Saturday, March 30, 2013

ኢህአዴግን “አድርባይ” አመራሮች አስግተውታል

 

አባላት “አድርባይነት የመመልመያ መስፈርት ነው” አሉ!!


eprdf 9th meeting

ኢህአዴግ አመራሮቹን “አድርባይነት የተጠናወታቸው” ሲል ፈረጀ። የከፍተኛ አመራሮች የግምገማ ውጤት የሆነውን ፍረጃ የሰሙ “የኢህአዴግ አባል ለመሆን አንዱና ዋናው መስፈርት አድርባይነት ነው” በማለት አድርባይነትን የፈጠረውና ያስፋፋው ራሱ ኢህአዴግ፣ በተለይም ህወሃት እንደሆነ አመለከቱ።
 
በባህር ዳሩ የኢህአዴግ ጉባኤ ላይ ተገኝቶ የነበረ ጋዜጠኛ በምሥጢር የላከው ዜና “አድርባይነት” ኢህአዴግን በሚፈታተን ደረጃ መስፋፋቱ መገለጹ አብዛኞችን የድርጅቱን አባላትን አስገርሟል።
ኢህአዴግን የፈጠረውና ከላይ ሆኖ የሚመራው ህወሃት “ነጻ” አመለካከት የማይወድ፣ የነጻ አስተሳሰብ ባህል የሌለው፣ ራሳቸውን የቻሉ ድርጅቶችን፣ ፓርቲዎችንና ማህበራትን አጥብቆ የሚጠላ፣ ሁሉም ለሱ እያጎበደዱ በሚሰፈርላቸው ቀለብ እንዲኖሩ ሌት ከቀን የሚሰራ መሆኑ እየታወቀ ማንን? ለምንና እንዴት አድርባይ በሚል እንደሚፈርጅ አብዛኞች ግራ መጋባታቸውን የደረሰን ዜና ያመለክታል።
 
ህወሃት በፈለፈላቸው ድርጅቶችና የአፈና ተቋማቱ አማካኝነት በሂደት የኢትዮጵያን አብዛኛውን ህዝብ “አጎብዳጅ” የማድረግና “አድርባይ” ሆነው የሚኖሩትን ቁጥር ማብዛት ዋናው ስትራቴጂው እንደሆነ እየታወቀ “አድርባይነት” እንዴት ለድርጅቱ በሽታ ሊሆን እንደቻለ ያልገባቸው እንዳሉት “አድርባይነት አስጊ ደረጃ ከደረሰ ህወሃት የለፋበትን ያገኘና በስኬት ጎዳና ላይ ለመሆኑ ማሳያ ነውና ስጋት ሊገባው አይገባም” የሚል የለበጣ አስተያየት መስጠታቸው ተጠቁሟል።
 
በስብሰባው ላይ በይፋ አስተያየት ከሰጡት መካከል አቶ አባይ ጸሐዬ ይጠቀሳሉ። በህወሃት የመከፋፈል ዘመን ቀደም ሲል ከውህዳኑ ጋር ያበሩ መስለው ሁለት ሳንጃ በመያዝ የተጫወቱት አቶ አባይ አሁን አድርባይ ተብሎ የተፈረጀው የኢህአዴግ አባል በሙሉ ወደ መካከለኛ አመራርነት ከተሸጋገረ አደጋው ከፍተኛ እንደሚሆን ተናግረዋል። ቀደም ሲል አባሉ በተመለመለበት ደረጃ ተግባሩን ሲያከናውን ባግባቡ አለመመዘኑ የአደጋው መነሻ ምክንያት እንደሆነ አመልክተዋል።

ወ/ሮ አዜብ ተጨንቀዋል!

