(ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)
ባለፈው ሰሞን አንድ ከ “ሰማእታት” የመታሰቢያ ሐውልቶች ጋር በተያያዘ ታሪክ ቀመስ ጽሑፍ መጻፌ ይታወሳል “አሳ ጐርጓሪ ዘንዶ ያወጣል” እንዲሉ ይህ ጽሑፍ ለንባብ ከበቃ በኋላ በፊት ለምን እንደሆነ በቅጡ የማይገቡኝ የነበሩ እጅግ የሚገርሙ ነገሮች ለምን ይደረጉ እንደነበር ከተለያየ አቅጣጫ በአካልና በመልእክት ካገኘኋቸው ግብረ መልሶች ተረዳሁ፡፡ በዚያ ጽሑፍ ላይ ኦሮሞና ትግሬ ነን የሚሉ ካድሬዎች በተለየ ሁኔታ ትኩረታቸው ተስቦ ነበር፡፡ አንዳንዶችም አነጋግረውኝ ነበር፡፡ በንግግራችን ውስጥ ከዚህ በፊት ያልተረዳኋቸው ነገሮች ግልጽ ሆኑልኝ፡፡ ለነገሩ ያልተረዳኋቸው ማለት ይከብዳል ነገሩ እጅግ የማገርምና ለማመንም የሚቸግር በመሆኑ ሁል ጊዜ እንግዳ ሰለሚሆንብኝና ለጉዳዩ ሁሌም አዲስ እንግዳ ስለሚያደርገኝ ነው፡፡ ባይሆን ስጠረጥራቸው የነበሩ ብል ይሻል ይመስለኛል፡፡
እናም እጅግ ገረመኝ በእርግጠኝነት እንደኔ ሁሉ ብዙው ሰው የሚደረጉ ነገሮች ዓላማቸው የገባው አይመስለኝም፡፡ ወያኔ ለካ አማራን እንዳያንሠራራ አድርጌ ሠብሬዋለሁ እንዳይነሣ አድርጌ አድክሜዋለሁ ብሎ ያምን ኖሯል፡፡ መቸም ሥራቸውን ያውቃሉና ነው እንዲህ ሊያስቡ የቻሉት፡፡ ለካ እንዲያው ሳናውቀው ገለውናል ጃል! ታዲያ እላቹህ እንዲህ ብለው እያሰቡ እያመኑ እያለ ይህ ጽሑፍ በዚያ ቅኝትና ይዘት መጻፉ አማራን በተመለከተ የነበራቸው ግምትና እምነት እንዳሰቡት ሳይሆን ቀርቶ ከ 20ዓመታት ቅጥቀጣና ድቆሳ በኋላ እንደነሱ አባባል እንደዚህ ዓይነት ጽሑፍ በእኔም ብቻ ሳይሆን ከእኔም በኋላ በሌሎች ወገኖችም በአጋጣሚ ተከታትሎ በአንድ ሰሞን በተለያዩ የብዙኃን መገናኛዎች መንጻባረቁና በአንባቢያን መወደዱ ለመግለጽ እጅግ በሚያስቸግር የመደነቅ ድባብ ውስጥ ከቷቸው ነበር፡፡
ይሄን ሁሉ ጉድ የማላውቀው የዋሁ የእግዚአብሔር በግ እኔ ደግሞ መደነቅ መገረማቸውን ሳይ እንዴ ይሄም ኖሯል ለካ ብዬ ሁኔታቸውና አስተሳሰባቸው ሁሉ እኔንም በተራዬ ከከባድ ድንጋጤ ጋር እጅግ እጅግ እጅግ አስደነቀኝ አስገረመኝ አዘንኩም፡፡ እንዲያው ሰው በተለያየ ምክንያት ዝም ሲል ጊዜ እጅ ሰጥቶ ተንበርክኮ መሰላቸውና ጭራሽም እንደሞተ ያህል ቆጥረውት ቁጭ አሉ፡፡ ወያኔ አማራን በተመለከተ አይቅበሩት እንጅ እንደሞተ እንዳበቃለት አድርገው ማሰባቸው ስሕተት እንደነበረ ከመጸጸት ጋር ይቆጩ ይዘዋል፡፡ እነሱ ዘመትንበት አጥፍተነዋል ያሉት ይህ ለሀገር፣ ለቅርስ፣ ለታሪክ፣ ለመለያ፣ ለማንነት፣ ለሃይማኖት ተቆርቋሪ የመሆንን ስሜት ወዴት ተደብቆ እንደተረፈ በአንከሮ እያጠኑት ይገኛሉ፡፡ በተለያዩ የብዙኀን መገናኛች ለመረዳት እንደቻላቹህት ማኅበረቅዱሳን አንዱ መደበቂያ መሸሸጊያ ነው ብለው በማመናቸው ማኅበሩን ለማፍረስ ለመዝጋት ሴራ እየጠነሰሱ ነው፡፡ በእርግጥ ይህ ማኅበር ከዚህ ቀደምም ቢሆን በወያኔ የዓይነ ቁራኛ የቅርብ ክትትል ስር የነበረ ማኅበር ነው፡፡ ማኅበሩን አቅጣጫውን ለማሳትና ወደ ሚፈልጉት መንገድ ለመውሰድ በርካታ ጥረቶችን ሲየደርጉ ቆይተዋል፡፡