Saturday, March 9, 2013

“በፌዴራል ተደብድባችሁ ትባረራላችሁ!”

benishangul asosa

ከዓመታት በፊት መተከል ዞን ፓዌ የተካሄደውን ያነሳል። 1984 – 85 ፓዌ መንደር አራት በሚባለው የገበያ ቦታ እየገበዩ የነበሩ የአማራ ተወላጆች ያላሰቡት ደረሰባቸው። በድንገት ገበያው ታወከ። የቻሉትን በቀስት፣ ሌላውን በጥይት ለቀሙት። 56 ሰዎች በቅጽበት ተረሸኑ። ይህ ሁሉ ሲደረግ አገር የሚመሩት ባለስልጣኖች ድምጻቸውን አላሰሙም ነበር። አሁንም በተቆራረጠ አንደበት አስተያየቱን ቀጠለ።

በወቅቱ ፓዌ እንደነበር ያስታወሰው አስተያየት ሰጪ “አሰፋ ኢናቦ” ሲል ስም ጠራ። አሰፋ ኢናቦ የመተከል ዞን አስተዳዳሪ ነበር። ድንገት በደረሰው ጭፍጨፋ የተበሳጩ ከመንደር አራት ስምንት ኪሎሜትር ርቆ በሚገኘው አውሮፕላን ማረፊያ አሰፋ ኢናቦን አስገድደው ወሰዱት። በመጨረሻም ሰፋሪውን እያሳዩ የበቀል ኃይላቸውን አሳረፉበት፤ ቦጫጨቁትና እዛው ተቀበረ። በስፍራው ስለተደረገው ሁሉ በቂ መረጃ ያለው መሆኑን የሚናገረው አስተያየት ሰጪ እንደሚለው በቀትር በአደባባይ ህዝብ የጨፈጨፉትና ያስጨፈጨፉት አልታሰሩም። ህግ ፊት አልቀረቡም። ለይስሙላ ታስረዋል ተብለው ተለቀዋል።

በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ የሚኖሩት የሺናሻ ብሔረሰብ አባላት ሲሆኑ ቀደም ሲል ጀምሮ “አገሩ የናንተ ነው። ባለመብቶች እናንተ ናችሁ። ውሳኔው ሁሉ የራሳችሁ ነው” ስለተባሉ በክልሉ በአንድ ትምህርት ቤት የሚማሩ የአማራ ብሔር አባላት እኩል የትምህርት እድል እንደማያገኙ፣ እሱም የችግሩ ሰለባ እንደሆነ ያስረዳል። ነጻ ሚዲያ ቢኖር ግፉ በተዘረዘረ ነበር ሲል ቁጭቱን ይገልጻል።

አገሬውን “ሆን ብለው ክፋት እየጋቷቸው በየጊዜው አማራ ውጣ፣ አማራ ሂድ …” በማለት እንደሚፎክሩ ያስረዳው ቅሬታ አቅራቢ አስገራሚውና አስደንጋጩ ጉዳይ የአማራ ክልል “እመራዋለሁ” የሚለው አካል ለህዝቡ መከራከር አለመቻሉ ነው።

በጉራፈርዳ በክልሉ መንግስት ትዕዛዝ የከፋ ወንጀል ሲሰራ፣ አንደኛ ክፍል ለሚማር ህጻን “ክልሉን ልቀቅና ውጣ” የሚል ደብዳቤ ሲሰጥ ተቆጣጣሪና ተቆርቋሪ አለመኖሩ መጨረሻ የሌለው ግፍ አማራው ላይ እንዲካሄድ ስምምነት ያለ እንደሚያስመስል የሚገልጹ ጥቂት አይደሉም።

ሰሞኑን በቤንሻንጉል-ጉምዝ ክልል አማራውን የማፈናቀል ዘመቻ መጀመሩ ይፋ ሆነ እንጂ ችግሩ የቆየና ማዕከላዊ አገዛዙም ሆነ የክልሉ መስተዳድር ጠንቅቀው የሚያውቁት ጉዳይ እንደሆነም አስተያየት ሰጪዎቹ ይናገራሉ። የካቲት 28፤2005 (ማርች 7፤2013) የተላለፈው የአሜሪካን ሬዲዮ አማርኛ ክፍል ያነጋገራቸው የችግሩ ሰለባ አሁን ያለውን ችግር የሚገልጹት በተማጽኖ ነው።

