Thursday, October 31, 2013

እረፍት የሚነሳው ህምም


የኮንትራት ሰራተኞች ስቃይ፣ የእኛ ፍርሃትና የፖለቲከኞች ጭካኔ

saudi 1


እረፍት አደርግ ብየ ከማህበራዊ መገናኛ መድረኩ ገለል ባልኩባቸው እንደ ብርሃን ፍጥነት በሚወረወሩት ባለፉት ጥቂት ቀናት ከበርካታ ወዳጆቸ በርካታ መልዕክቶች ይደርሱኛል። ብዙው መልዕክት ደግሞ የሚያጠነጥነው በጅዳ እና በአካባቢው በተፈናቃይ የኮንትራት ሰራተኞች አሰቃቂ ስቃይ ላይ ያተኮራል … ለነገሩ የአብዛኞቹ መልዕክቶች ብቻ ሳይሆኑ ከመልዕክቶች ጋር የሚላኩልኝ መረጃዎች እረፍት የሚነሱ ናቸው! …
አዎ ተንቀሳቃሽ ምስል ጭምር በመረጃነት የታጨቀባቸውን የመልዕክት መረጃ ጭብጦች እውነታ ለማረጋገጥ ወደ ጅዳ ቆንስል አመራሁ … መኪናየን አቁሜ ትንሽ እንደ ተራመድኩ እያለ ከፊት ለፊቴ  አንዲት ልጅ እግር ኢትዮጵያዊ ብቻዋን እያወራች ስታልፍ ስመለከት በመደናገጥ ሰላምታ አቅረብኩላት፣ መልስ ሳትሰጠኝ አለፈች!  ደነገጥኩና ባለሁበት ቆሜ በአይኔ ተከተልኳት … በፈጣን እርምጃ የሚያቃጥል የሚለበልበውን መሬት የምትደቃበትን የጠቆረ ባዶ እግሯን፣ እንደነገሩ ከላይዋ ላይ ደረብ ያደረገችውን ጥቁር “አበያዋን” እና ከፍ ሲል የተንጨፈረረ ጸጉሯን እያየሁ ፈዝዠ ቀረሁ … ከድንጋጤና ከፍርሃት ለአፍታ ነፍሴ መለስ ሲልልኝ ጠደፍ ጠደፍ ብየ ወደ ሔደችበት አቅጣጫ ተከተልኳት … ርቃኛለች … ሮጨ ልደርስባት ባለመቻሌ መኪናየን ወዳቆምኩት በመሔድ አስነስቸ ተከተልኳት … በደቂቃዎች ልዩነት ተሰወረችኝ! ምናልባት በዙሪያው በቆሙት መኪኖች መካከል፣ በመንገዱ ዳርም ሆነ በቤቶች አጥር ጥላ ፈልጋ ደክሟት አረፍ ብላ እንደሆነ በማለት መኪናየን አቆሜ ፍለጋየን ቀጠልኩ … ብዙ ሞክሬ አልተሳካልኝም … ከጥቂት ደቂቃዎች በፊት ሰላም እያልኳት ገላምጣኝ የሄደቸው እህት የለችም!
በትካዜ ተውጨ በአሳቻ መንገድ አገኛት እንደሁ በሚል ዙሪያ ገባው እያማተርኩ ሳቀና ከጅዳ ቆንስል ግቢ በግምት 600 መቶ ሜትር ርቀት በአንድ አረብ ቱጃር ቤት አጥር ስር በሚገኝ አንድ ዛፍ ስር፣ ከመንገዱ ዳር አንዲት እህት ወድቃ ተመለከትኩ! ክው ክው ብየ ደነገጥኩ … ተጠጋኋት! የሚያምረው አይኗ ወይቧል፣ ሰውነቷ ደግሞ ዝላለች፣ ላብ ፊቷን አውዝቶታል፣ አፏ ግን አመድ መስሎ ደርቋል!  ጠይም ባለ ሰልካካዋ አፍንጫ ለግላጋ መልከ መልካሟን እህት ከብዙ ጉትጎታ በኋላ ማውራት ቻልኩ … ለነገሩ ማውራት አይባልም! ለረጅም ደቂቃዎች ለማውራት ያደረግኩት ሙከራ በሰጠችኝ ጥቂት መልስ አፏ ተፈታ ማለቱ ይቀላል! ዝርዝር ማውራት ግን አትፈልግም … ምንም አይነት እርዳታ እንደማትፈልግ በአጭሩ ገለጸችልኝ! … በቃ ከዚህ ባለፈ ብዙ ማውራትና መቀጠል አልቻልኩም!  የማደርገው ባጣ ቢያንስ በቆንስሉ መጠለያ ግቢ ከታጨቁትና በከፋ አደጋ ላይ እንዳሉ ከሰማሁትና አይቸ ካረጋገጥኩት 150 ከሚሆኑት ተፈናቃዮች ጋር ቢደባልቋት በሚል ለጅዳው ቆንስል ሃላፊ ለአቶ ዘነበ ከበደና ለዲያስፖራው እና በመጠለያ ላሉት ተፈናቃዮች እህቶች ተጠሪ ዲፕሎማት ለወ/ሮ ሙንትሃ ደጋግሜ ስልክ ደወልኩላቸው አያነሱም …