 

“ከሁሉም ነገር ጽድት ብለን እንታገል”

azebb mesfin

አቶ መለስ ከሞቱ ጀምሮ በተለያዩ መድረኮች ንግግርና መዕልክት የሚያስተላልፉት ወ/ሮ አዜብ መስፍን መረጋጋት እንደማይታይባቸው ተገለጠ። አሁንም በባለቤታቸው ስምና መንፈስ ሙግትና ማብራሪያ ከማቅረብ አልተላዘቡም። ይህን የሚያደርጉት ከጭንቀት የተነሳ እንደሆነ ተመልክቷል።
 
ሰሞኑንን በተጠናቀቀው የኢህአዴግ ጉባኤ አቶ መለስን አስመልክቶ ወ/ሮዋ የተናገሩት ንግግር በጭንቀት ውስጥ ስለመሆናቸው ማሳያ እንደሆነ የተናገሩት አብረዋቸው ባህር ዳር ስብሰባ የተቀመጡ የድርጅታቸው ኢህአዴግ “ባልደረቦቻቸው” ናቸው።
በጉባኤው ወቅት አቶ መለስ ዜናዊን በማወደስ የተዘጋጀው “ዝክረ – መውደስ” ታሪካዊ ሰነድ እንዲሆን ከመጽደቁ በፊት ወ/ሮ አዜብ በሰጡት አስተያየት “በፔሮል የሚከፈለው ብቸኛ መሪ መለስ ብቻ ነው” በማለት ራሳቸውን ጨምሮ ሌሎች አመራሮች በፔሮል በሚከፈላቸው ገንዘብ ብቻ እንደማይኖሩ የሚያመላክት ንግግር አድርገዋል።

Thursday, March 28, 2013

ዕውን ኢትዮጵያን የሚመሯት ኢትዮጵያውያን ናቸው?

 

ethiopia
የኢትዮጵያ ክብር ተቆርቋሪ የግል ተነሳሽ ኮሚቴና ባለራዕይ ወጣቶች ማህበር ከሰማያዊ ፓርቲ ጋር በመሆን ያዘጋጁት ሰላማዊ ሰልፍ አላማ ለፋሺስቱና ለጦር ወንጀለኛው ግራዚያኒ በጣሊያን ሀገር የተገነባውን መናፈሻ ስፍራና ሀውልት ለመቃወም ነው፡፡ ይህ ግለሰብ ኢትዮጵያውያን ላይ የተፈፀመውን ዘግናኝ ጭፍጨፋ ታሪክ አይዘነጋውም፡፡

ግራዚያኒ በመርዝ ጋዝ በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ጨፍጭፏል፤ ከየካቲት 12 ጀምሮ ለቀናት በዘለቀው የበቀል ጭፍጨፋም በአካፋ ሳይቀር በአዲስ አበባና በአካባቢዋ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በግፍ ጨፍጭፏል፡፡ ግራዚያኒ በወቅቱ በሰጠው ትዕዛዝ የፋሺስት ወታደሮች ህይወት ያለውን ተንቀሳቃሽ ፍጥረትን ሁሉ ገድለዋል፡፡ ይህ እሩቅ በማይባል ጊዜ የተፈፀመ ድርጊት ነው፡፡
 
የኢህአዴግ ባለስልጣናት ለእንዲህ አይነቱ ጨፍጫፊ የተገነባን ሀውልት ለመቃወም በወጡ ዜጎች ላይ የወሰዱት የእስር ተግባር እውን ኢትዮጵያን የሚመሯት ኢትዮጵያውያን ናቸው? አስብሎናል፡፡ ኢህአዴግ በስልጣን ዘመኑ ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ላይ በተደጋጋሚ ጥፋት ፈፅሟል፡፡ ሀገራችንን የባህር በር ማሳጣትን ጨምሮ ሀገራዊ ስሜትን አንኳሶ ጠባብ የብሔር ስሜት እንዲንሰራፋ አድርጓል፣ ታሪክን ለስልጣኑ መደላድል ሲል በራሱ መንገድ የሚያዘጋጀው የኢህአዴግ መንግስት ኢትዮጵያን ጠፍጥፎ እንደሰራት ሁሉ ደርግን ለመጣል ካደረገው ትግል ውጪ ያለውን የአርበኞች ተጋድሎ እውቅና ሲሰጥ አይታይም፡፡

