Saturday, August 30, 2014

የአንዲት እናት ደብዳቤ፤


ለዝች ደብዳቤ ከአሌክሶ ሰዕል ወጪ የሚሆን ማገኘት አልቻልኩም፤ አሌስ ሰዕልህ ይባረክ!
ለዝች ደብዳቤ ከአሌክሶ ሰዕል ወጪ የሚሆን ማገኘት አልቻልኩም፤ አሌስ ሰዕልህ ይባረክ!
የአንዲት እናት ደብዳቤ፤
ይድረስ በውጪ ሃገር ለምትኖሪው ውድ ልጄ፤
ባለፈው ሰሞንልሽ… ያቺ ከበታቻችን ያለችው ቀጭኗ ሴትዮ… ምነው እንኳ ቀበሌ ገባ ወጣ የምትለው… እ… እርሷ ወደቤታችን ብቅ ብላ ነበር። እና ታድያ፤ ዲያስፖራዋ ልጅዎ እንዴት ነች… ብላ ብትጠይቀኝ ጊዜ ኧረ እኔ እንዲህ የምትባል ልጅ የለችኝም ፍቅርዬ አበራ… ማለትሽ ነው… ብዬ ጠይኳት፤ እርሷቴ ”በውጪ ሀገር የሚገኝ ማንኛውም ሰው ዲያስፖራ ነው የሚባለው” ብላ ነገረችኝ። አከል አድርጋም፤ ”በልማቱ ተሳታፊ ከሆነች ልማታዊ ዲያስፖራ ልማቱን አደናቃፊ ከሆነች ደግሞ የቀድሞ ስርአት ናፋቂ ነው የምትባለው!” ስትል ጨመረችልኝ፤ እኔም እንዳላወቀ እንዳልገባው ሆኜ፤ የወደፊቱ ስርዓት ናፋቂዎች የሚባሉስ የሉም…. ብዬ ብላት፤ ”ምን አሉኝ….” ብላ ስተደናበር፤ የለ…. እንደው ለቤተሰብ ሳታሳውቁ ስም መለዋወጥ ምን ይሉት ፈሊጥ ነው… ብዬ ገርሞኝ ነው…. እያልኩ፤ ሳዳርቃት ዋልኩልሽ… እንዲህ በሆነ ባለሆነ ያዝ ካላደረግናቸው የነርሱ ፓለቲካ ማለቂያም የለው ልጄ….
የሆነው ሁኖ… አንቺ እንዴት አለሽልኝ፤ እኔ እናትሽ ካንቺ ሃስብ እና ናፍቆት በቀረ እጅጉን ደህና ነኝ።
እንዳልኩሽ፤ ሰሞኑን የቀበሌ ሰዎች ወደቤት መጣ መጣ ማለት አብዝተውብናል… ምክኝያቱ ምን እንደሁ እስቲ ከእኛ እናንተ ታውቁታላችሁና ምን ፈልገው እንደሆነ አጣርተሽ ነግሪኝ፤ እውነቴን ነው ልጄ እንደውም አሁን ይቺን ኢሳቴን ከተከልኩ ኋላ ትንሽ ሻል አለኝ እንጂ ድሮማ ኢቶጵያ ቴሌቪዥን የሚለንን ብቻ እየሰማን የመረጃ ድርቅ ገብቶን ነበር። እርግጥ አንዳንድ ወቅት ዜናውን ገልብጦ በመስማት እውነቱን እንረዳዋለን ለምሳሌ፤ ”አንዳንድ አሸባሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ” የሚል ዜና የተነገረ እንደሆነ አንድንድ ጀግኖች እና ለሀገር ያገባኛል የሚሉ ወገኖች፤ ታግተዋል ማለት ነው… ብለን እየተረጎምን ሃቋን እናገኛታለነ!

