Wednesday, September 11, 2013

በ2005 እንዲህ ብለን ነበር!


ከማበስበሻው ባህር የሚወጣ የለም- ይሰፋል እንጂ

difo


በአዲሱ ዓመት የተመሰረትንበትን አንደኛ ዓመታችንን ምክንያት በማድረግ በተለያዩ ወቅቶች ለንባብ ካበቃናቸው ርዕሰ ጉዳዮች መካከል መርጠን ለትውስታ አቅርበናል። ካቀረብናቸውም ሆነ በድረገጹ ላይ ያሉትን ጽሁፎች በመምረጥና በማሰራጨት ልደታችንን ታከብሩልን ዘንድ ግብዣችን ነው።
በሌላ በኩል የዝግጅት ክፍላችን ኤዲሪቶሪያል ቦርድ አንባቢዎች በነጻነት አስተያየት እንዲሰጡ፣ አስተያየታቸውም ያለ አንዳች ገደብ እንዲታተም ወስኗል። በመሆኑም ጎልጉልን አስመልክቶም ሆነ በርዕሰ አንቀጽ ላይ ባስቀመጥነው ሃሳብ ላይ በመንተራስ አስተያየት ለምትልኩ “ከስድብና ከዘለፋ” ውጪ በደስታ የሚስተናገድ እንደሆነ አስቀድመን እንገልጻለን። የዓመቱ ምርጥ በማለት “መለስ የቆፈሩት ጉድጓድ” እና “ጥቁሩ ሰው ይናገራል” የሚሉትን ቃለ ምልለስሶች በስጦታ አቅርበናል። መልካም አዲስ ዓመት፣ ለኛም መልካም አንደኛ ዓመት!!
አዲሱ ዓመት ፍትህ የሰፈነበት እርቅ የሚከናወንበት ይሆን ዘንድ እንመኛለን።
የትግራይ ህዝብ ስማ
“ሰሞኑን በውዴታም ይሁን በግዴታ በመቀሌ እጅግ ከፍተኛ የሚባል ቁጥር ያላቸው የትግራይ ተወላጆች ሲጨፍሩ፣ ሲዘሉ፣ ከበሮ እየመቱ የባህላቸውን ዘፈንና ውዝዋዜ ሲያወርዱ አይተናል። ምክንያቱ በግልጽ ባይነገርም ሲደበቅ የነበረው የህወሃት ሃብትና ንብረት ውጤት የሆኑ፣ በልዩ የመንግስት ድጋፍ የተከናወኑ ግዙፍ ተቋሞች በጎዳና ለህዝብ ሲቀርቡም ተስተውሏል። ልማቱ መልካም ነው። ደስ ይለናል። ምንም ተቃውሞ የለንም። ግን መልዕክት አለን። ለማን?ምሬትን፣ ጭቆናና መንገፍገፍ ሲበዛ በፍቃደኛነት በቦንብ ላይ እንደሚያስሮጥ ለሚያውቀው የትግራይ ህዝብ!! የትግራይ ህዝብ ስማ!!
… “የ100 ዓመት የቤት ስራ ሰጥተናቸዋል” በሚል በየድረገጹ የሚለጠፉ ተራ ድንፋታና ትዕቢት የሚፈጠሩትን ሓውዜኖች ከማብዛት ውጪ ትርፍ የላቸውምና ወደ ደጉ መንገድ መመለስና ሰብዓዊነትን በማስቀደም፤ ተደጋግፎ መኖርን ማጎልበት ይሻላል ለማለት እንወዳለን። ተሳስበውና ተረዳድተው የሚገነቡት የትም ሆነ የት የአገር ነውና ሁሉም ይኮራበታል፤ ይጠብቀዋል። ተጠቃሚ ይሆንበታል። የሚያምርብንም ይህ ነው። ህወሃት አልሰማም ብሏል። የትግራይ ህዝብ ግን ስማ!! ይህ ሁሉ የሚደረገው በስምህ ነው!! …

ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ
ቤት መኖሩን እንመን፤  ከዚያ እንግባ!!
… ኢትዮጵያ ጠላት አይደለችም፡፡ ሰንደቅ ዓላማዋም ጨቋኝ አይደለም፡፡ አረንጓዴ፣ ቢጫ፣ ቀይ ከኢትዮጵያ አልፎ የአፍሪካና የመላው ጥቁር ሕዝብ በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ መለያ ሆኗል፡፡ ይህም የሆነው በአድዋ ድል ነው! አጼ ምኒልክን ንጉሣችን እንዲሆኑ አልመረጥናቸውም፤ ምርጫውም አልነበረም፡፡ የአድዋን ጦርነት ግን መርተዋል፡፡ በእርሳቸውና በሌሎች እጅግ ቆራጥ በሆኑ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ምክንያት “… አበሻ ግብሩ እንቁላል” ከመሆን ድኗል፡፡ ድሉ የኢትዮጵያ ነው፤ ሲቀጥልም የአዝማቹና የዘማቹ፡፡ ጦርነቱ በኢትዮጵያ ሽንፈት ቢጠናቀቅ ኖሮ ምኒልክን “አዋርደን” በታሪክ ከመጥቀስ አንቆጠብም ነበር፡፡
ባለፈው ምርጫ በዘርና ጎሣ ተከፋፍለው ደም ለመፋሰስ የበቁት ኬንያውያን ልዩነታቸው እንዳለ ሆኖ ሰሞኑን በተከናወነው ምርጫ ግን “ሁላችንም ራሳችንን ኬንያውያን ብለን በመጥራት እንኮራለን” ሲሉ የሰማን ጊዜ እኛስ የአመለካከት ልዩነታችን እንዳለ ሆኖ፤ ሁሉ ቀርቶ ታላላቅ ድሎቻችን ላይ ከፖለቲካና ግላዊ አመለካከት በላይ በመሆን “ኢትዮጵያውያን ብለን ራሳችንን በመጥራታችን ኩሩዎች ነን የምንል” በማለት እንድንጠይቅ ተገደድን፡፡ አውሮጳውያን በቅኝ ከያዙትና ለመያዝ ካሰቧቸው አገሮች የዘረፉትን “የ … ሙዚየም” እያሉ እንደራሳቸው ቅርስ ሲያሳዩና በየአደባባይ እያቆሙ ለትዕይንት ሲያበቁ እኛ ግን ዓይናችን ሥር ያለውን የራሳችን ለማድረግ አቅቶናል፡፡ ቤታችን አልገባንም፤ ምክንያቱም ቤት እንዳለን ከልብ አላመንንም! …
ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ
የ“አምላካችሁ ባሮች” የሆናችሁ “ሰላማዊ ሰልፈኞች” ቅድሚ የምትሰጡት ለማን ነው?