Monday, October 28, 2013

ኢህአዴግ የዘራውን አጨደ፣ ተጠያቂው ማን ነው?


እሳት አስነሳችሁ በሚል እስሩ ቀጥሏል

fire


በሰላማዊና በህጋዊ መንገድ ተቃውሞ ቢያቀርቡም የኢህአዴግን ጆሮ ማግኘት ያልቻሉ ተበዳዮች ርምጃ ወሰዱ። ሕዝብ ወዶና ፈቅዶ ያልተቀበለው ኢንቨስትመንት ከዘረፋ ተለይቶ እንደማይታይ የአካባቢው ነዋሪዎች አስታውቀዋል። ውድመት የደረሰበት የህንድ ኩባንያ በልማት ባንክ ላይ ኪሳራ ሊያስከትል እንደሚችል ስጋት አለ። ለደረሰው ጉዳት “ተጠያቂው ማን ነው?” የሚል ጥያቄ ተነስቷል። በጥርጣሬ የሚታሰሩ መበራከታቸው በክልሉ ባሉ ተመሳሳይ የእርሻ ኢንቨስትመንት ባለቤቶችን ስጋት ላይ ጥሏል።
ሻይ ቅጠል ለማልማት የተፈጥሮ ጥብቅ ደን እንዲያወድም የተፈቀደለት ቬርዳንታ ሀርቨስት የተባለ ኩባንያ በከፍተኛ ወጪ ያለማውና ለመለቀም በደረሰ ምርት ላይ ማንነታቸው በውል ያልታወቀ ሰዎች እሳት ለቀውበታል። ጥቅምት 12 ቀን 2006 ዓም ደረሰ በተባለው ቃጠሎ ኩባንያው የደረሰበት ሊሳራ እስከ 80 ሚሊዮን ዶላር ሊደርስ እንደሚችል ስለ ጉዳዩ የሚያውቁ አስታውቀዋል።
አንጋፋ እድሜ ጠገብና ረዣዥም የተፈጥሮ ደን በመጨፍጨፍ ጣውላ እያመረተ ሲቸበችብ የነበረው ኩባንያ ሙሉ ንብረቱና ከፍተኛ መጠን ያለው የጣውላ ምርት ከተለያዩ ማሽኖች ጋር ወድሞበታል። የአካባቢው የጎልጉል ምንጮች እንዳሉት ኩባንያው ላይ የደረሰው የእሳት ቃጠሎ ለመሰብሰብ የደረሰውን የሻይ ቅጠል ማሳ አጋይቶታል።
በጋምቤላ ክልል በመዠንግር ዞን፣ በጎደሬ ወረዳ በጉማሬና በካቦ ቀበሌዎች የሚገኝ 5000 ሄክታር በደን የተሸፈነ መሬት በኢንቨስትመንት ስም እንዲሸጥ መወሰኑን ተከትሎ የአካባቢው ነዋሪዎች ተቃውሞ አሰምተው ነበር። በወቅቱ ውሳኔውን “በባዕድ ወራሪ ሃይል እንኳን የማይፈጸም” በማለት የተቹና ቅሬታቸውን የገለጹ ነበሩ።
ሙሉ በሙሉ በደን የተሸፈነ 3012 ሄክታር ድንግል ለም መሬት በሄክታር111 ብር ሂሳብ ለ50 ዓመት የሊዝ ኮንትራት የተሸጠለት ይህ ኩባንያ ጥብቅ ደኑን ከማውደሙ በፊት ውሳኔው እንዲጤን የአካባቢው ህዝብ በወኪሎቹ አማካይነት ለፕሬዚዳንት ግርማ ወ/ጊዮርጊስ ጥያቄ አቀርበው ነበር። በወቅቱ ለጉዳዩ ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት የአዲሲቷ ኢትዮጵያ የጋራ ንቅናቄ ድርጊቱን በመቃወም የሚከተለውን ጽሁፍ አትሞ ነበር። ሰሚ ባለመገኘቱ የተፈራው ደረሰ።