በነገሬ ላይ ልጄ፤ እንዴት ነው አንቺ እስካሁን ድረስ አሸባሪ ያልተባልሽው… ስንት ጊዜሽ ሀገር ሀገር እያልሽ ስትለፊ እና ስትለፈለፊ አይደል እንዴ የምተውይው… እና ታድያ መንግስት እንዴት ነው እስከዛሬ አሸባሪ ያላለሽ… ልጄ… የጎረቤት ልጆች ሁሉ አሸባሪ ተብለው አንቺ ብቻ ይህንን ማዕረግ ሳታገኚ ቀርተሽ፤ ከሰው በታች አደረግሽኝ እኮ ልጄ… በይ ጠንከር በይ እና ስለ ሀገርሽ ስሪ… እና አሸባሪ ተብለሽ ከሰው እኩል አድርጊን እንጂ ልጄ….
እናልሽ ቀበሌዎቻችን ሰሞኑን ምን እንደሰሙ እንጃ ቤታችን እግር አብዝተዋል። ምርጫ እየደረሰ ስለሆነ እንድንመርጣቸው ሊሰብኩን ይሆን … ብቻ፤ ሰላምታቸው ፈገግታቸው ሁሉ ሌላ ሆኖልሻል። እንግዲህ እስከ ምርጫው ድረስ ኮብልስቶኑ እንዳያደናቅፋችሁ እንነጠፍላችሁ ማለት ነው የሚቀራቸው። ምርጫዋ ካለፈች በኋላ ለቀጣዩ አምስት አመት ሊያነጥፉን እኮ ነው…! ዘንድሮስ ልጄ እንጃ ሰይጣንም እንኳ ቢወዳደር ያሸንፋቸዋል…
ውይ ጋሽ ወንድሙ የነገረኝን ቀልድ ሳልነግርሽ፤ ሰይጣን እና አንድ የኢህ አዴግ ካድሬ መንገድ ሲሄዱ ይመሽባቸውና ማድሪያ ይቸገራሉ… ታድያልሽ፤ ከአቅራቢያቸው ካለ መንደር ለማድር ያስቡ እና ሰይጣን ሆዬ ኢህአዴግን ምን አለው መሰለሽ፤ ከእኔጋ ከሄድክ እኔን ሰዎች ስለምፈሩኝ እሺ ብለው አያሳድሩንም ስለዚህ በኔ የተነሳ አንተ ብርድ ከምተጎዳ ሂድና አሳድሩኝ በል እኔ እንደ ልማዴ አንዱ ዛፍ ጥግ አድሬ ጉዟችንን ጠዋት እንቀጥላለን… ይለዋል አሉ… (አንቺዬ ለካስ ሰይጣን ለኢህአዴግ ሲሆን ሩሩህ ነውና…. አትይልኝም…)
ከዛልሽ፤ እሺ ብሎ የዋሁ ካድሬ ወደ አንዱ ጎጆ ሄዶ አሳድሩኝ…ማለት፤ ሰዎቹም ማንነቱን ሲያውቁ ጊዜ ቦታ የለንም፤ ብለው ይመልሱታል… አንዱ ቤት ብቻ መሰለሽ የመንደሩ ሰዉ ሁሉ ቦታ የለንም እያለ ፊት ነሳው። ከዛ አንገቱን አቀርቅቅሮ ከወዳጁ ሰይጣን ዘንድ ሄደና፤ ”እኔ አላሳድር አሉኝ ባክህ… ምን አይነት ልማት አደናቃፊ ሰዎች እንደሆኑ እንጃ…” አለው። ለጠቅ አድርጎም፤ ”እስቲ አንተ ደግሞ ሞክራቸውና ጉዳቸውን እንይ”፤ ቢለው ጊዜ ሰይጣንም ”እስቲ እንዳልክ ይሁን” ብሎ ገና የመጀመሪያው ቤት አሳድሩኝ ብሎ ሲጠይቅ እሺ ይሉት እና ያስገቡታል… (ጋሽ ወንድሙ ይሄን ሲነግረኝ፤ ”ሰይጣን መሆኑንን ባያውቁ ነው በጄ ያሉት…” ብዬው ነበር… ለካስ እንደርሱ አይደለም ሰይጣን እንደሆነ አውቀዋል… ኢህአዴጉን ሰው አናሳድር ብለው እርኩሱን ሰይጣን ያሳደርሩት ምን ብለው መሰለሽ፤ ”ሰይጣን አለወጣ ቢል በጸበል ይወጣል ኢህአዴግ ግን አንዴ ከገባ መውጫም የለው….” ብለው ሰግተው ነው…. ብሎ በሳቅ ሊገድልኝ…