የሃይማኖት አክራሪነትንና ጽንፈኝነትን ብቻ ሳይሆን በነጻ አውጪ ስም የመንግሥት ሥልጣን ይዞ አገርን ላለፉት 22ዓመታት ሲያሸብር የኖረውን አክራሪውና ጽንፈኛውን ህወሃትን ራሱን እስካሁን የረገጥከው ሰብዓዊ መብት ይበቃሃል በማለት ሃይማኖታዊ ድርሻችሁን ተወጡ፡፡ የሰላም አስጠባቂ፣ የፍትህና የሰብዓዊ መብት አስከባሪ ካድሬ ሁኑ፡፡ በምድር ላለው ኑሮና ተድላ ሳይሆን ለመጪው ዓለም አማኞች እንዲያስቡ የምትሰብኩትን እስቲ ለአንድ ጊዜ ራሳችሁ ኑሩበትና ይህንን የሕዝብ እሮሮ በማሳወቅ ከዚህ ምድር አስተሳሰብ የላቃችሁ መሆናችሁን አሳዩ፡፡ መስዋዕትነት የሚያስከፍል ከሆነም ምዕመኖቻችሁን እንዳስተማራችሁት እናንተም ለተግባራዊነቱ በዝግጅት ቁሙ!
ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ
“መለስ የቆፈሩት ጉድጓድ…”
… ኢህአዴግ በሰበሰ ስንል ሰዎቹን እንጂ ሌላ ግዑዝ ነገር ባለመሆኑ በመበስበስ ባህር ውስጥ እየዋኙ አሉ። ከዚህ ባህር መውጣት አይችሉም። ልክ እንደ እውነተኛው አሳ እነዚህ ሰዎች ከበሰበሱበት ባህር ውስጥ ከወጡ ስለሚሞቱ ባህሩን ከማስፋት ውጪ ሌላ አማራጭ የላቸውም። የበስብሶ ማበስበሱ ዋና አላማ በበሰበሱበት መጠን አሽከር በመሆን የታዘዙትን ሁሉ ያለማቅማማት እንዲያከናውኑ ማድረግ ነው። ግደሉ ሲባሉ ይገላሉ። ቤተሰብህን አሳልፈህ ስጥ ሲባሉ ይስማማሉ። ከሰውነት ባህሪያቸው አርቀዋቸው እቃ አድርገዋቸዋል። ትንሽ ካፈነገጡና ሰላምታቸውን እንኳ ከቀየሩ ፋይላቸው ይከፈትና ራሳቸውን አዋርደው ይጣላሉ ወይም ይሰወራሉ። ራሳቸውን በድርጅት ግምገማ አባላትና ከፍተኛ አመራሮች ፊት “እኔ ጸረ ህዝብ ነኝ” ብለው ይረግማሉ። የሚገርመው …
… ራሱን ባመመው ቁጥር ፓናዶል መዋጥ የለመደ ሰው ያለ ፓናዶል ጤና አይሰማውም። ፓናዶል ከሌለ ራሱን ያመዋል። ፓናዶል በአገሪቱ ከጠፋ ችግሩ ይባባሳል። አቶ መለስ ለህዝብ ሳይሆን እሳቸው በፈጠሩት የበሰበሰ ባህር ውስጥ ላሉት ሁሉ እንደ ፓናዶል ይመሰላሉ። መለስ አንድ ነገር ከሆኑ ወይም መለስ አናት ላይ በቀድሞው ሃይላቸው መቀመጥ ካልቻሉ የሚታመሙ ብዙ ናቸው። ይህ አደጋ መተራመስ ይፈጥራል። እርስ በርስ እንተዋወቃለን። አሁን እንግዲህ ሁሉም ነገር አብቅቷል። መለስ አልፈዋል። ተቀብረዋል። አሁን የምናወራው ስለቀጣዩ ነው። መለስ አደጋ ውስጥ የመቆየታቸው ጉዳይ አብቅቶለታል …
… አቶ መለስ የቆፈሩት ጉድጓድ በጣም ትልቅ ነው። እስካሁን የገባበት የለም። አፉን ከፍቶ የሚጠብቀው። ጉድጓዱ የሚውጠውን አሰፍስፎ እየጠበቀ ነው። በስብሶ ማበስበስ የመለስ ፍልስፍና ውጤቱ አፉን የከፈተውን ትልቅ ጉድጓድ መሙላት ነው። በነገራችን ላይ እነዚህ ሃብታሞች ናቸው ስርዓቱን በስለላና የተቃዋሚ ወዳጆችን በማባበል መረጃ በማሰባሰብ የሚያገለግሉት። የኪነት ሰዎችን በኮንሰርትና በበዓላት እያሳበቡ ኢህአዴግ ጉያ ውስጥ በመክተት ህዝብ የሚወዳቸውን ሰዎችና ባለሙያዎች የሚያዋርዱት። ታዋቂ ሰዎችና የሚወደዱ ባለሙያዎች የበሰበሰውን ሰፈር ሲቀላቀሉ ህዝብ ተስፋ ይቆርጣል። ሌላም ብዙ ስራ አላቸው …
ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ
ጥቁሩ ሰው” ይናገራል
ጎልጉል፦አቶ መለስ በህይወት እያሉ ስለተጨቆኑና ስለተረገጡ ህዝቦች ሲሉ መታገላቸውን በተደጋጋሚ ይናገሩ ነበር። ባንተ አመለካከት ዋናው ስህተታቸው ምኑ ላይ ነው?