Saturday, October 26, 2013

ስብሃት ህወሃት ጠቦ ታሪኩን እንደሚቋጭ አረጋገጡ


ህወሃትን ገልብጦ “ከየትኛው ክልል ድጋፍ ሊገኝ?”

sebhat nega


ስብሃት ነጋ የኢህአዴግ አባትና ፈጣሪ የሆነው ህወሃት የመጨረሻው ታሪኩ ጠቦ እንደሚቋጭ ይፋ አደረጉ። ችግር የህወሃት ልዩ በረከትና ስጦታ እንደሆነ በማመልከት ህወሃት ውስጥ ልዩነትና መፈርከስ አደጋ ተከስቶ እንደማያውቅ ሸመጠጡ።
አቶ ስብሃት ጠቦ የሚጠናቀቀውን የህወሃት ስውር አጀንዳ የገለጹት ከጋዜጠኛ ደረጃ ደስታ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ በሰጡበት ወቅት ነበር። በኢህአዴግ የመከላከያ መዋቅር ውስጥ ከፍተኛ መከፋፈልና የኩዴታ አደጋ ሊያስከትል የሚችል አደጋ እንደተረጋገጠ ተጠቅሶ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ስብሃት “አዲስ አበባ መንግስት ገልብጠው የክልሎችን ድጋፍ ቢጠይቁ ማን እሺ ይላል” በማለት ነበር የመለሱት። አንዴ በመከላከያ ውስጥ የመከፋፈልና የመበታተን አደጋ ሊያጋጥም የሚችልበት አግባብ እንደሌለ፣ ጠያቂው እንዳለው የመፈንቅለ መንግስት አደጋ ቢያጋጥም እንኳ የህወሃት ስጋት እንዳልሆነ አስመስለው አቶ ስብሃት የመለሱት የክልሎችን ስም በመጥራት ተቀባይት እንደማይኖረው ነው። ይህም አባባላቸው እኛን ገልብጦ አገር አንድ አድርጎ መምራት አይቻልም የሚል እንደምታ ያለው ቢመስልም፤ “ሪፑብሊክ” ለመመሥረት የተነሳውና እስካሁን በነጻአውጪ ስም አገር እየገዛ ያለውን ህወሃት የመጨረሻ የመጥበብ ዓላማ በማስረጃ የገለጹበት ነው፡፡
ህወሃት “ኢህአዴግ” የሚባለውን ድርጅት ሲያበጀው የአገልግሎት ዘመን መድቦለት እንደሆነ ስለ ድርጅቱ የወደፊት መድረሻ ድንበሩ ከሚያወሱ የድርጅቱ የተለያዩ ማረጃዎችና ነባር አባሎቹ መጠቆሙ ይታወሳል። ህወሃት 40ና 50 ዓመት ኢትዮጵያን በብሔር ፖለቲካና በዘር እያጋጨ ለመግዛት የሳለው ስዕል እንዳሰበው ካላዘለቀው እንዴት ጠቦ እንደሚጠናቀቅ የጠቆሙት ስብሃት፣ አስተያየታቸው አካሄዱ የገባቸውን በሙሉ አበሳጭቷል።
በ1997 የምርጫ ወቅት ተፈጥሮ በነበረውና በራሱ በቅንጅት ሰዎች ሽኩቻ በተኮላሸው ህዝባዊ ድል ግለት ወቅት ኢንዲያን ኦሽን የተሰኘው ጋዜጣ “ህወሃት ወደ ትግራይ የማፈግፈግ እቅድ ይዟል” በማለት የዘገበውን ዘገባ በማስታወስ በአቶ ስብሃት መልስ ላይ አስተያየት የሰጡ፤ በቅድሚያ አቶ ስብሃትን “አቦይ ብላችሁ አትጥሩት። አባታዊ አንደበትና ምግባር የለውም” በሚል ማሳሰቢያ ከሰጡ በኋላ “የስብሃት ንግግር ህወሃት ታሪኩ ሲጠናቀቅ ጠቦ እንደሚቋጭ ነው። ለዚህ ሲል ነው ህዋሃት ከአንቀጽ 39 ጋር ቅበሩኝ የሚለውና የአማራ ክልል መሬትን እየዘረፈ የመውጫ ቀዳዳ ፍለጋ ሌት ከቀን መሬት እየቆረሰ አዲስ ካርታ የሚያመርተው፤ ዓለምአቀፋዊ ድንበርም ለትግራይ እንዲኖራት ያደረገው” ብለዋል።