በቤንሻንጉል መተከል ዞን ቡሎን ወረዳ የሰፈሩና ከ15 እስከ 20 ዓመት በረሃውን አልምተው፣ ወልደው ከብደውና ንብረት አፍርተው ይኖሩ የነበሩ አምስት ሺህ በላይ ነዋሪዎች ከየካቲት19 እስከ 30 ቀን 2013 ዓም መኖሪያቸውን ለቀው እንዲወጡ ታዝዘዋል። ለቪኦኤ የተማጽኖ ቃላቸውን ያስተላለፉት አቶ የሺህ ዋስ ትንሳኤ ድምጻቸው ያሰሙት ባህር ዳር “መንግስታቸው” ደጅ ቆመው ነው።

ባህር ዳር ሆነው “ሰሚ አጣን” በማለት ድምጻቸውን ያሰሙት አቶ የሺህ ዋስ “ለክልሉ መንግስት ለምን አመለከታችሁ በሚል ስለምንታሰር እባካችሁ ለፌደራሉ መንግስት አሳውቁልን” ሲሉ ተደምጠዋል። አገር ቤት የመንግስትም ሆነ “የግል” የሚባሉት የመገናኛ ዘዴዎች ጆሮ የነሷቸው በሚመስል ኑዛዜ ያቀረቡት አቶ የሺህ ዋስ “ፈልሶ የመጣ፣ ውጣ አማራ” እየተባሉ የውጭ አገር ዜጋ እንኳን በማይጠራበት ሁኔታ ክብረ ነክ ስድብ እንደሚሰደቡ አመልክተዋል።

ከመንግስታችሁ ሸኚ አምጡ መባላቸውን፣ በርካቶች ሸኚ ለማምጣት ከብቶቻቸውን በርካሽ መሸጣቸውን፣ ሸኚም ካመጡ በኋላ ተቀባይነት አለማግኘቱን አቶ የሺህ ዋስ ያስረዳሉ። አያይዘውም ባፋጣኝ ክልሉን ለቀው ካልወጡ የክልሉ መንግስት ባለስልጣናት ምን ሊከሰት እንደሚችል የዛቱባቸውን ተናግረዋል።

የብአዴን ሊ/መንበር ደመቀ መኮንን (ፎቶ: ምንጩ ያልታወቀ)

ባስቸኳይ ክልሉን ለቀው ካልወጡ “የፌደራል ፖሊስ ደብድቦ ያስወጣሃል” የሚል ማስፈራሪያ የደረሳቸው መሆኑንን ያመለከቱት አቶ የሺህ ዋስ፣ የአማራ ክልል ባለስልጣናትን ማግኘትና ማነጋገር አለመቻላቸውን ከክልሉ መንግስት መቀመጫ ባህር ዳር ሆነው መናገራቸው ጉዳዩን አወሳስቦታል። ለሰሚውም ግራ ሆኗል። ቪኦኤ እንዳለው የክልሉን ባለስልጣናትም አግኝቶ ማነጋገር አልተቻለም።

ለጊዜው የክልሉ መንግስት ማረፊያ እንዲያዘጋጅላቸው ወይም የሚሰፍሩበት ቦታ እስኪመቻችላቸው ከክልሉ ጋር በመነጋገር አደጋ ላይ ለሚገኙት ከአምስት ሺህ በላይ ሰዎች መፍትሔ እንዲያፈላልግ የተጠየቀው የክልሉ መስተዳድርም ሆነ “የጭቁኑ አማራ ተወካይ ነኝ” የሚለው ብአዴን/ኢህአዴግ ጉዳዩን አስመልክቶ እስካሁን ያሉት ነገርም የለም።

የአማራ ክልል ለምና ሰፊ መሬቱን ለሱዳን አሳልፎ በመስጠት፣ ሁመራንና ወልቃይት ገባውን ለትግራይ ክልል አሳልፎ በማስረከብ የሚታወቀውን ብአዴንን የሚመሩት አቶ ደመቀ መኮንን በአማራው ስም “ቅምጥ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር” ሆነው በውለታ መሾማቸው የሚታወስ ነው።

(ፎቶ፡ CSSP)


ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
 

No comments:

Post a Comment