Friday, May 31, 2013

የኮሚሽኑ መርማሪ ቡድን በተጠርጣሪዎች 60 የክስ መዝገቦች መቋረጣቸውን አስታወቀ


court
May 31, 2013 03:39 am By  Leave a Comment
- የ14 ቀናት ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ ተፈቀደለት

- ሁለት ተጠርጣሪዎች በምርመራ ወቅት መደብደባቸውን ተናገሩ

‹‹ተያዘ የተባለው ሰነድ ሁሉ በሀብት ምዝገባ ያስመዘገብኩት ነው›› አቶ ገብረ ዋህድ ወልደ ጊዮርጊስ

የፌዴራል የሥነ ምግባርና የፀረ ሙስና ኮሚሽን ምርመራ ቡድን፣ በተለያዩ የሙስና ወንጀሎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር በዋሉ ተጠርጣሪዎች እንዲቋረጡ ከተደረጉት 60 የክስ መዝገቦች ውስጥ 28 ያህሉን መሰብሰቡን ግንቦት 19 ቀን 2005 ዓ.ም. ለፍርድ ቤት አስታወቀ፡፡

መርማሪ ቡድኑ በፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ ሁለተኛ ወንጀል ችሎት ቀርቦ እንዳስረዳው፣ በተጠርጣሪዎቹ ላይ ባለፉት 14 ተጨማሪ የምርመራ ቀናት ላይ የሠራውን የምርመራ ሥራ እንዳብራራው፣ ከገቢዎችና ጉምሩክ ባለሥልጣን ሥራዎች ጋር ግንኙነት ያላቸውን የኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎችን ሰብስቧል፡፡ ከተለያዩ ባንኮች በተወሰኑ ተጠርጣሪዎች ላይ ከአራጣ ብድር ጋር የተያያዙ ማስረጃዎችን፣ በሕገወጥ መንገድ የተገኘን ገንዘብ ሕጋዊ አስመስሎ (መኒ ላውንድሪንግ) መጠቀምን የሚያሳዩ ሰነዶችን መሰብሰቡን ገልጿል፡፡

መርማሪ ቡድኑ ጨምሮ እንደገለጸው፣ ተጠርጣሪዎቹ በአራጣ ብድር የተከሰሱ ሰዎችን ክስ ያቋረጡባቸውን የክርክር መዝገቦችን መሰብሰቡንና በኮንትሮባንዲስቶች ላይ በፍርድ ቤት ተጀምረው ከነበሩትና በሕገወጥ ጥቅም ከተቋረጡት 60 የክስ መዝገቦች ውስጥ 28 የሚሆኑት መሰብሰቡንም ገልጿል፡፡

Thursday, May 30, 2013

የአሜሪካ የህግ ባለሙያዎችና አኢጋን በኅብረት ስራ ጀመሩ!


ዓርብ የፖለቲካና የሙስሊም እስረኛ ጠበቆችን ያነጋግራሉ

aba nsmne
May 30, 2013 08:40 am By  Leave a Comment
በኢትዮጵያ በግፍ የታሰሩ የፖለቲካና የህሊና እስረኞችን በተመለከተ የአሜሪካን የህግ ባለሙያዎች ማህበር (ABA – American Bar Association) ሙሉ በሙሉ ድጋፍ ለማድረግ የሚያስችለውን ስራ አርብ እንደሚጀምር ተገለጸ። አዲስ አበባ ካሉ የፖለቲካና የሙስሊም ወገን እስረኞች ጠበቆች ጋር የመጀመሪያ ስብሰባ አርብ ግንቦት 23፤2005ዓም ያደርጋሉ። አቶ ኦባንግ ሜቶ የተረሱ እስረኞች ጉዳይም እንደሚካተት ጠቅሰው በፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ ለታሰሩ ዜጎች ጥብቅና የቆሙ ካሉ የአዲሲቷን ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ /አኢጋን/ በቀጥታ እንዲገናኙ ጥሪ አቅርበዋል።

(ABA) በሚል ስያሜ የሚታወቀውና ከተቋቋመ 135ዓመታትን ያስቆጠረው የአሜሪካ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበር ከ400 ሺህ በላይ የህግ ባለሙያ አባላት አሉት። ይህ በአሜሪካ ትልቅ የተባለ ማህበር በግፍ ለሚሰቃዩ ኢትዮጵያዊያን እስረኞች ድጋፍ ለማድረግ የወሰነው የአኢጋን ዋና ዳይሬክተር አቶ ኦባንግ በይፋ የድጋፍ ጥያቄ ባቀረቡ በቀናት ውስጥ ሲሆን፣ በጋራ በተከናወኑ ንግግሮችና የሰነድ ውይይቶች በወር ጊዜ ውስጥ ወደ እንቅስቃሴ ለመግባት እንደተቻለ ለማወቅ ተችሏል።

Monday, May 27, 2013

የኢህአዴግና የሻዕቢያ ድርድር ተበጠሰ


ኢሳያስ፣ ደሚት፣ ግብጽ፣ ኳታር፣ ኢህአዴግ
haile and esayas
May 27, 2013 12:00 am By  Leave a Comment
ኳታር በተናጠል የጀመረችው ኢትዮጵያንና ኤርትራን የማሸማገል ሂደት መበጠሱ ተሰምቷል። ከሽምግልናው ዙሪያ የግብጽ ሚና ስለመኖሩ አመላካች ጉዳዮች አሉ እየተባለ ነው። በድርድሩ ኢህአዴግ በዋናነት እንደ ቅድመ ሁኔታ ያስቀመጠው የትግራይ ህዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ደሚት/ ጉዳይ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።

አቶ መለስ የኢትዮጵያን ወደብ እንደተራ ጉዳይ አሳልፈው በመስጠት ኤርትራን እንደ አገር እውቅና በሰጡበት ወቅት ድጋፍ ለማሰማት ቀዳሚ የነረችው ኳታር ከበረሃው ትግል ጀምሮ የሻዕቢያ ወዳጅ አገር እንደሆነች ይታወቃል።
ከዚሁ የከረመ ወዳጅነት በመነሳት ኳታር በ2008 ከኢህአዴግ ጋር ተፈጥሮ የነበረውን የጸብ ግድግዳ አፍርሳ ወደ ኢትዮጵያ የመጣችው በዋናነት ሁለቱን አገሮች መልሶ ለማስታረቅ በተያዘ እቅድ ስለመሆኑ ለጉዳዩ ቅርብ የሆኑ ይናገራሉ። በተለይም አሁን ያለው የኤርትራ አስተዳደር እጣ ፈንታ አብዝቶ ያስጨነቃት ኳታር በኤርትራ ወደብ ሊዝ በማድረግ፣ ኢንቨስትመንት ላይ በመሳተፍና ልዩ ድጎማ በማድረግ ቀዳሚውን ስፍራ ስለምትይዝ ችግር ከመፈጠሩ በፊት ላይ ታች ማለቷ እንደማይደንቅ ስምምነት አለ።

