Wednesday, November 27, 2013

በሳውዲ በኢትዮጵያውያን ላይ የሚደርሰው ሰቆቃ ቀጥሏል


ነፍሰጡር ኢትዮጵያዊት በአሰቃቂ ሁኔታ ሞታለች

saudi ethio13


ሪያድ አሚራ ኑራ ዩኒቨርስቲ በሚገኝ ጊዜያዊ መጠለያ ሜዳ ላይ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን እና በሳውዲ ፖሊሶች መሃከል በተነሳ ግጭት አንዲት ነፍሰጡር ኢትዮጵያዊት በአውቶብስ ተገጭታ ህይወቷ አለፈ።
ሪያድ መንፉሃ እየተባለ ከሚጠራ አካባቢ ሰሞኑንን በሳውዲ ፖሊሶች ታፍሰው ከከተማይቱ 120 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ወደ ምትገኝ፡ በተለምዶ ሚንዛህሚያ እየተባለ የሚጠራ እስርቤት ተወስደው ከነበሩ 10 ሺህ ኢትዮጵያውያን መሃከል ግማሽ ያህሉ በ17 አውቶብስ ተጭነው ማምሻውን ሪያድ ከተማ አሚራ ኑራ እየተባለ የሚጠራ ዩኒቨርስቲ ሜዳ ላይ መጣላቸውን ተከትሎ ከባድ ሁከት መቀስቀሱን ከሪያድ የሚደርሱ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ይህን ተከትሎ በዩኒቨርስቲው ግቢ ውስጥ በኢትዮጵያውያኑ ስደተኞች እና በሳውዲ ፖሊሶች መሃከል ከባድ ግጭት መከሰቱን የሚገልጹት እነዚህ ምንጮች አዲት ነፍሰጡር ሴት ከድንጋይ ውርወራው ለማምለጥ ከግቢው ለመውጣት ሲበሩ በነበሩ አውቶብሶች በአንዱ ተጭፍልቃ መሞቷን ገልጸዋል። ግጭቱ በጣም ዘግናኝ፡ አሰቃቂ እንደነበር የሚገልጹት የአይን ምስክሮች የሳውዲ ፖሊሶች ማንም ሰው ካሜራ እንዳይቀርጽ ለማገድ ከአካባቢው ኢትዮጵያውያኑንን በማራቅ አስከሬኑን ነጭ ነገር ሸፍነው በቅጽበት በአምቡላንስ ተጭኖ ወደ ሆስፒታል እንዲወሰድ ማድረጋቸውን ገልጸዋል።
ዛሬ ረፋዱ ላይ በ17 አውቶብስ ተጭነው ሚንዛህሚያ እየተባለ ከሚጠራ አካባቢ እንደመጡ ከሚነገርላቸው ኢትዮጵያውያን መሃከል በአብዛኛዎቹ ሴቶች ህጻናት እና ነፍሰጡር እንደሆኑ የሚናገሩት ምንጮች አውቶብሶቹ የተጠቀሰው አካባቢ ሲደርሱ በውስጥ የነበሩ ኢትዮጵያውያኖች ኤርፖርት እንወስዳችሃለን ብላችሁ እዚህ ባዶ ሜዳ ላይ አምጥታችሁ ለምን ትበትኑናላችሁ በማለት ከአውቶብሱ አንወርድም በሚል የኡ ኡ ታ ጩሀት በማሰማት ተቃውሞቸውን ሲገልጽ የሳውዲ ፖሊሶች የአካባቢውን ጸጥታ ያደፈርሰውን የህዝብ ኡ ኡታ ጩህት ለማርገብ ጥረት በሚያደርግበት ወቅት ድንጋይ ውርወራ መጀመሩን የሚገልጹ እማኞች በፖሊስ እና በህዝቡ መሃከል በተነሳው ግጭት አያሌ ህጻናት እና አረጋውያን መረጋገጣቸውን በመጥቀስ እስካሁን በወገኖቻችን ህይወት ላይ የደረሰው አደጋ በውል ባይታወቅም ብዛት ያላቸው አምቡላሶች ኢትዮጵያውያኑ ከተጠለሉበት ግቢ «ሳይረን» እያሰሙ ሲወጡ መታየታቸውን አክለው ገልጸዋል።

ተዋርደን አንቀርም!!!


