እርቅ ላይ የምትሰሩ የት አላችሁ?
ባለፈው ሳምንት የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ የተቃዋሚ ፓርቲ ወኪሎችንና አቶ ስብሃትን ባንድነት በየተራ አናግሮ ነበር። ከውይይቱ የተለመደ ክርክር በዘለለ አቶ ስብሃት እርቅ አስፈላጊ መሆኑንን ማመናቸው የተለየ ጉዳይ ነበር። እንደ እርሳቸው አነጋገር አሁን የተጀመረውን መልካም የልማት ስራ ለማስቀጠል እርቅ አስፈላጊ ነው። የእርቅን አስፈላጊነት በማመን ከባልደረቦቻቸው ጋር በመምከር የእርቅ ጉባኤ ለማዘጋጀት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።
አቶ ስብሃት “የተቃዋሚ ፓርቲ አለ ብዬ አላምንም” በማለት ተቃዋሚዎችን እንደወትሮው ሁሉ ዘልፈዋል። “መደብ የላቸውም” ሲሉ ተቃዋሚዎችን ጭራሽ እንደ ፓርቲ እንደማይቆጥሯቸው የተናገሩት አቶ ስብሃት ከዘለፋቸው በኋላ ስለ እርቅ አግባብ መናገራቸውን፣ ጠያቂው እሳቸው ባነሱት አዲስ ሃሳብ ላይ በመንተራስ ማረጋገጫ ሲጠይቃቸው “ከጓደኞቼ ጋር መክሬ” በማለት በቅርቡ የእርቅ መድረክ እንዲፈጠር እንደሚተጉ መናገራቸውን ተከትሎ እርቅ ላይ እንሰራለን ከሚሉ ወገኖች ምላሽ አልተሰማም።
አሁን ባለው ውጥረት የነገሰበት የኢትዮጵያ ፖለቲካ አብዛኞችን ስጋት ውስጥ የከተተ ነው። በስዊድን አገር በአንድ የእራት ግብዣ ላይ ተገኙ የትግራይ ተወላጅ ለጎልጉል እንደተናገሩት “በጎሳና በክልል ተለይቶ የሚንቦገቦገው የጥላቻ ፖለቲካ መጠኑ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ አስግቶኛል። እርቅ ብቸኛ መፍትሔ ነው። በዚህ ሃሳብ ላይ መስራት ግድ ነው” የሚል አስተያየት ሰጥተዋል።
በፍርሃቻ ከሁሉም ያጣ ላለመሆን ኢህአዴግን የሚደግፉ እንዳሉ ያመለከቱት እኚሁ ሰው የኢትዮጵያ ጉዳይ በእጅጉ ዕረፍት እንደነሳቸው አልሸሸጉም። “ስብሃት ነጋ እርቅ ላይ ለመስራት ከልብ ያሰቡ ይመስልዎታል?” በሚል አስተያየታቸውን የተጠየቁት እኚሁ ሰው “ኢህአዴግም ሆነ ህወሃት እኮ የሰዎች ጥርቅም እንጂ ሌላ ግዑዝ ነገር አይደሉም። ችግሩን ከሁላችንም በላይ ይረዱታል። እንደውም እነሱ የሚያውቁትን ያህል የችግሩን አሳሳቢነት ተራው ነዋሪ ቢረዳ ልቡ በድንጋጤ ሊቆም ይችላል” የሚል ምላሽ ሰጥተዋል። አያያዘውም ኢህአዴግ ችግሮች ገንፍለው እንዳይወጡ የሰጋበት ደረጃ እንደሚገኝ አመልክተዋል። በሁሉም አቅጣጫ የሚያገኟቸው ወገኖች የሚነግሯቸው ይህንኑ የስጋት ጉዳይ እንደሆነም ተናግረዋል።