ጎልጉል ምንጭ የሆኑ ዲፕሎማት እንዳሉት ኳታር አሁን እርቁን የፈለገችው በኤርትራ መረጋጋት እንዲፈጠርና የኤርትራ ኢኮኖሚ አንዲያገግም ለማድረግ በሚል ነው። በሌላ በኩል ህወሃት የዘወትር ስጋቱ የሆነውን ሻዕቢያን ለማስወገድ ሌት ከቀን እንደሚሰራና ይህም በድርጅት ደረጃ አቋም የተያዘበት ጉዳይ በመሆኑ የኤርትራ መንግስት መሰረታዊ የአቋም ለውጥ ሳያደርግ ከኢህአዴግ ጋር የድርድር ስምምነት ላይ መድረስ አስቸጋሪ እንደሚሆን ሁሉም ወገኖች የሚረዱት ጉዳይ ነው።

Friday, May 24, 2013

የደህንነት ሹሙ ስዊድን ይመጣሉ


አዲስ አደረጃጀትና አዲስ ሬዲዮ በስካንዲኔቪያ
eprdf1
May 24, 2013 08:21 am By  Leave a Comment
በእንግሊዝኛው ምህጻረ ቃል NISS (National Intelligence and Security Service) የብሔራዊ ደህንነትና የደኅንነት አገልግሎት ሁለተኛ ሰው የሆኑት አቶ ኢሳያስ ወ/ጊዮርጊስ ስዊድን እንደሚመጡ ተሰማ። በስካንዲኔቪያ አገራትና በድፍን አውሮፓ በሚኖረው ዲያስፖራ ላይ የሚያተኩር “የግል” መሰል የሬዲዮ ስርጭት ለመጀመር መታሰቡም ተሰምቷል።

የጎልጉል የመረጃ ምንጮች እንዳስታወቁት አቶ ኢሳያስ ስዊድን ይመጣሉ የተባለው በመጪው የሰኔ ወር ነው። የኤርትራዊ ዜግነት ያላቸውና አቶ መለስ በእጅጉ ይተማመኑባቸው እንደነበር የሚነገርላቸው አቶ ኢሳያስ ስዊድን ከደረሱ በኋላ ሊያከናውኑ ስላሰቡት ተግባር ዝርዝር ለመረዳት ጊዜው ገና እንደሆነ ምንጮቹ አመልክተዋል።

“ሆኖም ግን” ይላሉ ምንጮቹ፣ ” ሆኖም ግን አቶ ኢሳያስ ድርጅታቸው ኢህአዴግ በስካንዲኔቪያን አገሮች በተደጋጋሚ ያጋጠመውን ውግዘት አስመልክቶ አዲስ አደረጃጀት እንደሚገነቡ ታውቋል፡፡”
የኢህአዴግና የስርዓቱ ደጋፊዎችን ለማብዛት በልዩ ልዩ ጥቅማ ጥቅም አባላትን የመመልመሉ ስራ በተጠናከረ መልክ እንደሚሰራበትና የዲያስፖራውን ማኅበረሰብ ለመጠርነፍ ይዋቀራል የተባለው አዲሱ ድር /ኔትወርክ/ ትኩረት የሚያደርገው “አብዛኛው አድፋጭ” ወይም “silent majority” ላይ እንደሆነ መረጃ ሰጪዎቹ ተናግረዋል። ይህንኑ ተግባራዊ ለማድረግ የኢትዮጵያዊያን ኮሚኒቲዎችን ማደራጀት አንዱና ዋናው የአደረጃጀቱ አግባብ እንደሆነም ተጠቁሟል።

Thursday, May 23, 2013

በጥቁር ገበያ የዶላር ዋጋ በሰላሳ ሳንቲም መቀነሱ አነጋጋሪ እየሆነ ነው


dollar1
May 23, 2013 03:29 am By  Leave a Comment
በአዲስ አበባ የሚገኙ የጥቁር ገበያ ባለድርሻዎች በከፍተኛ የመንግስት ባለስልጣናት እና ታዋቂ ነጋዴዎች ከሙስና ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በመታሰራቸው በተፈጠረ መደናገጥ መነሻ ከፍተኛ የሆነ ኪሳራ እያጋጠማቸው መሆኑን ገልፀው፣ የዶላር ምንዛሪ በታሪኩ የሰላሳ ሳንቲም ቅናሽ አሳይቷል።

የከፍተኛ ባለስልጣናቱ በወንጀል የመጠርጠር ዜና ከመሰማቱ በፊት ሃያ ብር ከአርባ ሳንቲም የነበረው የዶላር ምንዛሪ ወደ ሃያ ብር ከአስር ሳንቲም በሳምንት ውስጥ ቀንሷል። በዚህ ቅናሽ ውስጥ አስደንጋጭ የሆነው ክስተት በማንኛውም አይነት ምንዛሪ መጠን ዶላር ወደላይ ሲጨምር ሆነ ሲቀንስ በሰላሳ ሳንቲም የልዩነት ምንዛሪ ውስጥ ወድቆ አለማወቁ መሆኑን ከስፍራው ያገኘነው መረጃዎች ያሳያሉ። በሙስና ከተጠረጠሩ ባለስልጣናት እና ነጋዴዎች ጋር በተያያዘ ይህ ልዩነት መፈጠሩ አብዛኛው የጥቁር ገበያ የዶላር ምንዛሪ ባለድርሻ አካላትን ማስደንገጡን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው ወገኖች ጠቁመዋል።

ባለፉት አራት ወራት ውስጥ ከፍተኛ የዶላር እጥረት በሀገሪቷ ሲከሰት የጥቁር ገበያ ባለድርሻ አካላት ከፍተኛ ተጠቃሚ መሆናቸውን ቢገለጽም፣ ከመንግስት እና ከግል ባንኮች ሰራተኞች የገጠማቸው ችግር ግን እጅግ ፈታኝ እንደነበር አስረድተዋል። ይህም ሲባል፣ ለአንድ የአሜሪካን ዶላር ከአንድ ብር እስከ አንድ ብር ከሃምሳ ሳንቲም የባንኩ ደንበኞች ክፍያ እየፈጸሙ ከፍተኛ መጠን ያለው የዶላር ምንዛሪ ከባንኮቹ ማግኘትን በአማራጭነት በመውሰዳቸው ወደ እኛ ከመምጣት ባንኮንችን ተመራጭ ያደርጉ ነበር። ሆኖም ከፍተኛ መጠን ዶላር የማይፈልጉ ደንበኞች በወቅቱ ስለነበሯቸው ከፍተኛ ተጠቃሚ መሆናቸውንም አልሸሸጉም።

ኦባንግ ለኬሪ የጥሪ ደብዳቤ ላኩ!



