Wednesday, January 2, 2013

ወሬ ይገድላል


(ርዕሰ አንቀጽ)
new years resolutions

በጎርጎሪያኑ የቀን መቁጠሪያ ለምትገለገሉ ሁሉ መልካም አዲስ ዓመት!! በአዲሱ ዓመት ከራስ ጋር በመታረቅ፣ ከህሊናና ከእዕምሮ ባርነት በመላቀቅ፣ ከይሉንታ ጥብቆ ውስጥ በመውጣት፣አካሄድን ለማሳመር ይቻል ዘንድ የተጠቀለለውን አሮጌ ዓመት ትምህርት ማድረግ ታላቅ ጉዳይ ነው። አዲሱ ዓመት ከባከኑት ዓመታቶች ጋር ተዳምሮ እንዳያጎብጠን፣ ተስፋችንን እንዳይበላውና ወደ ከፋ የፖለቲካ መሰላቸት ውስጥ እንዳይከተን መጠንቀቅ ደግሞ ከሁሉም በላይ ወሳኝ ይመስለናልና ከከንቱና የማያንጽ ወሬው ቆጠብ፣ ከተግባሩ ጨመር እናድርግ!! ወሬ ይገድላል እንዲሉ!!
ይሉኝታን እንቅበር ባለፉት ዓመታት የይሉኝታ ፖለቲካ ጉዳት አድርሷል። በይሉኝታ በመነዳት የማይረሳ ኪሳራ ተመዝግቧል። በይሉኝታ ብቻ የደረሰብን የፖለቲካ ጠባሳ ሰምበሩ በያንዳንዳችን ሰውነት ላይ ይታያል። በተፎካካሪ ፓርቲዎችና ለለውጥ በተነሱ ፓርቲዎች ውስጥ ብዙ የሚሰሙ ጉዳዮች አሉ። በየጓሮ የሚሰማው የሃሜት፣ የጀግንነትና የአሉባልታ ትግል የሚቆመው ይሉኝታ ሲሰበርና ፊትለፊት መግጠም ሲቻል ነውና የይሉኝታን አርበኝነት እንቅበር!! ይህ የአዲስ ዓመት የመጀመሪያው የቤት ስራ ይሁን!! በተግባርም ይታይ!!

ራስን ማክበር አብዛኛውን ጊዜ ስለ ህሊናና አእምሮ ባርነት ይነገራል። ሰዎች ከዚሁ ከአእምሮ ባርነት ራሳቸውን ነጻ እንዲያደርጉ ምክር ሲሰነዘር በተደጋጋሚ ይሰማል። ምክሮቹና ትምህርቶቹ ምን ያህል ተግባራዊ እንደሆኑ ባናውቅም ባጭሩ ግን የ“ባርነት” ዋናው መሰረት ራስን አለማክበር ነውና የራሳችንን ዋጋ እንወቅ። ራሳችንን አክብረን፣ ክብራችንንና ዋጋችንን ጠብቀን፣ ስንጓዝ ከባርነት እንላቀቃለንና ለራሳችን ክብር እንስጥ። በከበርን ቁጥር ከስሜትና ከግብታዊ የፖለቲካ ትግል ራሳችንን በማረቅ አካሄዳችንን የማስተካከል እድል እናገኛለን። በእንዲህ መልኩ ስንደግፍም ሆነ ስንደገፍ አንወድቅም። በዚህ ዓይነቱ መደጋገፍ ውስጥ ተግባር እንጂ ፕሮፓጋንዳ ቦታው ያንሳል። መተማመን ይሰፍናል። ዛሬ እልል ብለን ነገ ከማዘን እንድናለን።ሁላችንም ራሳችንን ስናከብር የጋራ ራዕይና የጋራ መሪ ለመሰየም አንቸገርም። የሰየምነውንም መሪ አምኖ ለመቀበል ጊዜ አናመነዥግም። ሰባኪና ደቀ መዝሙርም አያስፈልግም። እናም ራስን ማክበር ዋጋው ታላቅ ይሆናል። ከመነዳትም ያድናልና!!