ኦባንግ፦አቶ መለስ ህወሓትን ከፊት አድርገው አዲስ አበባ ሲገቡ እውነተኛ ብሔራዊ እርቅ አድርገው ቢሆን ኖሮ ዛሬ ተገፍተን በስደት ያለን ሁላችን በየሙያችን አገራችንና ወገኖቻችንን እናግዝ ነበር። የሆነው ግን የተለየ ነው። መለስ “እነሱ” ብሎ ሌሎችን በመወንጀል ጥላቻን ማወጅ ጀመረ። ትውልድን የሚያንጽ ብሄራዊ ሚዲያ ሳይቀር የጥላቻና የቂም ስብከት እንዲያስተጋባ ተደረገ። የዚህ መዘዝ ዛሬ ላይ ጣለን። የጋራ ንቅናቄያችን “እነሱ” የሚል ቋንቋ የለውም። ስንጀምር “እኛ” ብለን ነው። ይህ ልዩ ያደርገናል። የሰው ልጆች ጥላቻን ለመሸከም አይመጥኑም። ጥላቻ የሚዘራብን እንደሰው ስለማንታይ ነው። እንደ ሰው ስላልተከበርን ነው። ሰው መልካም ነገር እንዲያደርግ ከፈጣሪ የተሰጠው ልዩ ስጦታ አለው፡፡ መለስ ግን ይህንን ረስቷል። በብሄር ብሄረሰብ ስም ሲምል ሁላችንንም ሳያሳፍር ነው። ብቻውን ወይም ጥቂት ሰዎች ይዞ ወደ ጥፋት ሄደ፤
ጎልጉል፦ “መሳፈር” ብታብራራልኝ?
ኦባንግ፦ በምሳሌ ልግለጸው። ምሳሌው ለመለስ ብቻ አይደለም። ለሁላችንም የሚሆን ነው። አውሮፓና አሜሪካ ወይም ባደጉት አገሮች ተማሪዎች የጉብኝት ጉዞ አላቸው። ለጉብኝት ሲነሱ አውቶቡስ ይቀርባል። አወቶቡሱ እንደቀረበ ቀድመው የሚገቡት ተማሪዎች ናቸው። ተማሪዎች ገብተው ሲያልቁ አስተማሪዎቹ ይቆጥሯቸዋል። ሁሉም መግባታቸውን ካረጋገጡ በኋላ አስተማሪዎቹ ተሳፍረው ሾፌሩን አውቶቡሱን እንዲያንቀሳቀስ ይነግሩታል። አስተማሪዎቹ ተማሪዎቹን ቅድሚያ ሰጥተው ማስገባትና የተባለው ቦታ ድረስ የማድረስ ሃላፊነት አለባቸው። ጉብኝቱም ካለቀ በኋላ ሁሉም   ተማሪዎች አውቶቡስ ውስጥ ተመልሰው ሳይገቡ አውቶቡሱ ዝም ብሎ አይነሳም። ሁሉም ተማሪዎች መኖራቸውና ማንም እንዳልቀረ ደግመው ደጋግመው ያረጋግጣሉ። እንደመጀመሪያው ሁሉም ተማሪዎች መሳፈራቸው ሲረጋገጥ አውቶቡሱ እንዲንቀሳቀስ ለሾፌሩ ያስታውቃሉ።
ጎልጉል፡- ታዲያ ከዚህ ምሳሌ የምንማረው ምንድነው?
