገራቸውና ያወቁ ቢሆንም፣ ቀሪዎቹን ማወያየትና ማሳወቅ አስፈላጊ በመሆኑ መስከረም 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ማወያየታቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ መንግሥት ድርጊቱን እየፈጸመ ያለው ቅርስን ካለመፈለግና ነዋሪዎችን ከማፈናቀል አኳያ መታየት እንደሌለበት አስገንዝበዋል፡፡
ቅርስም ሆነ ሌላ ነገር ከባቡር ተርሚናሉ ጋር የሚገናኝ ከሆነ መፍረሱ የማይቀር መሆኑን የገለጹት ኃላፊው፣ እንዲፈርስ ውሳኔ የተላፈበት ቦታ 11.6 ሔክታር መሆኑንና ለተርሚናልና ለኃይል መሙያ ስምንት ሔክታር ተወስዶ ቀሪው 3.6 ሔክታር ለመልሶ ማልማት እንደሚውል አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡ ከባቡር ተርሚናል የሚተርፈው 3.6 ሔክታር ቦታ የግል ይዞታ ከሆነና በፕላኑ መሠረት ለመኖሪያ ቤት ወይም ለድርጅት የሚጋብዝ ከሆነ፣ ባለይዞታዎቹ እንዲያለሙት ቅድሚያ እንደሚሰጣቸው አቶ ግርማ ጠቁመዋል፡፡
“ማንም ነዋሪ እንዲንገላታ አንፈልግም፡፡ በፌዴራል አዋጅ ቁጥር 455/97 መሠረት ለልማት ለሚነሱ ነዋሪዎች ሁለት አማራጮችን እናቀርብላቸዋለን” ያሉት አቶ ግርማ፣ አንደኛው በቀበሌ ወይም በኪራይ ቤት የሚኖሩ ከሆነ ከስቱዲዮ እስከ ሁለት መኝታ ቤት የጋራ መኖሪያ ቤት እንዲያገኙና 20 በመቶ ቅድሚያ ክፍያ እንዲፈጽሙ ማድረግ ነው፡፡ ሁለተኛው አማራጭ ደግሞ በሌላ ቦታ የቀበሌ ወይም የኪራይ ቤት እንዲያገኙ ማድረግ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ ነዋሪዎቹ የኮንዶሚኒየሙን ቅድሚያ ክፍያ መንግሥት እንዲከፍልላቸው መጠየቃቸውን የገለጹት ኃላፊው፣ ጥያቄያቸው አግባብነት የሌለውና አሁን የሚኖሩት በትንሽ ክፍያ የነፃ ያህል መሆኑን፣ ቦታውና ቤቱም የመንግሥት በመሆኑ አቅም ከሌላቸው በመመርያው መሠረት በቀበሌ ቤት እንዲኖሩ እንደሚደረግ ገልጸዋል፡፡ ወደፊት በጋራ ሕንፃ ላይ መኖራቸው ስለማይቀር ያለዕጣ የማግኘት ዕድላቸውን እንዲጠቀሙ መክረዋል፡፡
የግል ይዞታ ያላቸው ነዋሪዎችን ለመለየትና ለማወቅ ትክክለኛው መረጃ ገና በመሰባሰብ ላይ ቢሆንም ከ105 በላይ እንደሚሆኑ የገለጹት ኃላፊው፣ እነሱም በአዋጅና በመመርያ ቁጥር 3/2002 መሠረት ሁለት አማራጮች እንደተዘጋጁላቸው ተናግረዋል፡፡ አንደኛ አማራጭ በመንግሥት መሬት ላይ የሠሩት ቤት ካሳ ተከፍሏቸው ኮንዶሚኒየም ቤት በቅድሚያ እንዲያገኙ ማድረግ ሲሆን፣ በሁለተኛ ደረጃ ካሳ ተከፍሏቸው በመሀል ከተማ ቦታ እንደሚሰጣቸው ወይም በማስፋፊያ አካባቢ እንዲመርጡ ማድረግ መሆኑን አቶ ግርማ አብራርተዋል፡፡ ነዋሪዎቹ በዚህ ዓመት መጨረሻ ሊነሱ እንደሚችሉ የጠቆሙት ኃላፊው፣ ምናልባት ነገሮች ከተመቻቹ በጥር ወር ሊያሸጋግሯቸው እንደሚችሉ በስብሰባ ላይ እንደነገሯቸው አስረድተዋል፡፡
ከቅርስ አጠባበቅ ጋር በተያያዘ ለተነሳላቸው ጥያቄ አቶ ግርማ በሰጡት ምላሽ፣ “አንዳንዶቹን ከቅርስ አኳያ የምናያቸው አሉ፡፡ በመመርያው መሠረት የሚሆነው ይሆናል፡፡ ለምሳሌ ያህል ዶሮ ማነቂያ አካባቢ እየተለዩ ነው፡፡ የባቡር ተርሚናሉና ኃይል መሙያው የሚሠራበት ከሆነ ግን ለድርድር አይቀርብም፡፡ ይፈርሳል፡፡ መታሰብ ያለበት ነገር ቢኖር ጊዜያዊውን ችግር ብቻ ሳይሆን ኅብረተሰቡ ወደተሻለ ሕይወት ማለፍ ስለሚኖርበት ነው” ሲሉ አቶ ግርማ ገልጸዋል፡፡
በደጃች ውቤ (ውቤ በረሃ) ሠፈር ከሚፈርሱት ቤቶች መካከል የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ዩኒቨርሲቲ ሲማሩ ይኖሩበት የነበረውና ከራስ መኮንን ድልድይ በስተቀኝ በኩል የሚገኘው ዓድዋ ሆስቴል፣ የታዋቂው አኮርዲዮን ተጨዋች አቶ ፍሬው ኃይሉ ቤት፣ የኢትዮጵያ ባለውለታ የነበሩትና በዳግማዊ ምኒልክ ዘመን ከቱርክ መሣሪያ በመግዛት ለኢትዮጵያ ያመጡ የነበሩት አርመናዊው ሚስተር ቴራዚያን ቤተሰቦች መኖሪያ ቤት፣ በቀይ ሽብር ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው አፈ ንጉሥ ተክሌ ቤት፣ በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን የነበሩት የጄነራል መልኬ ቤት፣ በደርግ ዘመን የዘመቻ መምርያ ኃላፊ የነበሩት ከበደ ስመኝ ቤት፣ በደርግ ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የነበሩት አቶ ቢልልኝ ማንደፍሮ ቤት፣ የመጀመሪያው ስፖርት ቤት መሥራች ሙሉ ስፖርት ቤት፣ የመጀመሪያው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በረኛ አቶ ታደሰ ጌጤ ቤት፣ የቡድኑ መሥራችና ተጨዋች የነበሩት አቶ አየለ አትናሸ ቤት ጥቂቶቹ ሲሆኑ፣ በአጠቃላይ ከ775 በላይ ቤቶች እንደሚፈርሱ ታውቋል፡፡ (ሪፖርተር)
No comments:
Post a Comment