ተፈጭና ተመረቅ – አስተምሮ መለስ
October 18, 2014 03:08 am By
Editor
በእንግሊዝኛው አጠራር የዲፕሎማ/የዲግሪ ወፍጮ ቤት (diploma/degree mills) ይባላሉ፡፡ በርካታዎቹ ሠለጠነ በሚባለው ዓለም ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህ “ወፍጮ ቤቶች” የ“ትምህርት መረጃ” ለማግኘት በጣም ቀላል ነው፡፡ ዋናው መስፈርት አስፈላጊውን “የትምህርት ክፍያ” መፈጸም ብቻ ነው ፡፡ ከዚያ በወርቅ ቅብ የተንቆጠቆጠ “የባችለር” ወይም “የማስተርስ” ወይም “የዶክትሬት (ፒ.ኤች.ዲ.)” ዲግሪዎችን ማፈስ ነው፡፡ በቀጣይ የሚሆነው የ…ሚ/ር ወይም የ…ሚኒስትር ደኤታ ወዘተ መሆንና “በሹመት መዳበር” ነው፡፡ ከዚያ ህዝብ አናት ላይ “በስያሜ” ተቀምጦ መጋለብ ነው።
ከዓመታት በፊት የአሜሪካው የመንግሥት ተጠያቂነት ቢሮ በዚህ ጉዳይ ላይ ምርመራ አካሂዶ ነበር፡፡ ያገኘውንም ውጤት ለእንደራሴዎች ምክር ቤት ሲያቀርብ “የወፍጮ ቤቶቹን” አሠራር በግልጽ ዘርዝሯል፡፡ ለምርመራው ያነሳሳው በአሜሪካ የመንግሥት መ/ቤቶች ውስጥ እስከ ከፍተኛ ደረጃ ድረስ የሚሠሩ “ከወፍጮ ቤቶቹ” የትምህርት ማስረጃ የሸመቱ መኖራቸውን በማረጋገጡ ነበር፡፡ ይህንንም ተከትሎ ቢሮው ያቋቋመው መርማሪ ቡድን ለሦስት ዓመታት በርካታ ዲፕሎማዎችንና ዲግሪዎችን ከአሜሪካና ከሌሎች የውጭ አገራት በቀላሉ በድብቅ ለመግዛት መቻሉን አረጋግጧል፡፡
አሠራሩን እንዴት እንደሆነ ሲገልጽም፤ ከመርማሪ ቡድን አባላት አንዱ ተማሪ በመምሰል “የትምህርት ተቋማቱን” ዲግሪ እንደሚፈልግ መስሎ ይጠይቃቸዋል፡፡ ክፍያ ካጠናቀቀ መግዛት እንደሚችል “ወፍጮ ቤቶቹ” በነገሩት መሠረት የሳይንስ ባችለር ዲግሪ በባዮሎጂ እንዲሁም የሳይንስ ማስተርስ ዲግሪ በሜዲካል ቴክኖሎጂ “ሸምቷል”፡፡ ክፍያ ለጨመረም ሥራ ቀጣሪዎች የትምህርት ማስረጃውን ለማረጋገጥ ሲደውሉ ሊያነጋግሩበት የሚችሉበት የስልክ መስመር አብሮ ይሰጣል፤ በዚሁ አንጻር በየዲግሪዎቹ “የማዕረግ ተመራቂ” መሆን እንደሚቻል ተረጋግጧል፡፡
በአሜሪካ!!!