ኦባንግ፡- የምንማረውማ አውቶቡሱ አገር ነው። ተማሪዎቹ ህዝብ ናቸው። እንግዲህ መለስ አገር ሲመራ ሁላችንንም ቆጥሮና መሳፈራችንን አረጋግጦ መሆን ሲጋባው ብቻውን ተሳፍሮ ሌሎች የሚፈልጋቸውን ጨምሮ ቆለፈብንና ብቻውን ነጎደ። አንዳንድ የሚጠቅሙትን ከጎኑ አደረገ። በመሪያችን ያልተቆጠርን በዛን። አታስፈልጉም የተባልነው በለጥን። የተቆለፈብንና የጉዞው ተመልካች የሆን ከልክ በላይ ሆንን። መለስ ካለፉት ስርዓቶች ትምህርት ተምሮ ጉዞውን አንድ ላይ በእርቅና በፍቅር ሊያደርገው ይችል ነበር። መለስ ተገፍቻለሁ ብሎ በረሃ ገባ። ከበረሃ ሲመለስና መሪ ሲሆን እኔንና እኔን መሰል ወገኖችን ገፋንና ከአውቶቡሱ ውጪ አደረገን። ሳንቆጠር የቀረን በሙሉ ሌላ አውቶቡስ ፍለጋ ተሰደድን፤ አሁንም እየተሰደድን እንገኛለን፡፡ በመለስ አውቶቡስ የሚቆጥረን ስላልነበረ ሌላ የሚቆጥረን እንፈልጋለን፡፡ ዛሬም ተመልሰን ይህንን ለመድገም መስራት ያለብን አይመስለኝም። አንዱ ሌላውን እየገፋ በበቀል ታሪክ መሄድ መቆም አለበት። ይህ የእኛ ትውልድ ቢያንስ ቢያንስ ይህንን ማድረግ አለበት። መለስ አልቆጠረንም ብለን የራሳችንን አውቶቡስ ይዘን ከመሄድ ይልቅ መጀመሪያ ወገናችንን እንሰብስብ፤ እንቁጠር፡፡ በተራ ብልጣብልጥነትና በተንኮል ሳይሆን በቀናነት!! ቀናነት!! ቀናነት!! …
ጎልጉል፦“ጥቁሩ ሰው” የሚሉህ ለምንድነው? ስሙ ተስማምቶሃል? ወይስ ……
ኦባንግ፦(ሳቀ!!) ቀለሜ ጥቁር ነው። ጥቁር ሰው ነኝ። በትክክለኛው ቀለሜ ተጠራሁ። ቀናህ እንዴ … !? (በፈገግታ ድምጽ)
ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ
በአልቃይዳ ሰበብ ቻይናን መቆጣጠር
የኦባማ አስተዳደር መጪው የአፍሪካ ዕቅድ
የአገራቸውን አጠቃላይ ሁኔታ እና መጪው ጊዜ ምን እንደሚመስል፤ የአገራቸውን የወደፊት የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ፣ የማኅበራዊ፣ … ሁኔታ እንዲሁም አሜሪካ በቀጣይ ዓመታት የምትከተለውን የአጭርና የረጅም ጊዜ የውጪ ፖሊሲ ዕቅድ በተመለከተ ለሁለተኛ ጊዜ ከተመረጡ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ማክሰኞ ምሽት ለምክርቤቱ ንግግር ያደረጉት ፕሬዚዳንት ኦባማ በርካታ ጉዳዮችን ዳስሰዋል፡፡ አፍሪካና ቻይናም የንግግራቸውን ሙሉ ቀልብ የሳቡ ነበሩ ባይባልም ሳይጠቀሱ አልታለፉም፡፡…
… በቅርቡ ከውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት ሥልጣን የለቀቁት ሒላሪ ክሊንተን በአንድ ወቅት ሲናገሩ ‹‹የእስያን ዕድገትና ታታሪነት መግታት የአሜሪካ ቀዳሚ የኢኮኖሚና የስትራቴጂ ፍላጎት ነው›› ብለው ነበር፡፡ በዚህ ንግግራቸው ‹‹እስያ›› ብለው በደፈናው ይጥቀሱት እንጂ ዋንኛ የንግግራቸው ዓላማ ቻይና ላይ ያተኮረ እንደሆነ በርካታ የአሜሪካንና የቻይናን የበላይነት እሽቅድምድም የሚያጠኑ የሚናገሩት ነው፡፡…
በአሁኑ ወቅት ቻይና ከአፍሪካ ጋር እየመሠረተች ያለው ግንኙነት እየጨመረ ብቻ ሳይሆን እየረቀቀም መጥቷል፡፡ ቀድሞ የምዕራብ አሸርጋጅ የነበሩ የአፍሪካ አምባገነኖች በአሁኑ ወቅት ከኮሙኒስት ቻይና ጋር በንግድና በኢኮኖሚ ብቻ ሳይሆን በአፈና፣ በስለላ እንዲሁም በሙስና እጅና ጓንት እየሆኑ መጥተዋል፡፡…
ቻይና ግን በበኩሏ በአፍሪካ ያላትን እንቅስቃሴ በከፍተኛ ሁኔታ በመቀጠል አቶ መለስን ጨምሮ በርካታ ቀን ምዕራባዊ ማታ ኮሙኒስታዊ የሆኑ መሪዎችን ማሽሞንሞን ቀጠለች፡፡ የሙሉ ቀን የቻይና ወዳጅ ለማድረግም በሁሉም ዘርፍ እንቅስቃሴዋን ገፋች፡፡ የዛሬ አምስት ዓመት ገደማ ቻይና በአፍሪካ ለምታደርገው እንቅስቃሴ ማስፈጸሚያ የሦስት ዓመት ዕቅድ በማውጣት ሦስት ቢሊዮን ዶላር መደበች፡፡ ይህም ቻይና አስቀድማ ከመደበችው ሦስት ቢሊዮን ብድርና ሁለት ቢሊዮን የውጭ ንግድ ዱቤ ሌላ መሆኑን ፕሬዚዳንት ሁ ጁንታዖ በወቅቱ ስምንት የአፍሪካ አገራትን በጎበኙ ጊዜ ያስታወቁት ጉዳይ ነበር፡፡