Saturday, March 23, 2013

“የህዳሴው ግድብ” ከግማሽ በላይ የኢትዮጵያ አይደለም

 
ትልቁን ድርሻ ኤፈርት ይዟል
hidassie dam

“በራሳችን መሐንዲስ፣ በራሳችን ገንዘብ፣ በራሳችን የተባበረ ክንድ እንገነባዋለን” በማለት ሟቹ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ዜናዊ በመስቀል አደባባይ ታላቅ ህዝባዊ ድጋፍና “መዓበላዊ መነቃቃት” ፈጠሩበት የተባለለት የ”ህዳሴው” ግድብ 51 በመቶ ድርሻ የኢትዮጵያ እንዳልሆነ ነዋሪነታቸው በአውሮፓ የሆነ ዲፕሎማት በተለይ ለጎልጉል ገለጹ።
ስማቸው ምስጢር እንዲሆን የጠየቁት ዲፕሎማት እንዳሉት 51 በመቶ ባለድርሻ የሆነችው አገር አውሮፓ የምትገኝ የኢትዮጵያ አጋር አገር ናት። ለጊዜው የባለድርሻዋን አገር ስም መግለጽና የውሉን ዝርዝር ይፋ ማድረግ ያልፈለጉት ዲፕሎማት ኢትዮጵያ በግድቡ ላይ የፈለገችውን ውሳኔ በራስዋ ለማስተላለፍ እንደማትችል፤ ያላት ድርሻ 49 በመቶ ብቻ በመሆኑ ድምጽን በድምጽ በሚሽረው በአብላጫ ድምጽ ህግ መሰረት በግድቡ ላይ የሚወሰነው ውሳኔ 51 በመቶ ባለድርሻ በሆነችው አውሮፓዊቷ አገር መሆኑን አብራርተዋል።
49 በመቶ ተብሎ የተገለጸው የድርሻ መጠን ጅቡቲን ጨምሮ የተለያዩ አገሮች የተቀራመቱት መሆኑን ያመለከቱት የመረጃው ባለቤት፣ አገር ውስጥ ካሉት የንግድ ተቋማት መካከል ኤፈርት ትልቁን ድርሻ መውሰዱን እንደሚያውቁ ተናግረዋል።
የመንግስት መስሪያ ቤቶች፣ የግል ባለሃብቶች፣ ማህበራት፣ ባንኮችና የተለያዩ ግለሰቦች በትዕዛዝ አክሲዮን መግዛታቸውን ያስታወሱት እኚሁ ዲፕሎማት “በግድቡ ዙሪያ ከሚፈራው የጸጥታ ችግር በላይ አስጊው ጉዳይ የባለድርሻዎች ምስጢር መሆን ነው” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።

Thursday, March 21, 2013

የትግራይ ህዝብ ስማ!!

(ርዕሰ አንቀጽ)
ሰሞኑን በውዴታም ይሁን በግዴታ በመቀሌ እጅግ ከፍተኛ የሚባል ቁጥር ያላቸው የትግራይ ተወላጆች ሲጨፍሩ፣ ሲዘሉ፣ ከበሮ እየመቱ የባህላቸውን ዘፈንና ውዝዋዜ ሲያወርዱ አይተናል። ምክንያቱ በግልጽ ባይነገርም ሲደበቅ የነበረው የህወሃት ሃብትና ንብረት ውጤት የሆኑ፣ በልዩ የመንግስት ድጋፍ የተከናወኑ ግዙፍ ተቋሞች በጎዳና ለህዝብ ሲቀርቡም ተስተውሏል። ልማቱ መልካም ነው። ደስ ይለናል። ምንም ተቃውሞ የለንም። ግን መልዕክት አለን።
ለማን?
 
