አብዲሳ የብዙ ጊዜ ወዳጄ ነበር፡፡ በየገጠሩ እየዞርን በርካታ ስራ አብረን ሰርተናል፡፡ የዋህነቱ እጅግ በጣም አስገራሚ ነበር፡፡ በየክልሉ ስንዞር አበሉን የሚጨርሰው “ቸገረኝ” ላለው ሁላ መበስጠት እንደነበር አብረነው የሰራ ሁላ እርሱን የምንለይበት ባህሪው ነው፡፡ ይሄ ልጅ በአንዱ ቀን ለስራ ልንሄድ የተቀጣጠርንበት ቦታ ሆነን ስንጠብቀው ስንጠብቀው ሳይመጣ ቀረ… ስልኩን ብንደውልልት አይሰራም፡፡ ካለንበት እየተንቆራጠጥን… ወደ ሶስት ሰዓት ድረስ ዘግይተን ጠበቅነው የውሃ ሸታ ሆነብን… ምን ሆነ ብለን እየተጨነቅን እንጀራ ነውና ጉዟችንን ቀጠልን…
አብረን ስንጓዝ ከነበርነው መካከል አብዲሳን በቅጡ የምናውቀው ሰዎች “ይሄኔ አንድ የታመ ሰው አጋጥሞት ሆስፒታል ሳላደርስ አልሄድም ብሎ ነው…” ….ወይ ደግሞ “…አንዱ ገንዘብ ተቸግሮ አጋጥሞት ምንም ሳያስቀር ገንዘቡን ሰጥቶ ወደ እኛ መምጫ ራሱ ተቸግሮ ይሆናል …” ካልሆነ ግን “…ዘራፊዎች አግኝተው ጉድ አድርገውት ሊሆን ይችላል…. እያልን መገመታችንን ተያያዝነው…
ግምታችን ሁሉ ትክክል አልነበረም፡፡
አብዲሳ በስንተኛው ጊዜ በቴሌቪዥን መስኮት መታየቱን ሰማን… በየዋህነቱ የተቸገረ በመርዳቱ የምናውቀው አብዲ “አሸባሪ” ተብሎ በመንግስት ቁጥጥር ስር ውሏል፡፡ አብዲሳ “አሻባሪ” ከተባለማ እኛ ምን ልንባል ነው… ብለን ራሳችንን እንደ ነውጠኛ የምናየው እኛ በጣም ተደነቅን!
አብዲ ወደ አምስት ወራት በማዕከላዊ፣ ወደ አምስት አመት በቃሊቲ እንዲሁም ሁለት ሶስት አመት ነው መሰለኝ በዝዋይ ማሰሪያ ቤቶች ቆይቶ ነፃ ነህ ተብሎ እስኪሰናበት ድረስ በአስር ቤቱ ውስጥ ሲደርስበት በነበረው መከራ ብዙ ጉዳት ደርሶበታል፡፡ ታድያ ከእስር ቤት ሊወጣ አካባቢ አንድ ባለስልጣን ብጤ ሰውዬ ጎብኝተውት ነበር፡፡