Wednesday, September 11, 2013

የ፩ኛ ዓመት መልዕክት – የሚዲያ ተሃድሶ ግድ ነው!!


(ርዕሰ አንቀጽ - የ"ጋዜጠኛነት" ውንብድና ይቁም!!)

media


ዛሬ ጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ከተቋቋመ አንድ ዓመቱ ነው። ባሳለፍነው አንድ ዓመት ውስጥ የደገፉን፣ ያበረታቱን፣ አስተያየት በመስጠት ያረቁንና በመድረካችን የተሳተፉ ያሉትን ያህል የምንሰራውን ስራ ለመቆጣጠር፣ የተመሰረትንበትን ግልጽ መስመር ለማስቀየር የሞከሩና ጨዋነት በጎደለው መልኩ የተዛለፉም አጋጥመውናል። ለሁላችም እንኳን ለአንደኛው ዓመት አደረሰን!!
“ወፌ ቆመች በሉን” በማለት ከዓመት በፊት የሚዲያውን ሰፈር በአሃዱ ብለን ከተቀላቀልንበት ጊዜ አንስቶ የሰራነውን ስራ በጥሞና ለመመልከት ሞክረናል። ሌሎች ሚዲያዎችንና ብሎጎችንም ዳሰናል። የራሳችን ደካማ ጎን ስንፈትሽ እግረ መንገዳችንን ዙሪያችንን ስንቃኝ የሚዲያ ተሃድሶ (ሪፎርም) አስፈላጊ እንደሆነ ተረድተናል። አምነናል። “መቼ” ለሚለው ጥያቄ ምላሹ ዛሬ፣ አሁን፣ አሁኑኑ የሚል ነው።

ድክመታችን

ስንጀምር በዘረጋናቸው ዓምዶች መሰረት ጊዜ በመጠበቅ መረጃ በወቅቱ አላስተላለፍንም። የሳምንቱ አጫጭር ዜናዎችና ድንቃ ድንቅ ወሬዎችን የምናቃምስበት የጎልጉል ቅምሻ ዓምድ በጀመርንበት አቅም መቀጠል አልቻልንም። የግጥም ጨዋታን በተከታታይ አላቀረብንም። ጦማሮች ሲላኩ ፈጥነን ያለ መለጠፍ ችግር አለብን። እነዚህ ከድክመቶቻችን መካከል በቅድሚያ የሚጠቀሱ ናቸው። ምንም እንኳን ስራችንን የምንሰራው በበጎ ፈቃደኞች በትርፍ ጊዜ ቢሆንም በግምገማችን በድክመት አስቀምጠነዋል። አንባቢዎችንንም ይቅርታ እንጠይቃለን።

ያጋጠሙ አንኳር ችግሮች

የተሳሳተ መረጃ በመላክ ታማኝነታችንን ለማሳጣት በተደጋጋሚ ሙከራ ተደርጓል። “እነማን ናቸው፣ ከየት መጡ፣” በሚል አጀንዳ ይዘው የተወያዩ አሉ። ማንነታችንና፣ ምንነታችንን እንድናብራራ በደብዳቤ የተጠየቅንበትም ጊዜ ጥቂት አይደለም። የኤዲቶሪያል ፖሊሲያችን ከሚፈቅደው ውጪ በዘለፋ የተሞሉ ጽሁፎች በመላክ እንዲስተናገድላቸው የወተወቱን በርካታ ናቸው። በቀጥታ በአድራሻችን የማይላክልንን ጽሁፍ ስለማናስተናግድ /ወደፊትም አናስተናግድም/ ወደ አንድ መንገድ ሊያጠጋጉን የሞከሩ አንቱና አንተ የሚባሉ አጋጥመውናል። ከሁሉም በላይ በተደጋጋሚ የጋዜጠኛነት ውንብድና ተፈጽሞብናል። ይህ መረን የወጣ ችግር ማቆሚያ ሊበጅለት እንደሚገባ አጥብቀን እናምናለን። ለሙያውና ለስነምግባሩ የሚገዙ በዚህ ሃሳባችን ድጋፍ እንደሚሰጡን እናምናለን።

የሚዲያዎች ሪፎርም ለምን?

