"ህይወት እንደዋዛ"
ዲፕሎማቱ እጅ ላይ ያረፈችው ኢትዮጵያዊት ወጣት ሬሳ ትላንት ከሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ግቢ ወዳልታወቀ ስፍራ ተወሰደ ።
ቀን መስከረም 8: 2006 ለ5ኛ ግዜ በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ግዜያዊ መጠለያ ኮኔትነር ውስጥ፡ የአንዲት ኢትዮጵያዊት አስዛኝ፡ ህልፈተ ህይወት የአካባቢውን ማህበረሰብ እምባ ሲያራጭ፡ ደረት ሲያዳቃ መዋሉን የአይን ምስክሮች ገለጹ። ወጣቷ በቤት ሰራተኝነት ኮንትራት የመጣች የክርስትና እምነት ተከታይ መሆኗን የሚናገሩት እነዚህ የአይን እማኞች የወጣቷ ሬሳ እስካሁን በውል ወዳልታወቀ ስፍራ መወሰዱን አረጋግጠዋል።
የእህቶቻችን ሞት ከሚፈበረክበት በሪያድ የኢትዮጵያ ኮሚኒቲ ማህበር የስደተኞች ጊዜ ያዊ መጠለያ ኮንቴነር፡ ያለምንም ህክምና እና በቂ መሰረታዊ ፍጆታ በለሌለበት ሁኔታ እንደ ወንጀለኛ የኮንቴነር የብረት በር ተከርችሞባቸው ከሚገኙ እህቶቻችን መሃከል አንድ ወር ባልሞላ ግዜ ውስጥ በተከታታይ የሁለት ኢትዮጵያውያን ህልፈተ ህይወት መሰማቱ የአካባቢውን ማህበረሰብ አስደንግጦል።
በተለይ ትላንት ማለዳ በኢትዮጵያ ሰዓት አቆጣጠር ከጠዋቱ 3 አካባቢ አስከሬንዋ ጊዜያዊ መጠለያ ኮንቴነር ውስጥ ሞታ የተገኘችው ኢትዮጵያዊት ወጣት ህመሙ አገርሽቶባት ስታቃስት «ጣዕረሞት ስታሰማ»፡ እንደ ነበር የሚናገሩ ወገኖች ዲፕሎማቱ ትብብር እንዲያደርጉላት ስልክ ቢደወልላቸውም በወቅቱ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው የወጣቷ ህይወት በሚያሳዝን ሁኔታ ማለፉን ይገልጻሉ።
ሟች እዚህ ደረጃ ላይ ከመድረሷ በፊት ዲፕሎማቱ በኤምባሲው ሃላፊነት ወደ ሆስፒታል ወስደው ማስመርመር እና ህይወቷን ከሞት መታደግ ሲችሉ ባሳዩት ግዴለሽነት እና ወገናዊ ርህራሄ የጎደለው አሰራር የወጣቷ ህይወት እዚህ በረሃ ላይ ቀርቷል ብለዋል። ወጣቷን ወደዚህ ግዜያዊ መጠለያ ግቢ ዲፕሎማቱ ከአሰሪዎችዋ ተረክበው ሲያመጧት “ሃኪም ቤት ውሰዱኝ ህይወቴን አጣሁ!! አድኑኝ ኧረ የወገን ያለህ!! ኧረ ያህገር ያለህ!! አናቴ ድረሺልኝ!!” እያለች ትማጸናቸው እንደነበረ በአካባቢው የነበሩ የአይን ምስክሮች አክለው ገልጸዋል። የወጣቷ የሰውነት አቋም እና አጠቃላይ ሁኔታ ያዩ አንዳንድ ታዛቢዎች በውስጥዋ የቆየ በሽታ እንደሌለባት እና ወጣቷ አንጀቴ ተቃጠለ ውሃ ውሃ ስትል እንደነበር እና ሃኪም ቤት ውሰዱኝ እያለች ልብ በሚነካ ሁኔታ ስትማፀን የታዘቡ ወገኖች ምናልባትም ከምግብ ጋር የተቀልላቀለ መርዝ ነክ ነገር በልታ ሊሆን እንደሚችል ጥርጣሬያቸውን ያጎላሉ።