Wednesday, October 31, 2012

“በፖለቲካ ቂም” የተመሰረተ ክስ ውድቅ ሆነ ዳኞቹና ዓቃብያነ ህጉ በፖለቲካ ውሳኔ ተባረሩ





ጋምቤላ ሁለት የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኞችና ሁለት ጠበቆች “በፖለቲካ ቂም ውሳኔያችንን አናዛባም” በማለታቸው ከስራና ከሃላፊነታቸው መሰናበታቸው ታወቀ። ሁለት የክልሉ የስነ ምግባርና የጸረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃብያነ ህግም በተመሳሳይ ውሳኔ ከሃላፊነታቸው መባረራቸው የተጠቆመ ሲሆን ውሳኔው የክልሉ ፕሬዚዳንት ወንድም የሆኑትን ዓቃቤ ህግ አላካተተም።
በሙስና ወንጀል ተጠርጥረው ክስ የተመሰረተባቸውን ሶስት የጋምቤላ ክልል ባለሥልጣናት የፍርድ ሂደት ያስቻለው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ተከሳሾቹን በነጻ የለቀቀው ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ነው። አስራ አንድ አባላት ያሉት የክልሉ አስተዳደር ስድስት ለአምስት ሆነ ውሳኔ የንግድና ኢንዱስትሪ ቢሮ ሃላፊ በነበሩት አቶ ጀምስ ዴንግ፣ ምክትላቸው ኮንግ ጋልዎክና የክልሉ የፖሊስ ኮሚሽነር በነበሩት ኦቲየንግ ኦቻን በሙስና እንዲወነጀሉ ውሳኔ አስተላልፎ እንደነበር በማስታወስ ለጎልጉል መረጃ ያስተላለፉት ክፍሎች እንዳሉት በተጠቀሱት የቢሮ ሃላፊዎች ላይ ክስ የመሰረተው የክልሉ ጸረ ሙስና ኮሚሽን ዓቃቤ ህግ ነበር።


የክልሉ ፕሬዚዳንት ወንድም ኦቦል ኦባንግ የሚገኙበት የኮሚሽኑ አቃቤ ህግ የመሰረተውን ክስ ያስቻለው የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት “ጥፋት አላገኘሁም።የተከሰሱት የንግድ ቢሮ ሃላፊዎችና ፖሊስ ኮሚሽነር የተጨበጠ ማስረጃ አልቀረበባቸውም” በማለት በነጻ እንዲሰናበቱ ወስኗል። የጎልጉል ዘጋቢ በስልክ ያነጋገራቸው የፍርድ ቤት ምንጮች ውሳኔውን ተከትሎ የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ኦሞት ኦባንግ ውሳኔውን በመቃወም የፍርድ ሂደቱ እንዲቀለበስ ትዕዛዝ አስተላልፈዋል።
“በፖለቲካ ቂም የፍርድ ውሳኔያችንን አንቀይርም” በማለት ኦሞት ኦባንግን የተከራከሩት የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕሬዚዳንት አቶ ጆን ዮንግ፣ ምክትላቸው አቶ ዶል ኦኩሪ፣ የጠቅላይ ፍርድ ቤት ጠበቃና የመምሪያ ኃላፊ ኒይንገው ኡጃይና ሌላው ጠበቃ ኦባንግ ኡጁሉ ከሃላፊነታቸውና ከስራቸው መባረራቸው ታውቋል፡፡ ይህ ዜና እስከተጠናከርበት ጊዜ ድረስ የተቀየረ ነገር የለም።
በተመሳሳይ በተካሳሾቹ ላይ ማስረጃ በማሰባሰብ ክስ የመሰረተው የክልሉ የጸረ ሙስና ኮሚሽን አቃብያነ ህግ ኦካች ኦሞድና ኦባንግ አብዱራዛክ “ክሱን በሚገባ አላቀነባበራችሁም” በሚል ከሃላፊነታቸው ተነስተዋል፤ ከስራቸውም ታግደዋል። በተከሳሾቹ ላይ መረጃ በማሰባሰብ ክስ ከመሰረቱት መካከል አንዱ የሆኑት የክልሉ ፕሬዚዳንት ወንድም አቃቤ ህግ ኦቦል ኦባንግ ግን በስራቸውና በሃላፊነታቸው መቀጠላቸው ታውቋል።ጎልጉል ያነጋገራቸው እንዳሉት ውሳኔው በተለያዩ ደረጃ ባሉ የክልሉን የስራ ሃላፊዎችና የአስተዳደሩን ስራ አስፈጻሚዎች መካከል መለያየት ፈጥሯል።

ከዓመታት በፊት ከአራት መቶ በላይ ለሚሆኑ አኙዋኮች መገደልና በሺዎች ለሚቆጠሩት መሰደድ በቀጥታ ተጠያቂ እንደሆኑ ከበርካታ የሰብዓዊ መብት ተቋማት ክስ የሚቀርብባቸውን የክልሉ ፕሬዚዳንት ኦሞት ኦባንግን በሙስናና በመልካም አስተዳደር በጥብቅ በመታገላቸው በፖለቲካ ቂም ሶስቱ የክልሉ ሃላፊዎች ሲታሰሩ የፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ የነበሩት አቶ ተስፋዬ ሬሳ ከፍተኛ ምስጢር ያላቸውን ሰነዶች በመያዝ ከመታሰራቸው በፊት መሰወራቸውን የሚገልጹት የጎልጉል የመረጃ ምንጮች “የቢሮ ሃላፊው ይዘው የተሰወሩት መረጃ አቶ ኦሞት የፈረሙባቸው ከፍተኛ የገንዘብ ሰነዶችና ሙስና የተከናወነባቸው የኮንስትራክሽንና የተለያዩ መረጃዎች ናቸው። መረጃዎቹ አንድ ቀን ህዝብ ፍርዱን ይሰጥ ዘንድ ይፋ ይሆናሉ” ሲሉ ተናግረዋል።
የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ነጻ የለቀቃቸው ሶስቱ ተከሳሾች ለጊዜው ከእስር ቢለቀቁም ከዛሬ ነገ ተመልሰው ይታሰራሉ የሚል ስጋት እንዳለ ለማወቅ ተችሏል።
ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን፡፡








No comments:

Post a Comment