ምሬትን፣ ጭቆናና መንገፍገፍ ሲበዛ በፍቃደኛነት በቦንብ ላይ እንደሚያስሮጥ ለሚያውቀው የትግራይ ህዝብ!! የትግራይ ህዝብ ስማ!!
ሰሞኑን ይፋ የሆነው የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ሪፖርት የትግራይ ክልል በትምህርት፣ በኤሌክትሪክ፣ በመንገድ፣ በእርሻ፣ በደን፣ በኢንዱስትሪ፣ በጤና፣ ወዘተ ከሌሎች ክልሎች ሁሉ ርቃ መሄዷን ይፋ አድርጓል። በዚህም ደስ ይለናል። አይከፋንም። ከዚህ በላይ እንዲሆን እንመኛለን። ነገር ግን አንድ መልዕክት አለን።
ለማን?
አሁንም ለትግራይ ህዝብ!!
ሓውዜን የትግራይ ወጣቶች ለትግል ግልብጥ ብለው እንዲወጡ አደረገ። ሓውዜን የደረሰው የቦንብ ድብደባ ማንና እንዴት እንደተቀነባበር ብዙ የሚባልለት ቢሆንም የምሬት ጫፍ ሆኖ ህዝብን አሸፍቷል። ዛሬ መጨቆን ያንገፈግፋል ብለው ለትግል በተነሱና በተሰው ታጋዮች ደምና አጥንት ላይ የቆሙ ሌሎች ሓውዜኖች እንዲፈጠሩ አድርገዋል። እያደረጉም ነው።

የኦህዴድ ምርጫ ውጤት ተራዘመ

 
ህወሃት አባረረ፣ ብአዴንና ደኢህዴን ባሉበት ቀጠሉ
tplf meeting
ድሮ “ላዩ ካኪ ውስጡ ውስኪ” እየተባለ በኢሰፓ አባላት ዩኒፎርም ይቀለድ ነበር። ዛሬ ደግሞ ኢህአዴግ ተመሳሳይ ልብስ አልብሶ በየክልሉ የሰየማቸውን ፓርቲዎችና አመራሮቻቸውን የተመለከቱ “ስቱኮ” እያሉ እንደሚቀልዱባቸው ተሰምቷል።
“ስቱኮ” ግልብጥና ግጭት የበዛበት መኪና ተቀጥቅጦ አልስተካከል ሲል፣ የተገጣጠበና አልመሳሰል ያለ ግድግዳ “በግድ” ለማመሳሰል የሚያገለግል ቶሎ የሚፈረካከስ ጭቃ መሰል የቀለም አይነት ማጣበቂያ ነው።
“ኮሚኒስቶች በችግርና በቅራኔ ውስጥ ሆነው በግድ ለመመሳሰል አንድ ዓይነት መለያ መልበስ ይወዳሉ። ኢህአዴግም በተመሳሳይ በችግር ውስጥ ተዘፍቆ ሳለ፣ ለተመልካችና ለካሜራ ተመሳሳይ ልብስ ለብሶ በግድ አንድ ነኝ ሲል ማየቱ ብዙም የሚገርም አይደለም” የሚለው አስተያየት በስፋት እየተሰጠ ነው። “በግድ አንድ” ሆነው በየክልሉ ስብሰባ የሚያካሂዱት እህት ፓርቲዎች የለበሱትን መለያ የሚያመርተው ደግሞ የህወሃት የንግድ ድርጅት አልሜዳ ጨርቃጨርቅ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
ባህር ዳር ላይ ለሚያካሂደው ጉባኤ በዝግጅት ላይ ያሉት “እህት” ፓርቲዎች በየክልላቸው በስብሰባና በምርጫ ተጠምደው ሰንብተዋል። ውሉ ያልታወቀውና ምስጢር የተደረገው የኦህዴድ ጉባኤ የምርጫውን ውጤት ማጠናቀቅ አልቻለም። ህወሃት በመተካካት ስም ነባሮቹን አራት አመራሮች ሲያሰናብት፣ አቶ በረከትና አዲሱ ለገሰ የኢህአዴግ የመተካካቱ ስልታዊ በትር ሳይነካቸው ማለፉ ተደምጧል። ደኢህዴን በነበረበት እንደሚቀጥል ይፋ ሆኗል።
ኦህዴድን ለመምራትና ሰባት አመራር በሚሰየምበት የኢህአዴግ ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ለመሆን አባ ዱላ ገመዳ፣ ግርማ ብሩ፣ ድሪባ ኩማ፣ ኩማ ደመቅሳ፣ አለማየሁ አቶምሳ፣ አስቴር ማሞና ደግፌ ቡላ ከተጠቆሙት መካከል ይገኙበታል። የህወሃት የንግድ ተቋምና አንደበት የሆነው ሬዲዮ ፋና “የተጠቆሙትን አመራሮች ለማሳወቅ የድምጽ ቆጠራው ጊዜ ስለሚወስድ ለነገ ተላልፏል” የሚል ዘገባ አሰራጭቷል።