በበርካታ ሚዲያዎች እኛን ጨምሮ ህዝብን የማስተማሩን አብይ ተግባር በሚጠበቅብን መጠን የተወጣነውና እየተወጣን ያለን አይመስለንም። “ነጻና ገለልተኛ ሚዲያ አለ” ለማለት ባያስደፍርም ጭፍን ድጋፍና ውዳሴ ዞሮ አደጋው የከፋ እንደሚሆን ልምዳችን ይነግረናል። ህዝብም ይህንኑ ችግር ጠንቅቆ ያውቃል። ሚዲያዎች ሃሳቦችን በማመንጨት፣ ከህዝብ የሚነሱ ጥያቄዎችን በማንሳት፣ አጀንዳ በመቅረጽ፣ የክርክር መድረክ በመፍጠር ፖለቲከኞችን፣ አደረጃጀታቸውን፣ አመራራቸውን፣ ቃላቸውን፣ ተግባራቸውን፣ ራዕያቸውን፣ ግባቸውን፣ ለዴሞክራሲ ግንባታ ያላቸውን የተስፋ መጠን በመመርመር፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ ነጻ የህዝብ አንደበትና መድረክ በመሆን ልናገለግል ይገባል። ከዚህ አንጻር ሲታይ አሁን ያለንበት ደረጃ “ገና ብዙ ብዙ … ” የሚለውን ዜማ ከማዜም የዘለለ አይሆንም።
ሁሉም ወገኖች እንደሚረዱት ድረገጾችና ብሎጎች ሞልተው ፈሰዋል። አባዛኛዎቹ ሙሉ በሙሉ ማለት እስከሚቻል ድረስ ጽሁፍ መዋዋስና መቀራመት ላይ ያተኮሩ ናቸው። ቢያንስ ቢያንስ ርዕሰ አንቀጽ እንኳን በወጉ በማዘጋጀት አቋማቸውን ለማስቀመጥ ሲቸገሩ ይታያሉ። የራሳቸውን ሃሳብና ጥረት የታከለበት ስራ በመስራት የተመጣጠነ ሪፖርት ማድረግ ተስኗቸዋል። የሪፖርት ስራ ለጋዜጠኝነት የጀርባ አጥንቱ ቢሆንም ጽሁፍ ወደ መዘራረፍና የጋዜጠኛነት ውንብድና ተዛውረናል። በዚሁ የጽሁፍ “ጠለፋ” ሳቢያ የብዕር ባለቤቱና የድርሰቱ ዋና ጌታ ተለይቶ የማይታወቅበት ጊዜ ላይ ደርሰናል።
የብሎግና ድረገጽ ባለቤት በመሆን በጋዜጠኛነት ስም ምንም ልፋት ያላደረጉበትን የሌሎች ጽሁፍ ለመለጠፍ የሚጣደፉ መበራከታቸው ያስደነግጠናል። አዲስ መረጃ ወይም ዜና ሲሰማ ለመቀራመት ያለው ፍጥነት ጽሁፉን በቅጡ አንብበው ስለመቀራመታቸው ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። በሚገርም ሁኔታ ስህተትና የፊደል ግድፈት ሳይቀር እንዳለ የሚገለብጡና በራሳቸው ገጽ ላይ የሚለጥፉ ጥቂት አይደሉም። ከሁሉም በላይ ከሰው ለወሰዱት ጽሁፍና መረጃ በቂ እውቅና ሳይሰጡ የራሳቸውን የግል ፎቶ በመለጠፍ ለራሳቸው የባለቤትነት ማዕረግ የሚሰይሙትን ስንመለከት ድንጋጤያችንን ወደ ፍርሃት ይቀይረዋል። ህዝብ ከሚዲያ ስለመማሩና እንዲማር የማድረጉ ስራ አደጋ ላይ ስለመሆኑ ይሰማናል። ደረጃው ይለያይ እንጂ በዚህ መልኩ የጋዜጠኛነት ወሮበላነት ሁሉም ደጅ አለ። እኛም በተደጋጋሚ ዝርፊያው ተከናውኖብናል፤ አሁንም እየተከናወነብን ይገኛል። ማስተካከያ እንዲደረግ የተላላክናቸው መልዕክቶች በመረጃ ተቀምጠዋል።
ይህንን ስንል ጽሁፍን መዋዋስና በጨዋነት መጋራት የተከለከለ ነው ለማለት አይደለም። በጣም ውሱን ከሆኑት በቀር አድፍጦ መቀራመትና ጽሁፍ መዝረፍ በዛ፣ ልክ አጣ፣ ገደብ ይደረግለት፣ ለመረጃው ባለቤት አስፈላጊው እውቅና ይሰጠው፤ ቢያንስ ምንጩ ይጠቀስ፤ ሥርዓት ይጠበቅ ነው የምንለው። ከመቀራመት በዘለለ ሚዲያዎች የራሳቸውን ወጥ ስራ ለመስራት ይነሳሱ፣ የተለያየ አይነት ያቅም ችግር ቢኖርም ጥረቱ ይጀመር ለማለት ነው። የሚዲያዎች ተሃድሶ ያስፈልጋል የምንለውም ለዚህ ነው። አንባቢም ተቃውሞውን መግለጽ አለበት። አንባቢዎች መረጃ ሲቀበሉ እንዲህ ያሉትን የጨዋነት ጥያቄዎች የማንሳት ግዳጅ ሊኖራቸው ይገባል። ትክክለኛ መረጃ ከሚጠሉትና ከሚጠየፉት ሚዲያም ሊያገኙ ስለሚችሉ ብዙ ጊዜ ከስሜትና ከፍረጃ ራሳቸውን ነጻ ቢያደርረጉ የተሻለ ነው ለማለት እንወዳለን። አንባቢያን ይህንን ቢያደርጉ ሚዲያዎች ራሳቸውን ለተሃድሶ ፈጥነው ያዘጋጃሉና!!