አኢጋን ለታቀደው ሰልፍ ድጋፍ ሰጠ
smne state


በቅርቡ በሚከበረው 50ኛው ዓመት የአፍሪካ ኅብረት ክብረበዓል ላይ በተጋባዥነት ለሚገኙት የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ (አኢጋን) ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶ በፋክስ የሚደርስ ቀጥታ ደብዳቤ ላኩ፡፡ በደብዳቤው ላይ አቶ ኦባንግ ሰሞኑን በአፍሪካ ህብረት አካባቢ ለተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ድርጅታቸው ድጋፍ እንደሚሰጥ አስታውቀዋል፡፡
በበርካታ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ለሚ/ር ኬሪ በደብዳቤያቸው ላይ ማሳሰቢያ የሰጡት ኦባንግ የአፍሪካ ኅብረት ሲቋቋም ቅኝ አገዛዝን መታገል፣ የህግ የበላይነትን ማስከበርና የዜጎችን መብት ማስጠበቅ ዋንኛ ዓላማው የነበረ ቢሆንም የያኔዎቹ መስራች መሪዎች አሁን በህይወት ቢኖሩና የዛሬዪቱን አፍሪካ ቢመለከቱ ምን ይሉ ይሆን በማለት ጠይቀዋል፡፡
በመላ አፍሪካ በዘመናችን ያለውን የሰብዓዊ መብት መጣስ፣ የሙስና መስፋፋት፣ የሕግ የበላይነት መጥፋት፣ … የጠቀሱት ኦባንግ በኢትዮጵያ የተንሰራፋውንና በዘረኝነት ላይ የተመሠረተውን የአገዛዝ ስልት፣ አፈና፣ ፍትህ አልባነት፣ ህገወጥነት፣ በፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች ላይ የሚደርሰውን እንግልት፣ በምርጫ ሰበብ የሚደረገውን ዓይን ያወጣ ማጭበርበር፣ ከውጭ የሚገባ ዕርዳታን ለፖለቲካ ዓላማ መጠቀምን፣ በጋዜጠኞችና ሃይማኖት መሪዎች ላይ የሚደርሰውን እስርና አፈና፣ ወዘተ ዘርዝረው በመጥቀስ የኢትዮጵያን ወቅታዊ ሁኔታ አስረድተዋል፡፡
ጆን ኬሪ (ፎቶ: SAUL LOEB/AFP/Getty Images)
ጆን ኬሪ (ፎቶ: SAUL LOEB/AFP/Getty Images)
ሚኒስትሩ ክብረበዓሉን በሚሳተፉበት ወቅት የተጠራ ህዝባዊ የተቃውሞ ሰልፍ መኖሩን የጠቆሙት የአኢጋን ዋና ዳይሬክተር ድርጅታቸው ይህንን ሰልፍ የሚደግፍ መሆኑንና ጆን ኬሪም ጉዳዩን በቅርብ እንዲከታተሉ ጠይቀዋል፡፡ በኢትዮጵያ የተንሠራፋውን የመናገር፣ የመሰብሰብ፣ ወዘተ መብት መነፈግ ለማመላከት ጥቁር በመልበስ ሰልፈኞቹ በሰላማዊ ሁኔታ ለሚያቀርቡት ሁሉን ዓቀፍ ጥያቄ ከአገዛዙ በኩል ሊወሰድ የሚችለው ዕርምጃ ምን ሊሆን እንደሚችል እንደሚያሳስባቸው ጠቁመዋል፡፡
አሜሪካ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትንና ግንኙነት ድርጅታቸው በውል እንደሚረዳው የጠቆሙት አቶ ኦባንግ የአሜሪካ አቋም አምባገነኖችን መደገፍ ሳይሆን ከህዝብ ጋር መቆም ሊሆን እንደሚገባው አሳስበዋል፡፡ በአፍሪካ ለተሰንሰራፋው አምባገነንነት ተጠያቂው አምባገነን መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ እነርሱን የሚደግፉ ሁሉ መሆናቸውን የጠቆሙት ኦባንግ የአሜሪካና የኢትዮጵያ ግንኙነት ዘላቂነት የሚኖረው የአሜሪካ ብሔራዊ ጥቅም ከኢትዮጵያውያን ሰብዓዊ ጥቅም ጋር ሲተሳሰር ብቻ መሆኑን በዚህ በቀጥታ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ በተላለፈው መልዕክታቸው አበክረው አሳስበዋል፡፡
አቶ ኦባንግ ሜቶ የላኩት ደብዳቤ ሙሉ ቃል ከዚህ በታች ይገኛል፡፡

Tuesday, May 21, 2013

ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት “የሰማያዊ” ፓርቲ ሊቀመንበር ከላይፍ መጽሄት ጋር ያደረጉት ቃለ-ምልልስ


ላይፍ መጽሄት
ኢንጅነር ይልቃል ጌትነት የ ‹‹ሰማያዊ›› ፓርቲ ሊቀመንበር ናቸው፡፡ ፓርቲው ከተመሰረተ ጥቂት እድሜ ያስቆጠረ ቢሆንም በአሁኑ ወቅት በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች የሚነሳ ለመሆን በቅቷል፡፡ የላይፍ መጽሄት አዘጋጅ የሆነው ዳዊት ሰለሞን ግንፍሌ አካባቢ በሚገኘው የፓርቲው ጽ/ ቤት በመገኘት ኢንጅነሩን በዋናነት ስለ አማሮች መፈናቀል አነጋግሯቸዋል፡፡
Interview Eng. Yilkal Getnet
ላይፍ ፡- ለፖለቲካ ስራ ሙሉ ጊዜን መስጠት በኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ አስቸጋሪ አይሆንም?
ኢንጅነር ይልቃል ፡- መኖር ስላለብኝ ጥቂት ስራ እሰራለሁ፣ የሚበዛውን ጊዜዬን ግን የማሳልፈው ለፓርቲው ስራ ነው፡፡ አንዳንድ ጊዜ ነገሮች ለምርጫ አስቸጋሪ ሲሆኑ የምትወስደው ውሳኔ አንዱን በማጠፍ ለአንደኛው ብቻ ራስህን መስጠት ይሆናል፡፡
ላይፍ ፡- የሚመሩት ፓርቲ ሰማያዊ የፖለቲካ ፍልስፍናው በምን ላይ የተመሰረተ ነው?
ኢንጅነር ፡- ጥያቄው ሰፋ ያለ ነው፡፡ በዋናነት ግን የፖለቲካ ፍልስፍናችን በግለሰብ መብት ላይ የተመሰረተ ነው፡፡ ሴንተር ራይት ሞደሬት ሊበራሊዝምን የፖለቲካ አመለካከት እናራምዳን ብለን ነው የምናምነው፣ የግለሰብ መብት ከተከበረ የሁሉም መብት ይከበራል እንላለን፣ መብት ከግለሰብ ይጀምራል፡፡ ለምሳሌ ይልቃል ወንድ ነው ስለዚህ ጾታ አለው፣ ይልቃል ቋንቋ፣ ትምህርትና ሞያ ያሉት በመሆኑ ሌላ የተለየ ነገር አያስፈልግም፡፡ የእኔ መብት ከተከበረ የምናገረውም ቋንቋ ይከበራል ማለት ነው፡፡ ቡድንና ግለሰብ እኩል ይታያሉ የሚለው አመለካከት ምክንያታዊ አይደለም፡፡ ከቡድን በፊት ግለሰብ ይቀድማል፡፡ እናም የግለሰቡ መብት ሲከበር የቡድኑ ይከበራል ብለን እናምናለን፡፡ የፖለቲካ ድርጅት በየጊዜው ራሱን እያረመ የሚሄድ እንጂ በቅድመ ድንጋጌ ላይ ተመስርቶ ፖለቲካ ሊሰራ አይችልም፡፡ ለምሳሌ የጎሳ ድርጅት እንጂ የጎሳ ፓርቲ መሆን አይቻልም፡፡ እዚህ አገር ጉዳዩ በጣም ስስ በመሆኑ አንነካውም እንጂ አንድ ሰው የኦሮሞ ድርጅት ነኝ ብሎ ከተነሳ ከኦሮሞ ወዴት መሄድ ይችላል? ምክንያቱም ከመነሻው የተወሰነ ነው፡፡ በጎሳ መደራጀት አሁን እየተፈጠሩ ያሉ ነገሮች መነሻ ነው ብለን እናምናለን፡፡ በቡድን መብቶች መከበር እናምናለን፡፡ ነገር ግን የሁሉ ነገር ማጠንጠኛ በኢትዮጵያችን ውስጥ ጎሳ መሆን ይገባዋል የሚል አመለካከት የለንም፡፡