ኢህአዴግ የሚነሳበትን ተቃውሞ በጥይት እያረገበ መዝለቅ እንደማይችል ብዙዎች እየተናገሩ ነው። ኢህአዴግ ችግሮችን በሰላማዊ መንገድ ከማስወገድ ይልቅ ጥይትን መምረጡ የበቀሉን ደረጃ እያናረው ስለመሆኑም ክርክር የለም። ኢህአዴግ የገደላቸው ወገኖች በሙሉ ወገን አላቸው፣ ዘር አላቸው፣ ተቆርቋሪ አላቸው፣ ጎሳ አላቸው፣ ምድር አላቸው፣ ቀበሌና ቀዬ አላቸው፣ ወዳጆችና ተከራካሪዎች አሏቸው በሚል ኢህአዴግ ያልተመከረበት ወቅትና ጊዜ ለም። እንደውም ባንድ ወቅት ለጎልጉል አስተያየት የሰጡ “ብሶት ህወሃትን ብቻ አይወልድም፣ የብሶት የበኩር ልጅ ህወሃት ብቻም ሊሆን አይችልም” ብለው ነበር።
ከግድያው፣ ከእስሩ፣ ከአፈናው፣ ከድብዳው፣ ከማስፈራራቱ በተጨማሪ በአገሪቱ ሃብት ላይ ኢህአዴግ እየፈጸመ ያለው ፍትሃዊነት የጎደለው የንግድ ስምምነትና የንግድ ውድድር ያስቀየማቸው ወገኖች ቁጥርም ቀላል አይደለም። አብዛኞች በተለያዩ ወቅቶች ሲገልጹት እንደነበረው ኢህአዴግ ባለስልጣናቱ የህዝብን ሃብት በሽርክና በመቸብቸብ ሃብት አፍርተዋል። እነርሱ እንዳሻቸው እየዘረፉ ምስኪን አርሶ አደሮች ለእለት ጉርስ እየጫሩ ከሚኖሩበት ቀዬ ከነቤተሰቦቻቸው እንደ ባዕድ በጎሳ እየተለዩ እንዲፈናቀሉ ተደርጓል። ኢህአዴግ ካለበት ፍርሃቻ በመነሳት በየጊዜው በደልን እያበዛ ጠላቶቹን በማብዛቱ ስጋት የገባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ሰላማቸውን አጥተዋል።
በበዳዩ ወገኖች ተርታ በተሰለፉና በተበዳዩ ወገኖች ጎን ባሉት ዜጎች መካከል እየታየ ያለው የበቀል ስሜት ልክ እንዳጣ የሚናገሩ ክፍሎች አሁን አገሪቱ ላለችበት አጣብቂኝ ወቅት መፍትሔው እርቅ እንደሆነ ሲወተውቱ ዓመታት ተቆጥረዋል። አቶ ስብሃት የተናገሩት እርቅ ሃሳብ እውነተኛ ይሁን ከምርጫ ጋር በተያያዘ የተቃዋሚዎችንና የህዝቡን ስሜት “ለማቀዛቀዝ” ኢህአዴግ እንደለመደው ሊጠቀምበት የፈለገው ማደናገሪያ ይሁን በእርግጠኝነት ለመናገር አይቻልም፡፡ ሆኖም ግን ስብሃት ለተናገሩት የእርቅ ሃሳብ ድጋፍ በመስጠት አገሪቱ ላይ የነገሰውን የጥላቻና የቁጣ ፖለቲካ ማምከን አስፈላጊ ቢሆንም እስካሁን ከሌሎች ወገኖች የተሰማ ነገር አለመኖሩ አስገራሚ ሆኗል። በወቅቱ የጀርመን ድምጽ ሬዲዮ ዘጋቢ ነጋሽ መሐመድ የጋበዛቸው የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ተወካዮች ግን ኢህአዴግ የእርቅ ጥሪ ካቀረበ እንደሚስማሙ ተናግረዋል።
