አሜሪካ መለስ ከቆፈሩት ጉድጓድ ለመውጣት ወስናለች
ለአፍሪካ ቀንድ ሰላም ብቸኛ ተዋናይና ፊት አውራሪ አድርጎ ራሱን የሾመው ኢህአዴግ ለቀጠናው ስጋት እንደሚሆን ተጠቆመ። አልሸባብንና አልቃይዳን ከምንጩ እናጠፋለን በሚል ስትራቴጂ መለስ ከቆፈሩት ጉድጓድ ውስጥ ሰምጣ የነበረችው አሜሪካ ከጉድጓዱ ለመውጣት ወስናለች። ኢትዮጵያዊያን የሚያምኑትና የሚቀበሉትን መሪ በድፍረት አደባባይ የማውጣት ሃላፊነቱ “አገር ወዳድ” በሚሉ ዜጎችና የተቃዋሚ ፓርቲ አመራሮች ጫንቃ ላይ ነው።
ህወሃት ያቋቋማቸው ጥቃቅን መንግስታት ከህዝብ ይልቅ ለህወሃት የወደፊት እቅድ ታማኝ በመሆን መጓዛቸው ከቀን ወደቅን የፈጠረው ስሜት ኢህአዴግን እየበላው እንደሆነ የጠቆሙ የዜናው ምንጮች፣ ኢህአዴግ የምስራቅ አፍሪቃ የሰላም አባት ሊሆን ቀርቶ የራሱንም ችግር መፍታት ወደማይችልበት የቁርሾ ማሳ ውስጥ እንደሚገኝ አመልክተዋል።
ህወሃት “በነጻ አውጪነት” ያሰላውና፣ ይህንኑ ዓላማውን በፈለገበት ቀን ተግባራዊ ለማድረግ ያመቸው ዘንድ በየክልሉ ለጣጥፎ ያቋቋማቸውን ፓርቲዎች ሲመሩ የነበሩት አቶ መለስ በድንገት ካለፉ በኋላ ኢህአዴግ ውስጣዊ ሰላሙ መናጋቱ በተደጋጋሚ እየተገለጸ ነው። ኢህአዴግ በበኩሉ “የጓድ መለስን ውርስና ራዕይ ያለማዛነፍ እናስቀጥላለን” እያለ አገሪቱን በደቦ እንድተመራ ማድረጉ የሚታወስ ነው።
አቶ መለስ በጓዶቻቸው ቋንቋ “ተሰው” ከተባለበት ጊዜ ጀምሮ ምክትል ጠ/ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝን ለመተካት ተቸግሮ ነበር። ደህንነቱን፣ መከላከያውን፣ ፖሊስና ዋንኛ የአገሪቱን ተቋማት ጠቅልሎ የያዘው ህወሃት በቀጥታ አሜሪካ ባደረገችው ጫና ሳይወድ በግዱ አቶ ሃይለማርያምን በጠ/ሚኒስትርነት ለመሰየም ተገደደ። የስልጣን ክፍተቱን በተመለከተ አቻ ድርጅቶችና ህወሃት ውስጥ አለመግባባት ተፈጥሮ ስለነበር “ምደባ” በሚል ኢትዮጵያ በደቦ የሚመሯት አራት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሮች ተሰየሙላት።