Monday, May 20, 2013

“መለስ የቆፈሩት ጉድጓድ…”



the hole
May 20, 2013 01:10 am By  13 Comments
ይህንን ቃለምልልስ ያደረግነው ለበርካታ ዓመታት ለኢህአዴግ ሲሰራ ከነበረና በአሁኑ ወቅት ለከፍተኛ ትምህርት ውጪ አገር ከሚገኝ ኢትዮጵያዊ ጋር ነው፡፡ ለደኅንነት ሲባል ስሙን ከመጥቀስ ተቆጥበናል፡፡

ጎልጉል ፦ የጠ/ሚኒስትር መለስ መታመም ድንገተኛ ነው የሚሉ አሉ፤ አሟሟታቸውም ድንገት ነው የሚሉ አሉ፤ በሌላ በኩል ደግሞ አጋጣሚው መልካም እንደሆነ የሚጠቁሙ አሉ አንተ ከየትኛው ወገን ነህ?

መልስ፦ ቅድሚያ አቶ መለስ ድንገት አልታመሙም። በሽታቸው የቆየ እንደሆነ ይታወቃል። ምስጢርም አይደለም። ለዚሁ እኮ ነው ቤተ መንግስት ውስጥ በአዋጅ የተፈቀደላቸውን ቤት አሰርተው በቅርብ ርቀት እየተቆጣጠሩ ለመኖር ቅድመ ዝግጅት ሲያደርጉ የነበረው። በዚህ ቢስተካከል ለማለት ነው። መለስ ለኢህአዴግ አጋር ድርጅቶች ሁሉ የጋራ ነጠብ ናቸው። በድልድይም ይመሰላሉ። በኢህአዴግ አባል ድርጅቶች፣ በተለይም ዋናዎቹ አራት ፓርቲዎች በውስጣቸው የያዙት 21 ዓመትና ከዚያም በላይ የታመቀ ቁርሾ አለ። የመለስ ማለፍ በየድርጅቱ ታፍኖ የኖረውን ቁርሾ ማፈንዳቱ አይቀርም። ከዚህ አንጻር ሳየው የመለስ ሞት አጋጣሚው መልካም የሚሆንበት አግባብ ከምን እንደሆነ ልረዳው አልችልም።

ጎልጉል፦ አዲስ ስርዓት ለመገንባት የሚያስችል አጋጣሚ ይሆናል ነው የሚሉት፤
መልስ፦ ምን አይነት አዲስ ስርዓት? አሁን እኮ ሁሉም ነገር “ባለበት፣ በነበረበት፣ በቀድሞው መልክ ይቀጥላል” እየተባለ ነው። እነሱም ባይናገሩ ህወሃት ወደ እርቅና ድርድር የመመለስ ፍላጎት ይኖረዋል ብዬ ለሰኮንድ አላስብም። ህወሃቶች አንገት ለአንገት ተናንቀው ትግል የሚያደርጉት ተቃዋሚ ከሌለ ብቻ ነው። ለህወሃት መኖር ፈተና የሚሆን ተቃዋሚ ካለ ህወሃቶችም ሆኑ በትግራይ ውስጥ መሰረት ያላቸው ተቃዋሚዎች ልዩነት አያሳዩም። ይህ ሳይታበል የተፈታ እውነት ነው። በ1997 ምርጫ ወቅት የታሰሩት የቅንጅት አመራሮች ሲፈቱ ደስተኛ አልነበሩም። እንዴት እንደተፈቱና ሂደቱ በህወሃት ውስጥ የፈጠረው ውዝግብ የሚረሳ አይመስለኝም። ሌላው ቀርቶ በወቅቱ የምርጫውን ውጤት ቅንጅት ማሸነፉ ሲታወቅ ህወሃት ያገለላቸው እንኳን ሳይቀሩ አንድ ላይ በመሆን አስፈላጊውን ሁሉ ለማድረግ ተማምለው ነበር። ታጥቀውም ነበር። ከዚህም በላይ…

የ“ቀዩ መስመር” ሰላባዎች?



የ"ማበስበሱ" ቁማርና የደኅንነቱ ሚና!!

red-tape2
May 20, 2013 01:31 am By  Leave a Comment
መለስ ህይወታቸው እንዳለፈ ከተሰጡት አስተያየቶችና ትንቢቶች መካከል ቀዳሚው የመለስ ሞት ለህወሃት ጊዜውን ጠብቆ የሚፈነዳ ፈንጂ መሆኑ ነበር። በዚሁ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ በስልጣን ላይ ያሉ የኢህአዴግ ዲፕሎማት “መለስ የቆፈሩት ጉድጓድ” በሚል ርዕስ በሰጡት ቃለ ምልልስ ይህ እንደሚከሰት ቁልጭ አድርገው ተናግረው ነበር።
መለስ አፍነው የያዟቸው የፖለቲካ ችግሮች ጊዜያቸውን እየጠበቁ የሚፈነዱና በመጨረሻም ፓርቲውን እንደሚፈረካክሰው የተገለጸው በየደረጃ የሚፈነዱት ችግሮች እየበረከቱ በመሄዳቸው ነበር። መለስ አፍነው የያዟቸው ችግሮች የእርስ በርስ መበላላት ደረጃ እንደሚያደርሱ በርካታ ወገኖችና መገናኛዎች ጎልጉልን ጨምሮ አመላክተዋል። አሁን አሁን ትንቢቱ የፍጻሜው ጅማሬ ላይ እንደሚገኝ የሚናገሩም አሉ።

የፖለቲካ አቋም ልዩነት ሳይኖር የአስተሳሰብ ልዩነት ማራመድ በህወሃት ዘንድ አይቻልም። ከተሞከረም ክህደት ነው፤ መፈንቅለ መንግስት የማካሄድ ያህል ነው። የርዕዮተ ዓለም ለውጥ የማቀጣጠል ያህል ያስፈርጃል። ሽብርተኛ ያስብላል። ከቶውንም ተቀባይነት ስለሌለው ድንበር ተበጅቶለታል። ድንበሩም “ቀይ መስመር” በመባል ይታወቃል። የ”ቀይ መስመር” ሃሳብ አመንጪና ደራሲ አቶ መለስ ናቸው። “በጠቅላይ ሚኒስትርነት ማዕረግ የቀድሞው ፕሬዚዳንት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ” በሚል የምጸት ስም የሚጠሩት አቶ ሃይለማርያም ደሳለኝም ይህንን የቀይ መስመር ጽንሰ ሃሳብ ለንግግር ያህል ይጠቀሙበታል።

haile and girma
ቀይ መስመር የሚሰመርበት በውል ተለይቶ የተቀመጠ ውስን ጊዜ የለውም። መስመሩ ሁሌም አለ። ሁሉም ቆመውበታል። ከልምድ እንደሚታየው በህወሃት ህመም ኢህአዴግ ሲያተኩሰው በድንገት መስመሩ በደማቁ እንዲቀባ ይደረጋል። መስመሩ የሚቀባበት ደማቅ ቀለም የሚቀዳው አቶ መለስ አፈር ሳይልሱ “በስብሰናል” ሲሉ ከሰየሙት የኢህአዴግ የ”ማበስበሻ” ባህር ውስጥ ነው።