ጥቅምት 25፤2006 ዓም (November 4, 2013) ላይ ጎልጉል “በህወሃት ውስጥ የዕርቅ ሃሳብ መነሳቱ ተሰማ” በሚል ርዕስ ባሰፈረው ዜና ላይ ምንጭ አድርጎ የጠቀሳቸው “የኢህአዴግ ከፍተኛ አመራርና ዲፕሎማት እንዳሉት ህወሃት ውስጥ “እርቅ አስፈላጊ ነው” በሚል እቅድ እንዲያዝና እንዲሰራበት ሃሳብ ቀርቧል። በድርጅቱ ውስጥ በተፈጠረ አለመተማመን ሳቢያ ስጋት የገባቸው የህወሃት ሰዎች የእርቅ ሃሳብ እንዲሰራበት ያቀረቡት ሃሳብ ግን በመደበኛ ስብሰባ አይደለም” ማለታቸውን ዘግበን ነበር፡፡
የዕርቁን ሃሳብ እንዲነሳ ያደረጉ ምክንያቶች በርካታ ቢሆኑም በዜና ዘገባው ላይ የቀረበው ቀዳሚ ሃሳብ “በህወሃትና ህወሃት በሚያዛቸው አቻ ፓርቲዎች መካከል ያለው የመከባበርና የመገዛት ስሜት ከመለስ ሞት በኋላ መበላሸቱ፣ በኢህአዴግም ሆነ በህወሃት ደረጃ የተፈጠረው ልዩነትና በሙስና ስም የተጀመረውን ዘመቻ ተከትሎ የተነሳው አለመግባባት አደጋ እንዳያስከትል መፈራቱ” ጎልጉል እንደ ምክንያት ጠቅሶ ነበር፡፡
ጎልጉል በዝርዝር ባሰፈረው በዚህ የዜና ዘገባ ላይ ምንጭ አድርጎ የጠቀሳቸው የኢህአዴግ አመራርና ዲፕሎማት በሰጡት አስተያየት ዕርቅ “በቅርብ ጊዜ ውስጥ የሚታይ ነው” ማለታቸውን ዘግቦ ነበር፡፡ ዲፕሎማቱ ሲቀጥሉም “አንዱ እኔ ነኝ። ሌሎችም አሉ። ብዙዎች ሰላማዊ ህይወት ናፍቆናል። የተወሳሰበውን አገራችንን ፖለቲካ አካሄድ ለመተንበይ ተቸግረናል። መፍትሔው የእርቅ ሃሳብ ብቻ ነው” ብለው ነበር።
አስተያየታቸውን ሲያጠናቅቁም “በድርጅታቸው ውስጥ የበላይና የበታች መጥፋቱን፣ የበታቹ የበላዩን እንደሚያዘው፣ አንዳንዴ የበላይ መስለው ምንም ዓይነት የውሳኔ ሰጪነት ሚና የሌላቸው ክፍሎች መኖራቸው የአደባባይ ምስጢር” መሆኑን አልሸሸጉም ነበር፡፡
በመጨረሻም በዕርቅ ሃሳብ ላይ ቀዳሚውን ቦታ የሚወስዱት ስብሃት መሆናቸውን ሲገልጹ “እርቅና ዋስትና የሚሰጥ አግባብ ቢያገኝ የመጀመሪያው ስምምነት ፈራሚና ደጋፊ ስብሃት ነው። ቀሪውን የጡረታ ዘመኑንን በትዝታ ያለውን እየበላ መኖር ይፈልጋል። እሱ ብቻ ሳይሆን ብዙዎች ተመሳሳይ ፍላጎት አለን። አስከማውቀው ድረስ ችግሩ ከራስ ምግባርና ከድርጅት ተልዕኮ በመነጨ የተሰሩት ጥፋቶችና ሃጢያቶች መብዛታቸው ከለውጥ በኋላ የሚያመጣቸው የተጠያቂነት ጣጣዎች ናቸው” ብለዋል፡፡
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
No comments:
Post a Comment