ይሄንን ፎቶ ልብ ብዬ እንዳየሁት፤
የሆነው ባለፈው አርብ የረመዳን ጁማዓ ጸሎት በሚደረግበት ወቅት ነበር። ሙስሊሙ ህብረተሰብ እንደተለመደው ሰላማዊ ተቃውሞውን ለማሰማት ገና ሲጀመር፤ ሌላ የፎቶ ማስረጃ እንዳሳየን ፖሊሶች ድንጋይ መወርወር ጀመሩ፤ (ይሄንን ስንናገር እየተሸማቀቅንም ቢሆን ግን እውነት ነው) በዚህም ብጥብጡ ተነሳ ፖሊሶች ያገኙትን መደብደብ ጀመሩ፤ ድብደባው እስላም ክርስቲያን ያለየ ለመሆኑ የሰማያዊ ፓርቲዋ ወይንሸት ሞላ እማኝ ነች። በእለቱ ፖሊሶች እና ደህንነቶች ያደረሱትን ስቃይ ድምጻችን ይሰማ ዎች ”ጥቁር ሽብር” ብለው ሰይመውታል።
በፎቶው ላይ የሚታዩት ሙስሊም ሰውዬም እንግዲህ ከተደብዳቢዎች አንዱ ነበሩ ማለት ነው። በዚህ ድብደባ ላይ የሚያስገርሙ ሁለት መሰረታዊ ነገሮች አሉ። አንደኛው እኒህ ሰውዬን ለመደብደብ ስምንት ፖሊሶች ከበዋቸዋል። ”አንድ ለአምስቱ አደረጃጀት ወደ አንድ ለስምንት አደገ” ብለን እንዳናሾፍ፤ እየተደደቡ ያሉት ሰብዓዊ ፍጡር ናቸው እና ለቀልድ አይመችም። ሁለተኛው እና በጣም የሚደንቀው ግን የፖሊሶቹ ፈገግታ ነው። አንዳንዶቹማ ፍንክንክ እያሉ ሲስቁ የሰርግ ጌሾ የሚወቅጡ እንጂ እንደነርሱ ሰው የሆንነ ፍጡር የሚደበድቡ አይመስሉም።
እነዚህ ፖሊሶች በአደባባይ እንዲህ ከደበደቡን በየእስር ቤቱ ጓዳማ ምን እያደረጉን እንደሆነ መገመት ይጨንቃል።
እወነቱን ለመናገር የመጨረሻው ቀን ቀርቧል። ሌላው ሁሉ ቢቀር እንዲህ እየተደበደብን ኢህአዴግን ከሚቀጥለው ምርጫ አናሳልፈውም። ኑሮ የሚደበድበን አንሶ ያልጠገቡ የመንግ ፖሊሶች ደግሞ እየደበደቡን መኖርን የምንመርጥ እኛ ማን ነን…
ፖሊሶቻችን ተዉ… ሞልቶ ለማይሞላ አዱኛ፤ ቀለባችሁን ብቻ አትመልከቱ ቀልብም ለመግዛት ሞክሩ።