ኢ/ር ይልቃል ጌትነት (የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር)

ethiopia


ሳውዲ አረቢያ በዜጎቻችን ላይ እያደረሰች ያለውን ግፍና በደል በሰላማዊ ሰልፍ ለመቃወም ፓርቲያችን በወሰነው መሰረት ለሚመለከተው ክፍል አሳውቀን ነበር፡፡ መቸም ህዝባችን በጭቆና ውስጥ ስለኖረ በመብቱና በግዴታው መሀል ያለውን ድንበር በውል ካለመረዳቱ የተነሳ ሰልፉ እንዲደረግ ስለመፈቀዱ በተደጋጋሚ ስንጠየቅ ነበር፡፡ ህጉ የሚለው ግን ማስፈቀድ ሳይሆን ማሳወቅ ብቻ ነው፡፡ በተቃራኒው መንግስት በተለያዩ ጉዳዮች ሳቢያ በእለቱ ለሰላማዊ ሰልፉ የደህንነት ከለላ መስጠት የማይችልበት ሁኔታ ከገጠመው ሰልፉን ለጠራው አካል ችግሩን ገልጾ ቀኑ እንዲተላለፍለት ይጠይቃል፡፡ በመሆኑም ይህን መሰል ጥያቄ ከሚመለከተው መስሪያ ቤት ለፓርቲያችን ባለመቅረቡ በሙሉ ልብ ቅድመ-ዝግጅት ማድረጉን ተያያዝን፡፡ ሁሌም ቢሆን መንግስት ሰበብ ፈልጎ ሊወነጅለንና ከመስመር ሊያስወጣን እንደሚፈልግ በሚገባ እናውቃለንና በጥቃቅን ጉዳዮች ላይ ሳይቀር ጥንቃቄ እናደርጋለን፡፡ ለሚመለከተው መስሪያ ቤት ባሳወቅን በአስራ ሁለት ሰአታት ውስጥ ምላሽ ስላልመጣ ሙሉ በሙሉ ህጋዊነታችንን አረጋግጠናል ማለት ነው፣ እነሱ ደግሞ ጠብ-መንጃ በእጃቸው አለና የፈለጉትን ሁሉ ማድረግ ይችላል፡፡
አቶ ሽመልስ ከማል ለሚዲያወች የሰጡትን ፍጹም ከእውነት የራቀ ውንጀላና ሰበብ አዳምጨዋለው፡፡ “ሰላማዊ ሰልፉን ያገድንበት ምክንያት ጸረ-አረብ መፈክሮች ስለነበሩ ነው” ብለዋል፡፡ መጀመሪያ ደረጃ ሰልፉ ገና ከግቢው ፈቅ ሳይል ነው ያፈኑት፣ ሆኖም የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም አንድ በአንድ እየሆንን ወደ ሰላማዊ ሰልፉ መዳረሻ ለመሄድ ስንሞክር የተወሰኑ አመራሮችን አራት ኪሎ አካባቢ ያዙን፣ እነሱ ቀድሞውኑ ሰልፉ እንዳይካሄድ ስለወሰኑ ነው እንጅ ትንሽ እንኳ ተንቀሳቅሶ የሰልፉን ባህሪ ለመገምገም ምንም እድል አልሰጡንም፡፡
ለምሳሌ ሰልፉን እንደምናደርግ ይፋ ባደረግን ማግስት ከራዲዮ ፋና ተደውሎ አንዳንድ ጥያቄዎች ተጠይቄ ነበር፡፡ በቃለ-መጠይቁ ሰላማዊ ሰልፉ በዜጎቻችን ላይ የሚደርሰውን በደል በመቃወም እንደምናደርግ ተናግረናል፡፡ ጋዜጠኛው ለሰላማዊ ሰልፉ ተሳታፊዎች መልዕክት ካለ ብሎ በጠየቀኝ ወቅት የሳውዲ አረቢያ ሰንደቅ አላማ ላይ ያለው ምልክትና ጽሁፍ ሀይማኖትን የሚመለከት በመሆኑ ዜጎች በስሜታዊነት ባንዲራ እንዳያቃጥሉ፣ እነሱ ቢያዋርዱንም እኛ ግን ክብር ያለን ዜጎች ስለሆንን ተቃውሟችንን ጨዋነት በተሞላበት ሁኔታ ማካሄድ እንዳለብን ተናግሬ ነበር፡፡ ከሰላማዊ ሰልፉ በፊት በዚህና በተለያየ መንገድ በማያሻማ ሁኔታ መልዕክት ባስተላልፍም እነሱ ግን ይህን በመቁረጥ አላስተላለፉትም፡፡ እነዚህና ሌሎች ምክንያቶች ሲደመሩ የአቶ ሽመልስ ከማል ንግግር ነጭ ውሸት መሆኑን ያስገነዝባል፡፡