በኢህአዴግ የ”ማበስበሻ” ባህር ውስጥ ያልተነከረ የለም። በዚህ ባህር ውስጥ ሆነው የሚንቦጫረቁት ተቆጥረው አይሰፈሩም። አዲስ አበባ በአራቱም ማዕዘን፣ በክልልና በክልል ዋና ዋና ከተሞች፣ እንዲሁም በተለያዩ አገራት የሚሰነፍጠው የባህሩ “ግልማት” የዜጎችን የመኖር ህልውና ከተፈታተነ ቆይቷል።

በባህሩ ውስጥ በመርከብ ሆነው በጀልባ የሚቀዝፉትን የሚመለከቱ አሉ። ጀልባ የሚቀዝፉት ጌቶቻቸውንና “ልዕልቷን” እያዩ ሽታውን በለመዱት ባህር ውስጥ ይምነሸነሻሉ። በዛው ባህር ውስጥ በደረታቸው እየዋኙና እየተንቦጫረቁ ግብር የሚያስገቡ አሉ። “ዲጂታል” የሚባሉትና “ምስለኔዎቹ” ደሞ የማበስበሻውን “መረቅ የማቅለሚያ ማዕድን” ይዘው አራት ኪሎ የባህሩ አናትና ማማ ላይ ሆነው ሁሉንም ይመራሉ። የባህሩን የመጫወቻ ህግ የሚበላቸውና ከበሰበሰው ባህር ወደ እቶን የሚወረወሩት “የቀይ መስመር ሰለባዎች ” ይለያሉ። ለይተው ሲጨርሱ ለባህሩ ካፒቴን የፌዴራል የስነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ያቀብሉታል። በዚሁ ሂደት ይቀጥላል። አዲስ ነገር የለም። ሊኖርም አይችልም። ይህ መነሻ ነው። ወደ ጉዳዩ እናምራ።

Sunday, May 19, 2013

የዜጎች መብት ረገጣና አፈና በኢትዮጵያ



መሠረት አባተ ከኖርዌይ ግንቦት 2005 

እንደምናውቀው አገራችን ኢትዮጵያ የዜጎች መብት ከማይከበርባት አገር አንዷ ናት ብል ሁሉም 
የሚስማማበት እውነት ነው። ዜጎችን ለትምህርት፣ ለልማት እንዲሁም መልካም ዜጋን ከመቅረጽ ይልቅ 
ቦዜኔ፣ ተረጂ፣ በራስ ከመተማመን ይልቅ ተመጽዋች ዜጎች ያሉባት አገር እንድትሆን ከወያኔ ቡድን 
የተሰጣቸው ገጸ በርከት ከሆነ ብዙ አመታትን አስቆጥሮአል። 

በአረብ አገራቱ ኢትዮጵያዊያን እህቶቻችን ላይ እየተፈጸመ ያለው ጥቃት ምን ይገርማል! ምክንያቱም ወያኔ 
በዜጎች ላይ እያደረሰ ያለው ከብዙ በጥቂቱ ይህንን ይመስላል። አንዲት ሴት እንደዜጋ ለአገሯ በሙያዋ 
ማገልገል እየቻለች ነገር ግን የሴቷ ጥቃት የሚጀምረው ከወያኔ ባለሥልጣናት የሚቀርብላትን ጥያቄ 
ከማሰተናገድ ይጀምራል። በኢትዮጵያ በሴቶች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለመከላከልና ግንዛቤ ለመጨበጥ 
ዋንኛው መንገድ መደራጀት እንደሆነ ሊሰመርበት ይገባል። ለዚህም አለም አቀፍ የኢትዮጵያ ሴቶች 
ማህበር International Ethiopian Woman Organization (IEWO) በአለም አቀፍ ደረጃ በሴቶች ላይ 
የሚደርሰውን ግፍና እንግልት እንዲሁም በየአገሩ በስደት ላይ መብታቸውን የሚያስከብርላቸው አተው 
የወገን ያለ እያሉ ሲጮሁ እየደረሰላቸው ያለው ይኔው ድርጅት ነው። 

የሴቶችን መብት ከመጠበቅ እና በሕግ እስከማረጋገጥ ድረስ በታሪክም በቁርጠኝነት የታገለ እንዲሁም 
የሴቶች አስተዋጾ ከወንዶች እኩል ነው ብሎ በትግሉም እኩል አላፊነት እና ድርሻ እንዳላት ያረጋገጠ 
ፓርቲ ሕዝባዊ አብዮታዎ ፓርቲ ኢሕአፓ ለመሆኑ በፓርቲው ተዘጋጀተው ለሕዝብ ለንባብ የበቁ የታሪክ 
መጽሐፍቶችን መመርመር በቂ ይሆናል።

Wednesday, May 15, 2013

ከሙስናው በስተጀርባ (ከኢየሩሳሌም አርአያ)



