Wednesday, March 12, 2014

አባ መላም፣ አባ ዱላም ሆነው ብቻ ኢሃዴግዬ በተሻላት


abamela-11አባ መላም፣ አባ ዱላም ሆነው ብቻ ኢሃዴግዬ በተሻላት
ኢሃአዴግዬን እንደኛ የሚወዳት ማን አለ… እውነቴን ነው የምላችሁ በፖሊሲዋ ተምረን በፖሊሷ ተገርፈን አድገን ዛሬ አንወድሽም ልንላት እንዴት ይቻለናል… ኢሃአዴግን ስለምንወዳት ነው በታመመች ጊዜ ትታከም፣ በሰከረች ጊዜ አልኮል ትቀንስ እያልን የምንወተውተው።
እንጂማ እብደቷ ካገር አባሮ እስኪያጠፋት ስካሯም አዙሮ እስኪደፋት ዝም ብለን እንጠብቅ አልነበርምን…
ኢሃአዴግዬ ታማለች! የሚለው ምንም ጥያቄ የለውም አከራካሪው ህመሙ መቼ ነው የጀመራት የሚለው ነው። አንዳንድ ወገኖች “ግንቦት ሃያ ሺ ዘጠኝ መቶ ሰማኒያ ሶስት ዓመተ ምህረት” ያለች እለት የጀመራት ነው ሲሉ፤ ሌሎች ደገሞ “የለም ገና ከእናቷ (ወይዘሮ ጫካ) ማህፀን እንዳለች ነው
የተለከፈችው” ይሉናል። ሌሎችም “ኧረ እሰከ ቅርብ ጊዜ ሰላም ነበረች አሁን እኮ ነው እያየናት እየለቀቀች እየለቀቀች የመጣችው” ይሏታል… አሁንም ሌሎች ያኔ አቶ መለስ ያገኙላት “የመበስበስ አደጋ” የተባለው በሽታ ነው ራሷ ላይ ወጥቶ የሚጫወትባት እያሉ መላ ምት ያቀረባሉ።
የሆነው ሆኖ ግን ኢሃአዴግ ታማለች! ይሄ እንኳን ሌላ “ዶክተር” መለስም የረጋገጡት ጉዳይ ነው። በህመሟ ሳቢያ ነው ያገኘችውን ሁሉ ልቀፍ፣ ትኩር ብሎ ያየኝን ሁሉ ወይ ልግርፍ ወይ ልሰር የሚያስብላት… ባጠቃላይ ሀመሟ መላ ቅጥም የለው።
የሚያሳዝነው ታድያ መታመሟ አይደለም ህምምማ የማንም ነው። ቸግሩ፤ የደረሰባቸው ሰዎች፤ “ህመምተኛ ሲብስበት አስታማሚ ይውፍራል” ብለው እንደሚተርቱት ኢሃአዴግዬ (እናቴ፣ አናቴ፣ ግንባሬ… ብዬ ስቀስቅ ብዬ ላልቅስ እንዴ…) ኢሃአዴግዬ በብርቱ ታማ ሳለ አስታማሚዎቿ እና አሳማሚዎቿ እየወፈሩ እየወፈሩ የመጡበት ሁኔታ ነው ያለው።

እየወፈሩ ብቻ ደግሞ አይደለም፤ እየፈሩ እየሸሹዋትም ጭምር እንጂ… እንደምሳሌ አቶ ኡሞት ኡቦንግ (እኒህ ሰውዬ በቃ የምር ስራሽ ያወጣሽ ብለው ጥለዋት ኮበለሉ አይደል…)፣ ሌላ ምሳሌ አቶ ጁነዲን ሳዶ (እርሳቸው እንኳ እዚሁ እኔው ጎረቤት ነው ያሉት) አሁንም ምሳሌ አቶ አባመላ (እኒህኛው ተመላላሽ ናቸው እንዴት… እንዴት ማለት ጥሩ ነው…) እንቀጥል…
ባለፈው ሰሞን እኒህ አባ መላ የተባሉ ሰውዬ “ኢሃአዴግ ታማለች ከዚህ በኋላ አትድንም” ብለው ፈርተው ትተዋት መሄዳቸው አጀብ ተበሎ ሲነገር ነበር። አሁን ደግሞ ተመልሰው፤ “ማሪኝ በዬሻለሁ እሞትብሻለሁ…” ብለው እያዜሙላት ነው በሎ አካባቢው ለጉድ እያወራ ነው።
እኔ በበኩሌ ይሄ የምስራች ነው ባይ ነኝ። ምንም እንኳ እርሷ (ኢሃአዴጋችን) ተመላላሽ ህክምና በሚያስፈልጋት ጊዜ ተመላላሽ አሰታማሚዎች መበራከታቸው ሀመሟን የሚያባብስው ሳይሆን እንደማይቀር ብንጠረጥርም፤ ቋሚው አባዱላም ሆኑ ተመላላሹ አባመላ ካገኙላት መላ ደስታው ወደር የለው አቶ አበበ ቶላ! ብዬ ከመግጠም ወደ ኋላ አልልም።
የምር ግን ኢህአዴግዬ ከተጠናወታት ደዌ ተፈውሳ ሰው ትሁንልን እንጂ እንኳን አባ መላ መንግስቱ ሃይለማሪያምስ ቢቀላቀሏት ምን ችግር አለው… !
ምንም!
እናም እንመክራለን አቶ አባመላ እንኳን ተመለሱ የእናት ድርጅታችን ጤና መቃወስ (አንዳንዶች ስካር ነው ይሉታል) ከእለት እለት እየባሰ ከራሷ ተርፎ በርካቶችን ጤና እየነሳ ነው፤ በዙሪያዋ ያሉት ዙሪያዋን ሰለሜ ሰለሜ እየጨፈሩ ጭራሽ ህመሟን ከማባባስ ወጪ መላ አላገኙላትም። (በነገራⶭን ላይ አቶ ሃይለማሪያም ቀበቷቸውን ፈተው ሰለሜ ሰለሜ ሲጨፍሩ አያችኋቸው…? ቆይማ አሳይዎታለሁ) …ምን ላይ ነበር ያቆምኩት እ…. በዙሪያዋ ያሉት እህአዴግዬ ለራሷ ታማ ሳለ ለራሳቸው ከመወፈር እና ከመጨፈር በዘለለ መፈተሄ አላመጡላትም ስለዚህ ሊያክሟት ከሆነ መላ ሊያበጁላት ከሆነ እውነትም አባ መላ እንለዎታለን እንጂ ምንም ቅር አይለን!
መግለጫ
ኢትዮጵያ የመትገኙ ወዳጆቼ አባ መላ ማናቸው ብላችሁ ግር ካላችሁ እናነተ የማታውቁት ስንት ጉድ አለ መሰላችሁ ከማለት ውጪ መልስ የለኝም!

No comments:

Post a Comment