Friday, November 22, 2013

በ1997ቱ የኢትዮጵያ ምርጫ ታዛቢ የነበሩት አና ጐሜዝ አዲስ አበባ ሊመጡ ነው


Photo: © Europen Parliament/P.Naj-Olearipietro.naj-oleari@europarl.europa.eu


በ1997 ዓ.ም. በኢትዮጵያ በተካሄደው አገር አቀፍ ምርጫና ምርጫውን ተከትሎ ተከስቶ በነበረው የፖለቲካ ውዝግብ አካል የነበሩት የአውሮፓ ኅብረት የምርጫ ታዛቢ አና ጐሜዝ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ ነው፡፡
በኢትዮጵያ በ1997 ዓ.ም. ተካሂዶ የነበረውን ምርጫ በአውሮፓ ኅብረት ተወክለው ምርጫውን በዋና ታዛቢነት የመሩትና የአውሮፓ ኅብረት ፓርላማ አባል የሆኑት አና ጐሜዝ፣ ምርጫውን አስመልክቶ ባወጡት ሪፖርት ኢሕአዴግ ከሚመራው መንግሥት ጋር ጥልቅ የሆነ ግጭት ውስጥ ገብተው ነበር፡፡
አና ጐሜዝ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር በምርጫው ሳቢያ ውዝግብ ከገቡበት ጊዜ አንስቶ የኢሕአዴግን ፖለቲካ በተለይም የሰብዓዊ መብት አያያዙን ከመተቸት ተቆጥበው አያውቁም፡፡ ይሁን እንጂ ከምርጫው በኋላ ወደ ኢትዮጵያ መጥተው አያውቁም፡፡
በሚቀጥለው ሳምንት በኢትዮጵያ አስተናጋጅነት በሚካሄደው የአፍሪካ፣ የካረቢያንና የአውሮፓ ኅብረት አገሮች የጋራ የፓርላማ አባላት ጉባዔ ላይ ለመገኘት በአገሮቹ ከተወከሉ ግለሰቦች መካከል አና ጐሜዝ እንዳሉበት በኢትዮጵያ በኩል anaየጉባዔው አስተባባሪ ከሆነው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምንጮቻችን ለመረዳት ተችሏል፡፡ የኢትዮጵያ መንግሥት ለፖርቹጋላዊቷ የፓርላማ ተወካይ አና ጐሜዝ ቪዛ ሰጥቶ ይሁን ከልክሎ ለማወቅ ያደግነው ጥረት አልተሳካም፡፡ ይሁን እንጂ ግለሰቧ በቲዊተር ገጻቸው ላይ በአዲስ አበባው ጉባዔ ላይ እንደሚገኙ አረጋግጠዋል፡፡ አና ጐሜዝ በ1997 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ምርጫ ትዝብት ሪፖርታቸው፣ ምርጫው ነፃና ፍትኃዊ እንዳልነበር ሪፖርት በማድረጋቸው ሪፖርቱ የውዝግቡ ምንጭ መሆኑ ይታወሳል፡፡ ይህንን ተከትሎ የቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ ሪፖርቱን ከማጣጣል አልፈው ግለሰቧን በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ መዝለፋቸው ይታወሳል፡፡
አና ጐሜዝ በበኩላቸው እስከቅርብ ጊዜ ድረስ በኢትዮጵያ መንግሥት ላይ የዕርዳታ ማዕቀብ እንዲጣልበት እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ ‹‹ዓለም አቀፉ ኅብረተሰብ በተለይም የእንግሊዝና የአሜሪካ መንግሥታት በኢትዮጵያ ዜጎች ላይ መንግሥት የሚፈጽመውን በደል እያዩ እንዳላዩ፤ እየሰሙ እንዳልሰሙ ችላ ብለዋል፤›› በማለት ከዓመት በፊት የሰላ ትችት በመሰንዘር የአውሮፓ ኅብረት ለኢትዮጵያ የሚደረገውን ዕርዳታ እንዲያቆም ተከራክረዋል፡፡ (ሪፖርተር)

Saturday, November 16, 2013

ጭንቁን ቀን እንዴት እንለፍ!?


