በስውርና በግልጽ አፈናው ተጧጡፏል
December 5, 2014 11:06 pm By
Editor
* የከምባታ ጠንባሮ ዞን ህዝብ ሰላማዊ ሰልፍ ማድረጉ ተገለጸ
* የሰማያዊ ፓርቲ ቢሮ በፖሊስ ተከብቦ አደረ
የሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት በፖሊስ ተከብቦ ማደሩንና አባላት ከውጭ እንዳይገቡ መደረጋቸውን ለአዳር ሰልፉ ቅስቀሳ ዝግጅት ቢሮ ያደሩ የፓርቲው አመራሮችና አባላት ለነገረ ኢትዮጵያ ገለጹ፡፡ አመራሮችና አባላቱ እራት በልተው ወደ ፓርቲው ጽ/ቤት ሲመለሱ ቢሮው በፖሊስ ተከብቦ እንዳገኙትና ወደ ውስጥ እንዳይገቡ እንደተከለከሉ በቦታው የነበሩት የፓርቲው አመራሮችና አባላት ገልጸዋል፡፡
አመራሮችና አባላቱ ፖሊስ ከ200 ሜትር ርቀት ውጭ ወደ ፖለቲካ ፓርቲ ጽ/ቤት መጠጋት እንደማይችል ቢከራከሩም ፖሊሶቹ “መመሪያ ተሰጥቶናል፤ አንሄድም!” ማለታቸው ገልጸዋል፡፡ አመራሮቹና አባላቱ ከፖሊስ ጋር ሲከራከሩ የአካባቢው ህዝብ በመውጣቱ ፖሊሶቹ ፓርቲው ጽ/ቤት እንደራቁ ታውቋል፡፡
በሌላ በኩል ከውጭ ወደ ቢሮ ከሚመጡበት ወቅት የፓርቲው ቢሮ አካባቢ ምንነቱ ያልታወቀ ወረቀት ተበትኖ እንዳገኙና እነሱ ሲደርሱ ፖሊሶቹ እንዳነሱት የፓርቲው የምክር ቤት አባል ወጣት እየሩስ ተስፋው ለነገረ ኢትዮጵያ ገልጻለች፡፡
*********************
በነገረ ኢትዮጵያ የፌስቡክ ገጽ ላይ የታተመው መረጃ እንደሚያመለክተው ፖሊስና ደህንነቶች ወደ ሰማያዊ ፓርቲ ጽ/ቤት የሚገቡና የሚወጡ አባላትንና አመራሮችን እያዋከቡ ይገኛሉ፡፡ የሰማያዊ ፓርቲ አመራሮችንና አባላትን “እንፈልጋችኋለን!” በሚል እየያዙ ሲሆን በተለይ ደህንነቶቹ መታወቂያ አሳዩ ሲባሉ ፈቃደኛ ሊሆኑ አልቻሉም፡፡