Thursday, March 21, 2013

የኦህዴድ ምርጫ ውጤት ተራዘመ

 
ህወሃት አባረረ፣ ብአዴንና ደኢህዴን ባሉበት ቀጠሉ
tplf meeting
ድሮ “ላዩ ካኪ ውስጡ ውስኪ” እየተባለ በኢሰፓ አባላት ዩኒፎርም ይቀለድ ነበር። ዛሬ ደግሞ ኢህአዴግ ተመሳሳይ ልብስ አልብሶ በየክልሉ የሰየማቸውን ፓርቲዎችና አመራሮቻቸውን የተመለከቱ “ስቱኮ” እያሉ እንደሚቀልዱባቸው ተሰምቷል።
“ስቱኮ” ግልብጥና ግጭት የበዛበት መኪና ተቀጥቅጦ አልስተካከል ሲል፣ የተገጣጠበና አልመሳሰል ያለ ግድግዳ “በግድ” ለማመሳሰል የሚያገለግል ቶሎ የሚፈረካከስ ጭቃ መሰል የቀለም አይነት ማጣበቂያ ነው።
“ኮሚኒስቶች በችግርና በቅራኔ ውስጥ ሆነው በግድ ለመመሳሰል አንድ ዓይነት መለያ መልበስ ይወዳሉ። ኢህአዴግም በተመሳሳይ በችግር ውስጥ ተዘፍቆ ሳለ፣ ለተመልካችና ለካሜራ ተመሳሳይ ልብስ ለብሶ በግድ አንድ ነኝ ሲል ማየቱ ብዙም የሚገርም አይደለም” የሚለው አስተያየት በስፋት እየተሰጠ ነው። “በግድ አንድ” ሆነው በየክልሉ ስብሰባ የሚያካሂዱት እህት ፓርቲዎች የለበሱትን መለያ የሚያመርተው ደግሞ የህወሃት የንግድ ድርጅት አልሜዳ ጨርቃጨርቅ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
ባህር ዳር ላይ ለሚያካሂደው ጉባኤ በዝግጅት ላይ ያሉት “እህት” ፓርቲዎች በየክልላቸው በስብሰባና በምርጫ ተጠምደው ሰንብተዋል። ውሉ ያልታወቀውና ምስጢር የተደረገው የኦህዴድ ጉባኤ የምርጫውን ውጤት ማጠናቀቅ አልቻለም። ህወሃት በመተካካት ስም ነባሮቹን አራት አመራሮች ሲያሰናብት፣ አቶ በረከትና አዲሱ ለገሰ የኢህአዴግ የመተካካቱ ስልታዊ በትር ሳይነካቸው ማለፉ ተደምጧል። ደኢህዴን በነበረበት እንደሚቀጥል ይፋ ሆኗል።
ኦህዴድን ለመምራትና ሰባት አመራር በሚሰየምበት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ለመሆን አባ ዱላ ገመዳ፣ ግርማ ብሩ፣ ድሪባ ኩማ፣ ኩማ ደመቅሳ፣ አለማየሁ አቶምሳ፣ አስቴር ማሞና ደግፌ ቡላ ከተጠቆሙት መካከል ይገኙበታል። የህወሃት የንግድ ተቋምና አንደበት የሆነው ሬዲዮ ፋና “የተጠቆሙትን አመራሮች ለማሳወቅ የድምጽ ቆጠራው ጊዜ ስለሚወስድ ለነገ ተላልፏል” የሚል ዘገባ አሰራጭቷል።

Tuesday, March 19, 2013

ህጻናት እየራባቸው መማር አቅቷቸዋል!

