ተፈጭና ተመረቅ – አስተምሮ መለስ
በእንግሊዝኛው አጠራር የዲፕሎማ/የዲግሪ ወፍጮ ቤት (diploma/degree mills) ይባላሉ፡፡ በርካታዎቹ ሠለጠነ በሚባለው ዓለም ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ “ወፍጮ ቤቶች” የ“ትምህርት መረጃ” ለማግኘት በጣም ቀላል ነው፡፡ ዋናው መስፈርት አስፈላጊውን “የትምህርት ክፍያ” መፈጸም ብቻ ነው ፡፡ ከዚያ በወርቅ ቅብ የተንቆጠቆጠ “የባችለር” ወይም “የማስተርስ” ወይም “የዶክትሬት (ፒ.ኤች.ዲ.)” ዲግሪዎችን ማፈስ ነው፡፡ በቀጣይ የሚሆነው የ…ሚ/ር ወይም የ…ሚኒስትር ደኤታ ወዘተ መሆንና “በሹመት መዳበር” ነው፡፡ ከዚያ ህዝብ አናት ላይ “በስያሜ” ተቀምጦ መጋለብ ነው።
ከዓመታት በፊት የአሜሪካው የመንግሥት ተጠያቂነት ቢሮ በዚህ ጉዳይ ላይ ምርመራ አካሂዶ ነበር፡፡ ያገኘውንም ውጤት ለእንደራሴዎች ምክር ቤት ሲያቀርብ “የወፍጮ ቤቶቹን” አሠራር በግልጽ ዘርዝሯል፡፡ ለምርመራው ያነሳሳው በአሜሪካ የመንግሥት መ/ቤቶች ውስጥ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ድረስ የሚሠሩ “ከወፍጮ ቤቶቹ” የትምህርት ማስረጃ የሸመቱ መኖራቸውን በማረጋገጡ ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ ቢሮው ያቋቋመው መርማሪ ቡድን ለሦስት ዓመታት በርካታ ዲፕሎማዎችንና ዲግሪዎችን ከአሜሪካና ከሌሎች የውጭ አገራት በቀላሉ በድብቅ ለመግዛት መቻሉን አረጋግጧል፡፡
አሠራሩን እንዴት እንደሆነ ሲገልጽም፤ ከመርማሪ ቡድን አባላት አንዱ ተማሪ በመምሰል “የትምህርት ተቋማቱን” ዲግሪ እንደሚፈልግ መስሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ ክፍያ ካጠናቀቀ መግዛት እንደሚችል “ወፍጮ ቤቶቹ” በነገሩት መሠረት የሳይንስ ባችለር ዲግሪ በባዮሎጂ እንዲሁም የሳይንስ ማስተርስ ዲግሪ በሜዲካል ቴክኖሎጂ “ሸምቷል”፡፡ ክፍያ ለጨመረም ሥራ ቀጣሪዎች የትምህርት ማስረጃውን ለማረጋገጥ ሲደውሉ ሊያነጋግሩበት የሚችሉበት የስልክ መስመር አብሮ ይሰጣል፤ በዚሁ አንጻር በየዲግሪዎቹ “የማዕረግ ተመራቂ” መሆን እንደሚቻል ተረጋግጧል፡፡ በአሜሪካ!!!