ቻይና በዚህ አልተገታችም፤ በ2003 መገባደጃ ላይ በተገኘው መረጃ መሠረት ቻይና ከአፍሪካ ጋር ያላት የንግድ ግንኙነት ወደ 170ቢሊዮን ዶላር የደረሰ ሲሆን ባለፉት አስር ዓመታት ብቻ አፍሪካ ለቻይና ኢንዱስትሪዎችን የምትልከው ግብዓት ከ5.6 ቢሊዮን ዶላር ወደ 93ቢሊዮን ዶላር አሻቅቧል፡፡ በሐምሌ 2004ዓም ደግሞ ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት ቻይና ለአፍሪካ አገራት ልትሰጥ ያሰበችውን ብድር በእጥፍ በማሳደግ 20ቢሊዮን ዶላር ለማድረስ መወሰኗን አሳውቃለች፡፡
ይህ እጅግ አሳሳቢ የሆነው ቻይና በአፍሪካ ላይ እያደረገች ያለው ተጽዕኖ ምዕራባውያን በዝምታ የሚያልፉት አይደለም፡፡ በቅርቡ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትርነት የተሾሙት ጆን ኬሪ በአሜሪካው የሕግ መወሰኛ ምክርቤት ለጥያቄ በቀረቡ ጊዜ በተለይ የቻይና እና የአፍሪካን ሁኔታ አስመልክቶ ሲናገሩ ‹‹ቻይና በመላው አፍሪካ ተሰራጭታለች – እውነቴን ነው የምለው በአፍሪካ በሙሉ! በመዓድንና በሌሎች … ጠርታችሁ በማትዘልቁት መስኮች በሙሉ የረጅም ጊዜ ስምምነቶች እየፈረመች ትገኛለች፡፡ እኛ ደግሞ ከጨዋታው ውጪ የሆንባቸው የተወሰኑ ቦታዎች አሉ፤ እንደዚህ ማለቱን ባልወደውም፤ ወገኖቼ በጨዋታው መሳተፍ አለብን›› ብለው ነበር፡፡ አሜሪካና ምዕራባውያን ባጠቃላይ ወደ ጨዋታው ለመግባት ቆርጠው ተነስተዋል፡፡
ይህ ደግሞ ተግባራዊ ሊሆን የሚችለው ‹‹በአሸባሪነት ላይ ጦርነት›› የሚል የሽፋን ስዕል ሲሰጠው ብቻ ነው፡፡ በአፍሪካ ይህንን የሽፋን ስዕል የመጽሐፋቸው መለያ ያደረጉ አገራት ጥቂት አይደሉም፡፡ መንገዱ ሲጨልምበት ቆም ብሎ ከማሰብ ይልቅ ጊዜያዊ ጥቅሙን ብቻ በማየት የሚጓዘው ህወሃት/ኢህአዴግ አገራችንን በዚህ ሽፋን ውስጥ ካስገባትና የቅርብና የሩቅ ጠላቶች በግድ ከፈጠረልን ቆይቷል፡፡ ዞር ብሎ ደግሞ ከቻይና ጋር ተጋብቷል፡፡
‹‹ባለራዕዩ›› መለስ ለሁለቱም ታዛዥና ታማኝ ሆነው የትኛውን አብልጠው እንደሚታዘዙና ለየትኛው እንደሚገዙ ውሉን ሳይዙ አገራችንን ውል አልባ አድርገው አልፈዋል፡፡ የኅልፈታቸውም መነሻ ይህ ነው ባይባልም ከጅምሩ ኮሙኒስታዊ መሆናቸውና ዞረው ወደ ማዖ አገር ፊታቸውን ማቅናታቸው የምዕራባውያን ወዳጅ ሆነው እንደማይቀጥሉ ጉልህ ማስረጃ ነበር፡፡ ምርጫቸውን ሳያስተካክሉ ተሰናበቱ እንጂ፡፡
ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ
የሚዘጋባቸው ህጻናት – ዝግ ቤቶች
… ሮዚና ወገቧ ሸንቃጣ፣ አንጀት የሚባል ነገር ያልሰራባት፣ ዳሌዋ ሰፊና ክብ፣ ሽክ ያለች፣ አንገቷ ውድ ነገሮች የሚቀመጡበት፣ ሽታዋ የሚያውድ፣ ዓይነ ርግቧ በቀለም እንደ ስዕል የሚዋብ፣ ሳሳ ያለ ልብስ የምትለብስ፣ እንግዳዎቿን በምትዘጋባቸው ቤት እየተዘዋወረች የምትቀበል አራዳ ነች። አስተናጋጆቿ በጣም ትንንሽ ልጆች ሲሆኑ ጸሃይ አይነካቸውም። ስራቸው ለሮዚና እንግዶች መስተንግዶ ሳይስተጓጎል መስጠት ነው – የሚጠጣ   ያቀርባሉ፤ ፍም እሳት አዘጋጅተው ቡና ያፈላሉ፤ ለማሟሟቂያ የቡናው ስነ ስርዓት በየክፍሎቹ ከተከናወነ በኋላ የጫቱ ሙቀት እየጨመረ ሲሄድ ሺሻ ይለኮሳል። ህጻናቱ ሺሻ እያሞቁ ደንበኞቹን ለማስተናገድ ከቡና ማፍያው በርጩማ ተነስተው ፍራሹ ላይ ሲወርዱ ከአባታቸው ጋር በሰንበት የሚጫወቱ እንጂ የስራ ግንኙነት ያላቸው አይመስሉም። ጫት እየቀነጠሱ፣ ሺሻ እያሞቁ ደንበኛቸውን ባፍ ባፉ መከደም ዋና ስራቸው ስለሆነ ተክነውበታል።