ከኢየሩሳሌም አርአያ

በሕወሐት የተፈጠረው የቀውስ ማእበል አድማሱን እየለጠጠ መሔዱን ተከትሎ «ታማኝ» ሆነው በሙስና ሲያገለግሉ የቆዩትን ጭምር እየበላ እንደሚገኝ የቅርብ ምንጮች አስታወቁ። በቀዳሚነት የሚያነሱት በጉምሩክ ቁልፍ ስልጣን የነበረውን የሕወሐት አባል ገ/ዋህድ ወ/ጊዮርጊስን ሲሆን እንዴትና በማን ወደስልጣን እንደመጣ እንዲሁም ምን-ምን ተግባራት ይፈፅምና ያስፈፅም እንደነበረ ምንጮቹ ሂደቱን እንደሚከተለው ይገልፁታል።
tplf rotten apple
ገ/ዋህድ በ1993ዓ.ም ፓርቲው ለሁለት መሰንጠቁን ተከትሎ ወደ ስልጣን እንዲመጣ ተደረገ። ከጉምሩክ ሃላፊነት በተጨማሪ የገቢዎችና ጉምሩክ ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተርነት ስልጣን እንዲጨብጥ የተደረገው በአቶ መለስ በተለይ በአዜብ ይሁንታ ጭምር እንደነበረ ምንጮቹ ይጠቁማሉ። ገ/ዋህድ ለዚህ ስልጣን የበቃው ለአቶ መለስ ቡድን በከፈለው መስዋእትነት ሲሆን በክፍፍሉ ማግስት የሙስና ዘመቻ ተከፍቶ እነአባተ ኪሾና ሌሎች እስር ቤት እንዲገቡ ቀጥተኛ ትእዛዝ ከመስጠት አንስቶ ራሱ ክስ አዘጋጅ፣ምስክርና ፈራጅ..በመሆን የላቀ ሚና መጫወቱን ያስታውሳሉ። በዚህ ተግባሩ የበለጠ ታማኝነቱን በማሳየቱ ከአዜብ በሚሰጠው ቀጥታ ትእዛዝ ሙስናውን ማከናወን መቀጠሉን ምንጮቹ አያያዘው ይጠቁማሉ። በ10ሺህ ቶን የሚገመት ቡና ከአዜብ በተቀበለው ትእዛዝ በህገወጥ መንገድ ከአገር ተዘርፎ የተሸጠበትና ጉዳዩም በፓርላማ ተነስቶ በጠ/ሚ/ሩ «የሌቦቹን እጅ እንቆርጣለን» የሚል አስቂኝ ምላሽ መሰጠቱን ያስታውሳሉ። በተጨማሪ በጉምሩክ ለረጅም አመት በመምሪያ ሃላፊነት ሽፋን የተቀመጠውና የቢሮውን የበላይ ሃላፊዎች በጥብቅ ከመቆጣጠር ጀምሮ እያንዳንዱን የሙስና ተግባር ከጀርባ ሆኖ የሚያስፈፅመው የአዜብ የቅርብ ስጋ ዘመድ ፍትሃነገስት ክንደያ እንደሚጠቀስና ግለሰቡ ቀረጥ ያልተከፈለባቸው 500 ሳተላይት ዲሾች እንዲገቡና በአዜብ በበላይነት ይመራ ለነበረው የዘረፋ ቡድን ለሰባት አመታት በየወሩ 20ሚሊዮን ከቴሌ በህገወጥ መንገድ እንዲዘረፍ ያደረገና በኋላም ከነገ/ዋህድ ጋር ሆኖ በርካታ ሙስናዎችን በዋናነት በማስፈፀም እንደሚጠቀስ ያመለክታሉ።

Monday, May 13, 2013

ሙስናን በስንጥር! ከዚያስ?



ዋናዎቹ “ሌቦች” በሞቀው ሆቴላቸው አሉ!!

inter


በቀረጥ፣ በሙስናና ባለስልጣናትን የንግድ ሸሪክ በማድረግ ኢትዮጵያን እየጋለቡዋት ያሉ “ባለሃብቶችና አሽከሮቻቸው” እስካልተነኩ ድረስ ኢህአዴግ በሙስና ላይ የጀመረውን ትግል ሙሉ ሊያደርገው እንደማይችል ተገለጸ። ጅማሮው የችግሩ ቁልፍና እምብርት በሆነው ተቋም ላይ መሆኑ የሚደነቅ እንደሆነ የሚገልጹ ክፍሎች ደግሞ ድሩ ያልተበተበው የለምና የመጨረሻው አካሄድ ወዴት እንደሚያመራ ለመገመት ቢቻልም ጅምሩ ይገፋል የሚል ጥርጣሬ እንዳላቸው አስታውቀዋል።
የባለስልጣናት ሚስቶችን፣ ዘመዶችና ወዳጆችን በተቋሞቻቸው ውስጥ በማይመጥኑት ሃላፊነት በመመደብ፣  ከተለያዩ የማማለያ ሽልማቶች ጋር ከፍተኛ ደሞዝ በመክፈል፣ አንዳንዴም ውጪ አገር ድረስ የህክምና ወጪ በመሸፈን ሰበብ የአገሪቱን የአመራር በትር ጨብጠው አገሪቱን እያለቡ ያሉት ወገኖች በይፋ እንደሚታወቁ የሚገልጹ ክፍሎች “አሁን ተጀመረ የተባለውና ይፋ የተደረገው የሙስና ትግል እነዚህን ክፍሎች ብብቱ ስር ይዞ የሚቀጥል ከሆነ ከቀልድ አይዘልም” ሲሉ ጥርጣሬያቸውን ያስቀምጣሉ።
አትራፊ የሆኑ የህዝብና የአገር ተቋማትን ወደ ግላቸው ያለ ክፍያ፣ ያለ ተመጣጣኝ ዋጋ፣ በተጭበረበረ ጨረታና አሰራር ወደ ግላቸው በማዞር አቶ መለስ “ተራው ህዝብ” በማለት በሚጠሩት ህዝብ ትከሻ ላይ እንዳሻቸው የሚዘሉትን “የሙስና አባቶችን” መታገል የማይችል የጸረ ሙስና ቀረርቶ ከተራ የፖለቲካ ልዩነት የዘለለ መነሻና መድረሻ ሊኖረው እንደማይችል እነዚሁ ወገኖች ይናገራሉ።
ሰሞኑን የመንግስት፣ የግል መሰል የድርጅት፣ የግል፣ የድረገጽ መገናኛዎች የተቀባበሉት ዜና የፌዴራሉ የጸረሙስናና የስነምግባር ኮሚሽን ይፋ ያደረገው የባለስልጣናት፣ የታዋቂ ነጋዴዎች እንዲሁም ተባባሪና የሙስናው ተዋናይ ናቸው የተባሉ አስራ ሶስት ሰዎች ስም የተጠቀሰበት እስር ነው። ይህንኑ ዜና በማድነቅ ጅምሩን የሚያበረታቱ ክፍሎች በበኩላቸው “ቢዘገይም፣ ችግሩና ንቅዘቱ እንዳለ ያደባባይ ሚስጥር ቢሆንም አሁንም አልረፈደምና ኢህአዴግ ለጀመረው የሙስና ትግል ድጋፍ መስጠት አግባብ ነው” ባይ ናቸው።
ኢህአዴግ “ገምተናል” በማለት ቃል ሳይመርጥ ራሱን ከፈረጀበት የሙስና አዘቅት አንድ ሁለት እያለ ዘመቻ መጀመሩ ሊበረታታ እንደሚገባ የሚጠቁሙ ክፍሎች “በአንድ ጀንበር ተዓምር መጠበቅ ከተራ የማንቋሸሽና ሁሌም የመቃወም አዝማሚያ ላይ የመኖር ያህል ያስቆጥራል። በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ጅማሬው ወዴት እንደሚያመራ አይታወቅምና በትዕግስት መከታተሉ የተሻለ ይሆናል” ሲሉ በቀጣይ ርምጃው እየሰፋ እንደሚሄድ ተስፋቸውን ይገልጻሉ። ዜናውን ያቀረበው ኢቲቪን ግን ይወቅሳሉ።

Monday, May 6, 2013

ኦባንግ የኢህአዴግ ደጋፊ ስደተኞችን አስጠነቀቁ

 

“በአስመሳይ ስደተኞች ላይ በቂ መረጃ አለ”
 
obang
 
“ክፉን በክፉ መመከት ባያስደስትም ወቅቱ ያስገድደናል” ሲሉ የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር ኦባንግ ሜቶ በተለይ ለጎልጉል ተናገሩ። አገዛዙን ሸሽተው በተለያዩ አገራት ከለላ አግኝተው በስደት የሚኖሩም ሆኑ ጉዳያቸው እየታየ ያሉ ወገኖች አካሄዳቸውን እንዲያስተካክሉ አስጠንቅቀዋል።
 