የመረጃው ክፍተት የለያየን ግፉአን ዜጎችና ዲፕሎማቶች

ethsaudi


ጥላቻው እያደገ ሔዷል፣ ሳውዲ አሰሪዎች ኢትዮጵያውያን የቤት ሰራተኞቻቸውን ድሮ ድሮ በአረቦች ዘንድ የተከበርን፣ የታፈርን የእኛን የሃበሻ ልጆች “ጨካኞች ፣ የማይታመኑ!” እያሉ ጥላቻቸውን መገልጽ ጀምረዋል። November 14,2013 የወጣው አረብ ኑውስ Recent clashes make Saudis wary of Ethiopian maids በሚል ርዕስ ስር ሳውዲ አሰሪዎች ኢትዮጵያን ሰራተኞችን ለማባረር እየዛቱ ነው! ይህ የአረብ ኒውስ ዘገባ በሹክሹክታ የምንሰማው ቁልጭ አድርጎ ያሳያል።
የሪያድ መንፉሃን ግጭት ተከትሎ ደም እድገብሮም ለኢትዮጵያን ተሰጠው ወደ ሃገር ቤት የመግባትን እድል ለመጠቀም ከሃያ ሽህ በላይ ኢትዮጵያውያን የሪያድ መጠለያዎችን አጨናንቀዋል። እንዲውም በሪያድ የኢትዮጵያ አምሳደር ቁጥሩን ወደ ሃያ ሶስት ሽህ እንደሆነ ረቡዕ November 14,2013 ለወጣው አረብ ኒውስ አስታውቀዋል። አሁንም በሽዎች የሚቆጠሩ ወደ መጠለያ ለመግባት እየጎረፉ ነው። በመጠለያው የምግብና የሚጠጣ ውሃ እጥረቱ ደግሞ ኢትዮጰያውያኑ አጥር ሰብረው እንዲወጡ እያስገደደ ነው ተብሏል።
saudi ethio9በጅዳ እና በተለያዩ የሳውዲ ከተሞች ያሉ ህጋዊ መኖሪያ ፈቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያንም የሚይዙት የሚጨብጡት አጥተው በቋፍ ላይ ናቸው ። በሪያድ እና በተለያዩ ከተሞቸ ባሳለፍነው ቅዳሜ በመንፉሃው ሁከት ጭካኔ የተቀላቀለበት በሃገሩ ነዋሪዎች ተወሰደ በተባለው እርምጃ ገና በመሰራጨት ላይ ያለው መረጃ ምስል ህጋዊ ሆነ ህገ ወጥ የሆነውን ሁሉንም እያስጨነቀ ነው። እኔም እዚያው መንፉሃ ሆነውን የአይን እማኝ ከሰማሁ ወዲህ ከ16 አመታት በላይ የማውቃቸው ሳውዲዎች ይህን ፈጸሙ ለማለት ብቻ ሳይሆን በዚህች ሃገር ይህ መሰል ግፍ በሰው ልጅ ይፈጸማል ለማለት ተቸግሬያለሁ። እውነት መሆኑን ደጋግሜ ሳሰላስለው ደግሞ የሳውዲ ኑሮ እየጎረበጠኝና ተስፋየን እየሟጠጠው ሄዷል። ብዙዎች በዚህና በመሳሰለው የማሳደድ ችግር ምክንያት ወደ ሃገር መግባት ይፈልጋሉ፣ በሪያድ ከመንፉሃ በተጨማሪ በኮንትራት ስራ የመጡና ለበርካታ አመታት በሳውዲ ነዋሪ የሆኑት ሳይቀሩ እንደ መንፉሃ ግፉአን በውድ የገዙትን እቃ በርካሽ እየሸጡና መኖሪያ ፍቃዳቸውን አሽቀንጥረው በመጣል ወደ መጠለያው እየገቡ ነው ።
“በመንፉሃ ቁጥራቸው የማይታወቅ ኢትዮጵያውያን ሞተዋል … ” በሚል ነዋሪው በሚሞግተውና መንግስት “ሶስት ብቻ ነው የሞተው!” ያላቸው ኢትዮጵያውያን ደም ፈስሶ በድርድርም ቢሆን ሳውዲዎች የጣሉትን ቅጣት አንስተው ህገ ወጥ ነዋሪዎች በፍላጎት እንዲገቡ ተፈቅዷል። ይህ ለሪያድ ነዋሪዎች የተሰጠው እድል በሁሉም ከተማ ላሉት ዜጎች ስለመስራቱ ማወቅ ባለመቻሉ ነዋሪው ተጨናንቋል። በመካ ያለው ከበድ እያለ መጥቷል። በጅዳ ከንደራ የሚፈራውን ያህልም ባይሆን በእለተ ሃሙስ November 14,2013 እኩለ ቀን ለግማሽ ሰአት የዘለቀ ፍጥጫ እንደ ነበር እለታዊው አረብ ኒውስ ጋዜጣ ከቀትር በኋላ ዘግቦታል። በጣይፍ፣ በጀዛንና በአቅራቢያ የተለያዩ አካባቢዎችም ጉዳይ አሳሳቢ ነው። ቢያንስ የመንግስት ሀላፊዎች መረጀ በመስጠት ሰውን ማረጋጋት ካልቻሉ ያየን የሰማነው የመንፉሃ አደጋ በከፋ መልኩ እንዳይጫር ስጋት አለኝ።

