ኦባንግ ለቴድሮስ መልክት ላኩ
December 4, 2013 06:47 pm By
Editor
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን)
ኅዳር 23፣ 2006 ዓም
ኢትዮጵያውያን ስደተኞችን ወዳገራቸው የመመለስ ግዴታው የህወሃት/ኢህአዴግ ነው!
ግልጽ ደብዳቤ ለሚኒስትር ቴድሮስ አድሃኖም ገ/የሱስ
____________________________________________________________
ለዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም ገብረየሱስ
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር
አዲስ አበባ
ኢትዮጵያ
ሚኒስትር ቴድሮስ አድሃኖም፤
ለአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ኢትዮጵያውያንን በቀለም፣ በዘር፣ በጎሣ፣ በቋንቋ፣ በጾታ፣ በክልል፣ ወዘተ ሳይከፋፍል በየትኛውም የዓለም ክፍል (ኢትዮጵያንም) ጨምሮ የሚደርስባቸውን ማንኛውም ዓይነት ማኅበራዊ ኢፍትሃዊነት ለመከላከል፣ ለማስቆም፣ ለማጋለጥ፣ ወዘተ እና ባሉበትም ቦታ ሁሉ ከፈጣሪ የተሰጣቸውን መብት ለማስጠበቅ የቆመ ድርጅት ነው፡፡ ሆኖም ግን እኔ ኦባንግ ሜቶ ይህንን ደብዳቤ የምጽፍልዎ የዚህ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር እንደመሆኔ ብቻ ሳይሆን የውቢቷ ኢትዮጵያ የደም ውጤት በመሆኔ እንደ አንድ ወንድም በመሆንም ጭምር ነው፡፡
ይህንን ደብዳቤ የምጽፍልዎ እርስዎንም ሆነ እርስዎ አባል የሆኑለትን የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) እና ኢህአዴግን ለመለመን ወይም ለማስደሰት ሳይሆን በሳዑዲ አረቢያና በሌሎች የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ውስጥ በኢትዮጵያዊ ሕዝቤ ላይ እየደረሰ ያለውን ከሰብዓዊነት ውጪ የሆነ አሰቃቂ ተግባር የማስቆምና አስቸኳይ መፍትሔ የማምጣት ግዴታ ህወሓት/ኢህአዴግ እንዳለበት ለማስታወቅ ነው፡፡
በመሆኑም እኔና እርስዎ የፖለቲካም ሆነ የአስተሳሰብ ልዩነት እንዳለን ግልጽ ቢሆንም አገር “እየመራሁ ነኝ” የሚለው ህወሃት/ኢህአዴግ የኃላፊነት ቦታ ላይ ያስቀመጥዎት እርስዎን በመሆኑ ይህ ጉዳይ በቀጥታ ከሚመለከታቸው ሰዎች አንዱ ነዎት፡፡ ከሥልጣኑም ጋር አብሮ ከፍተኛ የሆነ ኃላፊነት ይመጣል፤ ይህም በሁሉም ዘንድ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ህወሃት/ኢህአዴግም የሕዝብ ውክልና ባይኖረውም እንኳን ለእያንዳንዱ ነገር በቀጥታ ተጠያቂ ነው፡፡ ስለሆነም በዚህ ደብዳቤ ላይ የማሰፍራቸው ነጥቦች እርስዎንም ሆነ ህወሃት/ኢህአዴግን የሚያስደስት ላይሆን ይችላል፡፡ በተለይ በሳዑዲና በሌሎች የመካከለኛ ምስራቅ አገራት በወገኖቻችን ላይ የሚደርሰው ግፍ በዓለም ዙሪያ ተበትነው በሚገኙ ኢትዮጵያውያን ላይ ያሳረፈው ተጽዕኖና ኃፍረት እንዲሁም ቁጭት ይህ ነው ተብሎ የሚነገር እንዳልሆነ ህወሃት/ኢህአዴግ በሚከተለው የመረጃ ማፈን ፖሊሲ የኢትዮጵያ ሕዝብ መመልከት ባይችልም እርስዎና አብሮዎት ያሉት ሳታዩት ያለፋችሁት ጉዳይ አይደለም፡፡ ይህንን ደብዳቤ የምጽፍልዎ መረጃን በመመርኮዝ በመሆኑ ለምጽፈው እያንዳንዱ ነገር ሙሉ ኃላፊነት በመውሰድ መሆኑን አስቀድሜ ላስገነዝብዎት እወዳለሁ፡፡
ባለፉት ሳምንታት በ30 አገራት የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በ80 ከተሞች ውስጥ ሰላማዊ ሰልፍ በማድረግ በአንድ ድምጽ በሳዑዲ አረቢያ በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው ግፍ ይቁም በማለት ቁጣችንን ስናሰማ ቆይተናል፤ አሁንም ቀጥሏል፡፡ ይህ እየተደረገ ያለበት ምክንያትም በሳዑዲ ያሉት ኢትዮጵያውያን ከአንድ የተወሰነ ክልል ወይም የአንድ ጎሣ ቋንቋ ተናጋሪ ወይም የተወሰነ የኅብረተሰብ ክፍል ወዘተ ስለሆኑ ሳይሆን በቅድሚያ ሰብዓዊ ፍጡራን ስለሆኑ ከዚያም በላይ የእኛንም ኢትዮጵያዊነት ማንነትና ክብር የሚነካ በመሆኑ ነው፡፡ታዲያ ለዚህ ቀውስ መፍትሔው ለመንገድ ሥራ እንደሚገኝ ድጎማ ከዓለም ባንክ ወይም ከተባበሩት መንግሥታት ወይም ከሌሎች ለጋስ አገራት ወይም ደግሞ እንደ “ህዳሴ ግድብ ቦንድ” ከዳያስፖራ የሚገኝ አይደለም፡፡ በተጻጻሪው ለዚህ ቀውስ ዋንኛውን ኃላፊነት የሚወስደውና በሳዑዲ የሚሰቃዩትን ኢትዮጵያውያንን የመታደግ ግዴታው የህወሃት/ኢህአዴግ ነው!
ይህ በኢትዮጵያውያን ላይ እየደረሰ ያለው ሰቆቃ የሁላችንንም ህልውና የነካ በመሆኑ “በእርግጥ ኢትዮጵያዊን አገር አላቸው ወይ?” ብለን እንድንጠይቅ ያደረገን ሆኗል፡፡ በተጻጻሪው ግን በህወሃት/ኢህአዴግ በኩል የሚታየው የውሳኔ አሰጣጥ እና እርምጃ አወሳሰድ አናሳነት እንዲሁም ዝግተኝት በአመራር ላይ ያሉትን ሁሉ ስለ ችግሩ ያላቸው የግንዛቤና የአመራር ደካማነት ያለአንዳች ጥያቄ በጉልህ ያሳየ ነው፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ፈርጀ ብዙ ለሆነው የኢትዮጵያ ችግር ዋንኛ ተጠያቂ ህወሃት/ኢህአዴግ ቢሆንም የችግሩ አፈታት ግን ለሥራ ባልደረቦች ጊታር የመጫወት ያህል ወይም በጥቂት ቃላት ትዊተር ላይ መልዕክት የመላክ ያህል የቀለለ እንዳልሆነ እሙን ሆኗል፡፡