ተጋብዤ የተመለከትኩት ክፍል የነበረችው ልጅ ሪታ ትባላለች። ንግግሯ የቀምጣላ ልጆች አይነት ነው። ስትስቅ አማርኛ አይመስልም። ጠይም ቀለሟ የጸዳ፣ ለጋ ነች። እንደ ጋባዤ አገላለጽ “ጥፍሯ ይበላል”፤ ዕድሜዋ ከአስራ አምስት አይበልጥም። ቡና እንደጨረሰች ስስ ነገር ለብሳ ደንበኛዬ ጎን ቁብ አለች። መቃም ትችልበታለች። ጫት ላኪዎች በትዕዛዝ የሚልኩትን ጫት ትጠጣዋለች። ያለ ምንም ማጋነን የቅጠል አበላሏን ፍየል ብታየው በቅናት ምላሷን ትቆርጠዋለች። ምን አደከማችሁ ቅማ ታቃቅማለች። አልፎ አልፎ ሮዚና ለጉብኝት ብቅ ብላ ስትመለስ ቤቱን ታውደዋለች…
ምርቃናው ሲጨምር ወዳጄ ቀስ በቀስ ከልጅቷ ጋር ተጣበቀ። እጆቹም ሁለመናውም እሷ ላይ ሆነ። በቃ ደረቱ ላይ ጣላት። ደረቱ ላይ አንጋሏት ሺሻውን ይምጋል። ብቸኝነቱ ሊውጠኝ ሲደርስ መሄድ አለብኝ ብዬ ተነሳሁ። ፒኮክ እንደምጠብቀው ነገርኩትና ተለየሁት። ህጻኗን ልጅ ደረቱ ላይ አንጋሏት ስመለከት ልጄን አቅፌ ሳስገሳው ትዝ አለኝ። የሚያስገሳት እንጂ የሚዳራት አይመስልም። እንዲህ ያሉትን ትውልድ አምካኝ ቤቶች ማጥፋት ቀላል ነው። ግን ተጠቃሚዎቹ ህግ አስከባሪና ህግ አወጪዎቹ በመሆናቸው አይታሰብም። አንዳንድ ዝግ ቤቶች በሲቪል ጠባቂዎች የሚጠበቁ ናቸው። አንዳንዴ ቤተመንግስቱንና ሟቹን የቤተመንግስት ነዋሪ ይጠብቁ የነበሩት በፈረቃ ይታደማሉ። ዝግ ቤቶች …
ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ
ኢህአዴግ በሩን እንዲከፍት የዓለም ባንክ አዘዘ
የማነቂያው ገመድ ከርሯል፤ “ትግሉ ይቀጥላል” ኦባንግ ሜቶ
ኢህአዴግ ለሚገዛት ኢትዮጵያ ከፍተኛ መጠን ያለው ዕርዳታ የሚሠጠው የዓለም ባንክ፤ ለዕርዳታና ልማት የሚልከው ገንዘብ ኢህአዴግ የሕዝቡን ሰብዓዊ መብት ለመጣስ ተጠቅሞበታል በሚል ሙሉ ምርመራ እንዲካሄድ አዘዘ፡፡ የባንኩ ውሳኔ ኢህአዴግን የማነቂያው ገመድ እንደሚያከረው ተገለጸ፡፡ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ ሜቶ በተለይ ለጎልጉል በሰጡት መግለጫ “ይህ በጥናት ከምናካሂደው ትግል አንዱ ውጤት ነው፤ ገና ጅማሬ ነው፤ [...]
ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ
“ኦባማ መጀን” ወይስ “በእውቀት” መደራጀት?
የአሜሪካ ምርጫ ሲጠናቀቅ ተሸናፊው ሚት ሮምኒ ደጋፊዎቻቸው በተሰበሰቡበት አዳራሽ ምስጋና ካቀረቡ በኋላ እንዲህ አሉ፡- “… ሁለታችንም ለምንወዳት አገራችን የምንመኘውን ለማድረግ በተለያየ አቅጣጫ ሞከርን፤ … ሕዝባችን ደግሞ የሚፈልገውን መሪ መረጠ፤ … ስለዚህ ፕሬዚዳንቱን ደውዬ አነጋሬያቸዋለሁ፤ ባገኙትም ድል እንኳን ደስ አለዎ ብያቸዋለሁ፤ … በተለይ ለእርሳቸው፣ ለቀዳማዊ እመቤት እና ለልጆቻቸው ሁሉ መልካሙን እመኛለሁ፤ … አገራችን ከባድ ፈተናዎች ተጋርጠውባታል፤ … ባለቤቴና እኔ ለፕሬዚዳንቱና ቤተሰባቸው ከልብ እንጸልያለን፤ በሥራቸው ስኬት እንዲያገኙና ታላቋን አገራችንን በመምራት የሚያከናውኑት ሁሉ የተሳካ እንዲሁን እመኛለሁ፡፡” ይህንን ካሉ በኋላ ወደተለመደው ህይወታቸው ሄዱ – የፖለቲካ ገዳም ገቡ፡፡ ይህ ንግግር ወደራሳችን እንድንመለከት የሚያደርግ ነው፡፡ የእኛስ ፖለቲከኞች ዕድሜ ልካቸውን የፖለቲካ አክሮባት እየሰሩ አንደ ፓርቲ ሲያቋቁሙ፤ ሌላ ሲያፈርሱ፤ አንዱን ሲጠልፉ ሌላውን በሾኬ ሲሉ … ከመቆየት ይልቅ የሚሞክሩትን ሞክረው አልሆን ሲል በክብር ለተከታዩ ቦታ ለቅቀው ወደ ፖለቲካ ገዳማቸው የሚገቡት መቼ ይሆን?