እናልሽ ዘንድሮ ሰይጣንም እንኳ ቢወዳደር እርሱን እንመርጥ እና ኋላ አልወጣ ወይ አላዋጣ ካለ በጸበል እንሞክረዋልን እንጂ ዳግም ኢህአዴግ ስልጣን ላይ ይቆይ ብሎ መምረጥ፤ በራስ ላይ ሌላ ጦስ ማምጣት ነው…
”ይሄኔ አንቺ በሆድድሽ እስከዛሬስ መርጣችሁት ነው እንዴ ስልጣን ላይ ተጣብቆ የቀረው…” ብለሽ ልትሞግቺኝ ወገብሽን ይዘሻል… መች አጣነው፤ ኢህአዴግ ዋና ዘመዱ፣ ዋና መመኪያው ጠብመንጃው ነች። ያ በደሉ ሞቅ ሲለው ምን እንደሚል ሰምተሻል፤ ”የሚመካ በክላሽ ይመካ ብሏል ኢህአዴግ” እያለ አንዴም ሲያስቀን አንዴም ሲያሳቅቀን ባየሽ…
እርግጥ ነው ነው ልጄ ኢህአዴግ ምርጫን የሚጠቀመው ለመተዛዘቢያ ያክል እንጂ እንደ ዘጠና ሰባቱ ጊዜ ሆ… ብለን ወግድ ብንለው እንኳ ”አንዳንድ ጸረ ልማት ሃይሎች” የሚል ነጠላ ዜማ ይለቅ ይሆናል እንጂ ስልጣኑንስ በምርጫ እንደማይለቅ እናውቀዋለን። ቢሆንም ግን ልጄ እንደ ሁለት ሺህ ሁለቱ ምርጫ ምን አለፋን ብለን ካርድ ሳንወስድ እቤት ቁጭ ብሎ ዜና ከማየት፤ ካርዳችንን አውጥተን ለሆነው ተቃዋሚ ድምጻአችንን ሰጥተን ጉዱን ማየት ይሻለናል። ቢያንስ ቢያንስ የሚገዙን በግድ መሆኑን ብናሳያቸው ራሱ ቀላል አይደለም፤ ብለን እኔም የሰፈሩ ሰው ሁሉም በየ ቡናው በየ ሀዘን እና ደስታ ቦታው ሁሉ እየመከረን ነው….! በነርሱ ቤት ቦለቲካውን የሚያውቀው ቀበሌ ገባ ወጣ ያለ ብቻ ነው… እኛ እነርሱ ፊት ምንም የማናውቅ መስለን ውስጥ ውስጡን ያሰብንላቸው ብዙ ነው… እስቲ ብቻ ግዜው ይደርስ…
እና ልጄ እንዴት አለሽልኝ…
እናንተማ ምን አለባችሁ ልጄ፤ ባለፈው፤ ሚሚ ከፌስ ቡክ አየሁ ብላ እንደነገረችኝ፤ ሰሞኑን ውሃ በባልዲ እየሞላችሁ አናታችሁ ላይ እየደፋችሁ እየተራጫችሁት ነው አሉ። እኛ በጀሪካን አናታችን ላይ ጭነን ከየትና የት ወደቤታችን ለማምጣት አበሳ ስናይ እናንተ ተራጩት እንጂ… ደግሞ ሌላውም ሰው እንደናንተው ውሃ በበረዶ አድርጎ አናቱ ላይ እንዲያፈስ አልያ ግን በህምም ላሉ ወገኖⶭ ገንዘብ እንዲከፍል እያላችሁ ትፎካከሩልን ይዛችኋል፤ ነገሩስ ደሀና ነበር፤ ቢሆንም ልጄ እናንተ እዛው ርስ በርሳችሁ እንዳሻችሁ፤ ይሄንን ጥቆማ ወደኛ ታደርጉትና ኋላ እንቀያየማልን ልጄ… እንደምታውቂው የእኛ ሰው በረዶ ይሰራበት ኤሌክትሪክ እንዲሁም አናቱ ላይ ያፈሰው ውሃ የለውም። አንቺ አናትሽ ላይ ውሃ በበረዶ ደፍተሽ እኔ እናትሽን የጠቆምሽ እንደሆነ የግድ ያልሽውን ለማድረግ ጅቡቲ መሄድ ነው ያለብኝ፤ ውሃውም መብራቱም ለጅቡቲ ተሸጦ እኛ ዘንድ በስንት አንድ ቀን ነው…ልጄ። ስለዚህ ”ትጠጣው የላት ትደፋው አማራት” እንዳታሰኚኝ…አደራ እንዳትጠቁሚብኝ ልጄ!
በመጨረሻም እኔ፤
(ይቀጥላል… ) ብለን እናክብደው እንዴ…!

No comments:

Post a Comment