ህወሃትን ገልብጦ “ከየትኛው ክልል ድጋፍ ሊገኝ?”
ስብሃት ነጋ የኢህአዴግ አባትና ፈጣሪ የሆነው ህወሃት የመጨረሻው ታሪኩ ጠቦ እንደሚቋጭ ይፋ አደረጉ። ችግር የህወሃት ልዩ በረከትና ስጦታ እንደሆነ በማመልከት ህወሃት ውስጥ ልዩነትና መፈርከስ አደጋ ተከስቶ እንደማያውቅ ሸመጠጡ።
አቶ ስብሃት ጠቦ የሚጠናቀቀውን የህወሃት ስውር አጀንዳ የገለጹት ከጋዜጠኛ ደረጃ ደስታ ለቀረበላቸው ጥያቄ መልስ በሰጡበት ወቅት ነበር። በኢህአዴግ የመከላከያ መዋቅር ውስጥ ከፍተኛ መከፋፈልና የኩዴታ አደጋ ሊያስከትል የሚችል አደጋ እንደተረጋገጠ ተጠቅሶ ለቀረበላቸው ጥያቄ አቶ ስብሃት “አዲስ አበባ መንግስት ገልብጠው የክልሎችን ድጋፍ ቢጠይቁ ማን እሺ ይላል” በማለት ነበር የመለሱት። አንዴ በመከላከያ ውስጥ የመከፋፈልና የመበታተን አደጋ ሊያጋጥም የሚችልበት አግባብ እንደሌለ፣ ጠያቂው እንዳለው የመፈንቅለ መንግስት አደጋ ቢያጋጥም እንኳ የህወሃት ስጋት እንዳልሆነ አስመስለው አቶ ስብሃት የመለሱት የክልሎችን ስም በመጥራት ተቀባይት እንደማይኖረው ነው። ይህም አባባላቸው እኛን ገልብጦ አገር አንድ አድርጎ መምራት አይቻልም የሚል እንደምታ ያለው ቢመስልም፤ “ሪፑብሊክ” ለመመሥረት የተነሳውና እስካሁን በነጻአውጪ ስም አገር እየገዛ ያለውን ህወሃት የመጨረሻ የመጥበብ ዓላማ በማስረጃ የገለጹበት ነው፡፡
ህወሃት “ኢህአዴግ” የሚባለውን ድርጅት ሲያበጀው የአገልግሎት ዘመን መድቦለት እንደሆነ ስለ ድርጅቱ የወደፊት መድረሻ ድንበሩ ከሚያወሱ የድርጅቱ የተለያዩ ማረጃዎችና ነባር አባሎቹ መጠቆሙ ይታወሳል። ህወሃት 40ና 50 ዓመት ኢትዮጵያን በብሔር ፖለቲካና በዘር እያጋጨ ለመግዛት የሳለው ስዕል እንዳሰበው ካላዘለቀው እንዴት ጠቦ እንደሚጠናቀቅ የጠቆሙት ስብሃት፣ አስተያየታቸው አካሄዱ የገባቸውን በሙሉ አበሳጭቷል።
በ1997 የምርጫ ወቅት ተፈጥሮ በነበረውና በራሱ በቅንጅት ሰዎች ሽኩቻ በተኮላሸው ህዝባዊ ድል ግለት ወቅት ኢንዲያን ኦሽን የተሰኘው ጋዜጣ “ህወሃት ወደ ትግራይ የማፈግፈግ እቅድ ይዟል” በማለት የዘገበውን ዘገባ በማስታወስ በአቶ ስብሃት መልስ ላይ አስተያየት የሰጡ፤ በቅድሚያ አቶ ስብሃትን “አቦይ ብላችሁ አትጥሩት። አባታዊ አንደበትና ምግባር የለውም” በሚል ማሳሰቢያ ከሰጡ በኋላ “የስብሃት ንግግር ህወሃት ታሪኩ ሲጠናቀቅ ጠቦ እንደሚቋጭ ነው። ለዚህ ሲል ነው ህዋሃት ከአንቀጽ 39 ጋር ቅበሩኝ የሚለውና የአማራ ክልል መሬትን እየዘረፈ የመውጫ ቀዳዳ ፍለጋ ሌት ከቀን መሬት እየቆረሰ አዲስ ካርታ የሚያመርተው፤ ዓለምአቀፋዊ ድንበርም ለትግራይ እንዲኖራት ያደረገው” ብለዋል።