… የዛሬ አራት ዓመት ታሪካዊው የፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ሲፈጸም ኢትዮጵያዊ ሆኖ ምርጫውን ያልደገፈ፣ ያላለቀሰ፣ ያላጨበጨበ፣ ያልዘፈነ፣ … ይኖራል ለማለት እጅግ ያዳግታል፡፡ የልዕለኃያል ሰብዕና የተሰጣቸው ኦባማ በአምባገነን መሪዎች ተጠፍረው የሚገኙ የኢትዮጵያንና መሰል አገራት ችግር በቀጥታ ትዕዛዝ ያስወግዳሉ ብሎ ከማሰብ ባለፈ እንዲያውም የአሜሪካ ፖሊሶች አቶ መለስን ለፍርድ ሲያስጎትቱ የሚያሳይ የተሻሻለ ፎቶ እስከመሰራትና በድረገጾች እስከመበተን የደረሰበት ጊዜም ነበር፡፡ አገርቤትማ በኦባማ ስም ያልተከፈተ ሻይ ቤት፣ ዳቦ ቤት፣ ጆተኒ ቤት… የለም፡፡…
… ዓመታት እያለፉ ሲሄድ የብዙዎች ተስፋ መጨለም ሲጀምር የሚሰጡትም ማስተባበያዎች በዚያው መልኩ እየጨመረ ሄደ፡፡ “በመጀመሪያው ጥቂት ዓመታት ከፍተኛ ችግር የገጠመውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ የማሻሻል ኃላፊነት ስላለባቸው በውጪ ጉዳይ ላይ እምብዛም ላይጠመዱ ይችላሉ” የሚሉ ራስን የማታለያ መላምቶች ተሰጡ፡፡ ኦባማ ግን በአምባገነኖች ላይ ከንግግር ያለፈ በተግባር የታገዘ የፖሊሲ አቋም ሳይዙ ቀጠሉ፡፡ አቶ መለስም በየዓመቱ በሚደረገው የቡድን 7፣ 8፣ 20፣ 22፣ … ብቻ የተገኘው የቡድን ስብሰባ (የቡድን አባቶችን ሳይጨምር) ላይ ከኦባማ ጋር ሲጨባበጡ፣ ሲሳሳቁ፣ … መታየታቸው ለበርካታ ኢትዮጵያውያን “ዱሮውንም … ” የሚያስብል መራራ ክስተት እየሆነ መጣ፡፡ የዚያኑ ያክልም “የራሳችንን ችግር ራሳችን ነን እንጂ መወጣት ያለብን ኦባማ ነጻ ሊያወጣን አይችልም” የሚል የመከላከያ አስተያየት እንደተለመደው ቀጠለ – “አልተሸወድንም” ለማለት ነው፡፡ ገንዘቡና ዕርዳታው ግን አላቆመም፡፡
… የንግግር ተሰጥዖ የፈሰሰባቸው ፕሬዚዳንቱ ጋና ላይ ታሪካዊዉን ንግግር ባደረጉ ጊዜ “መለስ ጉድህ” ተባለ! “ሕግ የበላይ ባልሆነበት ጭከናና ጉቦ (ሙስና) በሰለጠኑበት ማኅበረሰብ ውስጥ መኖር የሚፈልግ አንዳችም ሰው የለም፡፡ ይህ ዴሞክራሲ አይደለም፤ ይልቁንም ይህ የጭቆና አገዛዝ ነው፡፡ እንዲህ ያለው አገዛዝ ያከትም ዘንድ ጊዜው አሁን ነው” አሉ ኦባማ፡፡ አፍሪካም በደስታ ሰከረች፡፡ በዚህ ደስታ እንደተለመደው “የለውጥ ተስፋ” ተግባራዊ ይሆናል ተብሎ ሲጠበቅ ኦባማ “ምነው አልበዛም እንዴ” የሚያሰኝ ንግግር በዓለም ፊት አደረጉ፡፡ በኒውዮርክ ከተማ የምዕተዓመቱ የልማት ዕቅድ (ትልም) ሴፕቴምበር 22፤ 2010ዓም በተካሄደ ስብሰባ ላይ ኦባማ ከመለስና “አብዮታዊ ዴሞክራሲያውያን” በላይ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ዕድገት አደነቁ፡፡ ማስረጃም አከሉበት፡፡ “ሥር ነቀል ለውጥ ለማምጣት ይቻል ዘንድ የለውጥ ማዕበልን (ሁሉን አቀፍ የኢኮኖሚ ዕድገትን ማለታቸው ነበር) ፈትተን መልቀቅ አለብን፡፡ ይህም ድህነትን በማስወገድና ዕድልን በመፍጠር ደረጃ ዓለማችን እስካሁን ካየችው ሁሉ ለየት ያለ ነው፡፡ ይህ ኃይል ደቡብ ኮሪያን ከዕርዳታ ተቀባይነት ወደ ዕርዳታ ለጋስነት ያሸጋገረ ነው፡፡ በብራዚልና ሕንድ የኑሮ ሁኔታን ያሻሻለ ነው፡፡ በአፍሪካ ደግሞ እንደ ኢትዮጵያ፣ ማላዊና ሞዛምቢክ ያሉ አገራትን የምዕተዓመቱን የልማት ትልም ተግባራዊ እንዳያደርጉ የተጋረጠባቸውን ሁሉ በመቋቋም እውነተኛ ዕድገት እንዲያስቆጥሩ ያደረጋቸው ነው” በማለት በኒውዮርክ ሰዓት ከሰዓትበኋላ 11 አካባቢ፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ ደግሞ የተራበ ሆዱን በእህል ሳይሞላ አሸልቦ ባለበት ኦባማ ቀለዱበት፡፡ በእንቅልፍ ተታልሎ ጉዱን ያልሰማው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሳይነቃ እነ አቶ መለስ ከኦባማ ንግግር የሰሟትን ቃል አሻሽለው “ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን” ብለው በህልሙ ቂቤ አጠጡት፡፡ ከመፍጠናቸው የተነሳ “ትራንስፎርሜሽን” ለሚለው የባዕድ ቃል የአማርኛ ትርጓሜ እስኪያገኙ መጠበቅ ያልቻሉ ይመስላል፡፡ የልማት አርበኛ፣ የልማት ሰራዊት፣ … የሚሉት የልማት ክተት አዋጆች የተጎሰሙትም በዚሁ ቅጽበት ነው።
… ከአምስት ወራት በፊት በሺካጎ ከተማ ከቡድን ስምንት ስብሰባ በፊት በእርሻና ምግብ ሰብል ራስን መቻል ርዕስ በተደረገ ስብሰባ ላይ ፕሬዚዳንት ኦባማ አቶ መለስን በስም ጠርተው በአፍሪካ ለብዙዎች ህይወት ሰለባ የሆነውን ረሃብ በመታገል ደረጃ ከፍተኛ ጥረት የሚያደርጉ አፍሪካዊ መሪ በማለት ከሌሎች ሁለት አፍሪካዊ መሪዎች ጋር በማሞገስ አስጨበጨቡላቸው፡፡ በዚህ ብቻ አላበቁም ኢትዮጵያ በግብርናና ምግብ ዋስትና ላይ በምታካሂደው በሳል ኢንቨስትመንት ምክንያት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በአሁኑ ጊዜ የአስቸኳይ ጊዜ ምግብ ተረጂዎች ከመሆን ተላቅቀዋል በማለት አቶ መለስ በስብሰባው ላይ የተጠሩበትን ምክንያት በማስረጃ ጠቀሱ፡፡ በማስከተልም “ፕሬዚዳንቱ በእርግጥ ኢቴቪን በደንብ ይከታተላሉ” የሚያሰኝ ንግግር በማድረግ ስብሰባውን አጠቃለሉ፡፡ የመለስ መንግሥት በሚከተለው የግብርና ፖሊሲ የገበሬው ህይወት እየተቀየረ መሆኑን በመጥቀስ ሲናገሩ “በነዚህ ስትራቴጂዎች ምክንያት በኢትዮጵያ ያለ ገበሬ (ከመንግሥት) ብድር በማግኘቱ ምርቱን ለማሳደግና ተጨማሪ ሠራተኞችን ለመቅጠር ችሏል፤ በመሆኑም ይህ ገበሬ እንዲህ ይላል ‘በዚህ ደመወዝ ምክንያት ሕይወቴ ተቀይሯል፤ አሁን ልጆቼ ትምህርትቤት መሄድ ይችላሉ’” በማለት ለኢትዮጵያ የሚቆረቆሩ ልማታዊ ፕሬዚዳንት የሚያስብል ንግግር ኦባማ አደረጉ፡፡
ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ
በለገጣፎ ገሃነምና ገነት አየሁ!