Friday, October 25, 2013

አህያው ማን ነው? የሚመለከተውስ ብሔር አለን?

(ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው)

donkey12


ይህንን ጽሑፍ ከጻፍኩት ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡ በወቅቱ ጽሑፎቸን  ያስተናግድ የነበረ አንድ ዝነኛ የሬዲዬ (የነጋሪት-ወግ) ዝግጅት የጽሑፉን ይዘት ነግሬው እንዲያቀርበው ስጠይቀው አይ ስላለ የሚስተናገድበትን የነጋሪተ-ወግ መድረክ በማጣት በኋላም ተዘንግቶ ቆይቶ አንድ ሰነድ ፈልጌ ካርቶን ሳገላብጥ አገኘሁትና አሀ……. ለምን ታዲያ አሁን ቢያንስ በጋዜጣና በመካነ-ድሮች በኩል ለአንባቢያን አላደርሰውም በሚል አምጥቸዋለሁ የተጻፈው እንዳልኳቹህ ከ4 እና 5 ዓመታት በፊት ነው እንካቹህ፡-
ሰሞኑን በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (ምርዓየ-ኩነት) ራሱ ጣቢያው ያዘጋጀውን አንድ ውይይት ተመለከትኩ የመወያያ ርእሳቸው የነበረው አዲስ አበባ ውስጥ ባሉ የሀብታም ልጆች በሚማሩባቸው የመጀመሪያ ደረጃ ት/ቤቶች በከፊሎቹ ልክ ተማክረው ያደረጉት በሚመስል መልኩ ማሰብ ከሚችሉ ዜጎች ፈጽሞ የማይጠበቁና የድፍረት ድርጊቶች በመፈጸሙ ማለትም ‹‹አማርኛ የሚያወራ አሕያ ነው ፣አማርኛ መናገርና ድንጋይ መወርወር ክልክል ነው›› የመሳሰሉትን ጽሑፎችን እየለጠፉ እንደ ውይይቱ አዘጋጆች አገላለጽ ‹‹ልጆቹ የገዛ ቋንቋቸውን እንዲጠሉና እንዲንቁ እየተደረጉ በመሆኑ በዚህ ጉዳይ ላይ ምን ልንል እንችላለን?›› በሚል የሚመለከታቸው የባለድርሻ መሥሪያ ቤቶች ኃላፈዎች ወይም ተወካዮች የሌሉበት ያልተገኙበት በራሳቸው ምክንያት በራሳቸው መንገድ ከየቦታው የጋበዟቸውን ግለሰቦች ይዘው ውይይቱን አድርገው ሲያበቁ ያንን ውይይትም እንደወረደ ለተመልካች አቀረቡ፡፡ መቅረቡ ባልከፋ እንዲህ ዓይነት አጥቂና አጸያፊ ድርጊት ተፈጽሞ ሲገኝ ማጋለጥ ሕዝቡም እንዲያውቀውና መፍትሔ እንዲሻ ማድረግ የብዙኃን መገናኛዎች ድርሻና ኃላፊነት ነውና፡፡ ስለእውነት ከሆነ ከባድ ጥፋትና ወንጀል ተፈጽሟል ፡፡ ምንም በማያውቁ ሕፃናት ላይ  እንዲህ ዓይነት የማሸማቀቅና ሥነ-ልቦናዊ ጥቃት ከመፈጸም የከፋ ጭካኔና ጠላትነት አለ ብየ አላስብም ፡፡ እንዴት የሰው ልጅ አሕያ ይባላል? ሕፃናቶቹን ምን ማስተማር ነው የተፈለገው? ለምን? ይሄ  ሚያሳየው ሰዎቹ ምን ያህል ደናቁርት መሆናቸውን ነው፡፡