ተማሪዎች ክፍል ገብተውም ሆነ በተልዕኮ ትምህርታቸውን የመከታተል ግዴታ እንደሌለባቸው፤ ሙሉውን ክፍያ በአንድ ጊዜ ሲፈጽሙ ለትራንስክሪፕት እንዲያመች ክፍያው በኮርስ ተሸንሽኖ ደረሰኝ እንደሚቆረጥላቸው በምርመራው ተደርሶበታል፡፡ ክፍያው በጨመረ ቁጥር የሚገኘው አገልግሎት እየጨመረና ዲግሪው “እውነተኛ” እየመሰለ እንደሚሄድም ተጠቁሟል፡፡
እንዲህ ያለው ምርመራ ከተካሄደ ዓመታት ያለፉ ቢሆንም አሁንም አሠራሩ ቀጥሏል፡፡ “ወፍጮ ቤቶቹ” አሁንም ዲግሪ መቸብቸባቸውን አላቆሙም፡፡ ከዚህም አልፎ ለዶክትሬት ዲግሪ ማሟያ የሚሆን ጽሁፍ (ዲሰርቴሽን) አብሮ ተገዝቶ በገዢው ስም እንደሚሰጥ፤ አከፋፈሉ ካማረም ጽሁፉ የሸማቹ መመረቂያ ጽሁፍ ሆኖ በስሙ በኢንተርኔት ይበተናል። እንዲህ ያለው አሰራር አሁን ድረስ ይሰራበታል፡፡ በዚሁ “ወፍጮ ቤት” አማካይነት ተፈጭተው “ዶ/ር” እየተባሉ የመጠራት ጥማት ያላቸው በተለይ የሦስተኛው ዓለም ባለሥልጣናት ገበያውን መቆጣጠራቸው ይታወቃል፡፡
“አቅም ግንባታ” እና “የወፍጮ ቤቶቹ” ሚና በኢህአዴግ
ወደ አገራችን ስንመለስ “በነጻአውጪ” ስም በረሃ የቆዩና አጫፋሪዎቻቸው ለሥልጣን ሲመቻቹ አስቀድሞ የሚደረገው የ“አቅም ግንባታ” ማከናወን ነው። በዚሁ መለስ በነደፉት አቅም አልባ የሚያደርግ የ“አቅም ግንባታ” በርካታዎች “ከወፍጮ ቤት” ደጅ እንዲገረደፉና እንዲፈጩ ተደርገዋል። አሁንም ለመፈጨት ተራ የሚጠብቁና እየተፈጩ ያሉ አቅም አልባ ካድሬዎቹ ቁጥር ቀላል አይደለም። በዚህ አሠራር ቀዳሚዎቹ የትግራይ ተወላጆች ቢሆኑም የሌሎቹ ድቃይ ድርጅቶች አባላትም በሸመታው ዋንኛ ተሳታፊ መሆናቸው ራሳቸው ሸማቾቹ የሚመሰክሩት ሐቅ ነው፡፡
ለጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን የሰጡ ሲናገሩ በአንድ ወቅት ያገኙት በመከላከያ ሚ/ር የሚሠራ የህወሃት ባለስልጣንን የትምህርት ሁኔታ ይጠቅሳሉ፡፡ ግለሰቡ በትግራይ ነጻ አውጪነት ተሰልፎ በነበረበት ጊዜ ራሱ እንደተናገረው የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አላጠናቀቀም ነበር፡፡ “ከድል” በኋላ ግን የአንደኛና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ብቻ ሳይሆን የኮሌጅ ትምህርቱን “አጠናቅቆ” በኢኮኖሚክስ የመጀመሪያ ዲግሪውን እንደተቀበለ ወዲያዉኑ የማስተርስ ዲግሪውን በመቀበል አዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር እንዲሁም መከላከያ ሚ/ር ውስጥ በኮሎኔል ማዕረግ የመምሪያ ኃላፊነት ደረጃ ላይ መድረሱን ተናግሯል፡፡ “ይህንን ሁሉ በርካታ ዓመታት የሚፈጅ ትምህርት እንኳን ተምሮ፣ በታክሲ ወይም በአውሮፕላን ተሳፍሮ ቢጋልብ፣ እንደ ጥይት አረር ቢተኮስ ሊደርስበት አይችልም፤ ከብርሃን ፍጥነት ጋር በሚስተካከል መተኮስ ለዚህ ሁሉ በመብቃቱ “የብርሃን ዲግሪ” ልንለው እንችላለን” በማለት አስተያየት ሰጪው ተሳልቀዋል፡፡
ህወሃት/ኢህአዴግ በውጭ ካሉት “የዲግሪ ወፍጮ ቤቶች” የሚሻውን የትምህርት ማስረጃ፣ ለሚወደው ለመሸመትና ያለከልካይ ለመጠቀም እንዲችል “ባለራዕዩ” መለስ ሥልጣን ላይ እንደወጡ ያደረጉት የመንግሥት አመራራቸውንም ሆነ የአስተዳደር ፖሊሲያቸውን አብጠልጥለው ብትንትኑን ሊያወጡ የሚችሉ 42 የኢትዮጵያን ድንቅ ምሁራን በዱሪ መሐመድ ሁለት መስመር ደብዳቤ ማባረር ነበር፡፡ ይህ ለኢትዮጵያ የተደገሰው አዲሱ “የአቅም ግንባታ” መሆኑ ነው። ከዚያም “ሲቪል ሰርቪስ” የተባለ “የዲግሪ/ዲፕሎማ ወፍጮ ቤት” አገር ውስጥ ከፈቱ፡፡ የህወሃት ሹማምንት ከውጪዎቹ “ወፍጮ ቤቶች” የፈረንጅ ዲግሪ ሲገዙ የተላላኪዎቹ ፓርቲዎች አባላት ደግሞ “ከአገር ውስጥ የመለስ ወፍጮ ቤቶች” እንዲሸምቱ ተደረገ፡፡
ይህ በሥርዓትና በጥናት የተደረገ አካሄድ መለስ በአንድ ወቅት ሚኒስትሮች ሲሾሙ በወቅቱ አቶ ቡልቻ ደመቅሳ የተሹዋሚዎቹን የትምህርት ደረጃ እንዲሁም ችሎታ በዝርዝር ይቅረብልን፤ ለቦታውም እንዴት ሊመጥኑ እንደቻሉ ይነገረን በማለት እንዲጠይቁ አድርጓቸዋል፡፡ “በዲግሪ ወፍጮ ቤት ምሩቃን” ራሳቸውን ከብበው “ቆራጡ፣ አስተዋዩ፣ ብልሁ …” መሪ ሲባሉ የነበሩት መለስ ሲመልሱ መሐይምም እንኳን ቢሆን የኢህአዴግን ዓላማ እስካስፈጸመ ድረስ ሚኒስትር መሆን ይችላል ብለው ነበር፡፡
መለስ የከተማ ጥሩንባ ነፊዎች ነበሩዋቸው። ቅጠል ከሚመነዠክበት የሴሰኞች ሰፈር ጀምሮ እስከ ላይ መለስን ሲያውድሱ የሚውሉ ድርጎ ለቃሚዎች ነበሩ። እነዚህ ድርጎ ለቃሚዎች “አንድ መለስ ብቻ” በማለት የመለስን ዝናና “ልዩ ብቃት፣ ስማርት መሆን” ሲሰብኩ ይውላሉ። መለስ ባይኖር ኢህአዴግ የሚባለው ድርጅት፣ ህወሃት የሚባለው “ነጻ አውጪ” አፍታ እንኳ እድሜ ሊኖረው እንደማይችል ይጠነቁላሉ። መለስ ዋለታና ምሰሶ ባይሆኑ አገር ጨለማ እንደሚውጣት ያስፈራራሉ። ወሬ ፈጣኑ እየነጎደ መለስን አገነነ።
