ኢህአዴግ በሁለተኛው መንታ መንገድ ላይ
ከቻይና ጋር የጀመሩት መወዳጀት ሥር ሰድዶ በሁለት እግሩ ከመቆሙ በፊት አቶ መለስ በሞት ከተለዩ በኋላ የኢህአዴግና የቻይና ግንኙነት በርካታ መንታ መንገዶች እየገጠሙት መጥተዋል፡፡ ከምዕራቡ ዓለም ከፍተኛ ገንዘብ በበጀት ድጎማም ሆነ በዕርዳታ የሚሠጠው ኢህአዴግ ምዕራባውያን ከቻይና ጋር ካላቸው ፍጥጫ አንጻር እየገባበት ያለው አጣብቂኝ በየጊዜው እየጨመረ መጥቷል፡፡ “ምርጫው በምርጫ” እየተወሳሰበበት የመጣው ኢህአዴግ በአንድ በኩል የአሜሪካንን ፍላጎትና ጥያቄ መፈጸምና ማስፈጸም፤ በሌላ በኩል ደግሞ አፈናውን ለማጠናከርና የግዛት ዘመኑን ለማርዘም ከቻይና የሚያገኘው በቅድመ ሁኔታ ያልታሰረ “ጥቅም” በሁለት ጽንፍ ወጥረውታል፡፡ አሁን ደግሞ ሌላ “ወጣሪ” ብቅ ብሎ በመንታው መንገድ ላይ ሌላ መንታ ፈጥሮበታል – ጃፓን!
ቻይና በተለይ በአፍሪካ እያደረገች ያለችው የንግድ እንቅስቃሴና ኢንቨስትመንት የምዕራባውያንን ዓይን ከሳበ ቆይቶዋል፡፡ በተለያዩ ሰበቦችም የቻይናን እንቅስቃሴ ለመሰለል ምዕራባውያን በግልጽ መረጃ ከመሰብሰብ እስከ ወታደራዊ ተ ቋማት መገንባት ከዚያም አልፎ በቻይና “ፍቅር” ተለክፈው እንቅፋት የሆኑባቸውን እስከ “ማስወገድ” ዓላማቸውን ሲያሳኩ ቆይተዋል፤ አሁንም እያደረጉት ይገኛሉ፡፡
በጂኦግራፊዊ አቀማመጥ ምስራቃዊ ከመሆን በስተቀር የምዕራቡ ዓለም አካል የሆነችው ጃፓን፤ የቻይናን ሁኔታ በቅርብ ስትከታተል ቆይታለች፡፡ በተለይ ሁለቱ አገራት ካላቸው ታሪካዊ ጥላቻ አኳያ ጃፓን ቻይናን በማሳደዱ ተግባር ከምዕራቡ ዓለም ጋር ሆና እስከ አፍሪካ ዘልቃለች፡፡
በቅርቡ የጃፓኑ ጠ/ሚ/ር ሺንዞ አቤ ኢትዮጵያን ጨምሮ በሦስት የአፍሪካ አገራት ያደረጉት ጉብኝት “የሁለቱ አገራት የቆየ ግንኙነት …” ብሎ ኢቲቪ እንደዘገበው የቀለለና ጥሩ የፎቶ ዕድል ፈጥሮ ያለፈ ብቻ አይደለም፡፡ ቀልደኛው የጃፓን መሪ አቤ “ትምህርት ቤት ሳለሁ ልጆች ሁሉ አበበ እያሉ ይቀልዱብኝ” ነበር እንዳሉትና የሻምበል አበበ ቢቂላን ፎቶ ተሸልመው የሄዱበት የመዝናኛ ጉብኝትም አልነበረም፡፡ ጠ/ሚ/ር አቤ አህጉር አቋርጠው የመጡት ለሌላ ጉዳይ ነው – ቻይና!!! ተያይዞም ከምዕራባውያን ጋር የተገመደ ወታደራዊ የበላይነት በአፍሪካ!
ጃፓን “ተለውጣለች”
ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በኋላ “ሰላማዊነት” መመሪያዋ አድርጋ ለዘመናት የቆየችው ጃፓን ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ በውጭ ፖሊሲዋ ላይ ለውጦችን አካሂዳለች፡፡ ጦርነቱ ከተጠናቀቀ በኋላ የሕገመንግሥቷ አንቀጽ 9 እንደሚለው ጃፓን ሰላማዊ መንገድን የምትከተል፤ በሌሎች አገራት ጣልቃ የማትገባ ብቻ ሳትሆን ድርጊቱን “ለዘላለም የምታወግዝ”፤ ዓለምአቀፍ ግጭቶችን ለማስወገድ የጦርነት እርምጃ በጭራሽ የማትወስድ አገር መሆኗን ያስረዳል፡፡ ሲቀጥልም የጦርነት እርምጃው በምድር፣ በባህር እና በአየር የሚደረገውን ሁሉ የሚጠቀልል እንደሆነ በግልጽ ይናገራል፡፡ ከዚህም የተነሳ ነበር ሌሎች አገራት ጦራቸውን “የመከላከያ ሠራዊት” እያሉ ሲጠሩ ጃፓን ግን የአገሯን ጦር “የጃፓን ራስን የመከላከል ኃይል” በማለት የሰየመችው፡፡