 
"ምሳ ያላቸው ሲበሉ እኔ የቤት ስራ እሰራለሁ"
students in addis
ህጻናት እየራባቸው ትምህርት መማር እንዳቃታቸው ሸገር አዲስ ኤፍ ኤም ያነጋገራቸው መምህራንና ተማሪዎች ተናገሩ። ሸገር ያነጋገራቸው ተማሪዎች በየተራ እንደተናገሩት በምግብ ችግር ትምህርታቸውን መከታተልና ክፍል ውስጥ ትኩረት ማድረግ ተስኗቸዋል።
“ሌሎች ምሳ ያላቸው ምሳ ሲበሉ እኔ የቤት ስራ እሰራለሁ። ወይም ቤተክርስቲያን እሄዳለሁ” በማለት አንድ ተማሪ ሲናገር፣ ሌላኛው ምሳ የሚባል ነገር እንደማያውቅ ገልጿል። በርሃብ ምክንያት ትምህርታቸውን በወጉ መከታተል ያልቻሉ ተማሪዎች ጉዳይ እንዳሳሰባቸው መምህራኑ ሲናገሩ ሸገር አስደምጧል። በሰሙት ዜና ረፍት ያጡ በርካታ ወገኖች ስልክ በመደወል ተማሪዎቹ በትምህርት ቤታቸው ውስጥ የምሳ አገልግሎት እንዲያገኙ የበኩላቸውን ለማድረግ ሲነጋገሩና ቃል ሲገቡ ለመስማት ተችሏል።
አዲስ አበባ በኑሮ ውድነት ሳቢያ የሚበሉ ያጡ፣ በክፍል ውስጥ ረሃብ እያዞረ ክፍል ውስጥ የሚጥላቸው፣ በየጥጋ ጥጉ አጥርና ጥላ ስር ቀን የሚገፉ፣ የባሰባቸው ቤተሰቦቻቸውን ለማትረፍ ያለ እድሜያቸው ስጋቸውን ለመሸጥ እንደሚገደዱና ቤተሰብ፣ በተለይም እናቶች ልጆቻቸውን ለገበያ ወሲብ ማበረታታት እየተለመደ መምጣቱን የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ አመልክቷል። (ፎቶ: ተማሪዎች በአንድ የአዲስ አበባ ት/ቤት)
(ተጨማሪ ዜናዎችን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን

Saturday, March 16, 2013

በስዊድን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ሰላማዊ ሰልፍ አደረጉ


ቴዎድሮስ አረጋ
ቁጥራቸው በግምት ከሁለት መቶ በላይ የሚሆኑ በስዊድን የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች የኢትዮጵያ መንግስት ያለዓግባብ አስሮ እያንገላታቸው የሚገኙትን የሃይማኖት መሪዎቻቸውንና እንዲሁም የመፍትሄ አፈላላጊ ኮሚቴ አባላትን በአስቸኳይ እንዲፈታ የሚጠይቅ ሰላማዊ ሰልፍ ዛሬ ከቀትር ሰዓት በኋላ እዚህ ስቶክሆልም ከተማ በሚከኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ፊትለፊት አደረጉ። ሰላማዊ ሰልፈኞቹ በተጨማሪም ኢትዮጵያ ውስጥ በሚኖሩ ሙስሊም ወገኖቻቸው ላይ የሚደርሰውን እንግልት፡ዝርፊያ እና ህገወጥ ብርበራ በአስቸኳይ እንዲቆም የጠየቁ ሲሆን መንግስት በዩኒቨርሲቲና በሌሎችም ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ውስጥ በመማር ላይ በሚገኙ ሙስሊም ኢትዮጵያውን ላይ እያደረሰ ያለውን ማዋከብና ማስፈራራት ከትምህርታቸው እያፈናቀለ ያለውን አፓርታዳዊ ተግባር እንዲያቆም ጠይቀዋል።
በእለቱ የእስልምና እና የክርስትና መሪዎች በየተራ ንግግር ያሰሙ ሲሆን በስልጣን ላይ ያለው መንግስት በእስልምናና በኦርቶዶክ ቤ/ክ ሃይማኖቶች ላይ እያደረገ ያለውን ጣልቃ ገብነት በማውገዝ ከዚህ ድርጊቱ እንዲቆጠብ አሳስበዋል። ከዚህ በተጨማሪም የተቋውሞ ሰልፈኞቹ የጸረአሸባሪነት ህግ ከለላ በማድረግ በስልጣን ላይ ያለው መንግስት ያሰራቸውን ጋዜጠኞች፡የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ደጋፊዎቻቸውን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲፈታ በአንድ ድምጽ ጠይቀዋል።

