Wednesday, August 21, 2013

በሰሜን ኮሪያ የደናግላት ቁጥር መመናመን ፕሬዚዳንቱን አሳስቧል!


በኢትዮጵያስ?

north korea


ወጣቱ የሰሜን ኮሪያ መሪ ኪም ጆንግ እን ለሚያካሂዱት የዳንስ ስኳድ በቂ ደናግልት ለማግኘት መቸገራቸውን የደቡብ ኮሪያ ዜና ቾሱን ኢልቦ ገለጸ፡፡
ሰሜን ኮሪያ ለፕሬዚዳንቷ ክብር የምትጠቀምባቸው ዳንሰኞች የሚውጣጡት ከደናግልት ሴቶች ነው፡፡ ለዚህ ፕሬዚዳንቱን ለማዝናናት የሚደረገው የዳንስና ሙዚቃ ሙያ አባል ለመሆን የሚችሉ ድንግል ሴቶች በአብዛኛው ወጣቶችና የኮሌጅ ተማሪዎች እንደሆኑ ተዘግቧል፡፡ ክብረንጽህናን መጠበቅም ዋንኛው ቅድመ ሁኔታ ነው፡፡
ሆኖም ሰሜን ኮሪያ ካለባት ከፍተኛ የኢኮኖሚ ችግር ባሻገር አሜሪካንን ጨምሮ ምዕራባውያን በጣሉባት የኢኮኖሚ ማዕቀብ የአገሪቱን ኢኮኖሚ አሽመድምዶታል፡፡ በመሆኑም ሴቶች የትምህርት ወጪያቸውን ለመደጎም እንዲሁም የኑሮውን ውድነት ለመቋቋም በሴተኛ አዳሪነት በመሰማራታቸው የደናግልቱ ቁጥር ባልተጠበቀ ሁኔታ ለማሽቆልቆሉ እንደ ምክንያት ተጠቅሷል፡፡
ሴቶቹን የመረመሩት ወታደራዊ ሃኪሞች እንደገለጹት ከተመረመሩት የ16 ዓመት ሴቶች መካከል 60በመቶው በወሲብ ግንኙነት ድንግልናቸውን ያጡ መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ሁኔታው ለፕሬዚዳንቱ የዳንስና ሙዚቃ ቡድን አባልነት የሚመዘገቡት “ብቃት” ያላቸው ዳንሰኞች ቁጥር ችግር ላይ ጥሎታል፡፡
ለሴተኛ አዳሪነት ያጋለጣቸው የኑሮው ሁኔታ እንደሆነ ቢገለጽም አብዛኛዎቹ ደምበኞቻቸው ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት ሲሆኑ ሴቶቹ በሚያገኙትም ገንዘብ ለኑሮ ከሚያስፈልጋቸው ሌላ ለጌጣጌጥ፣ ለሞባይል ስልክ፣ የጋብቻ ወጪያቸውን ለመሸፈን፣ ወዘተ እንደሚጠቀሙበት ዜናው ጨምሮ ገልጾዋል፡፡

በአገራችን እየተከሰተ ያለው ከህጻናት ጀምሮ እስከ አዋቂ አልፎተርፎ ደግሞ አሁን በተመሳሳይ ጾታ መካከል በሚደረግ ሰዶማዊነትና የዚህ ሰለባ የሆኑት ደግሞ ህጻናት ወንዶች ልጆች መሆናቸው፤ ከሰሜን ኮሪያው ሁኔታ ጋር ሲስተያይ በሰሜን ኮሪያ 40በመቶ ደናግልት መገኘታቸው “የጻድቃን አገር” ሊያስብላት የሚችል ነው፡፡
በፈረቃ የሚተኙ ልጆች ባሉበትና እናት ልጇን ለወሲብ ገፍታ የምትልክበት ሁኔታ ባለባት ኢትዮጵያ፤ ባለሥልጣናት “በዝግ ቤቶች” ወሲብ በሚታሙበት፤ የሴቶች አከፋፋይና መልማዮች ኢትዮጵያ ውስጥ ታላቅ ክብር እንደሚሰጣቸው በሚሰማበት፤ ዘመንና ጊዜ ገንዘብ ያርከፈከፈላቸው ማታ ለይምሰል በቤታቸው፣ ቀን ላይ ዱባይ ሄደው ወሲብ ፈጽመው ለመመለሳቸው መረጃዎች በሚወጡበት ባሁኑ ወቅት፤ በኢትዮጵያ የሰሜን ኮሪያ ዓይነት ተመሳሳይ ችግር አይኖርም ብሎ ማሰብ በሰማነው ዜና ለመቀለድ የሚያስችለን አይሆንም፤ ዜናውንም የመዝናኛ ዜና አያደርገውም፡፡
በሚያብረቀርቅ ሆቴል ውስጥ ተቀምጠው ህጻናትን እንደ ዶሮ በሽሮ እያስፈተጉ ሲፈልጉ ለወሲብ ሲያሻቸው ደግሞ ለሽያጭ የሚያቀርቡ “የልማት አልኝታዎች” መኖራቸውን በምንሰማበት ባሁኑ ወቅት፣ ሴቶች ልጆቻችን ብቻ ሳይሆኑ የአስርና የ15ዓመት ህጻናት ወንዶች የዚሁ ልቅና መረን ያጣ የወሲብ ሰለባ መሆናቸው የመሪያችንና “የዕድገታችን ብቃት” ማሳያ ብለን እንውሰደው ይሆን?
ይህንን “ዓይነቱን ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን እንዲሁም ህዳሴ” ለማንም አሳልፈው እንዳይሰጡ “በመስጋት ለትውልድ አውርሰው (“ሌጋሲ” ትተው)” ለሞት የበቁትን የኢትዮጵያ ሃፍረትና ውርደት የጡት አባት አቶ መለስ ዜናዊ አንደኛ ዓመት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ እየዘከረች መሆኗ “ምን እያደረግን ነው?” የሚያስብል ነው፡፡

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡

No comments:

Post a Comment