“ከተማዋ የሕዝብ መጸዳጃ ቤት ሆናለች”
በአዲስ አበባ ያለው የመጸዳጃ ቤት ችግር ከልክ ያለፈና መሆኑን የእንግሊዙ ዘ ጋርዲያን ጋዜጣ ዘገበ። ሐሙስ በወጣው የጋዜጣው ድረገጽ ላይ እንዳስነበበው ከ3 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ በሚኖርባት አዲስ አበባ ውስጥ ለሕዝብ መገልገያነት የዋሉት መጸዳጃ ቤቶች 63 ብቻ መሆናቸውን ዘግቧል። አማራጭ ያጡ የከተማዋ ነዋሪዎች ደግሞ ከተማዋ ወደ መጸዳጃ ቤትነት እየተለወጠች መሆኗን በምሬት ገልጸዋል።
ጋርዲያን “Wash Ethiopia Movement” የተባለ አገር በቀል ድርጅት ጠቅሶ እንደዘገበው በከተማዋ ከ10 ቤተሰቦች 9ኙ የጉድጓድ መጸዳጃ ቤት እንደሚጠቀሙና መቀመጫ ባለው መጸዳጃ ቤት የሚጠቀሙት ከ25 ቤተሰቦች አንዱ ብቻ መሆኑን ተናግሯል። በዘገባው መሠረት የከተማዋ ባለሥልጣናት የዛሬ ዓመት ይገነባሉ በሚል የ100ሚሊዮን ብር ዕቅድ የተያዘላቸው መጸዳጃ ቤቶች እንዳሉ መናገራቸውን ጠቅሷል።
ጋዜጣው በቀን 200 ሰዎች ስለሚጠቀሙባቸው 4 መጸዳጃ ቤቶች ሲዘግብ “ለመጠቀም አስቸጋሪ፣ ለሴቶች የማይመቹ፣ ንጽህናቸው ያልተጠበቀና ጠረናቸው እጅግ የሚሰነፍጥ” መሆኑን አስረድቷል። የመጸዳጃ ቤቶቹ ተጠቃሚ ከሆኑት መካከል ወ/ሮ ብርሃኔ በመጸዳጃ ቤቶቹ ንጽህና ጉድለት ምክንያት ከጥቂት ወራት በፊት በጠና ታምመው ሆስፒታል መግባታቸውን ገልጸዋል። በርካታ ያካባቢው ነዋሪዎችም በተስቦ፣ በተቅማጥና በሌሎች ተላላፊ በሽታዎች እንደሚጠቁ ተናግረዋል። መጸዳጃ ቤቶቹ የወንድና የሴት ተብለው ካለመከፋፈላቸው በተጨማሪ በተለይ ለሴቶች የሚመቹ ባለመሆናቸው አንዳንድ ሴቶች በፖፖ ቤታቸው እየተጠቀሙ ወደ መጸዳጃ ቤቶቹ እያመጡ እንደሚደፉ በግልጽ አስረድተዋል።