መቋጫ ያጣው የወገኖቻችን ስቃይ እና በደል በሳውዲ አረቢያ አሁንም ቀጥሏል!


ethio saudi 10


ትላንት አመሻሹ ላይ ሪያድ ከተማ በተለምዶ መንፉሃ እየተባለ የሚጠራ አካባቢ በሚገኙ ኢትዮጵያውያን አገርሽቶ በዋለው ተቃውሞ የሞተ ባይኖርም ኢትዮጵያውያኑ ድምጻቸውን ከፍ አድረገው አማራው አንድነን … ትግሬውም አንድነን … ጉራጌው አንድነን … መብታችን ይከበር … እኛም ሃገር አለን ወዘተ… በሚል መፈክር ታጅበው ብሶታቸውን ሲያሰሙ መዋላቸውን የሚገልጹ የአይን እማኞች የሳውዲ የጸጥታ ሃይሎች ተቃውሞውን ለመበተን በከፈቱት ተኩስ አካባቢውን ወደ ጦርነት አውድማ ለውጦት ማምሸቱን ይገልጻሉ።
የጸጥታ ሃይሉ በ10 ሺህ የሚቆጠሩ አውቶማቲክ የጦር መሳሪያ የታጠቁ ተጨማሪ ልዩ ፈጥኖ ደራሽ፡ ኮማንዶዎች በመታገዝ የኢትዮጵያውያኑን ተቃውሞው መግታት ተችሏል ብለዋል። እነዚህ ምንጮች ትላንት ተቀስቅሶ በነበረው ሁከት ጥቂት ተሽከርካሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱን በማውሳት ሰሞኑን የሳውዲ አረቢያ መንግስት በውጭ ሃገር ነዋሪዎች ላይ ያወጣው ህግ የጊዜ ገደብ መጠናቀቁን ተከትሎ የሳውዲ ጸጥታ ሃይሎች በኢትዮጵያውያኑ ላይ እየወሰዱ ባሉት የተናጠል እርምጃ አያሌ ወገኖቻችን ወደ ሃገሩ ለመመለስ ከየመኖሪያ ቤቱ ነቅሎ አደባባይ ቢወጣም ወደ ሃገር መግባት የሚያስችሉት ነግሮች በኢትዮጵያ መንግስ በኩል ባለመመቻቸቱ ከሳውዲያኑ ወረበሎች አሰቃቂ ግድያ ተርፈው ወደ እስርቤት የተጓጓዙ ከ20 ሺህ የሚበልጡ ወገኖቻችን በምግብ ውሃ እና የመጸዳጃ ቦታ እጦት ቁም ስቅላቸውን እያዩ መሆኑ ተግልጾል።

ኢህአዴግ ከሳዑዲ ጋር መቆሙን አረጋገጠ!