በእርግጥ ይሄ የተሳሳተና የማይገባ የቃላት አጠቃቀም (ዳኅፀ-ልሳን) እንደዚህ በትምህርት ተቋማት ውስጥ በሕፃናት ላይ ሆን ተብሎ ባይሆንም ሁሉንም ሰው የሚያስት ጥፋት ነው ማለት ይቻላል፡፡ እንኳንና እነኘህን ቁንጽላን ይቅርና መጀመሪያ የዐፄ ቴዎድሮስ 2ኛ ቀጥሎ የዐፄ ዮሐንስ 4ኛ በመጨረሻም የዐፄ ምኒልክ 2ኛ የፍትሕ ጉዳዮች ዋና ሹም (ሚንስትር) የነበሩትን የፍትሐ ነገሥቱ ፣የብሉያቱና የሐዲሳቱ መጻሕፍት፣ የቅኔውና የአቋቋሙን ታላቅ ሊቅ አባ ገብረ ሐናን እንኳን አሳስቷል ለከፉ ፈተናም ዳርጓል ዳኅፀ-ልሳን፡፡
 አባ ገብረሐና ተረበኛና ቧልተኝነታቸው ሰዎችን ለሚያስቀይም ለሚያስከፋ ክፉ የቃላት አጠቃቀም (ዳኅፀ-ልሳን) ዳረጓቸው ነበር፡፡ አባ ገብረሐና ያን ያህል ታላቅ ሊቅ እና የሃይማኖት አባት የነበሩ ስለነበሩ እንዲህ ዓይነት ስሕተት ያውም በተደጋጋሚ ይሠራሉ ተብሎ ጨርሶ አይታሰብም እይጠበቅምም ነበር፡፡ ነገር ግን እነኛን ተደጋጋሚ ስሕተቶች ሆን ብለው ይሠሩ በነበሩበት ወቅት ጤነኛ መሆናቸው እንኳን አጠራጣሪ የነበረና እንኳንና በእነ ሐድጎ የሃይማኖት መሠረት በሆኑት ቅዱሳት መጻሕፍት ሳይቀር ሲያፌዙና ሲሳለቁ በወቅቱ ቅንጣት ታክል እንኳን የማይሰቀጥጣቸው ሰው ነበሩ፡፡ ታሪኩ እረጅም ነው አባ ገብረሐና እራሳቸው በፈጠሩት መዘናጋት ከቁጥጥራቸው ውጪ በሆነ ምክንያት ምንኩስናቸው በመፍረሱ በእግዚአብሔር አኩርፈው የተበቀሉት መስሏቸውም ይሁን ተስፋ ቆርጠው አይታወቅም ቅዱስ ቃሉን መዘባበቻ አድርገውት ነበር ፡፡ የኋላ ኋላ ግን መድኃኔዓለም ሲታደጋቸው ልባቸውን መለሰላቸውና እጅግ በመጸጸታቸው በንስሐ ሕይወት ውስጥ እንዳሉ አርምሞ (በምነና ሕይዎት ያለ ሰው ከሚያደርጋቸው የተጋድሎ ዓይነቶች አንዱ ሲሆን ትርጉሙም ከማንኛውም ሰው ጋር ምንም አለመነጋገር ዝምታ ማለት ነው) እናም ዘመዶቻቸው አባ ገብረሐናን ጋኔን ልሳናቸውን ዘግቶት ነው ብለው ጸበል የተባለበት ቦታ ሁሉ እያዞሩ ብዙ ያንገላቷቸው ነበር፣ ከስንት ቀን አንድ ጊዜ ለቁመተ ሥጋ ታክል ጥቂት በመቅመስ ብቻም ሰውነታቸውን በመቅጣትና በማድከም መጻሕፍትን ከፊታቸው ደርድረው ድንጋይ እየተሸከሙ አብዝተው በመስገድ መዘባበቻ አድርጌያችኋለሁ ይቅር በሉኝ ይሉ ነበር፡፡ ሌሎች የመሳሰሉትን መንፈሳዊ ተጋድሎ ሲፈጽሙ ቆይተው በመጨረሻ ከአምላካቸው ለሠሩት ሁሉ ኃጢአት ሥርዬት ከማግኘታቸውም በላይ በቅተው (ከቅድስና ደረጃ ደርሰው) እንዳረፉ ታሪካቸውን በቅርብ የሚያውቁ አረጋዊያን ሊቃውንተ ቤተክርስቲያን ያስረዳሉ፡