የአሜሪካ ከፍተኛ ባለስልጣናትና ህግ አውጪዎች፣ የጀርመን የኢሚግሬሽን ሃላፊዎችና ከፍተኛ የፖለቲካ ሰዎች፣ ከኖርዌይ የኢሚግሬሽን ጉዳይ ሃላፊዎችና ተዛማጅ ሃላፊነት ካላቸው የህግ ክፍሎች፣ በካናዳ በተለያዩ ደረጃ ካሉ ባለስልጣናትና ወትዋቾች (አክቲቪስቶች)፣ በስዊድን አንዲሁም በእንግሊዝ በተመሳሳይ ግንኙነት ፈጥረው እየሰሩ መሆኑንን ያመለከቱት አቶ ኦባንግ “አገራቱ የስደት ፈቃድ ካገኙ በኋላ ለስደት ዳረገን ከሚሉት መንግሥት ጋር በቅርብ እየሰሩ ስላሉ አስመሳይ ስደተኞች አስገራሚ መረጃዎች መሰብሰባቸውን አውቃለሁ” ብለዋል።
 
አቶ መለስ በሞቱ በወር ጊዜ ውስጥ ብቻ በካናዳ ቫንኮቨር 27 አንድ አይነት ቋንቋ ብቻ የሚናገሩ ወጣቶች ጥገኛነት መጠየቃቸውን ጉዳዩን በጥብቅ እየመረመሩት ካሉ ክፍሎች ማረጋገጣቸውንና የምርመራውን ውጤት በመጠባበቅ ላይ እንደሚገኙ ያመለከቱት አቶ ኦባንግ፣ “ወጣቶቹ ካናዳ የገቡት ለእያንዳንዳቸው 75 ሺህ ዶላር በማውጣት ነው። ይህን ገንዘብ ማን ሰጣቸው? እንዴት አገኙት? እንዴት ከአንድ አካባቢ (ክልል) ብቻ ሊሆኑ ቻሉ? የሚሉት ጉዳዮች ምርመራውን በያዙት ወገኖች ላይ ግራሞት የፈጠረ ትልቅ ጉዳይ ነው” በማለት የጉዳዩን አሳሳቢነት ከገንዘብ ማሸሽ ጋር በማያያዝ አመላክተዋል። ለምሳሌ አንድ ጉዳይ አነሱ እንጂ በመላው ካናዳ በተመሳሳይ የምርመራ ስራ እየተሰራ መሆኑንን ተናግረዋል።
 
የካናዳው አንድ ማሳያ ሲሆን በአሜሪካ ግዙፍ ቪላዎችን እየገዙ ያሉት ክፍሎች ጉዳይ ከገንዘብ ማሸሽ ጋር ተያይዞ እየተመረመረ እንደሆነ አቶ ኦባንግ አስረድተዋል። ጥገኝነት ካገኙ በኋላ “ሊገለን ሲል አመለጥነው” ያሉትን ኢህአዴግን የሚደግፉ ክፍሎች ላይም ለሚመለከታቸው ባለስልጣናትና ተቋማት ከሚቀርበው መረጃ በተጨማሪ ከፍትህ ወዳድ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦች ጋር ድርጅታቸው በጥምረት እየሰራ መሆኑን አቶ ኦባንግ አልሸሸጉም፡፡
 
በጀርመን ኑረንበርግ በኢሚግሬሽን ጉዳዮች ዙሪያ የሚሰሩ ባለስልጣናት በተመሳሳይ የምርመራ ስራ እያከናወኑ እንደሆነ ያመለከቱት አቶ ኦባንግ፣ በግል በጉዳዩ ዙሪያ መነጋገራቸውን አስታውቀዋል። የጥገኝነት ፈቃድ ካገኙ በኋላ ዲያስፖራውን በመከታተልና አገር ቤት የሚገኙ ቤተሰቦቻቸው ለችግር እንዲዳረጉ የሚያደርጉትን ክፍሎች ማንነት ነቅሰው እንደሚያውቋቸው ባለሥልጣናቱ በግንኙነታቸው ወቅት እንዳረጋገጡላቸው አመልክተዋል።
 
“ኢህአዴግ ለጊዜው የጠመንጃ ሃይል አለው። የገንዘብ አቅም አለው። ወዳጆችም አሉት። እኛ ደግሞ በየአቅጣጫው ፍትህ ወዳድ አጋሮች አሉን። ከነሱ ጋር እየሰራን ነው” በማለት አስረግጠው የተናገሩት ኦባንግ በማንኛውም መስፈርት ስደት ላይ ያሉ ወገኖችን መከታተልና መሰለል ተቀባይነት የለውም ብለዋል።
 
“አሜሪካ፣ ካናዳ፣ ኖርዌይ፣ እንግሊዝ፣ ስዊድንና ጀርመን አገር ባለስልጣናቱ ከበቂ በላይ መረጃ አግኝተዋል። እኛም እየሰራንበት ያለ ተከታታይ ስራ አለ። በየአቅጣጫው የሚደረገው ትግል በቅርቡ ፍሬው መታየት ይጀምራል” የሚሉት ኦባንግ ርምጃው መወሰድ ሲጀምር ከስድስት እስከ አስራ ሁለት ዓመት እስር እንደሚያስከትል፣ ከዚያም የከፋ አደጋ እንዳለው ጠቁመዋል።
 
በትምህርትና በተለያዩ ስልጠናዎች ወደ ተለያዩ ዓለማት የሚሰማሩ የአገዛዙ አገልጋዮችም ቢሆኑ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው የሚያሳስቡት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ዋና ዳይሬክተር “አገዛዙ መድቧቸው በየኤምባሲው ውስጥ የሚሰሩ ሰራተኞች፣ የስለላ ሰዎች፣ ከፍተኛ ባለስልጣናት ምስላቸውንና ማንነታቸውን ባደባባይ አይገልጹም። በኤምባሲዎች ድረ ገጽ ላይ እንኳ ስለማንነታቸው በቂ መረጃ ለመስጠት ድፍረት የላቸውም። የስርዓቱ ባህሪና የወንጀለኛነቱ መጠን ራሳቸውን እንዲገልጹ አይፈቅድላቸውም” በማለት በተራ መደለያና ጥቅማ ጥቅም ደረታቸውን እየሰጡ ያሉ ወገኖች አካሄዳቸውን በመመርመርና የሚያስከብራቸውን ተግባር እንዲፈጽሙ ጥሪ አስተላልፈዋል።
 
“ምክር በመለገስ ሰፊ ጊዜ የወሰድነው ክፉን በክፉ የመመለስ እምነት፣ ክፉ እንድናደርግ የሚገፋን  ድርጅታዊ አቋም ስለሌለንና የሚጠሉንን ጭምር ነጻ የሚያወጣ ግዙፍ ራዕይ ስላለን ነው” የሚል ጥልቅ አስተያየት የሰነዘሩት አቶ ኦባንግ፣ በአገራቸው መኖር ያልቻሉ ወገኖች ተሰደውም ሰላም ሲያጡ መመልከት ግን የማይቻልበት ደረጃ መድረሱን አመልክተዋል። ከዚህም በተጨማሪ እሳቸው በግል፣ ድርጅታቸው በመርህ የሚታገሉለት የሰዎች መብት መከበር ብሩህ አጀንዳ በዝምታ እንዲቀመጡ እንደማይፈቅድላቸው ተናግረዋል።
 