ሰላማዊ ሰልፍ የወጡ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮች ታስረዋል

ethio saudi addis1


አዲስ አበባ ላይ በሳዑድ አረቢያ ኤምባሲ አጠገብ ሊካሄድ የነበረ የተቃዉሞ ሰልፍ በፖሊስ ተበተነ። አሶሺየትድ ፕረስ እንደዘገበዉ ፖሊስ በመቶዎች የሚቆጠሩን ሰልፈኞች ለመበታተን ኃይል ተጠቅሟል።
መንግስት ፈቃድ እንዳልተሰጠዉ በማመልከት ቁጥራቸዉን ባይጠቅስም የታሰሩ መኖራቸዉን ገልጿል። ሰልፉን ያስተባበረዉ የተቃዉሞ ወገን ሰማያዊ ፓርቲ በበኩሉ ሁለት ሊቃነመናብርቱን ጨምሮ አንድ መቶ ሰዎች ገደማ መያዛቸዉን አመልክቷል። የመንግስት ቃል አቀባይ አቶ ሽመልስ ከማል ፀረ አረብ ስሜት ሊፈጥር የሞከረ ያሉት ተቃዉሞ ሰልፍ አዘጋጆች ከሚመለከተዉ አካል ፈቃድ ባለማግኘታቸዉ እንደሚከሰሱ ለአዣንስ ፍራንስ ፕረስ ገልጸዋል። በፖሊስ ከተደበደቡት አንዱ እንደሆነ የገለጸዉ አስፋዉ ሚካኤል፤ መንግስት የሳዉዲ አረቢያን ድርጊት ላይ የቀረበዉን ተቃዉሞ ለምን ማገድ እንደፈለገ እንዳልገባዉ ለዜና ወኪሉ ገልጿል።
ethio saudi addis2ዘገባዉ አክሎም ፖሊስ አንዳንድ ጋዜጠኞች ያነሱትን ፎቶግራፍ መደምሰሱንም አመልክቷል። የመንግስት ቃል አቀባይን አስተያየት ማግኘት እንዳልተቻለም ተገልጿል። ለተለያየ ሥራ ሳዑድ አረቢያ የሚገኙ የዉጭ ዜጎች ሕጋዊ መኖሪያ ፈቃድ እንዲያወጡ የተሰጠዉ የጊዜ ገደብ ካለቀ ወዲህ እዚያ ያሉ ኢትዮጵያዉያን ጥቃት እየደረሰባቸዉ እንደሚገኝ እየገለፁ ነዉ።
የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም፥ በኢትዮጵያዉያን ላይ የሚፈፀመዉን በደል በመቃወም ዛሬ አዲስ አበባ በሚገኘዉ የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ አጠገብ አደባባይ ወጥተዉ ነበር። ይሁንና የአዲስ አበባዉ ወኪላችን ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር የጠቀሰዉ ጋዜጠኛ እንዳለዉ ሳዑዲ አረቢያ ዉስጥ በኢትዮጵያዉያን ላይ የተፈፀመዉ አዲስ አበባም ተደገመ።
የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት በሐገሩ በሚኖሩ ኢትዮጵያዉን ላይ የሚያደርሠዉን በደል፥ በተለያዩ አገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን በአደባባይ ሠልፍ እያወገዙት ነዉ። ትናንት እዚህ ጀርመን የሚኖሩ ኢትዮጵያዉያን ፍራንክፈርት ዉስጥ ባደረጉት ሠልፍ የሳዑዲ አረቢያ መንግሥት ኢትዮጵያዉያኑን፥ ማንገላታት፥ ማሠር፥ መደብደብ መግደሉን እንዲያቆም፥ የኢትዮጵያ መንግሥትም የዜጎቹን መብት እንዲያስከብር ጠይቀዉ ነበር።የአዲስ አበባ ነዋሪዎችም፥ በኢትዮጵያዉያን ላይ የሚፈፀመዉን በደል በመቃወም ዛሬ አዲስ አበባ በሚገኘዉ የሳዑዲ አረቢያ ኤምባሲ አጠገብ አደባባይ ወጥተዉ ነበር።

Friday, November 15, 2013

ሰባተኛው የለውጥ መዘውር ነጥብ እየቀረበ ይሆን?