Tuesday, October 22, 2013

ዶ/ር መረራ የፍንዳታውን ዜና “እንጠራጠረዋለን” አሉ


"በአዲስ አበባው ፍንዳታ የሞቱት ኢትዮጵያዊያን ናቸው"

bole 1


በአዲስ አበባ ቦሌ ክፍለ ከተማ ሩዋንዳ ሰፈር የደረሰውን ፍንዳታ አስመልክቶ ኢህአዴግ ያሰራጨውን ዜና የሚቃረኑ መረጃዎችና አስተያየቶች ቀረቡ። ለኢህአዴግ ቅርበት ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የድጋፍ አስተያየት ሲሰጡ ዶ/ር መረራ “አትፍቶ ጠፊ አጥፍቶ ይጠፋል እንጂ በሜዳ ዝም ብሎ አያጠፋም” ሲሉ ጥርጣሬ እንዳላቸው ተናግረዋል። የትግራይ ህዝብ ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ /ትህዴን/ በፍንዳታው የሞቱት ኢትዮጵያውያን ናቸው ሲል ስም ገልጾ የኢህአዴግን ዜና አጠጥሎታል።
በፓርላማ አስቸኳይ ስብሰባ እንዲጠራ የጠየቁት ከኢህአዴግ ጋር ግንኙነት እንዳላቸው የሚታሙ ፓርቲዎች “የጸረ ሽብርተኞች አዋጅ ሊጠናከርና ሊጠብቅ ይገባል” ሲሉ ተደምጠዋል። የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ያነጋገራቸው የኢራፓ፣ የኢሴዳፓ፣ ቅንጅትና አዲአን ተወካዮች በየተራ የኢህአዴግን ዜና የሚቃወሙና በጥርጣሬ የሚመለከቱትን አውግዘዋል። በወቅቱ የቴሌቪዥን ጣቢያውም አንድነትና የሰማያዊ ፓርቲ ጠርተውት በነበረው ሰላማዊ የተቃውሞ ሰልፍ ላይ “የጸረ ሽብርተኛነት አዋጅ ለሌላ ተግባር መዋሉን እንቃወማለን” በማለት የተቃውሞ ድምጻቸውን ሲያሰሙ በማሳየት ዜናውን ለማጀቢያነት ተጠቅሞበት ነበር።
በግል አስተያየታቸውን የተጠየቁት ዶ/ር መረራ ጉዲና በቴሌቪዥን መስኮት ቀርበው “ብዙዎች፣ እኔም ጓደኞቼም በጥርጣሬ ነው ያየነው” ሲሉ ከተቆረጠው ንግግራቸው ተደምጧል። ዶ/ር መረራ “አጥፍቶ ጠፊ አጥፍቶ ይጠፋል እንጂ በሜዳ ዝም ብሎ ራሱን አያጠፋም” ካሉ በኋላ “ስለዚህ እውነት ተደርጓል?” የሚለው ትልቁ ችግርና የጥርጣሬው መነሻ እንደሆነ አመልክተዋል።
ስለዚህ በሚል ድምዳሜ “ሰው አንዳንድ ጊዜ የኢትዮጵያ መንግስት ለራሱ ፖለቲካ ብሎ የሚያደርገው ያው የለመደው ስራ ነው” እንደሚል ዶ/ር መረራ በተቀነጨበው አስተያየታቸው ሲናገሩ ተሰምቷል። በተቃራኒ ከላይ በስም የተዘረዘሩት የፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች፣ ኢትዮጵያ የሽብር ጥቃት ኢላማና የአልሸባብ ስጋት ላይ ያለች አገር በመሆኗ ኢህአዴግ ህዝብን የመጠበቅና ደህንነትን የማስጠበቅ አደራ ስላለበት እነሱን ጨምሮ እንዲጠብቃቸው ጥሪ አቅርበዋል።

Wednesday, October 16, 2013

ስንቱን አጣን!