ያገባኛል ባብዛኛው የአገራችን ጉዳይ ለተወሰኑ ሰዎች የተሰጠ ይመስላል። የተወሰኑ ሰዎች ይናገራሉ።ስለወገኖቻቸውና ስለ አገራቸው ይከራከራሉ። ህዝብ አደራጅተው ለመታገል የበኩላቸውን ሲያደርጉ የሚታዩት እጅግ ጥቂቶች ናቸው። አብዛኛው ህዝብ ግን አድፋጭ ነው። አብዛኛው ምሁር ተመልካች ነው። ህወሃት/ኢህአዴግ ክፉ መንግስት እንደሆነ ከልሒቅ እስከ ደቂቅ ሁሉም ህዝብ፣ የኢህአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ጨምሮ ያውቃሉ። ግን ዳር ቆመዋል። ባልተመጣጠነ የኢኮኖሚ ፍሰት አብዛኞች ወደ ባርነት እየተመሙ፣ ልጅ ልጆቻቸውን ለባርነት በስጦታ ለማቅረብ እየገሰገሱ ነው። ልጅ ልጆቻቸው ከተወዳዳሪነት ተለይተው የበይ ተመልካች እንዲሆኑ ሲደረግ “አያገባኝም” የሚሉ እንዴት በረከቱ? ስለ ስርዓቱ ጸያፍነትና የህዝብ ምሬት ብዙ ማለት ይቻላል። ግን አድፋጩ ለምን በዛ? የፖለቲካ መሪዎቻችን ይህንን ጥያቄ መመለስ አለባቸው።አገሪቱና ህዝቧ ያስተማሯቸው የኢትዮጵያ ልጆች ካዳፋቸው የፖለቲካ ድብታ እንዴት እንዲነቁና “ያገባኛል” በሚል መንፋስ እንዲነሱ ምን ይደረግ? “የምሁራን” መንደሮች የያዛቸው እንቅልፍና የአድርባይነት ስሜት እንዴት ይነቀል? ተወደደም ተጠላም ያገባኛል የሚል ህብረተሰብ ሊፈጠር ግድ ነውና ወገብን ጠበቅ አድርጎ መስራት ግድ ይላል።

በቃኝ ህዝብ የተቃዋሚ ፓርቲዎችን የሚያዳምጠውና የሚከለታተለው አማራጭ ስለሚፈልግ ነው።በፉክክር ተጠቃሚ ለመሆን ነው። ህዝብ የሚጠብቀውን ማድረግ ያልቻሉ አሉ። ሰሞኑን በፓርቲዎች ክርክር ስም ቀርበው ኢህአዴግን እንሞግታለን የሚሉትን ስንሰማ አጥወልውሎናል። ህዝብ እነዚህ ናቸው ተቃዋሚ ብሎ ተስፋ እንዲቆርጥ ሆን ተብሎ የሚሰራ ስራ ቢኖርም እንዴት መናገር፣ የሚናገረውን የማያውቅ፣ ስለምን እንደሚናገር ያልተረዳ፣ እቁብና እድር እንኳን መዳኘት የማይችል ሰው ፓርቲ አቋቁሞ አገር ለመምራት ያስባል? እንዲህ ያሉ ብዙ ናቸው። የምርጫ አዳማቂዎች!! በውጪም አሉ፤ በህክምና ቋንቋ “የሼልፍ ጊዜያቸው ያበቃ” መኖራቸውም፣ መጥፋታቸውም ልዩነት የሌለው ምን አለበት “ሳናውቅ እየረበሽን ኖረናል፤ በቃን” ቢሉ? ሌላም ህይወት አለ። የሚሰሩትን ከጀርባ እየተከተሉ ጤና ከመንሳት “በቃኝ” በማለት ብቻ ለህዝብ ክብር መስጠት የሚቻል ይመስለናል።

ተግባር ስለ ህወሃት/ኢህአዴግ ብዙ ተብሏል። እንግዳ ብንሆንም እኛን ጨምሮ በየድረገጹ ያልተነገር ነገር የለም። በተለያዩ ማህበራዊ ድሮችና ሞገዶች ዛሬን ጨምሮ ስለ ኢህአዴግ እንሰማለን።የሚሰማው ብዙ ነው። በተግባር የሚታየው ግን እጅግ በጣም፣ እጅግ ጥቂት፣ በጣም በጣም ጥቂት፣ ኢምንት ነው። ወሬው እየገዘፈ ተግባሩ ሲያንስ፣ ሲኮሰምን፣ ሲሟሟ፣ ተስፋ መቁረጥ ያስከትላልና አልሞና መትሮ መንቀሳቀስ ግድ ነው። ዛሬ የሚሰሩ ስህተቶች እስከወዲያኛው የማያገግም ጠባሳ እንዳያትምብን እንጠንቀቅ። መልካም በዓል!!


No comments:

Post a Comment