በኢትዮጵያ ያለፉት 40 አመታት የፖለቲካ ሂደት 6ቱ የለውጥ መዘውር ነጥቦች (turning points)

turningpoint


ኢትዮጵያ የዘውድ ስርዓት ከወረደ በኋላ ባልተረጋጋ የለውጥ ማዕበል ውስጥ መናጥ ከጀመረች 40 ዓመታት እየደፈነ ነው። የየካቲት 1966 ዓም አብዮት ዘንድሮ 40 ዓመት ይሞላዋል። ከ 1966 ዓም በፊት በነበሩት ስልሳ አመታት ውስጥ ሀገራችን ከሁለት መቶ አመታት በላይ በዘመነ መሳፍንት የእርስ በርስ ግጭት ከቀረው ዓለም ጋር የነበራት ግንኙነት በብዙ መልኩ የተለያየ እና ጠንካራ የማይባል ነበር። ከ20ኛው ክፍለ ዘመን መጀመርያ እስከ አጋማሹ ማለትም 1966 ዓም በነበሩት ዓመታት ውስጥ ሀገራችን ፍፁም ከሆነው የፊውዳል ስርዓት ወደ ዘመናዊነት ለመግባት ብዙ ነገሮች በየዘርፉ የጀመረችባቸው አመታት ነበሩ። ዘመናዊ መንግስት ስርዓት- እንደ ፓርላማ፣ ዩኒቨርስቲዎች፣ የአየር መንገድ አገልግሎት፣ የመብራት ኃይል ማስፋፋት፣ በዓለም አቀፍ ግንኙነትም ሆነ በአህጉራዊ እና አካባቢያዊ ፖለቲካ ውስጥ ተፅኖ ፈጣሪነት እና የመሳሰሉት ባጭሩ ሊገለፁ የሚችሉ የዘመናቱ ስራዎች ነበሩ።
ከ1966 ዓም ወዲህ ባሉት አርባ አመታት ውስጥ ኢትዮጵያ የተረጋጋ የመንግስት ስርዓት እና ህዝብን ያማከለ አስተዳደር ቢኖራት ኖሮ ዛሬ ካለአንዳች ማጋነን ደቡብ ኮርያ ከደረሰችበት የስልጣኔ እና የእድገት ደረጃ የመድረስ ዕድል ነበራት። ይህ ግን አልሆነም።
በእነኚህ አመታት ውስጥ በተገቢው ደረጃ እንዳናድግ ያደረጉን ብዙ ምክንያቶች አሉ። ከእነኝህ ውስጥ በቀን በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ የበላ ጦርነት በሰሜናዊ የሀገራችን ክፍል ለአስራ ሰባት አመታት መካሄዱ፣ የነበሩት በእውቀት ክህሎታቸው እና በልምዳቸው ለሀገራቸው አስተዋፅኦ ያደርጉ የነበሩ ምሁራን የመስራት መብታቸው መታፈኑ፣ የኢትዮጵያ አለም አቀፍ ግንኙነት ብልህነት ያልተሞላበት የነበረ መሆኑ፣ ካለፉት 22 አመታት ወዲህ ደግሞ ብሄርን መሰረት ያደረገ የሀገሪቱ የአስተዳደር መዋቅር ወደባሰ አደገኛ የህዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ማምራቱ፣ ብሄርን መሰረት ያደረገ አድሏዊ ስርዓት ምጣኔ ሃብቱን በተወሰኑ እና ጥቂት ሰዎች እጅ እንዲገባ ማድረጉ፣ የፈጠራ ስሜት እጅጉን እንዲጎዳ መደረጉ፣ ሀገሪቱ ያለወደብ ቀርታ ለባሰ የባዕዳን ጥቃት ተጋላጭ መሆኗ ወዘተ የሚሉትን መጥቀስ ይቻላል።
ከላይ በተጠቀሰው 20ኛው ክ/ዘመን (1900 – 2000 ዓም) ውስጥ ኢትዮጵያ ስድስት የለውጥ መዘውሮች (turning points) ውስጥ አልፋለች። እነኝህ የለውጥ መዘውሮች (turning points) በሀገራችን የፖለቲካ መረክ ላይ ይከሰቱ እንጂ አብዛኞቹ ብሩህ ተስፋ ይዘው የመጡ የሚመስሉ ግን የከሸፉ ናቸው። የመክሸፋቸውን ምክንያት ለታሪክ ተመራማሪዎች ትቼ ክስተቶቹ ምንነት ላይ ብቻ ላተኩር።