“በኔ ዘመን የኦሮሞ ልጆች እንዳይታሰሩ አድርጌያለሁ” ጁነዲን
ስሙ እንዳይገለጽ የጠየቀ ወጣት የለገጣፎ ነዋሪ አንድ አብይ ማስረጃ ላሳይህ ሲል የጎልጉልን ሪፖርተር እየመራ ወደ ካንትሪ ክለብ ግቢ ወሰደው። ካንትሪ ክለብ በግፍ፣ በሚገርም ክፍያ፣ ያለ በቂ ዝግጅት ከአርሶ አደሩ ላይ የተነጠቀ ሰፊ መሬት ነው።
የካንትሪ ክለብ ዴቨሎፐርስ (COUNTRY CLUB DEVELOPERS P.L.C. – CCD) ድረገጽ እንደሚመሰክረው ሥፍራው ከ160 ሄክታር ወይም 16 ሚሊዮን ካሬ ሜትር አካሎ ይዟል። እያንዳንዱ ቪላ 1000 ካሬ ሜትር ይዞታ ሲኖረው፣ ከ282 እስከ 513 ካሬ ስፋት ባለው ቦታ ላይ ቪላዎቹ ተኝተው ይታያሉ።
ዋናውን መግቢያ እንዳለፉ ኢትዮጵያ ለገጣፎ ውስጥ ስለመገኘትዎ ማረጋገጫ የለዎትም። ቪላዎቹ ከመሬት ብዙም ከፍ ሳይሉ ተንጣለው ሲያዩዋቸው የተሽኮረመሙ ይመስላሉ። እየቀረቡ ሲሄዱ የቤቶቹ ድርድርና አሰራር ያስገርማል። ብዙ ሪል ስቴቶች ቢኖሩም እንደ ካንትሪ ክለብ ያለ አለ ማለት አይቻልም። ፎቅና ምድር ሆነው የተሰሩት ህንጻዎች የሲሚንቶና የድንጋይ ክምር አይመስሉም። መሬቱ የተዋበት ጡብ፣ በየመንገዱ ያሉት መብራቶች፣ የመዳመቂያ እጽዋቶቹ፣ ሳርና የተመረጠ አበባ የለበሰው መስክ ቀልብ ይሰልባል። ያለማገነን በለገጣፎ ገሃነምና ገነትን አይቻለሁ። አገርቤት መሆንዎን የሚያውቁት ባሬላ ተሸክመው ከወዲያ ወዲህ የሚሉትን “ምስኪኖች” ሲመለከቱ ነው።
ወጣቱ በቀስታ እያመለከተ እነዚህ ሁሉ የምታያቸው የቀን ሰራተኞች አብዛኞቹ የመሬቱ ባለቤቶች ነበሩ። አባት፣ እናት፣ ልጅ ቤተሰቦች ንብረታቸው ላይ ተፈርዶባቸው የቀን ሰራተኛ ሆነዋል። ለንብረታቸው የተከፈላቸው ካሳ ተመጣጣኝ ቢሆን ኖሮ እዚህ ጭቃ አያቦኩም ነበር። ወጣቱ አለቀሰ። ቤቶቹ የሚሸጡት ከአምስት ሚሊዮን ብር በላይ ነው። እንግዲህ አንድ አባወራ አራት ጥማድ መሬት ከተወሰደበት አራት ቪላ ይሰራበታል ማለት ነው። በአምስት ሚሊዮን ብር ሂሳብ ከሃያ ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ ግብይት ባንድ አባወራ መሬት ላይ ተፈጽሟል። እንደ ወጣቱ ገለጻ አራት ሄክታር የተወሰደበት አባወራ 120ሺህ የማይሞላ ብር ወስዶ ከጨዋታ ውጪ ይሆናል። እናም ኩሊ ለመሆን ይገደዳል። ይህንን ወንጀል ህዝባቸው ላይ የሚፈጽሙትና “ለምን” ብሎ ሲጠይቅ አስረው የሚገርፉት ኦሮሞዎች ናቸው። እንዲህ ያለው ግፍ የት አገር ተፈጽሟል?
ሙሉውን ጽሁፍ ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

No comments:

Post a Comment