ግልጽነትና ተጠያቂነት ፈረዱ ወይስ ተፈረደባቸው?
ለግልጽነትና ለተጠያቂነት ብሎም ለህዝቦች ጥቅም ቅድሚያ እንደሚሰጥ ህግ ደንግጎ የተቋቋመው ዓለም ዓቀፋዊ ተቋም ኢህአዴግ ያቀረበውን የይግባኝ ማመልከቻ ተቀብሎ ማጽደቁ አነጋጋሪ ሆኗል። በ2009 ኢህአዴግን “ያወጣሁትን መስፈርት አታሟላም” በማለት እውቅና የከለከለው ይህ ተቋም፣ ኢህአዴግ በሚከሰስባቸው ዋና ጉዳዮች ለውጥ ሳያደርግ የራሱን ውሳኔ የገለበጠበት አካሄድ እየተመረመረ እንደሆነ የጎልጉል ምንጮች ጠቁመዋል።
የኢህአዴግን የእውቅና ይግባኝ ጥያቄ ተቀብሎ ያጸደቀው የተፈጥሮ ሃብትን በትክክለኛ መንገድ ለሕዝብ ጥቅም መዋሉን በመከታተል ለአገራት እውቅና የሚሰጠው The Extractive Industries Transparency Initiative (EITI) የሚባለው ዓለም ዓቀፋዊ ተቋም ነው። ተቋሙ ኢህአዴግ በ2009 አቅርቦት የነበረውን የእውቅና ጥያቄ ውድቅ ሲያደርግ የሰጠው ምክንያት “የመያዶች ህግ የተሰኘው” አዋጅ ተግባራዊ እንዳይሆንና በአገሪቱ የተተከሉት አፋኝ ህጎች እስካልተወገዱ ድረስ ማመልከቻው እንደማይታይ በማሳወቅ ነበር።
በ2009 ጠ/ሚኒስትር የነበሩት አቶ መለስ “መሰዋት” በስተቀር ኢህአዴግ አንዳችም ለውጥ ባላደረገበት ሁኔታ ባለፈው ረቡዕ መጋቢት 19፤2006 (March 19፤2014) ይኸው እውቅና ሰጪ ተቋም የራሱን ውሳኔ ቀልብሶ ለኢህአዴግ እውቅና መስጠቱ የብዙዎችን ቀልብ ስቧል። ከውሳኔው ቀናት በፊት በጓሮ የሚወጠን ድርጊት እንዳለ መረጃ ደርሶት የማሳሰቢያ ተቃውሞ ያሰራጨው ሂውማን ራይትስ ዎች የተሰኘው የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት እንዳለው ከሆነ ከተገለበጠው ውሳኔ በስተጀርባ ሚስ ክሌር ሾርት ከፊት ረድፍ ተቀምጠዋል።