በመጨረሻ

በአንድ ድፍን ዓመት ቆይታችን የተረዳነው ከራሳችን ጀምሮ በርካታ ችግሮች ያሉበትን የመረጃ መቀያየሪያ መድረክ ከችግሩ እንዲድን አስቀድመን ቃል መግባት ያለብን ራሳችን ነን “ጋዜጠኛ” የምንባለው እኛ “ጋዜጠኛ” የሚለውን ስም ከወሰድን በኋላ እየረበሽን፣ እየበጠበጥንና ህዝብን “በኩረጃ” ዘገባና በጋዜጠኛነት ውንብድና ለማንቃት የምንተጋ ከሆን ራሳችን እስከ ማቀብ የሚያደርስ ውሳኔ መወሰን ይጠበቅብናል። “እኔ እየረበሽኩ ነው፤ ከዚህ ቦታ መውጣት ይገባኛል” ማለት በራሱ ታላቅ ክብር የሚያሰጥ ተግባር ነውና ለሪፎርም ራሳችንን እናዘጋጅ። ከሚዲያዎች ብዙ ይጠበቃልና የወደፊቱን አሻግሮ በመመልከት ለመስራት ለሚተጉት ደግሞ አንባቢዎች አስፈላጊውን እውቅናና ክብር በመስጠት ለሪፎርሙ ተግባራዊነት ድምጻችሁን አሰሙ። መልካም አዲስ ዓመት!! አዲስ የሚዲያ ተሃድሶ ዘመን!!

ይህ ርዕሰ አንቀጽ የ“ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ®” አቋም ነው፡፡

No comments:

Post a Comment