"የለዘብተኞችና የእስስት” ፖለቲካ ልዩነት እየፈጠረ ነው
መለስ በሁለቱ አገሮች ድንበር ላይ “የጅራፍ ድምጽ እንኳን አይሰማም” በማለት ሲመጻደቁበት የነበረው የኢትዮ-ኤርትራ ጦርነት በ”ወረራ” እና “ወረራን መቀልበስ” በሚል ድራማ ተጀምሮ ከተቋጨ አስራ አምስት ዓመት አልፎታል። ኢህአዴግና ሻዕቢያ ጉዳያቸውን በጠረጴዛ ዙሪያ ወይም በጡንቻ መቋጨት ያልቻሉበት ምክንያት ለብዙዎች እንቆቅልሽ ሆኖ እስካሁን አለ። ሁለቱም ወገኖች ድንበር ላይ ወታደር አፍስሰው መቀመጣቸውን አስመልከቶ “አውቀው ነው” ከሚለው ውሃ የማይቋጥርአስተያየት ጀምሮ በርካታ ጉዳዮች በገሃድና በሹክሹክታ ሲሰማ ቆይቷል።
የጎልጉል የዜና ምንጮች ሰሞኑን ከአዲስ አበባ የላኩት መረጃ ግን በይዘቱ የተለየ ነው። ይህንኑ አዲስ ጉዳይ የሚመለከታቸው ክፍሎች አስተያት እንዲሰጡበት ያደረግነው ሙከራ ባይሳካም ዜናው ለውይይት የሚጋብዝ በመሆኑ አትመነዋል።
የድንበር ውዝግቡ አንዲቋጭ ይፈለጋል?
የኢትዮ-ኤርትራ የድንበር ውዝግብ ጦርነት ከኢትዮጵያ ወገን ብቻ ከ100 ሺህ በላይ ጉዳዩ በውል ያልገባቸው ወገኖች ህይወት የተገበረበት ነው። የአይደር ትምህርት ቤት ህጻናትን ጨምሮ የበርካታ ሰላማዊ ዜጎችንና ህጻናትን ህይወትም ቀጥፎ አልፏል። አቶ መለስ ለዚህ ሁሉ ቀውስ ተጠያቂ ቢሆኑም በድንገት ተስፈንጥረው ፍርድ ቤት ህግ ሳይጠቀስባቸው አልፈዋል። “ታላቁ መሪ” በህይወት እያሉ በኤርትራ ጉዳይ በተፈጠረ አለመግባባት ትግራይ ውስጥ እስከመታገት ቢደርሱም ከጥንቃቄ ጉድለት በአንጋቾቻቸው ፈጥኖ ደራሽነት ተርፈው ተቃዋሚዎቻቸውን “ውህዳን” በማለት በየተራ አራግፈው ብቻቸውን “ውርስና ቅርስ” ለመሆን በቅተዋል።
ከህንፍሽፍሽ፣ የልዩነት ጊዜ ጀምሮ አደባባይ የወጣው የልዩነት መሰረት በወቅቱ ይፋ ሲደርግ ኢትዮጵያውያንን አሳዝኖና አስቆጥቶ እንደነበር በወቅቱ በስፋት የተዘገበበት ጉዳይ ነው። ዛሬም ይህ ወቅት ዳግም እየተመለሰ እንደሆነ እየተሰማ ነው። “የኤርትራን ጉዳይ እንቋጭ” የሚሉ የከረረ አቋም ያላቸው ተነስተዋል። እነዚህ ወገኖች ሁለት አማራጭ በማቅረብ ሃሳባቸው ተግባራዊ ሊሆን እንደሚችል እየወተወቱ ነው።
የመጀመሪያው አሁን ያለው የመከላከያ አቅም የድንበሩን ውዝግብ በሃይል ለመቋጨት አቅም እንዳለው እየታመነ ለምን “ቸልተኛነት ተመረጠ” በሚል በቂ ጡንቻ ስለመገንባቱ አበክረው የሚከራከሩበት አግባብ ነው። ሁለተኛው ደግሞ “የኤርትራን ተቃዋሚዎች አደራጅተናል፤ ለምን እነሱ ወደ ኦፕሬሽን አይገቡም” የሚል እንደሆነ መረጃዎቻችን ያስረዳሉ።
ቸልተኞቹ ምን ይላሉ?
በዚህ ጉዳይ ቸልተኛ የሚባሉት የተለየ ምክንያት ያላቸው፣ ነገር ግን “ጦርነት አያዋጣም” በሚል በገሃድ የሚከራከሩ ወገኖች ናቸው። እነዚህ ውስን የብአዴንና የህወሃት ቁልፍ ሰዎች በትግራይ ድንበር አካባቢ አስተዳደር የሚሰሩትን ጨምሮ የኤርትራ ደም አላቸው። በደህንነትና በጸጥታ ክፍሉ አጠቃላይ መዋቀር ላይ ቁልፍ ቦታ ተጎናጽፈዋል። የመረጃ ምንጮቹ ማብራሪያ እንደሚያመለክተው እነዚህ ወገኖች “ኢሳያስን የክፉ ቀን መጠባበቂያ” ነው የሚሏቸው። ሰዎቹ ኢህአዴግ ላይ አንዳችም አይነት ስጋት እንደማይሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ዋና ዓላማቸው “ከመሃል አገር ወይም ከመካከል ለውጥ ካልተነሳ አርፈህ ተቀመጥ” የሚል ዓይነት መንገድ የሚከተሉ ናቸው።