ከኖርዌይ የኢሚግሬሽን ባለስልጣናት ጋር በተገናኙባቸው ወቅቶች ይህንኑ ጉዳይ አስመልክቶ በግልጽ እንደነገሯቸው ያመለከቱት ኦባንግ ሜቶ፣ አሁን ስሙንና ዝርዝር ጉዳዩን ለመናገር ፈቃደኛ ካልሆኑት ክፍል ጋር በጋራ እየሰሩ መሆኑንን ጠቁመዋል። አኢጋን ያቋቋመው የግልጽነትና የተጠያቂነት ግብረ ሃይል አንዱና ትልቁ ስራው እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን መርምሮና አጣርቶ ለሚመለከታቸው በማቅረብ ፍትህን መጠየቅ መሆኑንን ያመለከቱት አቶ ኦባንግ “ዝርዝሩን መናገር ቢከብድም ብዙ ስራ እየሰራንበት ያለው የስደተኞች ጉዳይ የሌሎችንም ተሳትፎና ትብብር ይጠይቃል” ብለዋል።
 
“በስሜት መታገል አያዋጣም” የሚል የትግል ማስተካከያ ሃሳብ ፈንጠቅ ያደረጉት አቶ ኦባንግ የስደት ማመልከቻቸው ተቀባይነት አግኝቶ የመኖሪያ ፈቃድ ካገኙ በኋላ አገር ቤት በመመላለስ፣ ህግ በመተላለፍ ለአገዛዙ የሚሰሩ በሙሉ “ብልጥና አዋቂ ነን፣ ባለጊዜዎች ነን” በሚል አስተሳሰብ የሚንቀሰቀሱ አንደማያዋጣቸው ሲያሳስቡ “ለእንደዚህ አይነቶች ሁሉም ዓይነት መንገድ አይሰራላቸውም። ግለሰቦችንና ባለስልጣናትን ሳይሆን አሰራርን በማጭበርበር ይጠየቃሉ። አገራቱ እንደ ኢትዮጵያ ሳይሆን ስራ ላይ የሚውል ህግ አላቸውና ይተገብሩባቸዋል። አሰራራቸው ሲጭበረበር ዝም የማይሉት ለማንም ሲሉ ሳይሆን ለራሳቸው ሲሉ ነው። አሰራር / ሲስተም/ ሲበረዝ የሚያስከትለውን አደጋ ስለሚረዱ የሚታገሱ ካልሆነ በቀር በዝምታ አያልፉም። በኖርዌይም ሊሆን የታሰበው ይህ ነው። አሁንም ዝርዝር መረጃ ለመስጠት እቸገራለሁ” በማለት ነው። አቶ መለስ ህይወታቸው ባለፈ ወቅት በስደት ካምፕ የሚኖሩ ጭምር ለቅሶ መቀመጣቸው በኖርዌይ ሚዲያዎች አስገራሚ ተብሎ መዘገቡ፣ በህዝቡና በፖለቲከኞች ዘንድ መነጋገሪያ አጀንዳ እንደነበር አይዘነጋም።
 
በርካታ አሳዛኝና ህሊናን የሚፈታተኑ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሆነ ያወሱት ኦባንግ ሜቶ፣ ህጻናትን በጉዲፈቻ ስም በመቸብቸብ፣ ሴት እህቶቻችንን አረብ አገራት ያለ ዋስትና በመላክ ከፍተኛ ገበያ እየሰሩ ያሉት የህወሃት ሰዎች እንደሆኑ በበርካታ ማስረጃዎች መረጋገጡን ያስታውሳሉ። አያይዘውም አገራቸውን ለቀው ለስደት የሚወጡትን ወደ ኬኒያ፣ ታንዛኒያና ደቡብ አፍሪካ ብሎም በጅቡቲና በሶማሌ በኩል ገንዘብ እያስከፈሉ የሚያሻግሩት አሁንም እነሱ ናቸው ሲሉ አስቀድመው ስለ ጠየቁት ትብብር ማሳሰቢያቸውን ያጠናክራሉ።
 
aba“በማስተዋል እንስራ” የሚሉት ኦባንግ በየአቅጣጫው መረጃ ላይ የተኙና፣ በምን አገባኝ ስሜት ዝምታን የመረጡ ወገኖች ያላቸውን መረጃ በመስጠት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ከተለያዩ አካላት ጋር እየሰራ ያለውን ስራ እንዲያግዙ አሳስበዋል። ይህንን ማድረግ አቶ ኦባንግንና እርሳቸው የሚመሩትን ድርጅት መርዳት ሳይሆን ራስንና አገርን መርዳት እንደሆነም አጽንዖት ሰጥተው ተናግረዋል።
 
ከተቋቋመ 135ዓመታትን ያስቆጠረው የአሜሪካ ሕግ ባለሙያዎች ማኅበር (ABA) እየተባለ በሚጠራውና 400 ሺህ በላይ አባላት ባሉት የህግ ባለሙያዎች ዓመታዊ ጉባኤ ላይ ከሁለት ሳምንት በፊት ንግግር እንዲያደርጉ በተጋበዙበት ወቅት አቶ ኦባንግ ሜቶ በርካታ ጉዳዮችን በማንሳት ድጋፍ ጠይቀው አዎንታዊ ምላሽ እንዳገኙ ጠቅሰዋል፡፡ በርካታ የህግ ባለሙያዎች በተገኙበት ስብሰባ ላይ በኢትዮጵያ ያለውን የሰብዓዊ መብት ረገጣ፣ ኢህአዴግ ህግን ከለላ በማድረግ በዜጎች ላይ የሚፈጽመውን ወንጀል፣ ለእንደዚህ ዓይነት ተግባሩ ማስፈጸሚያም የጸረ ሽብርተኝነትን፣ የመያዶችን፣ ወዘተ ህጎች በማውጣት ዜጎችን ለእስር፣ ለስደት፣ ለስቃይ መዳረጉን፣ የፍትህ አካላቱን ህግን በሚያከብሩና ፍትህ በሚያስፈጽሙ ሳይሆን ራሱ በመሠረተው ተቋም እያመረተ ለፖለቲካ መጠቀሚያ እያደረገ መሆኑን፣ ከዚህ አልፎ ደግሞ በስደተኛነት ስም ደጋፊዎቹን ወደ ውጪ በመላክ በሃሰት የኢህአዴግ ሰለባ በማስመሰል በየምዕራቡ ዓለም የመኖሪያ ፈቃድ እንዲያገኙ በማስደረግ መልሶ ስደተኛውን እዲሰልሉና ለሥርዓቱ እንዲሰሩ እያደረገ መሆኑን፣ ወዘተ በስፋት አብራርተዋል፡፡ የባለሙያዎቹ ማኅበር ጉዳዩን በጥልቀት እንደሚያየውና ያለውን ከፍተኛ የሰው ኃይል በመጠቀም ከአኢጋን ጋር እንደሚሰራ ከሌሎች ማኀበራት ጋር በመሆንም በተለይ በምዕራቡ ዓለም የተሰገሰጉትን አስመሳይ ስደተኞች ወደ ፍትህ የማምጣቱ ጉዳይ ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን ለአቶ ኦባንግና ለድርጅታቸው አረጋግጠዋል፡፡
 

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