መለስ በባህሪያቸው የሚፎካከራቸውና እሳቸው የሚያስቡትን አስቀድሞ የሚረዳ የትግል አጋር ስለማይወዱ ህወሃት ላይ የወሰዱት የማጽዳት ዘመቻ ምስክር ነው። እነ ተወልደ /ውህዳኑ/ ብዙ ማለት ይችላሉ። ታዲያ የሚፎካከሯቸው ከሌሉ “አላዋቂዎችን ሰብስበው ገነኑ” እንዳይባል በዙሪያቸው ያሉትን ሚስታቸውን ጨምሮ ከ“ወፍጮ ቤት ዲግሪ” ሸመታ ደጅ ማሰለፍ ነበረባቸው። በዚሁ እንደ ግንፍልፍል ምግብ ባስቸኳይ በክፍያ ብቻ በሚሰጥ ዲግሪ ያንበሸበሿቸውን ካድሬዎች ሰብስበው ሲፈላሰፉ ብቻቸውን አዋቂ ሆነው አረፉት፤ “ስማርት መሪ ተባሉ”። በዚያው ስሜት “ተሰው”፤ ይህ ቀድሞ የተሰራና የተፈጠረ ስሜት ካድሬውን ውጦት ስለኖረ የመለስ “መሰዋት” ማረፊያው የማይታወቅ ጉድጓድ ሆነባቸው። ከመለስ ይልቅ ራሳቸው ላይ ሞትን አውጀው በሙት መንፈስ ለመመራት ተማማሉ። ሲማሩ ሳይሆን ሲፈጩ መኖራቸውን መሰከሩ።
የመጀመሪያ ዲግሪያቸውን የት እንዳገኙ የማይታወቀው መለስ የሥልጣን መንበሩ ላይ እንደተፈናጠጡ በትምህርት መስክ ራሳቸውን ለመቻል ባስመዘገቡት ፈጣን ሪኮርድ መሠረት በኢትዮጵያ ሃብት በከፈሉት ገንዘብ ሁለት የማስተርስ ዲግሪዎች ከአውሮጳ በፖስታ ቤት ተልኮላቸዋል፡፡ ከግለታሪካቸው ጋር አብሮ የሚጠቀሱት የትምህርት ማስረጃዎችም እነዚሁ በፈጣን መልዕክት አገልግሎት የተላኩላቸው የፖስታ “ዲግሪዎች” ናቸው፡፡ የኢትዮጵያን ሕዝብ ጭንቅላት ለሁለት ዓስርተ ዓመታት ሲበጠብጡ ቆይተው በመጨረሻም የራሳቸውን በጥብጠው “የተሰዉት” መለስ አጠገባቸው በራሳቸው ልክ እያሰፉ “በፈጠሯቸው” የዲግሪና የዲፕሎማ ሸማቾች ተከብበው በመኖራቸው ከዝንጀሮዎች መካከል እንደተገኘች “ቆንጆ” እና “ብልጥ” ጦጣ አድርጓቸው እንደነበር ብዙዎች ይስማማሉ።
በምዕራቡ ዓለም በተለይ በአሜሪካ እነዚህ የዲፕሎማ ወፍጮ ቤቶች በርካታ ከመሆናቸው የተነሳ እጅግ አደናጋሪ ናቸው፡፡ እነዚህ “ኮሌጆች” ለመግቢያ የሚያስፈልጉ ፈተናዎችን አይጠይቁም፡፡ በተለይ ለማስተርስ የዲግሪ ትምህርት መግቢያ የሚያስፈልጉትን ዓለምአቀፍ ዕውቅና ያላቸውን GMAT ወይም GRE ፈተናዎች ተመዝጋቢው እንዲወስድ አይጠይቁም፡፡ አቶ መለስ በፖስታ ከተላከላቸው ዲግሪዎች አንዱ MBA – Master of Business Administration ሲሆን ይህንን ዲግሪ ለማግኘት አብዛኛዎቹ ዕውቅና ያላቸው ተቋማት ተመዝጋቢው GMAT (Graduate Management Admission Test) ፈተና እንዲወስድ የግድ ይላሉ፡፡ ዲግሪው በፖስታ የሚላክ ከሆነ ግን ፈተናውን የመውሰድ አስፈላጊነት አይኖረውም፡፡ ፓርቲያቸው በግድ መሪ ሁን እያለ የሥራ ጫና እያበዛ የሰዋቸው መለስ ከፈተና አምልጠው ለዲግሪ መብቃታቸው ለሁለተኛ ሙት ዓመታቸው የተሠራው “ያልተጠኑ ገጾች” ዘጋቢ ፊልም ውስጥ ሳይካተት ያመለጠ “ያልተጠናው የመለስ ገጽ” ነው፡፡