በጋምቤላ፤ አሜሪካ የዜጋዋን መቃብር ከፍታ መረመረች



የጋምቤላ “አኬልዳማ” እየተደረሰ ነው


crime scene 1


በጋምቤላ የመከላከያ ሰራዊት ከጨፈጨፋቸው ሰዎች መካከል የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው አቶ ኡሞት ኡዶል ግድያ ለማጣራት ከአሜሪካ መንግስት የተላኩት የፎረንሲክ (ለህዝብ ይፋ የሚያደርጉ) ባለሙያዎችን ጋምቤላ ገብተው የማጣራት ሥራ ጀምረዋል። “የጋምቤላ አኬልዳማ” እየተዘጋጀ እንደሆነም ተሰማ።
የጎልጉል የጋምቤላ መረጃ አቀባዮች እንዳሉት ጋምቤላ የደረሱት የአሜሪካ ዜጎች የሄዱበትን ጉዳይ ለማከናወን ከክልሉና ከመከላከያ ሰራዊት ባለስልጣናት ዘንድ እክል ገጥሟቸው ነበር።
(ፎቶው የማሳያ ነው)
የፎረንሲክ ባለሙያዎቹ የዜጋቸውን አሟሟት መንስኤና የጉዳት መጠን ለማጣራት ጋምቤላ እንደደረሱ አስከሬኑ በስውር የተቀበረበትን ቦታ ማወቅ እንደሚፈልጉ፣ አስከሬኑ ላይ የዲኤንኤ ምርመራ በማካሄድ የሟችን ትክክለኛ ማንነት ለማረጋገጥ፣ የጉዳቱን መጠንና በምን ያህል ጥይት እንደተደበደበ ለማጣራት፣ ከዚያም በላይ ለምርመራ ስራቸው ይረዳቸው ዘንድ የሚፈልጉትን መረጃ ለመሰብሰብ ድርጊቱ የተፈጸመበት ቦታ መሄድ እንደሚፈልጉ ጠይቀው እንደነበር ለክልሉ መንግስት ቅርብ የሆኑ ለጎልጉል ገልጸዋል።
ጥያቄውን መቀበል የተሳናቸው የመከላከያና የክልሉ ባለስልጣናት አስከሬኑ መመርመር የማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱን፣ ከተቀበረ የቆየ በመሆኑ ለማውጣት አስቸጋሪ እንደሆነና እንደማይቻል ለመርማሪዎቹ ገልጸው ነበር። “ስራው የኛ ነው” ያሉት መርማሪዎቹ አስከሬኑ በየትኛውም ደረጃ ላይ ቢገኝም ማየት እንደሚፈልጉ፣ ይህ አቋም እንደማይቀየር መሆኑን አመልክተው አስከሬኑ የተቀበረበት ቦታ ደርሰው የሚፈልጉትን ምርመራ ማድረጋቸው ታውቋል። አከራካሪ የነበረውና ግድያው የተፈጸመበት ቦታ የመጓዙ ጉዳይ እንደነበር የጠቆሙት የመረጃው ምንጭ፣ የቀረበው መልስ አስገራሚ እንደነበር ይገልጻሉ።
“ቦታው ላይ ደም የለም፣ ማንንም አታገኙም፣ ምን ያደርግላችኋል?” የሚሉ መከራከሪያዎችን ባለሥልጣናቱ  ቢያቀርቡም ተቀባይነት ማግኘት አልቻሉም። አጣሪዎቹ ወደ ስፍራው ከመሄዳቸው በፊት ካድሬዎች ሽማግሌዎችንና ያካባቢው ነዋሪዎችን በማባበል የቅስቀሳና ፊልም የማዘጋጀት ስራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን የጎልጉል ምንጮች አመልክተዋል።

Friday, March 15, 2013

በሚዲያ መረሳት ያስፈራል



“ነጻ ፕሬስ ከሌለ አገር አደጋ ላይ ነው”



“ከምድር በታች ጨለማ ቤት ውስጥ የታሰሩትን በቀን ለ10 ደቂቃ እናያቸዋልን። ልብ የሚነካ ነው። የብርሃን ማነስ አይናቸውን እንደጎዳቸው ያስታውቃሉ … ሴቶችን በተገኘው ሰበብ ያስሯቸዋል። ምክንያት ፈልገው እስር ቤት ይከቷቸዋል። ከዚያም ይደፍሯቸዋል። በርካታ የተደፈሩ እህቶች አሉ። የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊትና መንግሥት ያሰማራቸው ሚሊሻዎች ይህንን አሳዛኝ ድርጊት እንደፈጸሙ ተነግሮናል” ይህ ማዕከላዊ እስር ቤት ታስሮ፣ ችግሩ ባለበት ቦታ ተገኝቶ የነበረው ስዊድናዊ የፍሪላንሰር ጋዜጠኛ ማርቲን ካርል ሻቢዬ ቃል ነው።
ስለ ማዕከላዊ እስር ቤት መስማት ይጨንቃል። ሰዎች በሲቃ የሚያሰሙት የጣር ድምጽ ለጆሮ  የተለመደ ነው። ከመሬት በታች የጨለማ ክፍል አለ። በዚህ መታጎሪያ ውስጥ ሆነው ስቃይ የሚፈራረቅባቸው ወገኖች ጥቂት አይደሉም። ማዕከላዊ ብዙ ጉድ ያለበት ሲኦል ነው። የሰው ልጆች በግፍ ማቅቀውበታል። እየማቀቁበትም ነው። ለውጥ እስከሌለ ድረስ የሚቆም አይመስልም። በመሃላ የሚነገርለት ውርስና ይቀጥላል የሚባለው የመለስ ራዕይ አንዱ ክፍል ይህ ነው።
መጋቢት 3፤2005 (3/12/2013) በኖርዌይ ኦስሎ የሥነጽሁፍ ቤት (ሊትሬቸር ሀውስ) በተዘጋጀ የመወያያ መድረክ ላይ ሁለቱ ስዊድናውያን ጋዜጠኞች ተገኝተው ነበር። መድረኩን ያዘጋጀው ደግሞ NOAS በሚል ስያሜ የሚታወቀው የስደተኞች ተሟጋች ድርጅት ነው። የተቋሙ ዋና ዳይሬክተር አን-ማግሬት ኦስቴና ሁለቱን እንግዶች ካስተዋወቁ በኋላ መድረኩን እየመሩ ውይይቱ ተካሄደ። በዚህ ውይይት ላይ ሁለቱ ጋዜጠኞች እየተፈራረቁ የደረሰባቸውንና በትክክል ያዩትን አስታወቁ።
ማርቲን ካርል ሻቢዬና ባልደረባው የፎቶ ጋዜጠኛ ጆሃን ካርል አበክረው የሚናገሩት ስለ ሙያቸው ነው። “ጋዜጠኛ ለመጻፍ ማየትና ማነጋገር አለበት። በተለያዩ አገራት ጋዜጠኞች ችግር ባለባቸው ቦታዎች ገብተው ለመዘገብ ድንበር ያቋርጣሉ። አሁን በሶሪያ፣ ቀደም ሲል በሊቢያ የሆነው ይህ ነው። በኢትዮጵያ ግን ሽብርተኛ ያሰኛል” ሲሉ ግርምታቸውን ይጀምራሉ።
የ19 ዓመት ወጣት ነው። ስራዉ ሹፍርና ሲሆን “ኦነግ ነህ” ተብሎ ነው የታሰረው። መርማሪዎች ባዶ ወረቀት እየሰጡ ስለ ኦነግ ጻፍ ይሉታል። ምንም የሚያውቀው ነገር ስላልነበር መጻፍ አልቻለም። በመጨረሻ ራሳቸው ጽፈው አዘጋጅተው በራስህ እጅ ጽሁፍ ገልብጥ አሉት። እናም የተባለውን ፈጸመ። ጋዜጠኞቹ ብዙ መረጃ አላቸው። እነሱንም ያልሆኑትንና ያላደረጉትን አድርገናል እንዲሉ መደረጋቸውን አስታውቀዋል። “በሶማሊያ አምስት ዓመት ተቀምጫለሁ እንድል አስገድደው አሳመኑኝ” በማለት ጆሃን ካርል ገለጸ።