Tuesday, March 19, 2013

ህጻናት እየራባቸው መማር አቅቷቸዋል!

 
"ምሳ ያላቸው ሲበሉ እኔ የቤት ስራ እሰራለሁ"
students in addis
ህጻናት እየራባቸው ትምህርት መማር እንዳቃታቸው ሸገር አዲስ ኤፍ ኤም ያነጋገራቸው መምህራንና ተማሪዎች ተናገሩ። ሸገር ያነጋገራቸው ተማሪዎች በየተራ እንደተናገሩት በምግብ ችግር ትምህርታቸውን መከታተልና ክፍል ውስጥ ትኩረት ማድረግ ተስኗቸዋል።
“ሌሎች ምሳ ያላቸው ምሳ ሲበሉ እኔ የቤት ስራ እሰራለሁ። ወይም ቤተክርስቲያን እሄዳለሁ” በማለት አንድ ተማሪ ሲናገር፣ ሌላኛው ምሳ የሚባል ነገር እንደማያውቅ ገልጿል። በርሃብ ምክንያት ትምህርታቸውን በወጉ መከታተል ያልቻሉ ተማሪዎች ጉዳይ እንዳሳሰባቸው መምህራኑ ሲናገሩ ሸገር አስደምጧል። በሰሙት ዜና ረፍት ያጡ በርካታ ወገኖች ስልክ በመደወል ተማሪዎቹ በትምህርት ቤታቸው ውስጥ የምሳ አገልግሎት እንዲያገኙ የበኩላቸውን ለማድረግ ሲነጋገሩና ቃል ሲገቡ ለመስማት ተችሏል።
አዲስ አበባ በኑሮ ውድነት ሳቢያ የሚበሉ ያጡ፣ በክፍል ውስጥ ረሃብ እያዞረ ክፍል ውስጥ የሚጥላቸው፣ በየጥጋ ጥጉ አጥርና ጥላ ስር ቀን የሚገፉ፣ የባሰባቸው ቤተሰቦቻቸውን ለማትረፍ ያለ እድሜያቸው ስጋቸውን ለመሸጥ እንደሚገደዱና ቤተሰብ፣ በተለይም እናቶች ልጆቻቸውን ለገበያ ወሲብ ማበረታታት እየተለመደ መምጣቱን የጎልጉል የአዲስ አበባ ዘጋቢ አመልክቷል። (ፎቶ: ተማሪዎች በአንድ የአዲስ አበባ ት/ቤት)
(ተጨማሪ ዜናዎችን ለማንበብ እዚህ ላይ ይጫኑ)

ማሳሰቢያ፤ በተለይ በስም ወይም በድርጅት ስም እስካልተጠቀሰ ድረስ በጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ® ላይ የሚወጡት ጽሁፎች በሙሉ የጎልጉል የድረገጽ ጋዜጣ®ንብረት ናቸው፡፡ ይህንን ጽሁፍ ለመጠቀም የሚፈልጉ ሁሉ የዚህን ጽሁፍ አስፈንጣሪ (link) ወይም የድረገጻችንን አድራሻ (http://www.goolgule.com/) አብረው መለጠፍ ከጋዜጠኛነት የሚጠበቅና ህጋዊ አሠራር መሆኑን ልናሳስብ እንወዳለን