አቶ መለስ ሁለተኛውን የማስተርስ ዲግሪያቸውን በፖስታ ቤት ፈጣን መልዕክት በተቀበሉበት 2004እኤአ በአሜሪካ በቴክሳስ ጠቅላይ ግዛት ዳላስ ከተማ ከሚገኝ Trinity Southern University ከተባለ “የዲግሪ ወፍጮ ቤት” ኮልቢ ኖላን የተባለ ድመት $299 ዶላር በመክፈል የባችለር ዲግሪውን ተቀብሏል፡፡ በድመታቸው ስም ማመልከቻውን ያስገቡትና በወቅቱ “ወፍጮ ቤቶቹን” እየመረመሩ የነበሩት የፔንስቬኒያው ግዛት ጠቅላይ አቃቤ ጄሪ ፓፐርት ነበሩ፡፡ ድመቱ የማመልከቻ ደብዳቤውን ሲልክ ከዚህ በፊት ሌሎች ኮርሶችን የወሰደ መሆኑን እንዲሁም ልጅ በመጠበቅ፣ ትኩስ ምግብ መሸጫ ቤት በአሻሻጭነትና በጋዜጣ አዟሪነት የሰራ መሆኑ በተጨማሪ ተገልጾ ነበር፡፡ ይህንን የትምህርት “ብቃት” እና “አመርቂ የሥራ ልምድ” የመረመረው “ዩኒቨርሲቲ” ለኮልቢ በላከው የምላሽ ደብዳቤ የሥራ ልምዱን እና በተጨማሪ የወሰዳቸውን ኮርሶች በመመልከት ለExecutive MBA ብቁ ስለሆነ $100 ዶላር ከጨመረ የባችለር ዲግሪውን ወደ [አቶ መለስ ዓይነት] MBA ዲግሪ እንደሚያሳድግለት ማረጋገጫ ልኮለታል፡፡
በ2010ዓም ደግሞ ለታወቀ የሕግ ኩባንያ የሚሠሩ ማርክ ሃዋርድ የተባሉ የሕግ ባለሙያ ውሻቸው ሉሉ ከኮንኮርዲያ ዩኒቨርሲቲ MBA ዲግሪ እንዲቀበል አድርገውታል፡፡ ሉሉ “ዲግሪውን” በማዕረግ መቀበል መቻሉ በወቅቱ አብሮ የተነገረ ሲሆን “በዩኒቨርሲቲውም” በአካል ተገኝቶ ክፍል ስለመከታተሉ (ስለውሻ እንደሚመሰክር ያላወቀው ምስክር) በሃሰት መስክሮለታል፡፡
ከላይ ለማለት እንደተሞከረው “የወፍጮ ቤቶቹ” መብዛት አደናጋሪነታቸውን የሰፋ አድርጎታል፡፡ በተለይም ደግሞ ከሚሰበስቡት ገንዘብ አንጻር የሚያካሂዱት የተጠና የማስታወቂያ ሥራ “እውነተኛ” እንዲመስሉ አድርጓቸዋል፡፡ በጉዳዩ ላይ አንዳንድ መረጃ ለመሰብሰብ የሚፈልጉ በተለያዩ ፎረሞች ላይ ምርምር ሲያደርጉ “ወፍጮ ቤቶቹ” ያሰማሯቸው “ካድሬዎች” የሚሰጡት ምላሽ በብዙዎች ዘንድ እንደ ትክክለኛ ምላሽ ይወሰዳል፡፡