ወ/ሮ ዙፋን አማረ
የኢትዮጵያ ስደተኞች ማህበር በኖርዌይ ሊቀመንበር ወ/ሮ ዙፋን አማረ እንደሚሉት ሁለቱ ጋዜጠኞች ኖርዌይ እንዲመጡ ከላይ ከተጠቀሰው ድርጅት ጋር ከመነጋገር ጀምሮ ማህበራቸው የበኩሉን ስለማድረጉ ይናገራሉ። ይህ እንዲሆን የታሰበው ደግሞ ጋዜጠኞቹ በትክክል ያዩትንና የደረሰባቸውን ለኖርዌይ ባለስልጣናት በማስረዳት በኢትዮጵያ ላይ የያዙትን አቋም እንዲያስተካክሉ የሚደረገውን የቅንጅት ትግል ለማጠናከር እንደሆነ ወ/ሮ ዙፋን ያስረዳሉ።
ሁለቱ ጋዜጠኞችም ያሰመሩበት ጉዳይ ይህንኑ ነው። ኖርዌይ የመጡበት ዋናው ምክንያት ከተለያዩ ፖለቲከኞች፣ አግባብ ካላቸው መስሪያ ቤቶችና ከዋናው ፓርላማ በመገኘት ስለ ኢትዮጵያ ማስረዳታቸውን ተናግረዋል። በርግጠኛነት ባለስልጣናቱ ያገኙትን መረጃ ለመልካም ይጠቀሙበታል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።

Saturday, March 9, 2013

“በፌዴራል ተደብድባችሁ ትባረራላችሁ!”

benishangul asosa

ከዓመታት በፊት መተከል ዞን ፓዌ የተካሄደውን ያነሳል። 1984 – 85 ፓዌ መንደር አራት በሚባለው የገበያ ቦታ እየገበዩ የነበሩ የአማራ ተወላጆች ያላሰቡት ደረሰባቸው። በድንገት ገበያው ታወከ። የቻሉትን በቀስት፣ ሌላውን በጥይት ለቀሙት። 56 ሰዎች በቅጽበት ተረሸኑ። ይህ ሁሉ ሲደረግ አገር የሚመሩት ባለስልጣኖች ድምጻቸውን አላሰሙም ነበር። አሁንም በተቆራረጠ አንደበት አስተያየቱን ቀጠለ።