deforested


እንደኢትዮጵያ ባለ ኋላቀር አገር አገር ውስጥ መሠልጠን ብዙ ችግር አለበት፤ እኔ ራሴ በኮምፒዩተር መጻፍ ከጀመርሁ ሠላሳ ዓመት ሊሆነኝ ነው፤ ታዲያ መብራት ጠፋና የምሠራው ባጣ የቆዩ ወረቀቶችን ሳገላብጥ አንድ እአአ በዲሴምበር 26 1965 ከዱሮ ተማሪዬ የተጻፈልኝን ደብዳቤ አገኘሁ፤ በዩኒቨርሲቲ ኮሌጅ በነበረ ከአንድ በጣም ጎበዝ ወጣት የተላከልኝ ነበረ፤ ከተመረቀ በኋላ በአንድ ኩባንያ ውስጥ ተቀጥሮ ለጥቂት ዓመታት ሠርቶ ትምህርቱን ለመቀጠል ወደአሜሪካ ሄዶ በሎዝ አንጄለስ አካባቢ ከሚገኝ ትምህርት ቤት ገብቶ ነበር፤ ደብዳቤውን የጻፈልኝ ከዚያ ነው፤ ደብዳቤው ሰባት ገጾች አሉት፤ ከሰባቱ ገጾች አምስቱ ስለኢትዮጵያ ያለውን ስጋት የሚገልጽ ነው፤ በሎዝ አንጀለስ አካባቢ ካሉ ኢትዮጵያውያን ጋር ውይይት በሚያደርግበት ጊዜ ሁሉ ብዙዎቹ የሚያሳዩት የመንደረኛነት ስሜት እያበሳጨው የተማሩት ሰዎች በእንደዚህ ያለ ማኅበረሰባዊ ኋላቀርነት ውስጥ ሆነው ኢትዮጵያ የምትባለው አገር እንዴት መራመድ ትችላለች? እያለ ይሰጋ ነበር።
ደብዳቤውን ላቋርጥና ስለሰውየው ትንሽ ልናገር፤ ተማሪ ሆኖ ክፍል ውስጥ ምንም ነገር የማያሳልፍ በጣም ተከራካሪ ተማሪ ስለነበረ አደንቀው ነበር፤ አንድ ጊዜ እንዲያውም የዘውድ መንግሥት ደጋፊ ነኝ አልሁና አንዴት በትከሻው ላይ ጭንቅላት ያለው ሰው ዓመቱን በሙሉ የዘውድ አገዛዝ የሚያደርስብንን በደልና ችግር ሲነግረን ቆይቶ አሁን ደግሞ ያንን ደጋፊ ነኝ ይላል ብሎ ወረፈኝ፤ ልጁን ስለማውቀው አነጋገሩ አሳቀኝ እንጂ አላስቆጣኝም፤ ጥያቄህ ይገባኛል፤ ግን እኔን ሳትወርፈኝ መጠየቅ ትችል ነበር በዬ ቢቀበለውም ባይቀበለውም ለጥያቄው መልሱን ሰጠሁት፤ በኋላም ጥሩ ጓደኛዬ ነበር።
ከአሜሪካ ትምህርቱን ጨርሶ እንደመጣ ተገናኘንና ወደቀድሞ ሥራው ወደወንጂ ተመልሶ እንደሆነ ስጠይቀው ‹‹እንዴት ብዬ! ዕድሜ ልኬን የፈረንጅ አሽከር ሆኜ መኖር አልፈልግም፤ አሁን ደግሞ ያስተማረኝን ሕዝብ ላገልግል እንጂ!›› ነበር ያለኝ፤ በመንግሥት መሥሪያ ቤቶችና በወንጂ ባሉት ደመወዞች መሀከል ከፍተኛ ልዩነት ነበረ፤ ቁም-ነገረኛነቱን፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ያለውን ታማኝነት፣ የግል ጥቅሙን ቀንሶ ኢትዮጵያን ለመርዳት ባሳየው ተግባራዊ አርአያነት የማደንቀው የወታደር ልጅ ነው።
ይህ ሰው በደርግ ጊዜም አልሸሸም፤ በአንድ ኢንዱስትሪ ውስጥ በሥልጣን ቦታ ላይ ነበር፤ ወያኔ/ኢሕአዴግ ወንበሩን ሲይዝ እንደዚህ ያሉ ሰዎች የማይፈለጉ መሆናቸው ሲታወቅ አገሩን ጥሎ ተሰደደ፤ በትልቅ ዓለም-አቀፍ መሥሪያ ቤት ጥሩ ሥራ አግኝቶ ዕድሜው ለጡረታ እስቲደርስ ቆየ፤ ወደሚወዳት አገሩ ለመመለስ አልቻለም፤ ከአንድ የትምህርት ቤት ጓደኛው ጋር ግንኙነት እንዳለው አውቃለሁ፤ አንድ ቀን ስለዚሁ የጋራ ጓደኛችን ስናወራ ለምን ወደኢትዮጵያ እንደማይመለስ ጠየቅሁ።