በዚህ የዲግሪ “ወፍጮ ቤት” ሙያ ከተካኑት መካከል የሚጠቀሱት ካፔላ ዩኒቨርሲቲ አንዱ ሲሆን በተደጋጋሚ እጅግ በርካታ ክሶችና ወቀሳዎች ደርሰውበታል፡፡ የሃሰት ዲግሪ በመስጠት፣ ብቃት የሌላቸው መምህራን በመቅጠር፣ የሚቀጥራቸው መምህራን ከአሜሪካ ውጪ የመጡና የትምህርት ማስረጃቸውን እርግጠኝነት መናገር የማይቻል መሆኑ፣ በቂ ገንዘብ እስከተከፈ ድረስ ማንኛውንም ዓይነት ዲግሪ (ዶክትሬትም ቢሆን) እንደሚሰጥ፣ … እጅግ ብዙ ተብሎበታል፡፡ በአሜሪካ የሚገኘው ብሔራዊው የሕዝብ ሬዲዮ (NPR) ከዚህ ጋር ተዛማጅነት ባላቸው ጉዳዮች ላይ የምርመራ ዘገባም ሰርቶበታል፡፡ “ዩኒቨርሲቲው” ብዙውን ነገር ለማሻሻል የሞከረ ቢሆንም ከዚያ ይልቅ ግን እየወሰደ ያለው እርምጃ ባሰማራቸው የማስታወቂያ ካድሬዎቹ አማካኝነት ስሙን እያደሰ እንደሆነ ብዙዎች ይናገራሉ፡፡
ካፔላ ዩኒቨርሲቲ እያተመ በፖስታ የሚልከው ዲግሪ ለብዙ ከፋዮች ደርሷል፤ የአንዳንዶችም “ማዕረጋቸውን” ከአቶነት ወደ “ዶ/ር” አስቀይረውበታል፡፡ አድዋ ተወልደው ያደጉትና የህወሃት የስለላ ሞተር እንዲሁም ዋንኛ የስልክ፣ የሬዲዮ፣ ወዘተ ሞገድ ጠላፊ የሆኑት “ዶ/ር” ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የካፔላ ዩኒቨርሲቲ “ምሩቅ” ናቸው፡፡ አሽቃባጭ ደጋፊዎቻቸው የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ከሃርቫርድ የተቀበሉ ለማስመሰል በየቦታው በሚለጥፉት ግለህይወታቸው ላይ ፕሮፓጋንዳ ለመንፋት ቢሞክሩም ካፔላ “ወፍጮ ቤት” ዩኒቨርሲቲ ግን “ዶ/ር” ብዬ ለዚህ ያበቃኋቸው እኔ ነኝ በማለት በማስረጃ የተደገፈ ምስክርነቱን ይሰጣል፡፡
ገዢው ኢህአዴግና ቁንጮው ህወሃት በዚህ መልኩ ታማኞቹን “አቅም እየነሳ” በየዘርፉ አሰማርቷቸዋል። በሽታውና ችግሩ ለህወሃት ባይሆንም አገርን ጤና እየነሳ ነው። ህወሃት እንደስሙ መቼ ነጻነቱን አውጆ አገር እንደሚሰራ ባይታወቅም በራሱ ምድር፣ ለራሱ “የተስፋ ቀበሌ” የተለያዩ “ስፔሻል” የሚባሉ እቅዶች እንዳሉት አይዘነጋም። በልዩ ክትትል የሚያስተምራቸው ተተኪ ካድሬዎችም እያመረተ ነው። የሚዋኝበት ሃብትም ሰብስቧል። ጉዞው ቀጥሏል። መለስ አስፈጪ የሆኑበት ወፍጮ የሚፈጫቸውና የተፈጩት ባለስልጣናት አልመው የሚያደቁት ህዝብ መጨረሻ ምን ይሆን? በዚህ ጉዳይ ላይ በውክልና ካድሬዎችን ወፍጮ ቤት /በሊደርሺፕ ስልጠና ስም/ የሚያጠምቁት ፕሮፌሰሩ ፓስተር ምን ይሉ ይሆን? “ተቋማቸው” በግልጽ ማስረጃ ከነፎቷቸው በዘረዘረው መሠረት ሃይለማርያም ደሳለኝ (ፊንላንድ በወጉ ተምረው በውክልና ሊደርሺፕ ተፈጭተዋል)፣ አባዱላ ገመዳ፣ አዲሱ ለገሰ፣ በረከት ስምዖን፣ አብዲ ሞሐመድ ዑመር፣ ጁነዲን ሳዶ፣ ኩማ ደመቅሳ፣ ሙክታር ከዲር፣ ሽፈራው ተክለማርያም፣ ሬድዋን ሁሴን፣ ሽፈራው ሽጉጤ፣ አስቴር ማሞ፣ ድሪባ ኩማ፣ ዘነቡ ታደሰ፣ ካሳ ተክለብርሃን፣ አርአያ ገብረእግዚአብሔር፣ ኦሞድ ኦባንግ፣ … ዝርዝሩ ሊያልቅ አይችልም፡፡ እነዚህ ሁሉ በአገር ውስጡ “ወፍጮ ቤት” የተመረቱና “በሊደርሺፕ የተጠመቁ” ናቸው – የአብዮታዊ ዴሞክራሲ አንጋፋ ምሁራን! እዚህ ላይ ከቅቅል ባቄላ ውስጥ አንድ ጥሬ እንደማይጠፋ አለመዘንጋቱ ይስተዋላል፡፡
ህወሃት በሚነዳት አገራችን አውራ ዶሮ “አኩኩሉ” ሲል በሚያሳይ ማስታወቂያ እስከ ገጠር ዘልቆ ብር እያመረተ ካለው ኮሌጅ ይቅርታ “ወፍጮ ቤት” ጀምሮ በበቅሎ ጀምረው በሃመር ገጠር ገብተው በራሪ ወረቀት የማሰራጨት ደረጃ የደረሱትን ማን ይመርምራቸው? የትምህርት ጥራት ገደል ገባ እየተባለ ደረት ሲመታ ማን ዋናውን ችግር ይንካው? አላቅሙ ዩኒቨርሲቲ የሚያስተምር፣ አላቅሙ ሚኒስትር የሚሆን፣ አላቅሙ አገር የመምራት ጭነት የሚጫንበት … ሁሉም አላቅሙ በከመረው የውድቀት ክምር ይኮራል፤ በእርሱ አላዋቂነት አገርን ያከለ ታላቅ ነገር ሲወድምና ትውልድ ሲጠፋ ምንም አልሰማ ብሎት ደንዝዟል፤ ስብ ደፍኖታል፡፡ በውድመቱ ውስጥ ግን የራሱን ማንነት ጨምሮ ልጆቹና የልጅ ልጆቹ አብረው እየወደሙ መሆናቸው አይታየውም፤ በሞራ የተሸፈነው ዓይኑ የሩቁን እንዳያይ ጋርዶታል፡፡ ይህ ውርደቱ ሊሆን ሲገባው እንዲያውም ኩራቱ ነው፡፡ በቃኝ፣ እኔ ለዚህ አልመጥንም፣ እስከዛሬ ያለ እውቀቴ ሳንቦራጭቅ ኖሬያለሁና ይቅርታ የሚል ትውልድ ሳናይ ሁለት መንግስታትና አንድ ቅኝ ገዢ ነዱን። ይህ መሰሉ በሽታ የገዢዎቻችን ብቻ ሳይሆን የተቃዋሚዎቻቸውም መሆኑ ችግሩን እጅግ የባሰ አድርጎታል፡፡ ግን እስከመቼ?
አሜሪካ ፓርላማ/ምክር ቤት ስላላት ጉዳዩን መረመረች። በጀት መድባ ሰለለች። መረጃውን በማስረጃ አረጋግጣ እውነቱን ደረሰችበት። እኛ ምን ፓርላማ አለን? ቢኖረንስ ማንን ሊመረምሩና ሊያስመረምሩ? አስፈጪውና ተፈጪው ብቻ ሳይሆን የወፍጮ ቤቱ ባለቤት ሁሉ አብረው ቀጥለዋል፤ ወፍጮው አሁንም ይፈጫል። የቀድሞውን አስፈጪ የተካቸው በግልጽ አልታወቀም። ለኢትዮጵያ አቅም ግንባታ መፈጨት አማራጭ የለውም። “ተፈጭና ተመረቅ” አስተምህሮተ መለስ!! ለጊዜው!!
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡
No comments:
Post a Comment