በወቅቱ ፓዌ እንደነበር ያስታወሰው አስተያየት ሰጪ “አሰፋ ኢናቦ” ሲል ስም ጠራ። አሰፋ ኢናቦ የመተከል ዞን አስተዳዳሪ ነበር። ድንገት በደረሰው ጭፍጨፋ የተበሳጩ ከመንደር አራት ስምንት ኪሎሜትር ርቆ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ አሰፋ ኢናቦን አስገድደው ወሰዱት። በመጨረሻም ሰፋሪውን እያሳዩ የበቀል ኃይላቸውን አሳረፉበት፤ ቦጫጨቁትና እዛው ተቀበረ። በስፍራው ስለተደረገው ሁሉ በቂ መረጃ ያለው መሆኑን የሚናገረው አስተያየት ሰጪ እንደሚለው በቀትር በአደባባይ ህዝብ የጨፈጨፉትና ያስጨፈጨፉት አልታሰሩም። ህግ ፊት አልቀረቡም። ለይስሙላ ታስረዋል ተብለው ተለቀዋል።

Monday, March 4, 2013

ኢህአዴግ አሣ አስጋሪዎችን ጨፈጨፈ

 

የአሜሪካዊው አስከሬንና አሟሟት ሊመረመር ነው

fisherman
 
የመከላከያ ሰራዊት በድንገተኛ ከበባ ከገደላቸው ንጹሃን ዜጎች መካከል የአሜሪካ ዜግነት ያላቸውን የአቶ ኡሞት ኡዶል ግድያ አስመልክቶ የአሜሪካ መንግስት አስፈላጊውን ሁሉ ምርመራ እንደሚያደርግ አስታውቋል። ግድያው ከተፈጸመ በኋላ የሰራዊቱ አባላት አስከሬን አደባባይ በማውጣት ለህዝብ እያሳዩ ደስታቸውን ሲገልጹ የተመለከቱ የጋምቤላ ከተማና አካባቢው ነዋሪዎች ክፉኛ መበሳጨታቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡ በጋምቤላ የደረቁን ወቅት ወይም በጋውን በወንዞች ዳር ውሃ ተንተርሶ መኖር የተለመደ ነው። ከቋሚ የመኖሪያ ቀዬ ወደ ወንዝ ዳርቻ በመሄድ አድኖ መመገብና አሳ አስግሮ ዕለትን ማሳለፍ የባህል ያህል ነው። በአገሬው ልምድ መሰረት ከቋሚ መኖሪያቸው ወደ ውሃ ዳር የሚሄዱት ወንዶች ሲሆኑ ጉዞውም የሚደረገው በቡድን ነው። በዚሁ መሰረት በጋምቤላ ክልል የጎክዲፓች ነዋሪዎች የደረቁን ወቅት ለማሳለፍ በጊሎ ወንዝ ዳርቻ ወደምትገኘው አብሌን ያመራሉ። በቡድን ወደ አብሌን ያመሩት ሰዎች ከወንዝ አሳ በማስገርና ያገኙትን በማደን ቀን እየገፉ ሳለ የካቲት 21፤2005ዓም (28/2/13) በድንገት የመከላከያ ሰራዊት ከበባቸው። ተኩስ ተከፈተ። ለጊዜው ስድስት ሰዎች ህይወታቸው ማለፉንና የቆሰሉ እንዳሉ ለተጎጂዎቹ ቅርበት ያላቸው ያስረዳሉ።
                                                   ኡሞት ኡዶል (ፎቶ: ጎልጉል: የድረገጽ ጋዜጣ)
 
ሰዎቹ ከጋምቤላ ከተማ 120 ኪሜ ርቀት ላይ በምትገኘው አብሌን ተቀምጠው ኑሯቸውን እየገፉ ሳለ በድንገት የተከበቡት በጥቆማ እንደሆነ ለጎልጉል የደረሰው መረጃ ያመለክታል። “አቶ ኡሞት ኡዶል እና ሌሎች መሳሪያ የታጠቁ አብሌን ታይተዋል” የሚል ጥቆማ የደረሰው ኢህአዴግ፤ ሰራዊቱን ሰዎቹ በቋሚነት ወደሚኖሩበት ጎክዲፓች በመላክ ቤተሰቦቻቸውን በመያዝ፣ በማሰርና፣ በመግረፍ ሰዎቹ ያሉበትን ቦታ እንዲያሳዩ አስገደዱ።