Friday, October 11, 2013

“የይሉኝታ ፖለቲካ ይገድላል”


mitmitta1


“ሙሉ ኢትዮጵያዊ ነኝ” ትላለች። የተወለደችው ዱከም ነው። በቀድሞው አጠራር በኢትዮጵያ የተለያዩ ጠቅላይ ግዛቶች ኖራለች። ሐረር፣ ባህርዳር፣ አስመራ፣ አዲስ አበባን በመጥቀስ ልዩ ትዝታዎች እንዳሏት ትናገራለች። ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት አሜሪካ ከትማለች።
“ፖለቲከኛ አይደለሁም፣ እኔ አገር ወዳድ ነኝ። አገሬ የማንኛውም ጉዳዮቼና የውሳኔዎቼ በሙሉ መለኪያ ሚዛኔ ናት” ትላለች። ለአገሯ ማድረግ የሚገባትን እንዳላደረገች ይሰማታል። የይሉንታ ፖለቲካ ችግርና መዘዝ ያሳስባታል። በመናገርና ሃሳብን በነጻነት ስለመግለጽ ያላት አቋም የጸና መሆኑን አትደብቅም። በማህበራዊ ገጾች ንቁ ተሳታፊና መረጃ በማስተላለፍ በርካታ ተከታታዮች አሏት። በኢትዮጵያውያን የወቅታዊ ጉዳዮች መወያያ መድረክ አስተባባሪ ከሆኑት አንዷ ኃላፊ (አድሚን) ናት። ቤተሰቦቿ ካወጡላት መጠሪያዋ ይልቅ ራስዋ ለራስዋ ስም ተክላለች። ሚጥሚጣ ትባላላች። ሚጥሚጣ ከጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ ለቀረበላት የቃለ ምልልስ ጥያቄ ተባባሪነቷን በመግለጽ የሚከተለውን አውግታናለች። ለጥያቄያችን ፈጣን ምላሽ በመስጠቷ የዝግጅት ክፍላችን ምስጋናውን ያቀርብላታል። ሚጥሚጣን እነሆ!
ጎልጉል፦ ሌሎችን የሚያቃጥል ስብዕና አለሽ?
ሚጥሚጣ፦ ምን ማለትህ ነው?
ጎልጉል፦ ስምሽ እኮ ሚጥሚጣ ነው፤ ያወጣሽውም ራስሽ ነሽ፤
ሚጥሚጣ፦ ጉድ እኮ ነው፤ አንተ ሚጥሚጣ ትወዳለህ?
ጎልጉል፦ በጣም፤ ግን መጠሪያዬ አላደርገውም።
ሚጥሚጣ፦ ሚጥሚጣ ምኑ ነው የሚያስደስትህ?
ጎልጉል፦ ማቃጠሉ፤
ሚጥሚጣ፦ አሁን ገባህ? ሚጥሚጣ የተባልኩበት ምክንያት ተገለጸልህ?
ጎልጉል፦ ጠያቂዋ እኮ አንቺ ሆንሽ። ስለ ሚጥሚጣ የተለየ ማብራሪያ አለሽ?
ሚጥሚጣ፦ ሚጥሚጣ እንደሚያቃጥል የምታውቀው ስትቀምሰው ነው። ካልቀመስከው ያው ዱቄት ነው የሚመስለው። እኔም ልክ እንደሚጥሚጣው አቃጥላለሁ። የማቃጥለው ክፉ ነገር አይቼ ባለማለፌ ነው። አየህ በይሉንታ መኖር የሚያመጣውን ጣጣ አውቀዋለሁ። አንናገርም እንጂ በይሉንታ ያልተጎዳ ሰው የለም። አገራችንም በይሉንታ …